Thursday, December 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ቃልና ተግባር ሳይጣጣሙ መንግሥት የሕዝብ አመኔታ እንደማያገኝ ማመን አለበት!

የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መሥራችና ዋነኛ አባል የሆነው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ35 ቀናት ያካሄደውን የግምገማ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ፣ በራሱ ላይ የሰላ ሒስ በማካሄድ የእርምት ዕርምጃና የአመራር ሽግሽግ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ሕወሓት ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ አስተማማኝ መሆኑን፣ ፈተናዎች በገጠሙት ቁጥር ራሱን በሚገባ እየፈተሸና ወቅቱን የጠበቀ ማንኛውም ዓይነት ዕርምጃ በመውሰድ ጥንካሬዎቹን የሚያጎለብት፣ ድክመቶቹን ያለምሕረት በማስወገድ በመስዋዕትነት የደመቀ ታሪክ መሥራት የቻለ አመራር ባለቤት መሆኑን፣ ከእህትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተከፈለ እጅግ ከባድ መስዋዕትነት አዲሲቷን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ መቻሉን አስታውቋል፡፡ በአገሪቱም ታሪክ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የህዳሴ ምዕራፍ መከፈቱን በአፅንኦት ገልጿል፡፡ እንዲህ ዓይነት ስኬት አለኝ የሚል ድርጅት ምን ገጥሞት ነው አገሪቷና ሕዝቡ ችግር ውስጥ የገቡት? አባል የሆነበት ግንባር ማለትም ኢሕአዴግ ምን ቢፈጠርበት ነው አገሪቷን ቀውስ ውስጥ የከተተ ትርምስ የተፈጠረው? መልሱ ቀላል ነው፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ሕወሓት የሚናገሩትና ተግባራቸው ለየቅል መሆኑ ነው፡፡ ሕዝብን አለማዳመጥና ለፍላጎቱ ተገዥ አለመሆንም ልማድ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርቶችና ግምገማዎች ችግሮችን ማድበስበስ በመለመዱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አመኔታ አሳጥቷል፡፡  

ሕወሓት የገዥው ግንባር አስኳል እንደ መሆኑ መጠን በትጥቅ ትግል ታሪኩና ከዚያም በኋላ ነበሩኝ በሚላቸው ስኬቶቹ ላይ ብቻ በመንጠልጠል ሕዝብን ረስቷል፡፡ እንኳንስ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ፣ የትግል ጓዶቹ የከፈሉትን የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት በመርሳት ሌላ ዓለም ውስጥ ገብቷል፡፡ ራሴን በራሴ ገመገምኩኝ ባለው መሠረት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ስትራቴጂካዊ አመራሩ በመዳከሙ ተልዕኮውን መወጣት አልቻለም፣ አደረጃጀቱ ተሸርሽሯል፣ ሕዝባዊነቱ ቀንሷል ወይም የለም የሚባልበት ደረጃ ደርሷል፣ የሕዝቡን ችግር መፍታት አቅቶት በትንንሽ ድሎች የሚረካ በመሆን የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ግምገማዎቹ የይስሙላ፣ አስተሳሰቡ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ለራሳቸው ጥቅምና ክብር የሚዳክሩ አመራሮች ያሉበት ድርጅት በመሆን ራሱንና አገርን ችግር ውስጥ መክተቱን ማመኑ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ግምገማ እውነት ከሆነ የሚፈለገው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ከአስመሳይነትና ከሸንጋይነት የተላቀቀና ቃልና ተግባር የሚጣጣሙበት መሆኑ በገቢር መታየት አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ማዕበሉን በዘዴ ለማለፍ የተሞከረ ብልጥነት ከሆነ አደጋው የከፋ ነው፡፡

የሕወሓትን ግምገማ መሠረት በማድረግ አገርን የሚመራውን ኢሕአዴግ በወፍ በረር ማየት ተገቢ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ አሁንም ትልቅ የሚባል ተፅዕኖ ያለው ሕወሓት በአመራሩ ውስጥ የታየው ድክመት በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የአመኔታ መሸርሸር ችግር መፍጠሩን ማመኑ እንዳለ ሆኖ፣ ሰፋ አድርገን ስናይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ  ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት ላይ ያለው እምነት በጣም መሸርሸሩን መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ኢሕአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት የሠራውን ያህል መወደስ ያልቻለው፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር ባለመቻሉ ነው፡፡ አገሪቱን ወደ ሌላ ምዕራፍ እያሸጋገረ ያለው ልማት በሕዝብ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ለምን አልፈጠረም ሲባል፣ ትንሽ ችግር ሲያጋጥም መሠረተ ልማቶችና ኢንቨስትመንቶች ሲወድሙ የሚታየው በዚህ ምክንያት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርቶችና በተድበሰበሱ ግምገማዎች የታጀቡ ተሃድሶዎች በሕዝብ ዘንድ እምነት በማጣታቸው ሳቢያ፣ መንግሥት የሚናገረውና በተግባር የሚያሳየው በመለያየቱ ምክንያት አገሪቱ ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶችን ማስከበር ባለመቻሉ ቅሬታዎች ወደ ቅራኔ አድገው፣ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋትና አካል መጉደል ብሎም እንግልት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው መጤ እየተባሉ ከየክልሉ ሲባረሩና ሀብታቸው ሲዘረፍ፣ የሕዝቡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በብሔርተኞች እየተናደ ግጭቶች ሲስፋፉ፣ የሕዝቡን መብት የሚያፍኑ የመጨቆኛ መሣሪያ የሆኑ ሕጎች እየወጡ ከፍተኛ ጥፋት ደርሷል፡፡ በዚህ መሠረት ጥፋትን አምኖ ከሕዝብ መታረቅ ተገቢ ነው፡፡ አመኔታ የሚገኘው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

የአንድ መንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት የሕዝብን ሰላም፣ ደኅንነትና ጥቅሞች ማስከበር መሆኑ እየታወቀ፣ ለዓመታት ሕዝብን የሚያዳምጥ በመጥፋቱ ብቻ አገር ላለፉት ሦስት ዓመታት ችግር ውስጥ ናት፡፡ የሥልጣን ጥያቄ ከሚያቀርቡ ወገኖች ጀምሮ የፍትሕ ዕጦት፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መገለል፣ በነፃነት መደራጀትና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ማጣት፣ በሐሰተኛ ክስ ፍዳ መቁጠር፣ በገዛ አገር ባይተዋር መሆን፣ ከብሔራዊ ጉዳዮች ተሳትፎ መገለል፣ ወዘተ. ምክንያት የተጠራቀሙ ብሶቶች አገሪቷን አጣብቂኝ ውስጥ ከተዋታል፡፡ ይህ ሁሉ ችግርና መከራ በደረሰበት አገር ውስጥ ምንም ያልተፈጠረ ይመስል፣ ነገሮችን ባሉበት እንዲቀጥሉ የማድረግ አምባገነናዊ ፍላጎቶች በስፋት ሲታዩም ነበር፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌበት አገር ውስጥ ምን አገባን በማለት የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት አንቀሳቃሾች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዝምታ ተሸብበዋል፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸውም ሆነ በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖዎች ምክንያት ተሽመድምደዋል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ጠቃሚ ነገሮች ተዳፍነዋል፡፡ ምርጫ መቀለጃ እስኪመስል ድረስ ዋጋ ቢስ ሆኗል፡፡ ገዥው ፓርቲ ውስጥ አባል መሆን በሥልጣን አማካይነት ጥቅም ለማጋበስ አቋራጭ መንገድ በመሆኑ፣ የአገሪቱ ሀብት የዘራፊዎች ሲሳይ ሆኗል፡፡ ሕዝብ ደግሞ ለጉስቁልና ተዳርጓል፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ተስፋ በመቁረጥ በስደት የበረሃና የባህር ሰለባ ሆኗል፡፡ የቀረው ደግሞ ተስፋው ጨልሞ ባገኘው አጋጣሚ ያሻውን ዕርምጃ ለመውሰድ የማይመለስ መስሏል፡፡ በተግባርም ታይቷል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አስፈሪ ቀውስ እንዴት ነው መውጣት የሚቻለው? የአሁኑ ራስን መውቀስና ቃል መግባት ቁርጠኛ መልስ ይዞ ይመጣል? ወይስ የተለመደው አዙሪት ውስጥ መዳከር ነው? ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ታጋሽና አስተዋይ ሕዝብ ኢሕአዴግንም ሆነ የሚመራውን መንግሥት በትዕግሥት ጠብቋል፡፡ ይህ ትዕግሥት መጠኑ አልፎ በመጠኑ ሲገነፍል በቅርቡ የደረሰውን አደጋ ማየት ተችሏል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚኖረው መገንፈል የሚፈጥረው ማዕበል አገርን ቀውስ ውስጥ እንደሚከት በጥሞና ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ማግኘት የሚቻለው እንደተለመደው ቃል ገብቶ እብስ በማለት አይደለም፡፡ የተገባው ቃል በቁርጠኝነት ወደ ተግባር ይተረጎም ዘንድ ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ በአደባባይ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በምላሹ ላይም በመመሥረት የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ የግድ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ በመጀመርያ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዱ፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የሕዝብን ፍላጎት የሚያስተናግድ አሠራር ይዘርጋ፡፡ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ፣ በፈለጉት የፖለቲካ ድርጅት እንዲደራጁ፣ ሲቪክ ማኅበራት ያለምንም ተፅዕኖ እንዲያብቡ፣ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ፣ ለአምባገነንነት መስፈን ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በነፃነት ሁሉንም ወገን በእኩልነት እንዲያስተናግዱ፣ ለብሔራዊ ጉዳዮች መነጋገሪያ መድረኮች በአስቸኳይ እንዲዘጋጁ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ በፍጥነት ተከፍቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ በሠለጠነ መንገድ እንዲካሄድ፣ ለነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መደላድሉ እንዲመቻች፣ ወዘተ. ራስን ማዘጋጀት የወቅቱ የማይታለፍ ጥያቄ ነው፡፡ ቃል ከገቡ አይቀር ተግባርን ማስቀደም ከሕዝብ ጋር ያስታርቃል፡፡ አመኔታንም ያተርፋል፡፡

ይህች የታፈረችና የተከበረች አገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን እናት ናት፡፡ ለዘመናት ከነበረችበት የድህነት አረንቋ ውስጥ ወጥታ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሆነው ሕዝቧ በነፃነት የመኖር መብት እንዳለው መተማመን ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ በውስጡ የተፈጠረውን ችግር የመፍታትና ወደ ትክክለኛው መስመር የመመለስ ኃላፊነቱ የራሱ ቢሆንም፣ የአገሪቱን ህልውና ከሚፈታተኑና የሕዝቡን ሕይወት አደጋ ውስጥ ከሚከቱ ድርጊቶች ደግሞ መታቀብ አለበት፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ በክልሎች መካከል ባለው ግንኙነት ለሚታየው ችግር ዋነኞቹ ባለቤቶች የኢሕአዴግ አመራሮች ናቸው፡፡ እነሱ ይህንን አገር ሊያጠፋ የሚችል ችግር በጊዜ ፈተው ለትልቁ አገራዊ ጉዳይ መፍትሔ ለማምጣት መረባረብ አለባቸው፡፡ በዚህም መሠረት አሁን የተፈጠረው ችግር የአንድ ፓርቲ የበላይነት ያመጣው አሠራር መሆኑን በማመን፣ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ መደላድሉን ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ በአገሪቱ ሥልጣንም ሆነ ሀብት መገኘት ያለበት በፍትሐዊ ጥረት እንጂ በጉልበት ወይም በቡድንተኝነት መሳሳብ እንዳልሆነ ሊታመን ይገባል፡፡ ሥልጣን በነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ብቻ መገኘት አለበት፡፡ ሀብትም ላብን ጠብ በማድረግ ሊገኝ ይገባል፡፡ ንፋስ አመጣሽ ሀብትና ሥልጣን አገርን መቀመቅ ከመክተት ውጪ ጥቅም የላቸውም፡፡ ለሥልጣን የሚደረገው ትንቅንቅ ለሕግ የበላይነት የማይገዛ ከሆነ ግን ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡ ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲህ ዓይነቱን ከንቱ ድርጊት አይፈልግም፡፡ ቃል ሲገባ ይህንን ጭምር ማካተት አለበት፡፡ መንግሥት ይህንን ሳያሟላ አመኔታ አገኛለሁ ብሎ ካሰበ ውጤቱ ውድቀት ነው!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...