Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአንድነት ተፈርቶ አገርን ማዋሀድ እንዴት!?

አንድነት ተፈርቶ አገርን ማዋሀድ እንዴት!?

ቀን:

በዳግም አሳምነው ገብረ ወልድ

ከቀደመው የትግል አስተዋፅኦቸውም ሆነ ከአየር ኃይል ዋና አዛዥነታቸው ይልቅ (በዙም በዚያን ጊዜ ስለ እርሳቸው መረጃ ስለሌለኝ)፣  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወዳጁ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በሚያቀርቧቸው ጠንካራ ምሁራዊ ሐሳቦች የማከብራቸው ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት ሰሚ ካገኙ ጠቃሚ ሐሳቦችን እያነሱ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም በዚሁ ጋዜጣ ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊነት በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያብባል-ይለመልማል›› በሚል ርዕስ ጥልቅ ትንታኔ በተከታታይ አቅርበዋል፡፡ በግሌ ተሳትፏቸውንም ሆነ ሐሳባቸውን አከብራለሁ፡፡

ይሁንና የምሁሩ (የፖለቲከኛው) ዕይታ በአብዛኛው በማንነትና በብሔር ልዩነት ላይ የሚያተኩረውን ሕገ መንግሥት አወድሶ፣ አሁን ባለው ዓለም አሀዳዊ በሚባሉት አገሮችም ሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች እየተነሳ ያለውን ማንነትን የመፈለግና ተነጥሎ ራስን ለማስተዳዳር መሻትን የሚዳስስ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ይህንን ጥያቄ በተለይ በአንቀጽ 29 አማካይነት ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት መመለሱን በአድናቆት ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አገር እየተነሳ ያለውን የማንነት ጥያቄ ከአገራዊ ብሔርተኝነትና አንድነት ጋር አስተሳስሮ መመለስ አለመቻሉ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲላላ ማድረጉን አልሸሸጉም፡፡ መፍትሔው የብሔር ማንነትንም ሆነ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ኅብረቱን አጣጥሞ መቀጠል እንደሆነ  አመላክተዋል፡፡

እኔ ግን እንደ አንድ አገሩን የሚወድ ዜጋ ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ የተበለሻሸው አካሄድ እንዴትና በምን ተቃንቶ ነው አባባላቸው ዕውን የሚሆነው  እላላሁ፡፡ ልዩነት፣ ብሔርተኝነት (በውስጡ ዴሞክራሲያዊ ቢባልም ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆነው ጠባብነት የተጫጫነው ነበር)፣ አለፍ ሲልም ጎጥና መንደርተኝነት የተቀነቀነውን ያህል ምን ዓይነት አገራዊ አንድነትና ኅብረ ብሔራዊ አብሮነት ተቀነቀነ? ይህን ዕውን ማድረግ ይቻላል? ስል ልሞግታቸው እወዳላሁ፡፡

ዕውን አሁን ባለችው አገራችን ስለአንድነት ማውራትም ሆነ መሥራት የሚያስፈራውን ያህል ምን የሚያስፈራ (የሚያስወነጅል) ነገር አለና ነው፣ በዚሁ አካሄድ ከቀጠልን ያልዘራነውን አንድነት ከየት ለማጨድ ይቻለናል ስልም መጠየቅን እሻላሁ፡፡

ሐሳቤን ለመደወር እንደ መነሻ በአገር ደረጃ የወረደብንን የአንድነት መላላትና የመለያያት በረዶ ወደ መተረክ አልገባም፡፡ ግን ምንም ተባለ ምን ኢትዮጵያዊያን (በአንቀጽ 29 ምክንያትም ይባል እርሳቸው እንደሚሉት በሕገ መንግሥት የአፈጻጸም ችግር)  ከመቼውም ጊዜ በላይ በሚባል ደረጃ በመለያየት ቀፎ ውስጥ ገብተን መባዘናችንን  ማስተባባል አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በአንድ የጋራ መድረክና የመተማመን መንፈስ የሚያቆሙን የወል እሴቶቻችንን ሸርሽረናል፡፡ እምነት፣ ኅብረትና መረዳዳት የመሳሰሉትን ግዙፍ  የኢትዮጵያዊነት የሞራል እሴቶች በብሔር መፈላለግ ብቻ ለመመንዘር ይዳዳን ጀምሯል፡፡

 ቀስ በቀስ መተማመንና መከባባርን እንደ በረዶ ስንንድ ተቆጪም አላገኘንም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት አንድ ብርቱና የማትደፈር ኅብረ ብሔራዊት አገር ለመገንባት ይቻለናል? ለወዲፊቱስ ከዚህ አረም በበዛባት አካሄድ ምን ውጤት ልናመጣ እንችላለን ነው የእኔ ሥጋት አዘል ጥያቄ?! እንደው ለነገሩ ባለማስተዋልም ይባል በመረገም ችላ እየተባለ አንጂ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 88 ንዑስ አንቀጽ 2 እኮ እንዲህ ይላል፡፡

‹‹መንግሥት የብሔሮችን፣ የብሔረሰቦችንና የሕዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነት፣ አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር  ግዴታ አለበት፡፡››

ከዚህ አንፃር መንግሥት ፊት ለፊት መጠየቅ ያለበት ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን ለመፈጸም ምን ያህል ኃላፊነቱን ተወጣ የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ለዚህ ከባድና የማያሻማ ጥያቄ አንዳንድ ካድሬዎች አገሪቱ በመንገድ ተሳስራለች ወይም መብራትና ስልክ በዚህ በዚህ በኩል ገብተዋል፡፡ ለወደፊትም ባቡር ሊያስተሳስረን ሥራ ተጀምሯል ሊሉ ይችላሉ፡፡ ወይም በአብዛኛው ሁሉም ብሔረሰቦች ስለራሳቸው ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ የሚዘምሩበትንና በፉክክር ልዩነትን ወደ ማጉላት የሚያዘነብለውን የብሔረሰቦች ቀንን ይጠቅሱ ይሆናል፡፡

ከመሠረታዊ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አንፃር በአገሪቱ በተለይ የሕዝቦች አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር የተሠራው ግን ፍፁም የተዳከመ ከመሆኑ በላይ አልነበረም ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ የተጣለበት መንግሥት ለብሔሮችና ብሔረሰቦች ማንነት፣ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ በእኩልነት መከበርና መስፋፋት የሰጠውን ትኩረት ያህል ለሕዝቦች አብሮነት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትም ይባል ወንድማማችነት መስፈን በእምነት ይዞ በተግባር ያከናወነው ይኼ ነው የሚባል ተግባርን መጥቀስ እጅግ አዳጋች ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ እንደ አሁኑ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ዓይነት ኢትዮጵያዊነትን የገለጠና ወደነበርንበት ጠንካራ አንድነት እንመለስ ማለት የጀመረ ፋና ወጊ በ27 ዓመታት ውስጥ አለመታየቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አሁንም አንዳንድ የጠባብነት የሸማኔ ጉድጓዳቸውን መልቀቅ የማይፈልጉ ደካሞች (የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችም ይሁኑ ተቃዋሚዎች) የሰውዬውንና የደጋፊዎቻቸውን አዲስ አስተሳሳብ፣ በተለይ ከአንዳንድ ማኅበረሰቦች ጋር የጀመሩትን የምክክር መድረክ ሊተቹና ሊጠራጠሩ መሞከራቸው የሥርዓቱ ቅኝት ምን ዓይነት ሆኖ እንደቆየ አመላካች ነው፡፡

እስካሁንም ድረስ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ (ሰንደቅ ዓላማ የተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ እንደ ፀረ ሽብር ሕግ የመሳሰሉ ሕግጋት ላይ…) እንደ አገር ብሔራዊ መግባባት ማምጣት አለመቻሉ አብሮ የመቆም ውስንነታችን ነው፡፡ ያመነ ወይም አሸናፊ የሆነ ብቻ አገራዊ ጉዳዩን ይዞ ይነጉዳል፡፡ ያላመነ ደግሞ ከዳር ቆሞ ወይም የእኔ አይደለም እያለ ያጥላላል፣ ሲያመቸውም ይዘምትበታል፡፡ መሀል ቤት የሚባል ባህል እስካሁን የለም፡፡

የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ብሔራዊ መዝሙሩን አውቀው ጮክ ብለው መዘመር ለምን ሳይችሉ ቀሩ? ውድድሮቹስ ቀስ በቀስ ከሰላማዊው ጦርነት ይልቅ ወደ ብሔር መጋጫነት እንዴት ተቀየሩ? በአገሪቱ 44 የሚደርሱ ዩኒቨርሲቲዎች ቢገነቡም ለምን አንዳቸውም አገራዊ ገጽታን ከመላበስ ይልቅ፣ የክልልና የብሔረሰብ መልክ ይዘው የአንተ፣ የእኛ መዘባበቻ ሆነዋል፡፡

ተቋማቱ ለሥራ ዕድል መፍጠሪያ ብቻ እንደተገነቡ ሁሉ ከፅዳት ሥራ እስከ ፕሬዚዳንት ድረስ በአካባቢ ተወላጆች ተይዘው አገራዊውን ማንነት ለመገንባት ለምን  አቃታቸው ብሎ መመርመር ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ እንዴት በጋራ የሕዝብ ሀብትና  በፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚነት የተገነቡ የትምህርት ተቋማት በጎጥ ታጥረው፣ የኢትዮጵያን ልጆች ያለምንም ዓይነት መድልኦ ማስተናገድ ተሳናቸው? አሳዛኝ ደረጃ  ላይ የመድረስ ሁነኛ ምልክት ነው፡፡

በፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ስም አንዳንድ ክልሎች ነባርና መጤ በሚል የዜጋ ክፍፍል የኢትዮጵያዊያንን ሕገ መንግሥታዊ መብት በይፋ እስከ መግፈፍ ሲደርሱ፣ በታሪክ አጋጣሚ ተዋልደውና ተዋህደው ለዘመናት የኖሩ ሕዝቦች በውጭ ጠላትም ይባል በውስጥ ጥገኛ ሲታመሱ፣ ገና ከመጀመሪያው (አደጋው እንደ ዛሬው ሁሉንም ሳያዳርስ) አንዱ ሌላውን ሲያሳድድ ማን ደፍሮ ፊት ለፊት አወገዘው? በእንጭጩ እንዲታረምስ ምን ተሠራ? በአንዳንድ ክልሎች ብሔራዊው ሰንደቅ ዓላማ ከክልሉ  ባንዲራ ዝቅ ብሎ ሲሰቀል፣ አለፍ ሲልም ሕጋዊው አገራዊ ዓርማ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገሮችም ሲዋረድና ሲንቋሸሽ ምን ተደረገ? ሕዝቡስ መቼ በአንድ ተነስቶ አወገዘው?

በአገር ደረጃ ከፋም ለማም ለሺሕ ዓመታት የኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸው ማንነትና ታሪክ ያላቸውን ያህል የጋራ ታሪክና ማንነትም አላቸው፡፡ ይህ እየታወቀ ለምን እንደሌላቸው ተቆጠረ? ከአንዳንድ በፖለቲካ ከተበረዙ የታሪክ ድርሳናት ጋር ተያይዞ ዛሬም ሆነ ትናንት እውነትን የማዛባት ችግር እንዳለ  ይታወቃል፡፡ ይህ ስህተት መታረም ያለበት በቅንነትና በምሁራዊ ውይይት መሆን ሲገባው፣ የታሪክ ሽሚያና ማጣመም ውስጥ የከተተንስ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ዛሬ በፀፀት የሁሉንም ጭንቅላት የሚያዞሩ ሆነዋል፡፡ ጸሐፊው ይህን ሀቅ እንዴት ይመለከቱታ ስል የምጠይቀውም ለዚሁ ነው፡፡

ከዚያም አልፎ አንዳንዱን ቋንቋ፣ ማንነትና እምነት ከቀደሙት አገዛዞች ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በማስመሰል ሕዝብና ሕዝብን ወደ ማጠራጠር መግባት ለምን አስፈለገን? (በነገራችን ላይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኦሮሚያ፣ ደቡብና አንዳንድ ታዳጊ ክልሎች በሚደረግ የካድሬዎች ቅስቀሳ የአማራ ገዥ መደብና አማራ የሚባለው ሕዝብ አንድ እንደነበሩ በማሳመን ላይ ያተኮረ እንደነበር አሁን ራሳቸው ካድሬዎቹ ማጋለጥ ጀምረዋል) ይህ ባልጠራበት ሁኔታስ የቀድሞ አገዛዞችን ጥፋት ለማውገዝ ሲባል የቂምና የጥላቻ ሐውልት መገንባትን እንዴት ከተግባራት ሁሉ ቀዳሚው ሥራ አደረግነው? የሚሉ አስገምጋሚ ጥያቄዎች ዛሬ ፊት ለፊት እያፋጠጡን ይገኛሉ፡፡

በነገራችን ላይ ባለፉት 27 ዓመታት እነዚህ በእንጭጩ ያልታረሙ የጠባብነትና የመለያያት ጀልባዎች በአገራዊ ውቅያኖሱ እንዳሻቸው ሲቀዝፉ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለረጅም ጊዜ በየክልሉ ለዘመናት የኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች (እንደ ዜጋ የሚፈጽሟቸው ጥፋቶች ቢኖሩ እንኳን በሕግ መዳኘት ሲገባቸው) የተለያዩ ጥቃቶች ደርሰውባቸዋል፡፡ ሀብታቸውን ከማውደም አንስቶ በአካልና በሕይወት ላይ የደረሰው ጉዳት መጽሐፍ እስከ መታተም የደረሰ አሳዛኝ  የታሪክ ጠባስ አሳርፏል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በትግራይና በአማራ፣ በኦሮሞና በሶማሌ፣ በአፋርና በሶማሌ፣ በኦሮሞና በደቡብ (ለምሳሌ ከቀናት በፊት በባቱ ወይም ዝዋይ ከተማ በግል ጠብ ምክንያት ሕይወቱ ካለፈ አንድ ወጣት ጋር በተያያዘ ስድስት የወላይታ ብሔረሰብ ተወላጆች ተገድለዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩም በመንግሥት በፍጥነት ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን ከአካባቢው የደረሱኝ ምንጮች ገልጸውልኛል፡፡ እንግዲህ ይህ ነባራዊ ሁኔታ ነው አብረን ለመኖር የማንችልበት ዘመን እንዳይፈጠር ያሠጋል ነው የሚያስብለው፡፡)

ከዚያም አለፍ ሲል በሕገ መንግሥቱም ሆነ በመንግሥት ፖለሲዎች አገራዊ ኅብረትን የሚያጠናክሩ አንቀጾችና ምዕራፎች መጉደል ደጋግመው የሚጠቅሱ ወገኖች እንዳሉ መካድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት መባቻ ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከየት ወደ የት? (ፈተናዎችና መልካም ዕድሎች)››  በሚል ርዕስ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚያ  መድረክ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከምሁራንና ከንግዱ ማኅበረሰብ የተወከሉ ግለሰቦች የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ሜጀር ጄኔራሉም ተሳተፍውበት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡  የዚህ መድረክ ተሳታፊዎች ግን የተስማሙበት አንድ ጉዳይ ነበር፡፡

ይኸውም በአገሪቱ እየመጣ ካለው የኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ከኅብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ጋር ተመጣጣኝነት ያለው ዴሞክራሲያዊ አንድነት አለመዳበሩን የተመለከተው ነው፡፡ አንዳንዶች ሕገ መንግሥቱን በመጥቀስ የሕዝብ አንድነትን አያስጠብቁም ያሏቸውን አንቀጾች አንስተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለብሔር ብሔረሰቦች የተለጠጠ ሥልጣንና ዕውቅና በመስጠቱ ኢትዮጵያዊ ማንነትና አንድነት ዋስትና አጥቷል ያሉም ነበሩ፡፡ እንዲህ ዓይነት ከቅንነትና ከአገራዊ ስሜት የሚመነጩ ሒሶችን በሆደ ሰፊነት ፈትሾ አዋጭው የትኛው ነው የሚለውን ሕዝቡን እያሳተፉ ከማስተካከል ይልቅ፣ ጆሮን በጥጥ ደፍኖ በኖረው በሬ ወለደ ታሪክ ወይም ኢትዮጵያዊያን ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ከልብ እንዲሚሹ በመዘንጋት ለመቀጠል መሞከር የሚያፋጥነው ውድቀትና ውድቀትን ብቻ ነው፡፡

በእርግጥም አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በብሔር ለመነጣጠል ለሚነዙ ውዥንብሮች በቀላሉ ተጋልጠዋል፡፡ በጣት በሚቆጠሩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች የጥላቻ አራማጆች በሚነዛ የተለጠጠ ብሔርተኝነት ውስጥ ተወሽቀን ለችግር መጋለጥ የጀመርነውም ከዚሁ እውነታ ነው፡፡ ጥቂት ጥገኛ  ኃይሎችና በአቋራጭ ሥልጣን የሚሹ ወገኖች የሚያናፍሱት ዘረኝነትን የተላበሰ ቅስቀሳ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማለያየት ምቹ መሠረት ያገኘውም ከዚህ በመነሳት ነው ቢባል ስህተት አይመስለኝም፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ መሠረት መንግሥት የሕዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት የማጠናከር ግዴታ  እንዳለበት ተገንዝቦ መነሳት ለነገ መባል የለበትም፡፡ በእርግጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታትም ይህን ተግባር ለማጎልበት በሚመስል  መንገድ (በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጀማምረውት ነበር) እየተወሰዱ የነበሩ በጎ ዕርምጃዎች (የሚሊኒየም በዓል፣ የፖለቲካ እስረኞችን በፍርድ ሒደትም ቢሆን የቅንጀትና የደርግ አመራሮችን ልብ ይሏል በመፍታት)፣ የሰንደቅ ዓላማ ቀን፣ ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበት ቀን፣ የመከላከያ ቀን በዓላትን… በማክበር ላይ ነበር፡፡

  እነዚህ ጥረቶች ብቻ ግን በቂ ስላልነበሩ ባሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች፣ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፡፡ አሁንም ዜጎች መጠራጠራቸውን ያቆሙበት አገራዊ እርቅና አንድነት በብሔራዊ ደረጃ አላደረጉም፡፡ በመሆኑም እስካሳለፍናቸው ሳምንታት ድረስ ዜጎች ለዘመናት በኖሩበት አካባቢ በማንነታቸው ብቻ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ለዘመናት በላባቸው ለፍተው፣ ጥረው ያፈሩት ሀብት ወድሞባቸዋል፣ ተዘርፈዋልም፡፡ ከትውልድ አካባቢያቸው በታሪክ አጋጣሚ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ የተሳሰሩ፣ ተዋልደውም ሀብት ያፈሩም  አሁንም በሥጋት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው ብሎ መመርመርና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ነው እንግዲህ የዚህ ትውልድ ትልቁና ዋነኛ የቤት ሥራ ሆኖ የሚገኘው፡፡

በመሠረቱ ለዓመታት ልንተገብረው አይደለም ስሙን ልንጠራው ይከብደን የነበረው አገራዊ አንድነት (ማን ነበር ቃሉ ራሱ የደርግና የትምክህት ፍረጃ ተሰጥቶታል ያለው) የግድ የሚፈለግበት ወሳኝ ወቅት አፍጥጦ መጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጠቀስኳቸው ጸሐፊም እንዳሉት ብሔራዊ ዕርቅና መግባባትን በድፍረት አምጥቶ የተሻለ መሠረት ላይ መቆም ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ ይህ ለምን ይሆናል የሚለኝ ደረቅ ካለም እንዲህ ስል ልጠይቀው እሻለሁ፡፡

አሁንም በጭቆናና በባሰ ድህነት ወቅት እንኳን ብሔር፣ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያያቸው ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የብሔር ማንነትን  በመፈለግ ስም ለምን ወደ መነጣጠልና መገፋፋት ገቡ? እለዋለሁ፡፡ በአገሪቱ በትልልቅ ባለሀብቶች ላይ ይቅርና በተራው ዜጋ ላይም ሳይቀር እንደ ልቡ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የሚያውክ ዘረኛ አመለካከት እንዴት ሊያቆጠቁጥ ቻለ? የሚል ጥያቄም በግልጽ አነሳላሁ፡፡

በእርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከሚፈጥሩት ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ይልቅ መነጣጠላቸውን የሚሹ የውጭ ጠላቶችም እንዳሉብን መዘንጋት የዋህነት ነው፡፡ ሕዝብን እንደ ሕዝብ አክብሮ በግለሰብ ደረጃ ያለን የተዛባ ባህሪ ከማጋለጥ ይልቅ፣ ሕዝቡን የትምክህትና የጠባብነት በሽታ የተጠናወቱት እያሉ ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላም መፈረጅ ጥላቻን ለመጠንሰስ እንደሚገፋ እያወቁ  የሠሩም ትንሽ አይደሉም፡፡

 መፍትሔው ግን ይኼ የውስጥና የውጭ አሉታዊ ግፊት ወደፊትም ላይቆም የሚችል የጋራ ሥጋት መሆኑን በግልጽ ተገንዝቦ፣ ስንሸሸውና ስንፈራው የነበረውን አገራዊ አንድነት በፅናት እንገንባ ስል ሐሳቤን እቋጫለሁ፡፡ ጸሐፊውና ሌሎችም ከንድፈ ሐሳባዊ ትወራ (Theory) ይልቅ፣ በዚህ ላይ አተኩረው ሐሳባቸውን ቢፈትሹ ይበጃል እላላሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...