መንግሥት የዜጎቹን መብት ለማስከበር የውጭ ሥራ ሥምሪትን አስመልክቶ የሁለትዮሽ ስምምነት ካደረገባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች አንዷ ከሆነችው ከሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያዎችንና ቢሮዎችን በመወከል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው የሳዑዲ ልዑካን ቡድን፣ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ያደረገው የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ውድቅ መደረጉ ታወቀ፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተለይ በቤት ሠራተኝነት በሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ላይ ይፈጸም የነበረን የሞት፣ የአካል መጉደልና የተለያዩ እንግልቶችን በመመልከት ዜጎች እንዳይሄዱ ከአራት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ ዕግድ መጣሉ ይታወሳል፡፡
መንግሥት ቀደም ብሎ የነበረውን የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 632/2001ን በአዋጅ ቁጥር 923/2008 በመቀየር፣ የውጭ ሥራ ሥምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች አሠሪ ማኅበር አባላትን መብትና ጥቅምን ለማስከበር ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
መንግሥት ስምምነቱን ከፈጸመ በኋላ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አገልግሎት ሰጪ ማኅበር፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኩባንያዎችንና ቢሮዎችን ወክሎ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው ቡድን ጋር አዲስ አበባ በሚገኘው ሮያል ሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ውስጥ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ እንደነበር ሪፖርተር ካገኛቸው ሰነዶች አረጋግጧል፡፡
ማኅበሩ ከልዑካን ቡድኑ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረም፣ ቡድኑ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኩባንያዎችንና ቢሮዎችን መወከሉን የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ሰነድ እንደሚያሳይ በተደጋጋሚ የገለጸ ቢሆንም ሊያቀርብ አለመቻሉ ተጠቁሟል፡፡
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዳይሬክቶሬት ጽሕፈት ቤት በመግባቢያ ሰነዱ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውንና ልዑኩ ሕጋዊ ወኪል ስለመሆኑ የሚያረጋግጡ ሰነዶች ሊካተቱ እንደሚገባ ቢያሳስብም፣ የልዑካኑ ቡድን ተግባራዊ አለማድረጉም በሰነዶቹ ተገልጿል፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑካን ቡድን ከላይ የተገለጹትን ሕጋዊ ሰነዶች ሊያሟላ ባለመቻሉ፣ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች አሠሪ ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ የልዑካን ቡድኑ ምላሽ ሊሰጥ እንዳልቻለ በመነጋገር ተፈራርሞ የነበረውን የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ እንዳደረገውና በግልባጭም ለሚኒስቴሩ ማሳወቁ ታውቋል፡፡
ማኅበሩ ቡድኑ ‹‹እወክላቸዋለሁ›› ያላቸው ኩባንያዎችን አሠራር ለማወቅ ባደረገው ጥረት፣ ኩባንያዎቹ ሠራተኞችን ከኤጀንሲዎች ጋር ተፈራርመው ከወሰዱ በኋላ በሳዑዲ ለሚገኙ ሠራተኛ ፈላጊዎች መቅጠር ሳይሆን፣ የማከራየት ወይም በሥራው ልክ ተነጋግረው በተስማሙት ክፍያ እንዲሠሩ ማድረግ መሆኑን ለማወቅ መቻሉን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም አሠራሩ ሕጉን የሚጥስ መሆኑንም አክሏል፡፡ ሠራተኞች የሚቀጠሩበት ክፍያም የሌሎች አገሮች ዜጎች ከሚከፈላቸው ዋጋ በታች ወይም እስከ 700 ሪያል ድረስ ልዩነት እንዳለው ለሚመለከተው አካል ማሳወቁ በሰነዱ ተጠቅሷል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ጉዳዩን በድጋሚ በማጤን፣ የዜጎችን ጉዳት ወደኋላ ብለው የራሳቸውን ጥቅም ለማጋበስ ሃይማኖትንና ቋንቋን ሽፋን በማድረግ የሚሯሯጡ ጥቂት የኤጀንሲ ባለቤቶች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርጉና ዕርምጃ እንዲወስዱ ማሳሰቡን ሰነዱ ያሳያል፡፡