Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ የፍጥነት መንገዶች ግንባታ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በኢትዮጵያ እየተገነቡ ለሚገኙና ወደፊት እንደሚገነቡ ለሚታሰቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ድጋፍ የመስጠት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ፡፡ በአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ለመሳተፍ የኮሪያ መንግሥት ኩባንያ ከመንግሥት ጋር ድርድር ጀምሯል፡፡

የኮሪያ የፍጥነት መንገድ ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኡም ኢን ሱብ፣ በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ ተገኝተው ከትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና ከሌሎችም የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር  ተነጋግረዋል፡፡ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣ ሚኒስትር አህመድ እንዳስገነዘቧቸው ኢትዮጵያ ከፋይናንስ ባሻገር የኮሪያ ባለሙያዎችን ትፈልጋለች፡፡ በመንገድ፣ በባቡርና በማሪታይም መስክ የሠለጠኑ ኮሪያውያንን ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ ለኢን ሱብ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ አህመድ በፕሮጀክት ዕቅድ፣ በዲዛይን፣ በፕሮጀክት ክትትልና ትግበራ ረገድ ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎችን ከኮሪያ እንዲመጡ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

የኮሪያ የፍጥነት መንገድ ኮርፖሬሽን ኃላፊው በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብበር ለመሥራት ፍላጎት መኖሩን፣ በፋይናንስና በቴክኒክም ድጋፍ እንደሚደረግ ለሚኒስትሩ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከኮሪያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ከኮሪያ ዘመቻ ጋር እንምታያይዘው የገለጹት ኢን ሱብ፣ ኢትዮጵያ ለኮሪያ ነፃነት የከፈለችውን መስዋዕትነት እንደሚዘክሩም ጠቅሰዋል፡፡ አቶ አህመድ በበኩላቸው የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት በደምና በመስዋዕትነት የተሳሰረ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

ይሁንና ባለፈው ዓመት በተደረሰው ስምምነት መሠረት የኮሪያ የፍጥነት መንገድ ኮርፖሬሽን ከነቀምት እስከ ቡሬ በሚዘረጋው የመንገድ ግንባታ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታ 5.7 ቢሊዮን ብር መመደቡም ይታወሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ370 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በኮሪያ ኤግዚም ባንክ፣ በቻይና ኤግዚም ባንክና በዓለም ባንክ ድጋፍ በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተገነባ የሚገኘው የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ሥራ ውስጥም ኮርፖሬሽኑ ተሳትፎ እንዳለው ሁለቱ ኃላፊዎች አስታውሰዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የኮሪያ የፍጥነት መንገድ ኮርፖሬሽን ኃላፊ ጄኡንግ ኪም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በአዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ለመሳተፍ ድርድር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሆኖም የፕሮጀክቱ ዝርዝር ይዘት በቅርቡ እንደሚገለጽ ጠቁመዋል፡፡

የኮሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከ690 ሚሊዮን ዶላር ግምት ባላቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ከሥልጣናቸው በተሰናበቱት በፕሬዚዳንት ፓርክ ጌዩን-ሃይ አስተዳደር ወቅት በተፈረሙ ስምምነቶች መሠረት፣ የኮሪያ መንግሥት የወጪና ገቢ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ከሚካሄዱ ፕሮጀክቶች መካከል የፍጥነት መንገዶች የልማት ድጋፍ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት የባለብዙ አገሮች ድጋፍ ያለው ሲሆን፣ የኮሪያ መንግሥት 227 ሚሊዮን ዶላር ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበት ብድር መፍቀዱም ይታወሳል፡፡ ለመንገድ ማሻሻያ ከተጠሰው የ117 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ፣ ለግብርና ዘርፍ የተፈቀደው የ100 ሚሊዮን ዶላር ብድርም ባለፈው ዓመት ከተደረጉ የፋይናንስ ስምምነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ሰፋፊ የፋይናንስ ስምምነቶችን ያስተናገደው ያለፈው ዓመት ክንውን፣ ዘንድሮም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እንደሚያካትት ከሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት ጉብኝት እየታየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ልዑክ በቅርቡ ወደ ኮሪያ በማቅናት ጉብኝት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎም ከኮሪያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የተውጣጡ ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ኩባንያዎችን የሚመሩ ሹማምንት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ድርድሮችን ለማፋጠን እየሞከሩ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች