በውብሸት ሙላት
የፍትሕ ተደራሽነት መብት የሚያጠነጥነው ፍትሕ በሚፈልገው ሰው ዙርያ ነው፡፡ የፍትሕ ተደራሽነት ሲባል አንድ ነጠላ የፍትሕ ዘሃ ላይ ብቻ ሙጥኝ ያለም አይደለም፡፡ ይልቁንም ፍትሕ የሚፈልገው ሰው መብቱን በማስከበር ረገድ ተገቢ የሆነ እልባት ለማግኘት የሚከተለውን ሥርዓትና ሒደት በሙሉ ያካልላል፡፡
ማንኛውም ግለሰብም ይሁን በሕግ የሰውነት መብት የተጎናጸፈ ሰው የመብት ጥሰት ሲያጋጥማቸው የደረሳባቸውን በደል ምንነቱን ለመረዳት እንዲሁም ይህ የመብት ጥሰት የሕግ የበላይነትን ወይም ሕግን መሠረት አድርጐ እንዲታረም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ መፍትሔ የሚያገኙበትን ሒደት የፍትሕ ተደራሽነት መብት ውስጥ የሚካተት ነው፡፡
ምንም እንኳን የፍትሕ ተደራሽነት በውስጡ ብዙ መብቶችን የያዘ ነው ብለናል፡፡ ለአብነትም የሕግ ተደራሽነት፣ በጠበቃ (በሕግ ባለሙያ) የመታገዝና የፍርድ ቤት ተደራሽነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሕግ ተደራሽነት መብት በአገሪቱ የሚወጡትን ሕጎች ኅብረተሰቡ የሚያገኝበትንና መብትና ግዴታውን የሚረዳበትን ሥርዓት ይመለከታል፡፡ በሕግ ባለሙያ የመታገዝ መብት ደግሞ አንድ ተጠርጣሪ ወይም የፍትሐ ብሔር ወይም የአስተዳደር ሙግት ተሳታፊ የሆነ ግለሰብ ለጉዳዩ የሚረዳውና ብቃት ያለው የሕግ ምክር በክፍያ ወይም ያለክፍያ ለማግኘት የሚችልበት አግባብ ነው፡፡
ሌላው የፍትሕ ተደራሽነት መብት አካል የፍርድ ቤት ተደራሽነት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቶች መልክዓ ምድራዊ ሥርጭታቸው፣ በባለጉዳይ አያያዛቸውና ምላሽ አሰጣጣቸው በሚከተሉት አሠራር ሁሉ ለሕዝቡ የቀረቡ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ነው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ለሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ከፍትሕ ተቋማት መፍትሔ የማገኘት መብትንም ያካትታል፡፡ በመሆኑም የፍርድ ቤቶቹ ተደራሽ መሆን፣ ፍትሐዊ የመሰማት ሥርዓት መኖር፣ የሕግ አገልግሎት ማግኘት፣ በቂ መፍትሔ የማግኘት፣ እንዲሁም እነዚህን ሁሉ በወቅቱ ማግኘትንም ያካትታል፡፡ የሥነ ሥርዓት ጉዳይ ከመሆን አልፎም በራሱ መሠረታዊ የፍትሕ ዘርፍም ነው፡፡ ግቡም ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን ነው፡፡ ይኼ ጽንሰ ሐሳብ እየጎለበተና እያደገ መጥቶ የሰብዓዊ መብት አካልም ሆኗል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣንን በሚመለከት የሰጣቸው ውሳኔዎች የፍትሕ ፈላጊዎችን ፍትሕ የማግኘትና የፍትሕ ተደራሽነት ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ማሳየት ነው፡፡ ተፅዕኖዎቹም ሁለት ዓይነት መልክ የያዙ ናቸው፡፡
የሰበር ችሎቱ እስከ ቅጽ 14 ድረስ ሙሉ በሙሉ በሕግ ተለይቶ ለፍርድ ቤቶች የመዳኘት ሥልጣን እስካልተሰጣቸው ድረስ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን እንደሌላቸው ይሰጥ የነበረው የውሳኔ አሰጣጥን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው አዝማሚያ ግን ከቅጽ 14 በኋላ እየተወሰኑ ያሉትን የሚመለከት ነው፡፡ በተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎች አማካኝነት ለሌላ ተቋም እስካልተሰጠ ድረስ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው መሆኑን በመቀበል እየተወሰኑ ያሉትን የሚያካትት ነው፡፡
እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች በቀጥታ ፍትሕ የማግኘት መብትና የፍትሕን ተደራሽነት ላይ በአወንታዊም በአሉታዊም ተፅዕኖ አላቸው፡፡ እነዚህን ሁለት ዓይነት አዝማሚያዎችን ይበልጥ ለመረዳት ይቻል ዘንድ ሚርጃን ዳማስካ የሚባለው ሊቅ የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን በሚመለከት የሰጠውን ትንተና መሠረት በማድረግ ለማሳየት ጥረት ይደረጋል፡፡ የዚህ ሊቅ ሥራ ለምን እንደተመረጠ ወደ ኋላ ላይ እንመለስበታለን፡፡
ሚርጃን ዳማስካ ክሮሽያዊ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1931 ነው የተወለደው፡፡ አሁን ላይ የ86 ዓመት አዛውንት ነው፡፡ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች አስተምሯል፡፡ አሁንም ቢሆን በየል ዩኒቨርሲቲ በዕድሜ ልክ ፕሮፌሰርነት ያስተምራል፡፡ የክሮሺያ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ነው፡፡ በዩጎዝላቪያ የዘር ጭፍጨፋ ምክንያት የጦር ወንጀለኞችን ለመዳኘት ለተቋቋመው ፍርድ ቤት የክሮሽያን መንግሥት በመወከል ተሳትፏል፡፡ እንደውም ክሮሽያዊ የሆኑ የጦር ወንጀለኞች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ከሚዳኙ በአገራቸው ይዳኙ ዘንድ ተደራዳሪ ነበር፡፡
ዳማስካ፣ በእዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተነሳው ግን ለአገሩ መንግሥት በሰጣቸው ግልጋሎቶች ሳይሆን በጻፋቸው ምርምራዊ የሕግ ድርሰቶቹ ነው፡፡ ከመቶ ያላነሱ የምርምር መጣጥፎችንና ስድስት መጽሐፍት አሳትሟል፡፡ ስለምሁራዊ አበርክቶውም በስሙ የጥናትና ምርምር ጉባዔዎች ተከናውነዋል፡፡ ሁለት መጽሐፍትም ለአክብሮትም ለተዘክሮም በስሙ ታትመዋል፡፡
ዳማስካ፣ በሰፊው ከሚታወቅባቸው የምርምር ትኩረቶቹ መካከል ንጽጽራዊ ሕግ፣ የወንጀል ሥነ ሥርዓት፣ የማስረጃ ሕግ፣ ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግና የሲቪል (ኮንትኔንታል) የሕግ ሥርዓት ታሪክና መለያ ገጽታዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሲቪል የሕግ ሥርዓት በመባል የሚታወቀው ከእንግሊዝ ውጭ ያሉት የአውሮፓ አገሮች የሚከተሉትና ቀስ በቀስም ወደ ተለያዩ የዓለም አገሮች የተሰራጨው የሕግ ሥርዓት ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ስለዳኝነት ሥልጣን ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ዳማስካ የሲቪል የሕግ ሥርዓት መገለጫ ናቸው በማለት ካስቀመጠው ጋር የሚመሳሰሉት በመለየት እንመለከታለን፡፡ እስከ ቅጽ 14 ድረስ ያሉትን የሰበር ውሳኔዎች ከፊተኛው ምድብ በማካተት ከዚያ በኋላ ያሉትን ደግሞ ከእሱ ሐሳብ የተለዩ መሆናቸውን እንመለከታለን፡፡ ልዩነታቸውን ለመረዳት ግን ዳማስካ በዓይነተኛው የሲቪል የሕግ ሥርዓት የፍርድ ቤት ሥልጣን ምን እንደሚመስል የገለጸውን እንመልከት፡፡
ሚርጃን ዳማስካ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን በማስታከክ የኮመን ሎውና የሲቪል ሎው የሕግ ሥርዓቶችን ያነጻጽራል፡፡ በሁለቱ ሥርዓቶች መካከል ያለውን የፍትሕ የማስተዳደር ጠገግና ሥልጣን የመጀመርያውን ቅንጅታዊ (Coordinate Model) ሲለው የሁለተኛውን ተዋረዳዊ (Hierarchical) በማለት ይከፍላቸዋል፡፡
ተዋረዳዊው የሲቪል የሕግ ሥርዓት ዋና ግቡ የፍትሕ ሥርዓቱ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች እርግጠኛነትን ማስፈን ነው፡፡ የትኛውም የፍትሕ አካል (ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ ወይም ፍርድ ቤት) የሚያከናውናቸውን ተግባራት፣ የሚያስተላለፋቸውን ፍርድና ውሳኔዎች እንዲታወቁና እርግጠኝነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ እርግጠኝነትን ለማስፈን ደግሞ ወጥ የሆነ አሠራር ማስፈን ተገቢ ነው፡፡ እርግጠኝነትና ወጥ የሆነ አሠራር በባሕሪያቸው በማዕከላዊነት መወሰንና መመርያ ማስተላለፍን ይፈልጋሉ፡፡ የሲቪል የሕግ ሥርዓትም ይኼንኑ ያደርጋል፡፡ ይኼ ዓይነቱ አሠራር የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራሙ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ይበልጥ ደግሞ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ በየፍርድ ቤቶቹ ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ በኋላ የፍርድ ቤቶችን አሠራር ልብ ይሏል፡፡
ይኼ የተማከለና ተዋረዳዊ አሠራር ለእያንዳንዱ ኃላፊም በሥልጣን የበላይነትና የበታችነቱን አክብሮ እንዲሠራ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም፣ በተዋረድ ያሉ ፍርድ ቤቶችም ይሁኑ ሌሎች የፍትሕ ተቋማት በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚኖራቸው ሥልጣን የተገደበና ጠባብ እንዲሆን የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ይሰፍናል፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ ተቋም በሕግ በግልጽ ተለይቶ ያልተሰጠውን ተግባር ማከናውን አይችልም፡፡ ለመመርመርም፣ ለመክሰስም፣ ለመዳኘትም አስቀድሞ በሕግ ይኼንኑ ተግባር ይፈጽሙ ዘንድ ሥልጣን ሊሰጣቸው ግድ ነው፡፡
ዳኞችም ይሁኑ ሌሎች አካላት በሕግ የተሰጣቸውን ተግባር የሚያከናውኑ አገልጋዮች ብቻ ናቸው፡፡ ሁሉ ነገራቸው በሕግ የተቀነበበና የታጠረ ነው፡፡ ሕግ አውጭው ያወጣቸውን፣ አስፈጻሚው አካል የወሰናቸውን፣ የበላይ ኃላፊ ያሳለፋቸውን መመርያዎች ለመጠየቅም ሆነ ለመሻር የሚያስችል የሚያፈናፍን ሥልጣን ይኖራቸው ዘንድ አይፈለግም፤ አይጠበቅም፡፡ በሲቪል የሕግ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች ዘንድ እንደ ዳማስካ ክርክርና ገለጻ ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን የላቸውም፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ልክ እንደዳማስካ አረዳድ ፍርድ ቤቶችን ከዳኝነት ተግባር እንዲቆጠቡ የወሰነባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለያዩ ፍርዶች ላይ የሰጣቸው ምክንያቶች ሲጠቃለሉ እንደሚከተለው ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱትን አቤቱታዎች ሲያፀና ወይንም ሲሽር ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የሆነ ሥልጣን እንደሌለው በተደጋጋሚ በመግለጽ ነው፡፡ ይልቁንም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37(1) ላይ የተደነገገውን ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይንም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይንም ፍርድ የማግኘት መብት ያላቸው እንዲሁም በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቶች አንድን አቤቱታ ተቀብሎ ውሳኔ መስጠት የሚችሉት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን የተሰጣቸው መሆኑን በማረጋገጥ ነው የሚል ነው፡፡
እንግዲህ በሕገ መንግሥቱ ላይ ነፃ የዳኝነት አካል በአንቀጽ 78 ተቋቁሟል፡፡ ዳኞች፣ የዳኝነት ተግባራቸውን ከማንኛውም ባለሥልጣንም ሆነ ሌላ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው በሕግ ብቻ በመመራት መሥራት እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 ተመልክቷል፡፡ ይህ የዳኝነት ነፃነት በሕገ መንግሥቱ የተካተተው በራሱ ግብ ሆኖ ሳይሆን ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ለማድረግ ገለልተኛና ነፃ የዳኝነት አካል ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ማንኛውም ፍትሕ ፈላጊ ሰው ፍትሕ የማግኘት መብት ያለው በመሆኑ ያንን ለማሳካትም ጭምር ነው፡፡
ከእዚህ አንፃር ፍርድ ቤቶች ከተለያዩ ሕጎችና ሕጋዊ ውጤት ካላቸው ሁኔታዎች የሚመነጩ መብቶችንና ግዴታዎችን መነሻ በማድረግ ፍትሕ ፈላጊው ዳኝነት ሲጠየቅ አንድ ጤናማ የዳኝነት ሥርዓት የሚያከናውናቸውን የሚተገብር ፍርድ ቤት ሊኖር ይገባል፡፡ ነፃና ገለልተኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የመጨረሻ ግቡ ፍትሕን ማስፈን ነው፡፡ እነዚህን ለማከናወን ደግሞ የዳኝነት ሥርዓቱ እንደ አንድ የመንግሥት አካል በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ግዴታ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
እነዚህን ከግብ ለማድረስም በሕገ መንግሥቱ 79(1) ላይ የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ በተገለጸው መልኩ ከማንኛውም የመንግሥትም ይሁን ከሌላ አካል ነፃ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ ስለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሚናገረው አንቀጽም ላይ በፌዴራልም ይሁን በክልል ፍርድ ቤቶች ከሚሰጧቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች በተጨማሪ ማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ከተፈጸመባቸው የማስተካከል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ይኼንን በሚያጠናክርና የሰብዓዊ መብት በሚያደርግ መልኩ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 37(1) ላይ ደግሞ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይንም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ የማግኘት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡
ከላይ በመንደርደሪያነት ከቀረቡት መረዳት የሚቻለው ሕገ መንግሥቱ ስለፍርድ ቤቶች ሁኔታና አቋም በሚናገርባቸው አንቀጾች ላይ በግልጽ እንደተገለጸው የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠው ለፍርድ ቤት ብቻ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቹ የክልልም የፌዴራልም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ የተፈጠሩት ወይንም የተዋቀሩት የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ተልዕኮ የላቸውም፡፡ የተፈጠሩት ወይንም የተቋቋሙት ለዳኝነት ከሆነ ሌሎች የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች በልዩ ሁኔታ ሊቋቋሙ ከመቻላቸው በስተቀር ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን አላቸው አያሰኝም፡፡ እነዚህ የአስተዳዳር ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ወይንም በሌላ ሕግ ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ግን በሕገ መንግሥቱ ተፈጥረዋል፡፡
ማንኛውም ሰው በሌላ ሕግ የተቋቋመ የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠው ተቋም እስከሌለ ድረስ ማንኛውም በፍርድ ሊያልቅ የሚችልን ጉዳይ ዳኝነት የሚጠይቁት ከፍርድ ቤት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ፍርድ ቤቶች በጉዳዮች ላይ ዳኝነት እንዳይሰጥ እስካልተከለከለ ድረስ የተፈጠረው ለዳኝነት ነውና የዳኝነት ሥልጣን አለው ማለት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቶችም በራሳቸው በሕግ ተለይቶ ለፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን እስካልተሰጠ ድረስ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን (Inherent Judicial Power) የላቸውም በማለትም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በተደጋጋሚ ወሰኗል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ መነሻው ኢትዮጵያ ትከተለዋለች የሚባለው አውሮፓዊው (Continental Legal System) የሕግ ሥርዓት የመነጨ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከሕገ መንግሥት ይልቅ ለሕግ ሥርዓት ታማኝ ለመሆን መሞከር ሌላው የዳኝነት ሥልጣንን ለመተው ማበረታቻ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡
ቅጽ 14 ላይ ታትሞ የወጣ አንድ ውሳኔ ግን በግልጽም ባይሆን ከእዚያ በፊት የነበረውን አካሔድ ቀይሮታል፡፡ ይኼ ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ለሰበር ሰሚ ችሎት አያስቀርብም ተብሎ ውድቅ ሆኖ ነበር፡፡ ከእዚያም ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አምርቶ ምክር ቤቱ በሰበር ታይቶ እንዲወሰን ጉዳዩን ስለመለሰው እንጂ በራሱ የወሰነው አይደለም፡፡ እስኪ ጉዳዩን በመጠኑ እንቃኘው፡፡
ጉዳዩ የንግድ ቤት ይመለስልኝ የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው ለኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጂንሲ ቀርቦ ከተመረመረ በኋላ አቤቱታ የቀረበበት ንግድ ቤት ለአመልካቾች እንዲመለስላቸው ሲል ውሳኔ ሰጠ፡፡ ከዚህም በኋላ በወቅቱ አጠራር ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ተብሎ የሚታወቀው አካል በመሰል ጉዳዮች የይግባኝ ሥልጣን ላለው የፕራይቬራይዜሽን ቦርድ ይግባኙን አቅርቦ ቦርዱም ጉዳዩን አመልካቾች በሌሉበት አይቶ ንግድ ቤቱ ለአመልካቾች አውራሽ እንዲመለስ በማለት የተሰጠውን የኤጀንሲውን ውሳኔ ይሽረዋል፡፡ አመልካቾችም በእዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም፣ የሰበር ችሎቱ አጣሪ ችሎት ጉዳዩን መርምሮ የኤጀንሲው ቦርድ ውሳኔ አስተዳደራዊ ከመሆኑ ባሻገር ይኼንን አስተዳደራዊ ውሳኔ የሕግ ስህተት ተፈፅሞበታል ወይም አልተፈጸመበትም ለማለት ችሎቱ ሥልጣን የለውም በሚል ምክንያት ወደ ፍሬ ጉዳዩ ሳይገባ ውድቅ ያደርገዋል፡፡
አመልካቾች ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስነሳ ነው በማለት ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ጥያቄ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ያጡ ሲሆን፣ ጉዳዩን በመጨረሻ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው ምክር ቤቱም ጉዳዩን ተመልክቶ የኤጂንሲው ቦርድ ዳኝነት መሰል አካል በመሆኑና ይህ አካል የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ ጉዳዩን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በዳኝነት ሥልጣኑ ማየት እንደሚችል በመግለጽ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37፣ 803(ሀ))፣ አዋጅ ቁጥር 110/87 አንቀፅ 2(3)፣ 5(3) እና አዋጅ ቁጥር 87/86 አንቀፅ 8(5) ድንጋጌዎች በአስረጅነት በመጥቀስ ጉዳዩን ሰበር ችሎት እንዲመለከተው በማለት እንዲመለስ ይደረጋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ለጉዳዩ የመጨረሻ ሲሆኑ በሰበር ችሎትም ሆነ በሌሎች በሚመለከታቸው አካላት መከበርና መፈፀም ያለባቸው በመሆኑ፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዲህ ዓይነት ክርክሮችን የመወሰን ሥልጣን እንዳለው ተወሰነ፡፡
በእዚህ መንገድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስገዳጅ ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በራሱ ጊዜ እየተዋቸው መጥቶ የነበረውን የዳኝነት ሥልጣን መመለስ ጀመረ ማለት ይቻላል፡፡ ለወትሮው አስተዳደራዊ መሥሪያ ቤቶች የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች መከለስ እንኳን እንደማይችል፣ እንዲሁም በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ባልተሰጠበት ጉዳይ ፍርድ ቤቶች ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን የላቸውም ከሚለው ዳማስካዊ አካሄድ የተለየ ነው፡፡
ከእዚህ ውሳኔ በፊት የነበረው አካሔድ የፍትሕ ፈላጊዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚያጣብብ ነበር፡፡ ፍትሕ መስጠት ለፍርድ ቤት ተለይቶ በሕግ እስካልተሰጠ ድረስ ለኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ ሥልጣን አይደለም ከተባለ በበቂ ሁኔታ ፍትሕ ማገኘት ላይ እክል ይፈጥራል፡፡ ብዙዎች አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ደግሞ እንደ ፍርድ ቤቶች ፍትሐዊ ሊባል የሚችል የክርክር ሥርዓት ስለማይከተሉ ዞሮ ዞሮ ፍትሕ የማግኘትን ተደራሽነቷንም ማወኩ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ውሳኔዎች ደግሞ ፍትሕ ፈላጊዎችን የሚሄዱበት የሚያሳጣም ጭምር ነበሩ፡፡
ለማጠቃለል፣ የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራሙና መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ መተግበር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የዳማስካ ሐሳቦች በሙሉ ልብነት መተግበር ጀምረው የነበረ መሆኑን አንድም ከውጤቱ፣ አንድም የፕሮግራሙና የሥራ ሒደት አተገባበር ተዋናይ ከነበሩት ውስጥ ዋናዎቹ ለዳማስካ የነበራቸውን አክብሮትም ፍቅርም በእዚያ መሠረት መቃኘታቸውንም ለሚያውቅ ጉዳዩ አዲስ አይሆንም፡፡ ከቅጽ 14 በኋላ ግን ከአዝማሚያው መገንዘብ የሚቻለው የዳማስካዊ ሐሳብ ተፅዕኖ እየቀሰነ መምጣቱን ነው፡፡ ስለዳኝነት ሥልጣን በሰበር ችሎት የተወሰኑትን ማጤን ነው፡፡ ዳማስካ ከአዲስ አበባ ወደ አገሩ እየተመለሰ ነው ማለት ይቻላል ቢያንስ ከዳኝነት ሥልጣን አንፃር፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡