Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለ35 ቀናት ግምገማ ላይ የቆየው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ...

ለ35 ቀናት ግምገማ ላይ የቆየው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አዋቀረ

ቀን:

ለ35 ቀናት በግምገማ ላይ የከረመው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት (ትግራይ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴውን እንደገና በማዋቀር ተጠናቀቀ፡፡

ሐሙስ ኅዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከአንድ ወር በላይ የፈጀ ስብሰባውን ያጠናቀቀው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ዘጠኝ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል፡፡ ባወጣው የአቋም መግለጫም ራሱ ላይ አካሂጃለሁ ያለውን ሥር ነቀል ግምገማ በዝርዝር አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሕወሓት ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከለንደን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማግኘታቸውን ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡

አዲሱ ሊቀመንበር በሕወሓት ትግል ወቅትም ከመረጃና ከግንኙነት ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶችን ሲወጡ እንደነበር፣ ከትግል በኋላም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ውስጥ ያለፉ ስለመሆናቸው የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሕልፈት በኋላ ድርጅቱን በምክትል ሊቀመንበርነት ሲመሩ ቆይተዋል፡፡

የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ በድርጅቱ የ43 ዓመታት ታሪክ የመጀመያዋ ሴት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ተመርጠዋል፡፡ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ቀደም ሲል የሕወሓት ጽሕፈት ቤት በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ሲሠሩ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ወ/ሮ ፈትለወርቅ ከእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የፋይናንሺያል ኢንተለጀንስ ሴንተር (የፋይናንስ ዘርፍ መረጃ ማዕከል) ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፡፡ ይህ ተቋም የኢኮኖሚውን የደኅንነት ዘርፍ አካል በመሆን መረጃዎችንና የወንጀል መረጃዎችን የሚተነትን ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተመረጡት ደግሞ የአገሪቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ናቸው፡፡

አቶ ጌታቸው የአገሪቱን ብሔራዊ የደኅንነት መረጃዎች የመሰብሰብና የመተንተን ኃላፊነት ያለበትን ተቋም የመምራት ኃላፊነትን በመያዝ ላለፉት በርካታ ዓመታት በመምራት ላይ ናቸው፡፡

በበርካታ የዓለም አገሮች የደኅንነት ዘርፍ ባለሥልጣናት ከፖለቲካ ተቋማት ውጪ እንዲሆኑ የሚደረግ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የደኅንነት ኃላፊዎች የፖለቲካ ተቋም ውስጥ ተሳታፊ አልነበሩም፡፡ አቶ ጌታቸው ወደ ሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተቀላቀሉት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሲሆን፣ በመንግሥት ካቢኔ ውስጥም እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በሥራ አስፈጻሚነት እንዲቀጥሉ ቢደረግም፣ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ሁለት አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ሌላኛው ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አባል የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ዓለም ገብረዋድ ሲሆኑ፣ በአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ተካተዋል፡፡

ከሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ ሥራ አስፈጻሚነት ከፍ እንዲሉ የተደረጉት ሌሎች ሦስት አባላት በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህም አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር፣ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) የፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር፣  እንዲሁም አቶ ጌታቸው ረዳ ቀደም ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትርነት ቆይታቸው የበለጠ የሚታወቁ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሕግና ፍትሕ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በመሆን እየመሩ ነው፡፡

የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የተቀላቀሉት ሌላዋ አባል ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ናቸው፡፡ ወ/ሮዋ በትግራይ ክልል የተለያዩ ኃላፊነቶች የሠሩ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሕወሓት ሥራ አስፈጻሚነት የመጡ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ፈትለወርቅ በቅርቡ በግምገማ ከሥራ አስፈጻሚነት ወደ ማዕከላዊነት ዝቅ በተደረጉት የትግራይ ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ወልዱ ምትክ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ የሚሉ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ይህም የክልሉ ፕሬዚዳንት ለመሆን የክልል ምክር ቤት አባል መሆንን የሚጠይቅ ስለሆነ፣ ይህንን የሚያሟሉት እርሳቸው በመሆናቸው እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ደብረ ጽዮንና ዶ/ር አዲስ ዓለም የፌዴራል ፓርላማ አባል በመሆናቸው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት መሆን አይችሉም፡፡

ባለፈው ሳምንት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ዓባይ ወልዱን፣ አቶ በየነ ምክሩንና ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ማንሳቱ ይታወሳል፡፡

የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ አቶ ጌታቸው አሰፋና ወ/ሮ ፈትለወርቅ በደኅንነት ተቋማት ውስጥ በመረጃ ትንተና ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ቀጣዩን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከተመሳሳይ የደኅንነት ተቋማት የመጡ አመራሮች ተፅዕኖ የሚጎላበት ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ ኦሕዴድን በመወከል የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተወከሉት አቶ ለማ መገርሳ፣  ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት የመጡ አመራሮች ናቸው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ35 ቀናት ባካሄደው ስብሰባ፣ የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር ክልላዊና አገራዊ ተልዕኮውን ከመወጣት አንፃር ያለበትን ቁመና ለማየት የሚያስችል ሥር ነቀል ግምገማ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መዋቅራዊ ለውጥ ከማረጋገጥ፣ የሕዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመመለስ አንፃር ያሉበትን መሠረታዊ ክፍተቶችንና አዲሲቷን ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከመገንባት አኳያ የተጋረጡ አሳሳቢ አዝማሚያዎች በጥልቀት መገምገሙን ባወጣው የአቋም መግለጫ ገልጿል፡፡ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ ላይ የተዘጋጀው ሰፊ ዘገባ በፖለቲካ ዓምድ ላይ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...