Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ላቀረቡት ምርት ክፍያ ያጡ አገር በቀል ኩባንያዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቀረቡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቱርክ ኩባንያ ኤልሲ አዲስ ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት ጥጥ በብድር ሲያቀርቡ የቆዩ 12 አገር በቀል ኩባንያዎች ክፍያ ስላልተፈጸመላቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን በመግለጽ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠየቁ፡፡

አሥራ ሁለቱ ጥጥ አምራቾች በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምቤላ ክልሎች በእርሻ ሥራ የተሠማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አምራቶቹ በአገር በቀልና በውጭ ባለሀብቶች ለተቋቋሙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጥጥ ሲያቀርቡ የቆዩ መሆናቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ኤልሲ አዲስ ኢንዱስትሪያል 22.2 ሚሊዮን ብር ሳይከፍላቸው ከአገር መውጣቱን፣ ኅዳር 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሰጠው ብድር ባለመመለሱ ይህንን ፋብሪካ የወረሰ ሲሆን፣ ፋብሪካው በባንኩ ቁጥጥር ሥር ሆኖ የዕለት ተዕለት ሥራውን በማካሄድ ላይ ነው፡፡

‹‹ኤልሲ አዲስ ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት በ2008 ዓ.ም. ያመረትነውን ጥጥ  በጥሩ ዋጋ እገዛችኋለሁ በማለት ለእያንዳንዳችን የሰጠን ቼክ በዝርዝር የቀረበ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ 22,238,438 ብር እንዲከፍለን በተናጠልም ሆነ በጋራ ብንጠይቅም፣ ድርጅቱ ከዛሬ ነገ ይከፍላችኋል እያለ ሲያዘናጋ ከቆየ በኋላ ከውጭ ያመጣቸውን ሠራተኞች ይዞ ከአገር ወጥቷል፤›› ሲሉ አገር በቀል ጥጥ አምራቾች በጻፉት ደብዳቤ ገልጸው፣ ‹‹ፋብሪካው ለሰጠው ብድር ዋስትና የያዘው የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ጥጡን ተጠቅሞ ቢያመርትም፣ ክፍያውን ግን ላለመፈጸም አንገራግሯል፤›› ሲሉ አምራቾቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አምራቾቹ ላመረቱት ምርት ዋጋውን ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር እንደተዳረጉ በመግለጽ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ችግራቸውን እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል፡፡

ኤልሲ አዲስ ኢንዱስትሪያል ከመወረሱ በፊት የፋብሪካው ፋይናንስ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተፈራ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አምራቾቹ ጥጥ አቅርበዋል፡፡ በወቅቱ ሊከፈላቸው ግን አልተቻለም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወረሰው በኋላ የአቅራቢዎቹን ጥጥ ተጠቅሞ ምርት አምርቷል፡፡ ክፍያቸውንም ሊፈጽም ይገባ ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡   

ኤልሲ አዲስ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በ150 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ የተገነባ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነው፡፡ ፋብሪካው ለግንባታ የሚሆን ገንዘብ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበደረ ሲሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ ባለቤቶቹ ከአገር ወጥተዋል፡፡ ልማት ባንክ ኦፕሬሽኑን እያካሄደ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታሁን ናናን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች