Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ የ13 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ባላቸው ፕሮጀክቶች አማካይነት ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ያደረገውን የኢትዮጵያ የአጋርነት ማዕቀፍ የድጋፍ ሰነድን በማስመልከት ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ የ13 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ባላቸው ፕሮጀክቶች አማካይነት ለአገሪቱ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት፣ ባንኩ በአገሪቱ ድጋፍ በሚሰጥባቸው ፕሮጀክቶች አማካይነት የሚመዘገቡት ውጤቶች ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ይልቅ የባንኩን ድጋፍ በማግኘት ቀዳሚ እንድትሆን አብቅተዋታል፡፡

በአገሪቱ ለሚታዩት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ፕሮግራሞችን በቴክኒክና በፋይናንስ እየደገፈ የሚገኘው የዓለም ባንክ፣ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚተገበረውን የአጋርነት ማዕቀፍ ሰነድ ከቀናት በፊት ይፋ ማድረጉ አይነዘጋም፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ዳይሬክተሯ በሰጡት ማብራሪያ፣ ባንኩ ድጋፍ እያደረገባቸው ከሚገኙት ሥራዎች መካከል ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚውለው አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋው የፋይናንስ ድጋፍ ይጠቀሳል፡፡

በአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ በዚህም የትምህርት ዘርፉ እንዲስፋፋ፣ የገጠርና የከተማ ምርታማነት እንዲጨምር፣ ወጣቶች ሥራ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ የሚያተኩረው የአጋርነት ማዕቀፉ አንዱ ተልዕኮ ነው፡፡ አሳታፊና ለቀውሶች የማይገበር የኢኮኖሚ አቅም እንዲፈጠር ማገዝ በሚለው የባንኩ የአጋርነት ማዕቀፍ ውስጥ ከሚካቱት ውስጥ፣ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ይጠቀሳል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ከ14 ሚሊዮን ያላነሱ ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግሮች በመዳረጋቸው፣ ባንኩ ለዕለት ደራሽ ዕርዳታዎች እንዲሁም ለሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህም ሆኖ በአገሪቱ በየጊዜው የድህነት መጠን እየቀነሰ ቢመጣም፣ ከድርቅና ከምርታማት መቀነስ ጋር በሚያያዙ በምግብ ዋስትና ችግሮች ሳቢያ የሚያጋጥመው ፈታኝ ሁኔታ ባንኩ ከሚጠቅሳቸው ችግሮች መካከል ይመደባሉ፡፡ የሕፃናት መቀንጨርና የተመጣጠነ ምግብ ማጣትም የአገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል፡፡ የጤና፣ የትምህርት ሽፋን፣ የውኃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን አገልግሎቶችን ጨምሮ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በአዲሱ የአጋርነት ማዕቀፍ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲህ ያሉ ግቦችን ለማሳካት ባንኩ መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉና የሙስና ወንጀሎች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አሠራሮችንም እንደሚከተል ይፋ አድርጓል፡፡ መንግሥት የሚተገብራቸውን ፕሮጀክቶች ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን ባንኩ የሚንቀሳቀስባቸውን ማዕቀፎች እንዳከተተ የገለጹት ካሮሊን ተርክ፣ ከዚህ ቀደም በባንኩ ድጋፍ በአገሪቱ ሲተገበር በቆየውና በመንደር ማሰባሰብ በሚባለው ፕሮጀክት አማካይነት ስለደረሰው ችግርም ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸው አብራርተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2012 በባንኩ ፀድቆ የ600 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ የተለቀቀለትና የመሠረታዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት (Promoting Basic Services) ምዕራፍ ሦስት ትግበራ ፕሮግራም፣ በመንግሥትና በባንኩ ላይ ተቃውሞን አስከትሎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በአኙዋ ጎሳ አባላት አማካይነት ለባንኩ የኢንስፔክሽን ቡድን የቀረበውን ጥሪ መነሻ በማድረግ በተካሄደ ምርመራ፣ የጋምቤላ ክልል መንግሥት 45 ሺሕ አባወራዎችን በመንደር የማሰባሰብ ዕቅድ ነበረው፡፡ ይህም በክልሉ ከሚገኙ አባወራዎች ውስጥ 70 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ዕቅድ እንደነበር አጣሪው ቡድን ከሦስት ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርት ጠቅሶታል፡፡ ከክልሉ ዕቅድ ውስጥ 37,883 ወይም 60 በመቶው አባወራዎች በአንድ መንደር እንዲሰባሰቡ መደረጉንም የአጣሪው ቡድን ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ይህ በመሆኑም ባንኩ ለማኅበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች የተቀመጠውን የጥበቃ መሥፈርት አላከበረም ተብሎ ተተችቷል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድም ስለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጥ አስገድዶት ነበር፡፡

እንዲህ ያሉ ስህተቶች እንዳያጋጥሙ ባንኩ እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ሪፖርት ውጪ እስካሁን በአካባቢና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የባንኩን አቋም በሚጣረሱ ፕሮጀክቶች ውስጥ አለመሳተፉን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ቢሆን ባንኩ ለሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ግምገማ እያደረገ የሚስከትሉት አካባቢያዊና ማኅበራዊ ጉዳት እየተፈተሸ ፕሮጀክቶችን እንደሚያፀድቅ አብራርተዋል፡፡  የመንግሥትን አቅም ለመገንባት ረጅም ጊዜ በመውሰዱ ምክንያት የተፈጠረ ክፍተት እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ የባንኩን ድጋፍ በማግኘት በአፍሪካ ቀዳሚ እንደሆነች ያብራሩት ዳይሬክተሯና የሥራ አጋሮቻቸው፣ ቃል በተገባውም ሆነ ባንኩ በለቀቃቸው የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ረገድ ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት እያሳየች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡ ባለው ዓመት የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ብድር መልቀቁን የባንኩ ኃላፊዎች ጠቁመው፣ በዚህ ዓመትም 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚለቀቅ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአማካይ በየዓመቱ ቃል ከተገባው ውስጥ ከ39 እስከ 42 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ እየተለቀቀላት እንደምትገኝ ያስታወቁት ካሮሊን፣ ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚውል የአምስት ቢሊዮን ዶላር አዲስ የፋይናንስ ማዕቀፍ በመምጣቱ፣ በጠቅላላው የ13 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ፕሮጀክቶች በባንኩ ድጋፍ እየተደረጋላቸው ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የአጋርነት ስትራቴጂ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ እንደነበረው የባንኩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች