Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መታረቅስ ከራስ ጋር ነው!

 ሰላም! ሰላም! “የዕድሜን ሚስጥር ማን አውቆት?” ብላቸው “የኖረው!” ብለው መለሱልኝ ባሻዬ። እንግዲህ አዲስ አበቤ 131 ዓመት ሲደፍን ዕውቀቱ የት እንደ ደረሰ አስቡት፡፡  “በቻፓ ዘመን ስለዕውቀት ትጨነቃለህ? ሞኝ፤” የሚለኝ ደግሞ የባሻዬ ልጅ ነው። ዳሩ አልቆጠርኩበትም። ዳቪንቺም እኮ በዘመኑ ሞኝ ነበር። ማን በዘመኑ ያልተሞኘ አለ አትሉም እናንተስ? እንዲያ ነው እንጂ። እየተቀባበልን ካልሆነ እኮ ጊዜው አልገፋ ብሏል። ሰው እንደሆነ እንኳን ገፍታችሁት ሳትነኩት በመውደቅ አባዜ ሰርከስ መጫወት ሆኗል ኑሮው። በነገራችን ላይ ዕውቀት ብትሉት ገንዘብ ውደቅ ተብሎ ለታዘዘ ሰው አወዳደቅን ያሳምር ይሆናል እንጂ፣ ከውድቀት ሲያድን ታይቶ አያውቅም። ግን እኔ ምለው እንዲህ ትንሽ ትልቁ በዳዊት አምላክ እየተመካ በጎልያድ አወዳደቅ የተካነው ምን በድሎ ነው? ብላችሁ ጠይቃችሁ አታውቁም?

አንድ ወዳጄን እንዲህ ብዬ ብጠይቀው፣ “ምን እዚያ ድረስ አስኬደህ? መንገዱን አታይም? ጉድጓድ ብቻ እኮ ነው። ፈጣሪን እዚህ ምን ዶለው?” ብሎ አሽሟጠጠኝ። ምን ይታወቃል? የዘመኑ ሰው የሚምሰው ጉድጓድ እኮ እንኳን ለሥጋ ለባሽ ለአማልክቱም የሚያንስ አይመስልም።፡ የእኔ ነገር ተሳስቻለሁ? ብቻ እኔ አንድ ነገር ከያዝኩ ችክ የምለው አለ። አነሳሴ ስለአዲስ አበባና ነዋሪዎቿ ላጫውታችሁ ነበር። ግን እንዳልኳችሁ ችክ ስል አንዱ ጉድጓድ ገብቼ ቀረሁ። ታዲያ በቀደም ሠፈር ውስጥ ውኃ ጠፍቶ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ጎረቤቴ ተናዶ እንዲህ አለ። “አሁን እስኪ በምኒሊክ ጊዜ የተጀመረ የውኃ ቧንቧ በዚህ ዘመን ውኃ ተሸክሞ ማስተላለፍ እንዴት ያቅተዋል?” አለ ተብሎ ባሻዬ ሲሰሙ፣ “እንኳንም በአብርሃም ጊዜ አልተወለደ፤” አሉ ተባለ። የሰው ዕድሜ እንደ ወረቀት ተቀዶ ተቀዶ ሰባ ሰማንያ ላይ ባይደረስ ኖሮ አስቡት፡፡ የማቱሳላን ዕድሜ ሙሉ አዲስ አበባና አዲስ አበቤ በመሠረተ ልማት ሲባላ። ወይ ዕድሜ!

ነገር ከማስፋታችን በፊት ባሻዬ ስለአብርሃም ጊዜ የሚሏት ነገር ትመቸኛለች። መቼም ለሁሉም ጊዜ አለው። ዛሬ ፌስቡክ ኖሮ ሳይሆን ጥንትም ቢሆን ከነገሥታትና ከኃያላን እኩል ብዙ ግለሰቦች አካውንት ነበራቸው። ያውም ኑሮዬን እዩልኝ፣ ጉንጬን መዝኑሉኝ ባዮች ፎቶ በየሰላሳ ደቂቃው እየተነሱ የሚለጥፉበት ሳይሆን የኑሯቸው የዕርምጃቸው ውጤት የሆነ የተኖረ ታሪክ የዘከሩበት ‹አካውንት› ነው የማወራችሁ። እና ባሻዬ እንደ ቀልድም እንደ ምፀትም አድርገው፣ “አብርሃም ቤት ሥራ ሲለው እግዜር. . .” ይላሉ “ምን ሊሠራልኝ? ለዚህች ዘጠኝ መቶ ዓመት ለማትሞላ ዕድሜ ደግሞ ድንኳን አይበቃኝም? ብሎት ዘመኑን ሙሉ በድንኳን ኖረ. . .” እያሉ ፈገግ ያሰኙኛል። አይ ባሻዬ? የዘመኑ ሰው በኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ተስፋ ቆርጦ በቢራና በኤስኤምኤስ የሎተሪ ዕጣ ጣራ ሊያስመታ ደፋ ቀና ሲል አያዩትም ማለት ነው? ብዬ አንዳንዴ ከማንጠግቦሽ ጋር አማቸዋለሁ። 

መቼም አንዳንዴ ደህና ሐሳብ የሚታሰበው በጨለማ ነው ይባል የለ?  በሐሜት ላይ ሐሜት ስደርብ የባሻዬ ድንኳን አንድ ሐሳብ አስጫረኝ። ተደራጅተን ሠፈራችንንና ኑሯችንን በሕንፃ ማልማት ሲያቅተን ታዲያ ለምንድነው ተደራጅተን ድንኳን የማንሰፋው? የማይፈቀድልንስ ለምንድነው? ትንቢቱን ትታችሁት ሆሊውድ ሳይቀር ደጋግሞ የሚያሳየን መጨረሻው ዘመን እንደቀረበ ነው። ደግሞም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጥፋት ፎቅና ፎቅን እንደ ባልጩት ድንጋይ ሲያጋጭ ነው። አውሮፕላን የተሠራው ወፍ ሲበር ታይቶ ነው ሲባል ሁላችንም አጨብጭበናል። ከሆሊውድ የዓለም ፍፃሜ ፊልሞች ተነስተን ኑሯችን በድንኳን ይሁን ብንል የሚያሳፍረው ታዲያ ለምድነው? አውሮፕላን ለመሥራት ልብ እንደጠየቀን ሁሉ ድንኳንም ለመትከል ካስማ እንደሚያስፈልግ አልገባንም ልበል? ልብን የያዘው ካስማ ነው ብላችሁ ደግሞ ሰው ሁሉ ድንኳን ነው ልትሉኝ ነው። ጉድ ነው ዘንድሮ!

ሐሳብ እያበዛሁ ነገር ማውጠንጠን በሽታ ቢሆንብኝ ትንሽ ልሸቃቅል አልኩና ከረፈደ ከቤቴ ወጣሁ። ፍጥረት ላይሞላለት ሊደክም ወደ ሚባክንበት ጎዳና ተቀላቀልኩ። አልሠራ እያለ ያስቸገረን ‘አደገኛ ቦዘኔው’ ‘ኔትወርካችን’ ስልኬን ቢዳስሳት በድንገት ተንጫጫች። ‘መቼም ለደህና ነገር በዚህ ሰዓት እንዲህ ደመቅ ብላ አትጮህብኝም’ እያልኩ “ሄሎ?” ስል፣ በወዲያ በኩል በቀጭኑ ሽቦ የሚያነጋግረኝ ወዳጄ የአንድ ጓደኛችን እህት በድንገት ስላረፈች ለድንገተኛ ቀብር አስፈጻሚዎች ስለሚከፈል ክፍያ መዋጮ ይጠይቀኛል። ነገርኳችሁ የወጪ እንጂ የገቢ ኔትወርክ ድራሹ ከጠፋ ዘመን ተቆጥሯል። ከአገር እስከ ግለሰብ በመዋጮ እየኖርን እስከ ዛሬ መዝለቃችን ግን ይገርመኛል።

መቼም ሐበሻ ኖሮት አይነፍግም። ባይኖረንም፣ ገንዘብ ብናጣም ኩራት አናጣምና ተበድረንም ቢሆን እናበድራለን (ይህ ባህሪያችን በጊኒስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ሳይመዘገብ ቀርቷል ብላችሁ ነው?) ወዲያውኑ ወዳጄን የጠየቀኝን መዋጮ ካለሁበት ሥፍራ ድረስ መጥቶ እንዲወስድ ነገርኩት። እሱም ወዲያውኑ ከተፍ ብሎ ተቀበለኝ። ለሞትና ሕይወት እያዋጣን ሲመጡ ስንቀበል፣ ሲሄዱ ስንሸኝ የራሳችንን ግን መጀመርያውንም መጨረሻውንም ሳናውቀው እንዲሁ መቅረታችን አያበሽቅም?

 ደግሞ በስንተኛው ቀን አንድ የሚሸጥ አይሱዙ ነበርና ገዥ ፍለጋ እባክን ጀመር። የአብዛኞቻችን ትከሻ የአይሱዙን የሥራ ድርሻ ከተረከበ ቆየት ቢልም፣ የሚታይ የሚታየውን ጭኖ ለማራገፍ ገዥ እንደማላጣ እግርጠኛ ሆኛለሁ። እንደ ቀድሞው ሙቀቱ የጠፋው የአይሱዚዎችን መንደር ሳይ ‘ምን ያለው ደፋርና ቆራጥ ይገዛት?’ ይሆን ማለት ጀመርኩ፡፡ (ምን ያልቀዘቀዘ ነገር አለ ከሌብነቱ ሠፈር በቀር?)፡፡ ይኼኔ ነው አንድ ደርባባ ጎልማሳ ገዥ ነኝ ባይ ያገኘሁት። መኪናውን ከሞዴል እስከ አቋም አስፈትሸን አስተማማኝነቱን ቢያረጋግጥም ጎልማሳው ፊቱ ደስተኛ አልነበረም።

“ምነው ቅር ያለህ ነገር አለ?” ብለው፣ “አይ እንዲያው ነው። ነገ መልሼ ጆሮውን ማለት ብፈልግ ያዋጣኝ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ ተስኖኝ ነው፤” አለኝ። “ሳትገዛው ለመሸጥ እንዴት ታስባለህ? ለማትረፍ ነው የምትገዛው ማለት ነው?” ብዬ ብለው፣ “የለም! እንዲያው አዝማሚያው ባይጥምህ ዝም ብለህ አትቀጥልም እኮ፡፡ ‘አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው’ አይደል የሚባል?” ብሎኝ ሲያበቃ ድምፁን ዝቅ ዓይኑን ቅልስልስ አድርጎ፣ “አታይም ስንቱን ቱጃር እዚህም እዚያም ብሎ ሲተኮስ? ማን ነው በጀመረው ጨርሶ የተጨበጨበለት?” ሲለኝ ነገሩ ገባኝ። ይበልጥ እየገባኝ ተመጣጣኝ በሆነ የዕድገት ሒደት በጀመረው የጨረሰ እንደሌለ ተገለጸልኝ። ይኼኔ ዕድሜ ጠገብ ፋብሪካዎች፣ ዕድሜ ጠገብ ድርጅቶች፣ ዕድሜ ጠገብ የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የተቀላጠፈና አስተማማኝ የዕድገት ሒደት፣ ዕድሜ ጠገብ ሕገ መንግሥት ማየት ናፈቀኝ። እውነት አይናፍቅም?  

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ሥራዬን ጨራርሼ ድክም ብሎኝ በጊዜ ገብቼ ልተኛ ስንደፋደፍ ባሻዬ ደወሉልኝ። የት እንዳለሁ ስነግራቸው፣ “ቶሎ ብለህ ቤት ና፤” አሉኝና ቤታቸው ሄድኩ። ለባብሰው ተዘገጃጅተው ይጠብቁኛል። “የት ልንሄድ ነው ባሻዬ?” ስላቸው፣ “ዛሬ ጊዜ የሰው መጨካከን ከልክ እያለፈ ነው። ኖሮት ባይሰጥህ፣ ባያበድርህ፣ ተርፎት ባያጎርስ ምናለበት ከወዳጅ ከዘመድ ስትጣላና ስትኳረፍ ምን ሆንክ ብሎ ቢያስታርቅ? ነውር አይደለም ግን?” አሉኝ አትኩረው እያዩኝ። ምን እንደሚያወሩ ስላልገባኝ፣ “ደግሞ ማን ተጣላ?” ብዬ እንዲያብራሩልኝ ስጠይቃቸው፣ በቅርብ የሚያውቋቸው ሊጋቡ የሚጠበቁ ጥንዶች ተኳርፈው እነሱን ሊሸመግሉ እንደምንሄድ ነገሩኝ። ተስማምቼ ሄድን። መቼም ትልቅ ሰው ትልቅ ነው! ከፀባችን ብዛት ሰላምታችን ሁሉ ሰላምን በማረጋገጥ ላይ መመሥረቱ ራሱ ቁጣ ማብረድ ነበረበት እኮ። ግን ምቀኛ አያሳጣን ነው መቼስ፡፡

የቅናት ዛር የሰፈረበት ሁሉ እንኳን በሰው ሰላም በሰው ኪስ ይቃጠል የለ፡፡ አንዳንዴ እኮ አለመፈጠርን የሚያስመኘኝ፣ ከተፈጠርኩ ጀምሮ ያየሁት ትርጉም የለሽ ክፋት ተቆጥሮ የማይልቅ ሲሆንብኝ ነው። ዘንድሮ ቆጥራችሁ አይደለም ገና ሳትጀምሩት የሚያልቀው ገንዘብ ብቻ ሆኗል። በተረፈ ሌላው ጉድ የሚያልቅ አይደለም። እና ሰላም በራቀን ልክ እኛም የምንመፃደቀው እንደ ግዳይ መቁጠር የጀመርነው እኩይ እኩዩን ሆነ። ብቻ ስንትና ስንት እሴቶቻችን ማንቀላፋታቸው ስለሚቆጨኝ ነው። ሰው መሆን እኮ ከምንም ይቀድማል። አይደለም እንዴ? ታዲያ በዚህ ዓይነት ዳግም ውልደት ዳግም ትንሳዔ የሚያስፈልጋቸው ማኅበራዊ እሴቶቻችንን ቁጠሩማ፡፡ ቆጥሮ ለመድረስ ዕድሜ ሳይሆን ልብ ይበቃል እኮ? እኛስ ዋሽተንም ቢሆን አስታርቀን ተመልሰናል። ለጠብ ያሰፈሰፉ ልቦችን ማብረድ መቻል ብልኃት ይጠይቃል፡፡ ብልኃት የጎደለው ድርቅና እርባና ቢስ ስለሆነ ትዕግሥትና ጥበብ ያስፈልጉናል፡፡ የባሻዬን ልጅ ግሮሰሪ ተቀጣጥረን ቢራችንን ፉት ስንል ውሎዬን ስነግረው፣ ‹‹መታረቅስ ከራስ ጋር ነው፤›› ሲለኝ አባባሉ ገባኝ፡፡ ከራሱ ጋር ያልታረቀ ምን ይፈይዳል? መልካም ሰንበት!     

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት