Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልእስላማዊ ቅርሶች እምን ላይ ናቸው?

እስላማዊ ቅርሶች እምን ላይ ናቸው?

ቀን:

ሰዎች ተቻችለውና ተከባብረው አብረው እንዲኖሩ ከሚገዛቸው ምድራዊ ሕግ ባሻገር እምነት (ሃይማኖት) ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ዓለማዊ ሕግጋትን መጣሳቸው እስካልተደረሰባቸው ድረስ ንፁሀን ናቸው፡፡ ነገር ግን የትኛውንም ያልተፈቀደ ድርጊት ሲያደርጉ ከአምላካቸው መደበቅ እንደማይችሉ ያምናሉና በተቻላቸው መጠን ምክንያታዊ ሆነው ፈጣሪን ፈርተው በሰላም መኖርን ይመርጣሉ፡፡ በዚህም ነው ከምድራዊ ሕግጋት ይልቅ ሃይማኖት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው፡፡

የማንነታቸው አንድ አካል እስኪሆን የተዋሐዳቸውን ሃይማኖታቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ምንም ነገር ቢያደርጉ በሃይማኖት ሕግ ከፃድቅ ወገን እንጂ ከጥፋተኛ አይቆጠሩም፡፡  ሃይማኖት የብዙ እልቂቶች መነሻ፣ ማብረጃም ነው፡፡ ‹‹ለሃይማኖቴ አንገቴን እሰጣለሁ›› ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ለማስከበር የሚሄዱበትን ጥግ የሚገልፁበት መንገድ ነው፡፡ የከፋ እልቂት ሊያስከትሉ ከሚችሉ አጋጠሚዎች አንዱም በኃይል ሃይማኖት እንዲቀይሩ ማስገደድ ነው፡፡

የተለያዩ ሃይማኖቶች እንደዛሬው በልዩነታቸው ተማምነውና ተቻችለው መኖር በማይችሉበት ዘመን የአንድ አዲስ ሃይማኖት መምጣት ብቻ  በነባሩ ላይ እንደተቃጣ ጥቃት ይቆጠር ስለነበር የጦርነትና የግጭት መነሻ በመሆን በርካቶችን ለዕልቂት ይዳርግ ነበር፡፡ የእስልምና ሃይማኖት መጠንሰሻ በሆነችው ሳዑዲ ዓረቢያ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች በነበሩ ሰሃባዎች ላይም የደረሰው ይህ ነበር፡፡

ጣኦት አምላኪ ለነበሩ የመካ ቁሬይሾች ፈጣሪ በዓይን የምታዩት ቁስ (ጣኦት) ሳይሆን አንድ አምላክ ብቻ ነው የሚል ፅንሰ ሐሳብ ይዞ የመጣውን እስልምና በነበረው ሃይማኖት ላይ እንደተቃጣ ጥፋት ነበር የቆጠሩት፡፡ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች መብዛት ያስጨንቃቸው ስለነበረም በሙስሊሙ ምዕመን ላይ ያደርሱት የነበረው ጭቆና እና ግፍ ከባድ ነበር፡፡ ቶርች ይደረጉ፣ ይገደሉም ነበር፡፡ ለዚህም ከቦታ ቦታ ለመሰደድ ይገደዳሉ፡፡ ከመካ ወደ መዲና እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ስደትም በእስልምና ታሪክ ትልቁን ስፍራ ከሚሰጣቸው የታሪክ አጋጣሚዎች መካከል ናቸው፡፡

እስላማዊ ቅርሶች እምን ላይ ናቸው?

 

ወደ ኢትዮጵያ የተደረገው ስደት የመጀመሪያው ሒጅራ ይባላል፡፡ የነቢዩ መሐመድን ሴት ልጅ ጨምሮ 80 የሚሆኑ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አገሪቱ ገናና በነበረችበት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ አክሱማውያኑ እንደ ቁሬሾች ጣዖት አምላኪ ሳይሆኑ የክርስትና እምነት ተከታይ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁለቱ እምነቶች የተለያየ ርዕዮት የሚያራምዱ ቢሆንም በፈጣሪ አንድ መሆን መስማማታቸው ከመካ ቁሬሾች በተለየ ስደተኞቹን ሙስሊሞቹ ማስተናገድ አልተቸገሩም፡፡ ነቢዩ መሐመድም ሰሃባዎቻቸውን የክርስትና እምነት የተቀበሉ አገሮች እንዲሰደዱ ይመክሩ እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡

ይህ ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ቀጥሎ በእስልምና ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲኖራት ያደረገ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡ በዓለም ቀዳሚ ከሆኑ መስጊዶች መካከል በትግራይ ክልል የሚገኘው የነጋሽ መስጊድ አንዱ መሆኑ ደግሞ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ሌላው ሚዛን የሚደፋ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የታሪክ አጋጣሚ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከ1440 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ሃይማኖቱ በርካቶች ተቀብለውት እምነታቸው አድርገውታል፡፡ ያኔ ጥቂት የነበሩት የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች በአሁኑ ወቅት ወደ ቢሊዮኖች አድገዋል፡፡

መውሊድ

የእምነቱ መሠረት የሆኑት ነቢዩ መሐመድ በ570 የጋራ አቆጣጠር በሙስሊም አቆጣጠር በ3ኛው ወር ረቢል አል አወል እንደተወለዱ ይታወቃል፡፡ የተወለዱበት ዕለትም መውሊድ (ልደት) ይባላል፡፡ የተወለዱበትን ቀን አስመልክቶ በሁለት ጎራ የተከፈሉ ክርክሮች አሉ፡፡ የሱኒ ሙስሊሞች እርሳቸው የተወለዱት ረቢ አል አወል ወር 12ኛው ቀን ነው ይላሉ፡፡ በተቃራኒው ያሉት የሺአ ሙስሊሞች ደግሞ ነቢዩ የተወለዱት በተመሳሳይ ወር ነገር ግን 17ኛው ቀን እንደሆነ ይከራከራሉ።

ይህንን የልደት ቀን መከበር አለበት በሚሉና መከበር የለበትም በሚሉ የእስልምና ርዕዮተ እምነት ተከታዮች ዘንድ ሰፊ ልዩነት አለ። የወሃቢ፣ የሰለፊያ ርዕዮት ተከታዮች መውሊድን ማክበር የእስልምና እምነት እንደሚከለክል፣ ከሌሎች ሃይማኖቶች የተወረሰ ባህል እንደሆነ በመግለፅ በዓሉ መከበር እንደሌለበት ይናገራሉ። ብዙዎቹ ሙስሊም ሀገራት መውሊድን እንደ ብሔራዊ ቀን ሲያከብሩ ከዚህ በተቃራኒው የወሃቢያ ርዕዮተ እምነት አራማጅ የሆኑት ሳውዲ ዓረቢያና ካታር ግን በተቃራኒው እንደ ብሔራዊ ቀን አይቆጥሩትም።

መውሊድን እንደ ብሔራዊ ቀን ከሚቆጥሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ መውሊድ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል ጅማ አንዱ ነው፡፡ በዓሉ በተለያዩ መስጊዶች በፀሎት የሚታሰብ ሲሆን፣ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው ቁባ አባረቡ ደግሞ በተለየ ድምቀት ይከበራል፡፡

አባረቡ ለእስልምና መስፋፋት ትልቁን ድርሻ ያበረከቱ የእምነቱ ባለውለታ ናቸው፡፡ ቅዱስነታቸው፣ በአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጣቸው ቦታም ከፍተኛ ነው፡፡ አባረቡ የተቀበሩበት ቦታ ከንጉሥ አባ ጅፋር መኖሪያ አቅራቢያ በሚገኝ ተራራማ ቦታ ላይ ነው፡፡ ይህ ተራራማ ቦታ ቁባ አባረቡ በመባል ይታወቃል፡፡ በአካባቢው የሚገኙና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ምዕመናኑ መውሊድን ለማክበር ወደ ቁባ አባረቡ የሚሄዱት በዓሉ ቀናት ሲቀሩት ጀምሮ ነው፡፡ ለወትሮው ጭር ብሎ የሚውለው የቁባ አባረቡ መስጊድ በመውሊድ ይደምቃል፡፡ ድምፀ መረዋዎች በአንድ ጣታቸው ጆሯቸውን ይዘው መንዙማ ያወርዳሉ፡፡ ፀሎት ይደረጋል፣ ስለታቸው የሞላላቸው በግ፣ በሬ፣ ዕጣን፣ ሰንደልና ሌሎችም ስለቶቻቸውን ያስገባሉ፡፡

በወሎ ጀማ ንጉሥም የመውሊድ በዓል አከባበር በደመቀ ሁኔታ የሚከበረው የተለያዩ የሃይማኖቱ ኡለማዎች (አስተማሪዎች) በተገኙበት በሚደረግ ፀሎት ነው፡፡ እንዲያውም በጀማ ንጉሥ የሚከናወነው የመውሊድ አከባበር ከሌሎቹ አካባቢዎች በተለየ እንደሚደምቅ የሚናገሩት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የእስላማዊ ቅርሶችና ታሪክ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ አብዱልሰላም አሊዳውድ፣ ‹‹መውሊድ  መከበር የጀመረው በወሎ ጀማ ንጉሥ ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡ የአወልያ ዕርዳታና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅነትንም የያዙት ሐጂ አብዱልሰላም እንደገለጹት፣ የዘንድሮውን የመውሊድ በዓል በሰሜን ወሎ በምትገኝ ዚያን በተባለች ቦታ እንዲከበር ምክር ቤቱ የወሰነው የበርካታ ኡለማዎች መገኛ በመሆኑ ነው፡፡ በሌሎቹ አካባቢዎችም በደመቀ ሁኔታ እንዲከበርም ምክር ቤቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ሳያወሱ አላለፉም፡፡

ይህንን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በደመቀ መልኩ ለዘመናት ሲከበር የቆየውንና በመከበር ላይ ያለውን የመውሊድን ክብረ በዓል በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ዘንድሮ እንደሚጀመር ሐጂ አብዱልሰላም ተናግረዋል፡፡

ቅርስና ምዝገባው

እስልምና  ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በተቆጠሩት ሺሕ ዓመታት ውስጥ ሃይማኖቱን መሠረት ያደረጉ በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ተፈጥሯዊ ቅርሶችን አፍርቷል፡፡ ዩኔስኮ እንደ ድሬ ሼህ ሁሴንና የሶፍ ዑመር ዋሻ ያሉ የሚዳሰሱ ቅርሶች በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት) የዓለም ቅርስ ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ተይዘዋል፡፡ በሌላ በኩልም ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል የሐረሪ ውርሻቶ (አሹራ) በዓል ለማስመዝገብ ቀደም ብሎ የተጀመረ ሥራ እንዳለ ይታወቃል፡፡

 አንድን መንፈሳዊ ወይም ቁሳዊ ባህል በቅርስነት ለመመዝገብ የተለያዩ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ፡፡ አዋጅ ቁጥር 209/92 ቅርሶቹን በሦስት ደረጃ ይከፍላቸዋል፡፡ ተነቅለው ወደየትም ቦታ መሄድ የማይችሉ ሐውልቶች፣ የእምነት ተቋማት ቤተ ክርስቲያናትና መስጊዶች፣ የአርኪዮሎጂና ፖሊዎንቶሎጂ ቦታዎች የመሰሉትን ቋሚ ቅርሶች ይላቸዋል፡፡ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች የሚባሉት ደግሞ እንደ ብራና ጽሑፎች፣ ጥንታዊ የዕደ ጥበብ ሥራዎች፣ የየብሔረሰቡ የወግ ዕቃዎችና የመሳሰሉት ሲሆኑ ለሕገወጥ ዝውውር የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሦስተኛው የቅርስ ዓይነት የማይዳሰስ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርስ የሚባለው ነው፡፡

ዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ... 2003 (1995 .ም.) የማይዳሰሱ ቅርሶች ሀብቶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ለማስተዋወቅ የወጣ አንድ ስምምነት አለ፡፡ ስምምነቱን ኢትዮጵያ 1998 .ም. ፈርማለች፡፡ በዚህ መሠረትም በአገሪቱ የሚገኙ አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎቻቸው፣ ትውን ጥበባት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ የዕደ ጥበብ ክህሎትና ማኅበራዊ ክዋኔዎች፣ ፌስቲቫሎች በማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ዝርዝር ይመዘገባሉ፡፡

የቅርሱ ፋይዳ፣ ለታሪክና ባህል ጥናት ያለው ጠቀሜታ፣ በሥነ ጥበባዊና በኪነ ሕንፃዊ አሠራር ጥበብ ልዩ መሆኑ፣ በዕድሜው ጥንታዊ የሆነና የአንድን ዘመን የታሪክና የባህል አሻራ የሚያሳይ መሆኑ፣ የተሠራበት ቁስ ውድ መሆኑ፣ ሌላው ለሳይንስና ምርምር ያላው ጠቀሜታ የጎላ ከሆነ በቅርስነት ለመመዝገብ መስፈርቱን አሟልቷል ማለት ነው፡፡

‹‹ቅርሶችን መዝግበን ይኸን ያህል ቁጥር ያለው ቅርስ አለን ብለን ለመናገር የምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ሒደቱን ግን ጀምረናል፤›› ያሉት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተንቀሳቃሽ ቅርሶች ልማትና ኤግዚቢሽን አገልግሎት  ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የተመዘገቡ ቅርሶች ቁጥር በተንቀሳቃሽ ቅርሶች ደረጃ ወደ 70,000 በቋሚ ቅርስ ደረጃ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶችን፣ መንደሮች እንደ ሾንኬ ዓይነት፣ የአርኪዮሎጂና ፖሌዎንቶሎጂ ቦታዎች በተመለከተ 2,500 ተመዝግበዋል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታም 80 በመቶ ያህሉ ተመዝግቧል የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡                     

እሳቸው ይህንን ቢሉም አርኪዮሎጂስቱ ሐሰን ሰኢድ (ዶ/ር) በቅርስ አያያዝና የማስተዋወቅ ሥራ በተለይም የእስልምና መሠረት ባላቸው ቅርሶች ላይ ሰፊ ክፍተት እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ የተለያዩ አዋጆች እንዲሁም ስምምነቶች ለእስላማዊ ቅርሶች ሽፋን መጠበቅና መመዝገብ ሽፋን የሚሰጡ ቢሆኑም ማንኛውም ቅርስ የሚሰጠውን ቦታ እያገኙ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሊያውቃቸው ቀርቶ የእምነቱ ተከታይ የሆኑ እንኳን ያውቃቸዋል ለማለት አያስደፍርም፤›› በማለት ለቅርሶቹ ተገቢው ትኩረት እንደተነፈጋቸው ‹‹እስላማዊ ቅርሶች ዓይነትና ስርጭት ከሰሜን ሸዋ እስከ ደቡብ ወሎ›› በሚል በ2008 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ገልፀዋል፡፡

በመጽሐፋቸው በአማራ ክልል አልዩ አምባ፣ አበዱል ረሱል፣ ጎዜ፣ ጎንዶሬ፣ ገታ፣ ጀማ ንጉሥ፣ ሾንኬ፣ ጠለሐ፣ ገዶ፣ ዶዶታ፣ ጡርሲና በተባሉ ቦታዎች የሚገኙ የእስላማዊ ቅርሶች ታረካዊና ነባራዊ ሁኔታ አሳይተዋል፡፡ እንዲሁም በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ የሚገኙ ገቸኔ፣ ጨኔ፣ ገበሮች፣ ካይር አምባ፣ አሊ ግምብና መጠቅለያ በተባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችም የጽሑፋቸው አካል ነበሩ፡፡

በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ እስላማዊ ቅርሶች መካከል ‹‹የመለሳይ አገር መስጊድ›› አንዱ ነው፡፡ የመለሳይ አገር መስጊድ ከፍታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአግባቡ አለመያዙን በዙሪያው የሚገኙ ፍርስራሽ የድንጋይ ቤቶች እንደሚመሰክሩ ዶ/ር ሐሰን  በመጽሐፋቸው ይተርካሉ፡፡ መስጊዱ ስያሜውን ያገኘው ከኢማም አህመድ ጦር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ወደ ጎን 24 ሜትር፣ ቁመቱ ደግሞ 3.3 ሜትር ከፍታ ያለው የመለሳይ መስጊድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር የአካባቢው አዛውንቶች ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የመለሳይ መስጊድ እንኳንስ ምዕመናን ሊያገለግል ራሱን ችሎ መቆምም ተስኖታል፡፡ ጣሪያው ፈራርሶ የቀረው ግድግዳው ብቻ እንደሆነ ዶክተሩ የታዘቡትን አስፍረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሌሎች በርካታ ነገር ግን ያልታወቁ እስላማዊ መሠረት ካላቸው ቅርሶች በተቃራኒው በብዙኃኑ የሚታወቁ ድሬ ሼህ ሁሴን፣ የሶፍ ዑመር ዋሻም ተገቢውን ትኩረት አግኝተዋል ማለት እንደማያስደፍር አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አናጅና በተባለ ቦታ የሚገኘው ድሬ ሼህ ሁሴንን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ምን ያህል ገፍቶ መሄድ ተችሏል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ ድሬ ሼህ ሁሴን በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚከበሩ በዓላት መካከልዛራ ገልገላ ጎበናይጠቀሳል፡፡ ድሬ ሼህ ሁሴን የእስልምና እምነት ተከታቶች በዓመት ሁለት ጊዜ በአረፋና ለሼህ ሁሴን የትውልድ ቀን በዓላት ፈጣሪያቸውን የሚያመልኩበት ቦታ ነው። በዓላቱ እስከ 15 ቀናት እየተከበሩ የሚቆዩ ሲሆን፣ ምዕመናን በሥፍራው ቆይተው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን ያከናውናሉ።

እንደ ዶ/ር ሐሰን ገለፃ፣ በቅርስ አጠባበቅና አያያዝ ዙሪያ ለሚታዩ ችግሮች ማኅበረሰቡ በተለይም ሙስሊሙ በጥንታዊ መስጊዶች የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ያላቸውን ፋይዳ አለመረዳቱ ዋናው ችግር ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እንደ ብሔራዊ ቅርስ ሳይሆን የአንዱ ወገን ብቻ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዚህ ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አለመሥራቱ ዋና ዋና ክፍተቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...