Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሠራው የእንቦጭ መንቀያ ማሽን አጥጋቢ ሙከራ ማድረጉ ተገለጸ

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሠራው የእንቦጭ መንቀያ ማሽን አጥጋቢ ሙከራ ማድረጉ ተገለጸ

ቀን:

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመንቀል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አማካይነት የተሠራው ማሽን አጥጋቢ ሙከራ ማድረጉ ታወቀ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ማሽኑን ለመሥራት ሙከራ ሲደረግ ቆይቶ፣ ሰሞኑን በተደረገው ጥረት ማሽኑ አረሙን መንቀል እንደቻለ ታውቋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለሪፖተር እንደተናገሩት፣ የአገሪቱንና የክልሉን ሕዝብ ሊያኮራ የሚችል ማሽን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ተሠርቶ አረሙን በመንቀል ላይ ይገኛል፡፡ ማሽኑ በሰዓት 50 ኩንታል አረም መንቀል እንደሚችልም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከብዙ ጥረትና ልፋት በኋላ ተሞክሮ አጥጋቢ ውጤት እንዳስመዘገበ የሚነገርለት ማሽን፣ አሁንም ቢሆን መሻሻል የሚቀሩት ሥራዎች እንዳሉ አቶ ንጉሡ አስረድተዋል፡፡

በዓመት ከ13 ሺሕ ቶን በላይ የዓሳ ምርት እንደሚመረትበት የሚነገረው የጣና ሐይቅ፣ እስካሁን ከ5,000 ሔክታር በላይ የሐይቁ ክፍል በአረሙ ተሸፍኖ እንደሚገኝ አቶ ንጉሡ ገልጸዋል፡፡

ጣናን የወረረው ዓረም ከዚህ በሰፋ መጠን የጣና ሐይቅን ሸፍኖ እንደነበር የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በዙሪያው ባሉ አርሶ አደሮች፣ በክልሉ ወጣቶችና ከኦሮሚያ ክልል ‹‹ጣና ኬኛ›› ብለው በመጡ ወጣቶች አማካይነት መጠኑ ሊቀንስ እንደቻለ አስረድተዋል፡፡

ከአረሙ በቶሎ የመስፋፋት ባህሪ የተነሳ በቀላሉ በሰው ጉልበት ተነቅሎ የማያልቅ እንደሆነ በመገንዘብ፣ የክልሉ መንግሥት አረሙን ለማስወገድ ማሽን ለመግዛት ጨረታ ማውጣቱን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የክልሉ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት አድርጎት በነበረው ጉባዔ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ‹‹የክልሉ መንግሥት ሌላው ልማት ይቀራል እንጂ ጣናን ለመታደግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ማሽኑ ከተገኘ ለመግዛት ወስነናል፡፡ በጣና ጉዳይ አንደራደርም፤›› ብለው ነበር፡፡

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረምን ለመከላከል የባህር ዳርና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ጥናት ሲያደርጉ እንደነበር መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሠርቶ ያቀረበው ማሽን አበረታች ውጤት እንደታየበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከውጭ አገር ጢንዚዛዎችን በማምጣት እያራባ የሚገኘው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ጢንዚዛዎችን ወደ ሐይቁ በመልቀቅና አረሙን እንዲበሉት የሚያደርገውን ሙከራ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ ዩኒቨርሲቲው አረሙን ለመንቀል በዝግጅት ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ቢሰማም፣ እስካሁን ድረስ ውጤታማ ሥራ ማከናወን አለመቻሉ ይታወሳል፡፡

የእንቦጭን አረም ለመከላከል የተለያዩ ተቋማትና ባለሀብቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ሲነገር ቢሰማም፣ እስካሁን ከዳሸን ባንክ በስተቀር የተደረገ የገንዘብ ድጋፍ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዳሸን ባንክ የእንቦጭን አረም ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ያግዝ ዘንድ፣ ሁለት ሚሊዮን ብር ስጦታ ለአማራ ክልል መንግሥት አበርክቷል፡፡

ኅዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተካሄደው የስጦታ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት አቶ ንጉሡ፣ እንቦጭ ከጣና አልፎ ወደ ዓባይ ወንዝ መሸጋገሩን ተናግረዋል፡፡ አረሙ በዚህ ከቀጠለና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመረባረብ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ መረጋገጡንም ጠቁመዋል፡፡

አረሙን ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት እገዛ አናሳ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ መነሳቱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ያለው ድጋፍና ክትትል አበረታች እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ቢሆን በቂ እንዳልሆነ የክልሉ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት አድርጎት በነበረው ጉባዔ ላይ ተገልጿል፡፡

ከ5,000 በላይ ዜጎች ሕይወታቸው ከጣና ሐይቅ ጋር እንደተቆራኘ የሚነገር ሲሆን፣ የእነሱን ህልውናና የሐይቁን ተፈጥሮአዊ ሀብት ጠብቆ ለማቆየት አሁንም ድረስ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አሻራ የሚፈልግ እንደሆነ የአማራ ክልል ጉባዔውን ባደረገበት ወቅት ወስኗል፡፡

በዚህም የተነሳ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የክልሉ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...