የሰዎች የሕይወት አንዱ ገጽታ፣ በሕይወት ዘመናቸው አብሮ የሚኖርና በማንኛውም አጋጣሚ ሊከሰት ለሚችለው አካል ጉዳተኝነት ወረቀት ላይ ከሰፈረው ፖሊሲ በዘለለ ይኼንንም ያህል ትኩረት ሲቸረው አይስተዋልም፡፡ በመሆኑም አካል ጉዳተኞች በየዕለት ኑሮዋቸው ከማኅበራዊው፣ ከኢኮኖሚውም ሆነ ከፖለቲካው እምብዛም ተጠቃሚ ሲሆኑ አይታዩም፡፡
በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰውን አድሎና መገለል ብሎም የተሳታፊነትና የተጠቃሚነት እክሎችን ለመግታት በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበር ከጀመረ የዘንድሮው 26ኛ ዓመቱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ዓመቱ በባተ በኅዳር 24 መከበር ከጀመረ ዛሬ 25 ዓመታትን ያስቆጥራል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር ፌዴሬሽን ኅዳር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃንና ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ባዘጋጀው መድረክ እንደተነገረው፣ በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ከሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚና ተሳታፊ ለማድረግ ፖሊሲዎች ቢቀረጹም፣ አተገባበሩ ላይ ክፍተት አለ፡፡
የዘንድሮው መሪ ቃል ‹‹ሁሉን አቀፍ ጠንካራና ዘላቂ ማኅበረሰብ እንገንባ›› የሚል ሲሆን፣ ይኼም በአገሪቱ ኅብረተሰብ አወቃቀር ውስጥ ብዙም ቦታ ያልተሰጣቸውን አካል ጉዳተኞች ታሳቢ ከማድረግ ነው፡፡
የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ደረሰ ታደሰ እንደሚሉት፣ በአገሪቱ ውስጥ በሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ ሁሉን አቀፍ ጠንካራ ማኅበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ጠንካራና በኢኮኖሚ የበለፀገ፣ የረዥም ጊዜ ግብ ያለውና እስከመጨረሻው ሊዘልቅ የሚችል ኅብረተሰብ መገንባት ወሳኝ ሲሆን፣ በዚህም 15 ሚሊዮን የሚደርሱትን አካል ጉዳተኞች ማካተትና ማሳተፍ ግድ ነው፡፡ ይኼ ካልሆነ ግን ይኼን ያህል ቁጥር ያለውን ሕዝብ ትቶ የሚጓዝ ልማት፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ዘላቂና ፍትሐዊ ሊባል አይችልም፡፡ ለውጥ ማምጣትም አይቻልም፡፡ በመሆኑም አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ አሠራሮች ወሳኝ ናቸው፡፡
ሆኖም አካል ጉዳተኞችን በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ዘርፉ አካቶና አሳትፎ በመጓዝ ላይ ችግሮች አሉ፡፡
በዓለም ሥራ ድርጅት የአካል ጉዳተኞች ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ፋንታሁን መለሰ እንደሚሉትም፣ አካል ጉዳተኞችን ካሉባቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለማላቀቅ የሚያስችል አዋጅ ብሎም ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ቢኖሩም፣ ወደትግበራው ሲገባ ችግሮች አሉ፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡
የአካል ጉዳተኞችን በእያንዳንዱ ዘርፍ ውስጥ አካቶ ለመሄድ የእውቀት ክፍተት መኖር፣ ማሳተፍን በአሉታዊ ጎኑ መረዳት፣ ምቹ ሁኔታዎች አለመኖር፣ የተደራሽነት ችግር፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚደረግን ነገር እንደ መብት ሳይሆን እንደ ችሮታ ማየት ከችግሮቹ እንደሚጠቀሱ አቶ ፋንታሁን ይናገራሉ፡፡
የማኅበረሰቡ አመለካከትም ሌላው ችግር ነው፡፡ ኅብረተሰቡ አካል ጉዳተኛነትን ከመርገምት ጋር ማያያዙን ገና አልተወውም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እስካሁንም አካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች ደብቆ ማስቀመጡ አልቀረም፡፡
የበጀት፣ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በየዘርፉ ለማካተከት የፍላጎት ማነስ እንዲሁም በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ተግባብቶና አብሮ ያለመሥራት ችግሮችም አካል ጉዳተኞው ካለበት ችግር ራሱ በሚያደርገው ተሳትፎ እንዳይወጣ ማነቆ ሆነዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ አምሮ የተረቀቀው ፖሊሲ ምድር ላይ አለመተግበሩ አካል ጉዳተኞች ዛሬም ትምህርትን ጨምሮ ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኛ ያልሆኑት ከሚጠቀሙት ያህል ጥቂቱን እንኳን እንዳይቋደሱ አድርጓል፡፡
ሕጎች ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ያስቀመጧቸው አሠራሮች ቢኖሩም በአገሪቱ እየተስፋፉ ያሉ መሠረት ልማቶች ሲታዩ አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም፡፡ ብዙ ሕንፃዎች ከመግቢያቸው ጀምሮ መወጣጫቸው ለአካል ጉዳተኛው የተመቹ አይደሉም፡፡ አገልግሎት መስጫዎችም ቢሆኑ እንዲሁ፡፡
በየሕንፃው የሚገኙ አሳንሰሮች አንዳንዶቹ አንድ ዘሎ አንድ የሚሠሩ ሌሎቹ ደግሞ ከተወሰነ ወለል በላይ የሚጀምሩ መሆናቸው አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ አካል ጉዳተኞችን፣ አዛውንቶችን እንዲሁም ሕሙማንን የሚፈትኑ ናቸው፡፡ ይኼ በትምህርት ተቋማትም የሚታይ ችግር ነው፡፡
በትምህርት ቤት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መቀመጫዎች፣ መፀዳጃዎች ወደ ሕፃናቱ ወረድ ሲል ደግሞ የአካል ጉዳት ያለባቸውንና የሌለባቸውን ልጆች በአንድ ክፍል ለማስተማር የሚያስችል መሠረት ልማትም ሆነ መምህር አለመኖር ሁሌም የሚወሳ ችግር ነው፡፡
አቶ ደረሰ እንደተናገሩት፣ መገናኛ ብዙኃንም ለአካል ጉዳተኛው የሰጡት ትኩረት ትንሽ ነው፡፡ ስለ አንድ ክንውን ሲዘገብ የሚሠሩ ሥራዎች ምን ያህል ሁሉንም ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ የሚለው ላይ እምብዛም ትኩረት ሰጥቶ የሚዘግብ መገናኛ ብዙኃንም አይስተዋልም፡፡ አዘጋገብ ላይ የሚውሉ ቃላትም አሉታዊ ገጽታን የሚያጎናጽፉ ናቸው፡፡
ባለሥልጣናት ስለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ብዙም የማያውቁ መሆናቸው፣ ለሴቶች፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት እየተባለ የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ለአካል ጉዳተኞች አለመሰጠቱን አካል ጉዳተኞች በየመድረኩ የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ለውጦች ቢኖሩም፣ ብዙዎቹ ዘርፎች የአካል ጉዳተኛውን አጀንዳ አካቶ መሄዱ ላይ ችግር አለባቸው፡፡ በመሆኑም በዓለም ለ26ኛ በኢትዮጵያ ለ25ኛ ጊዜ ዛሬ ታስቦ የሚውለው ዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ቀን መሪ ቃል ‹‹ሁሉን አቀፍ ጠንካራና ዘላቂ ማኅበረሰብ እንገንባ›› የሚል ሆኗል፡፡
ፌዴሬሽኑም ይኼንን አስመልክቶ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በግሎባል ሆቴል መድረክ አዘጋጅቷል፡፡