Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ነዳጅ ድርጅት የአንድ ዓመት ነዳጅ ግዥ ውል ተፈራረመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለ2010/2011 በጀት ዓመት ፍጆታ የሚውል የነዳጅ አቅርቦት ስምምነት ትራፊጉራ ከተሰኘ የስዊዘርላንድ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከኩዌትና ሱዳን መንግሥታት ጋር በገባው ውል መሠረት አብዛኛውን ነዳጅ የሚገዛው ከሁለቱ አገሮች ሲሆን፣ የተቀረውን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በየዓመቱ በሚያወጣው ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶችን አወዳድሮ ይገዛል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በመስከረም 2010 ዓ.ም. ባወጣው ጨረታ፣ ተቀማጭነቱ በጄኔቭ ስዊዘርላንድ የሆነው ትራፊጉራ የተሰኘው ኩባንያ አሸናፊ መሆኑ ታውቋል፡፡ የጨረታ ሰነዱን 14 ኩባንያዎች የገዙ ቢሆኑም የጨረታ ሰነዱን የመለሱት አምስት ብቻ ናቸው፡፡ ፔትሮ ቻይና፣ ቪቶል ኦይል፣ ትራፊጉራ፣ ኢኖክና አፍሮ ዓረብ የተሰኙ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ ለጨረታ ኮሚቴ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአምስቱ ተጫራች ኩባንያዎች የተሟላ የቴክኒክና የፋይናንስ ሰነድ ያቀረቡት ፔትሮ ቻይና፣ ቪቶል ኦይልና ትራፊጉራ ናቸው፡፡ ከሦስቱ ተጫራች ኩባንያዎች ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበው ትራፊጉራ በመሆኑ የጨረታው አሸናፊ ለመሆን እንደቻለ አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡

የጨረታው ውጤት ለተሳታፊ ኩባንያዎች የተገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከአሸናፊ ኩባንያው ጋር የነዳጅ ግዥ ስምምነቱን ኅዳር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያምና የትራፊጉራ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ረሻድ ኩሳድ ናቸው፡፡

የ2010/2011 በጀት ዓመት የአገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በአጠቃላይ የሚገዛው 408,378 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን፣ 2,546,786 ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣ፣ 661,790 ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅ፣ 124,914 ሜትሪክ ቶን ነጭ ጋዝ፣ 38,805 ሜትሪክ ቶን ቀላል ጥቁር ናፍጣና 39,470 ሜትሪክ ቶን ከባድ ጥቁር ናፍጣ እንደሆነ ታውቋል፡፡

አገሪቱ በአጠቃላይ ለምትገዛው 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚወጣ ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱን 80 በመቶ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያሟጥጥ ታውቋል፡፡ ከአጠቃላይ የነዳጅ ፍጆታ ውስጥ 65 በመቶ ነጭ ናፍጣ፣ ቤንዚን አሥር በመቶ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 17 በመቶ፣ ነጭ ጋዝ ሦስት በመቶና ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ አምስት በመቶ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ ነጭ ናፍጣ የሚያቀርበው ንብረትነቱ የኩዌት መንግሥት የሆነው ኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ነው፡፡ የአውሮፕላን ነዳጅና ነጭ ጋዝ ፍጆታ ሙሉ በሙሉ የሚያቀርበው ይኼው የኩዌት ኩባንያ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ንብረትነቱ የሱዳን መንግሥት የሆነው ሱዳን ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን 40 በመቶ የሚሆነውን የቤንዚን ፍጆታ ያቀርባል፡፡  

ባለፈው ሳንምት በተገባው ውል መሠረት ትራፊጉራ 245,000 ሜትሪክ ቶን ቤንዚንና 1,270,000 ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣ ከጥር 2010 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2011 ዓ.ም. ድረስ ያቀርባል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ታደሰ፣ ትራፊጉራ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በየዓመቱ በሚያወጣው ጨረታ ሲካፈል መቆየቱን ገልጸው ኩባንያው ጨረታውን ሲያሸንፍ ለመጀመርያ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ ትራፊጉራ በዓለም ቀዳሚ ከሆኑት የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ በነዳጅ አቅርቦት መሠረተ ልማት ያለውን ፈታኝ ሁኔታ ተቋቁሞ የነዳጅ ውጤቶቹን በወቅቱ እንደሚያቀርብ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡  

‹‹በጂቡቲ ሆራይዘን የነዳጅ ተርሚናል የአቅም ውስንነት አለ፡፡ ይህን ሁሉ ተቋቁማችሁ ነዳጁን በወቅቱ ማቅረብ ይኖርባችኋል፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፡፡ ትንሽ ችግር ከፈጠራችሁ 100 ሚሊዮን ሕዝብ እንደምትጎዱ ማወቅ አለባችሁ፤›› ብለዋል፡፡

የትራፊጉራ ተወካይ ረሻድ ኩሳድ በበኩላቸው ኩባንያቸው በቅርቡ በህንድ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ መግዛቱን ጠቁመው፣ ለኢትዮጵያም ነዳጁን የሚቀርበው ከህንድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትራፊጉራ በተለያዩ አገሮች የነዳጅ ምንጮች ያሉት በመሆኑ በአንድ ምንጭ ብቻ እንደማይተማመን ገልጸው፣ ነዳጁን ከተለያዩ አገሮች ለማቅረብ እንደሚችል ሚስተር ኩሳድ አስረድተዋል፡፡

‹‹ያሉባችሁን የአቅም ውስንነት እናውቃለን፡፡ በምንም ዓይነት በአቅርቦቱ ላይ እንከን እንደማይፈጠር ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤›› ያሉት ሚስተር ኩሳድ፣ ትራፊጉራ  ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ለአንድ ሥራ ብቻ ሳይሆን የረዥም ጊዜ ራዕይ ሰንቆ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ትራፊጉራ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሱዳን ገበያ ውስጥ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ለሱዳን 250,000 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ በማቅረብ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የትራፊጉራ ዋና መሥሪያ ቤት በጄኔቭ ስዊዘርላንድ የሚገኝ ሲሆን በሲንጋፑር፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና በደቡብ አፍሪካ ክልላዊ ጽሕፈት ቤት እንዳለው ታውቋል፡፡ ትራፊጉራ በተለያዩ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀስ ፑማ ኢነርጂ የተሰኘ እህት ኩባንያ እንዳለው ታውቋል፡፡ ትራፊጉራ በፑማ ኢነርጂ ላይ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለው ሲሆን፣ 51 በመቶ በአንጎላ መንግሥት የተያዘ ነው፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከትራፊጉራ ጄኔቭ፣ ሲንጋፑር፣ ዱባይና ጆሃንስበርግ ጽሕፈት ቤት የመጡ ሰባት ኃላፊዎችና የኩባንያው የኢትዮጵያ ተወካይ ተገኝተዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች