በጌታቸው አስፋው
የዓለም ባንክና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በሯን ለንግድ ክፍት ለማድረግ የምትወስዳቸውን ዕርምጃዎች እያደነቁና እየሸለሙ ይገኛሉ፡፡ እኛ ከድህነታችን ጋር አገናዝበን በምሬት እርር ድብን ያልንበትን በውጭ ምንዛሪ ለውጥ ምክንያት የተከሰተ የዋጋ ንረት በአጠገቡ ቢያልፍም፣ የማይነካው የዓለም ባንክ አሳሳቢ አይደለም ለማለትም በቅቷል፡፡ በልማታዊ መንግሥት አጥር ታጥራ ከግሎባላይዜሽን የአንድ መንደር ገበያ ጠፍታ የከረመችውን አገር ፈልገው ወደ ኒዮ ሊበራሊዝም ፍልስፍና የቀላቀሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሙገሳ ውጪ ሌላ እንዲሉም አይጠበቅም፡፡
በቻይና አጋርነት መሠረተ ልማት በመገንባት ላይ ተጠምዳ የቆየች አገር የገበያ ሸቀጥ እንዲያመርቱላት የውጭ ኢንቨስተሮችን ከማግባባት ውጪ ምንም አማራጭ እንደ ሌላት ባለሥልጣናቷ ስለተገነዘቡ፣ አክራሪ የገበያ ኃይላት ይሏቸው ከነበሩ ኒዮ ሊበራሎች ጋር እየተወዳጁ ነው፡፡ በቻይና፣ በኮሪያ፣ በጃፓን፣ በህንድና በቱርክ የተጀመረው የውጭ ኢንቨስተሮችን የማግባባት ሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ጎራ ተብሎ ሳዑዲ ዓረቢያን በጨረፍታ ከነካካ በኋላ ወደ ኳታር ፊቱን አዙሯል፡፡
በውጭ ምንዛሪ መጣኙ ለውጥ የዋጋ ንረት አንድምታ ላይ ብዙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየጻፉ እያሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚኒስትሮቻቸውን አስከትለው በድንገት ወደ ኳታር የመጓዝ ዜና የጋዜጦችን ዓምዶች ተሻምቶ ነበር፡፡ ዓምዶቹ ከዜናነት ባለፈ የሰጡት ትንታኔ ግን አልነበረም፡፡
ሰሞኑን የግብፅ መሪ ለሕዝባቸው ያስተላለፉት የዓባይ ውኃ ድርሻችሁን ማንም አይነካባችሁም ፉከራ መንስዔ፣ ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር በፈጠረችው የኢኮኖሚ ግንኙነት ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ለማቃቃር አመቺ ጊዜ ተፈጥሮልኛል ብለው በማሰብ ይሆን እንዴ?
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወደ ኳታር ያቀኑት የግብፅ አካሄድ መረጃ ደርሷቸው ነው? ወይስ የግብፅ ፉከራ የኢትዮጵያን አካሄድ ተከትሎ የመጣ ዱብ ዕዳ ነው? ከመንግሥት አካላት ውጪ የሆኑ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ባለሙያዎች ሊተነትኑልን ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
በሕክምናው የዓይን፣ የጥርስ፣ የአጥንት ስፔሻሊስት፣ በምህንድስናው የሲቪል፣ የሕንፃ፣ የመንገድ ስፔሻሊስት እንዳለው ሁሉ በኢኮኖሚክስም የንግድ የሥራ፣ የብሔራዊ፣ የልማት፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ ወዘተ ስፔሻሊስት ዘርፎች ቢኖሩም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት የሚታወቀው በጅምላ ስሙ እንጂ በተካነው የኢኮኖሚ መስክ አለመሆኑ በጣም የሚቆጭ ነው፡፡
የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነታችንን አንድምታ የሚተነትንልን የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ባለሙያ ብቅ እንዲል እያሳሰብኩ፣ ከሙያዬ ከብሔራዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ ጋር አጠጋግቼ በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ምክንያት በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን አንዳንድ ሁኔታዎች በማንሳት እተነትናለሁ፡፡
መሪዎቻችን የሚቀምሩልን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀመር በተጓዙባቸው አገሮች ቁጥር ልክ የሚለካ ሆኗል፡፡ ቻይና ደርሰው ሲመጡ ቻይናዊ ይሆኑብናል፣ ኮሪያ ደርሰው ሲመጡ ኮሪያዊ ይሆኑብናል፣ ሲንጋፖር ደርሰው ሲመጡ ሲንጋፖራዊ ይሆኑብናል፡፡ የቴክኒክና ሙያውንና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ዕድገት ቀመር ከጀርመን የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ጋር ለማዛመድ ምልክቶች ያሳዩበት ወቅትም ነበር፡፡
ሰሞኑን ከልማታዊ መንግሥታት ተሞክሮ ወደ የውጭ ኢንቨስተሮች ተሞክሮ እያደሉ ስለሆነ፣ የእነ ዓለም ባንክ ሊበራል ኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ሰለባ መሆናችን የማይቀር እየሆነ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ባይሆንም ቢያንስ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ጭልጥ ካለው የልማታዊ መንግሥት ሠፈር ጭልጥ ወዳለ የኒዮ ሊበራሊዝም ሠፈር እያመራን ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያ ወሬ ወደ የውጭ ኢንቨስተሮች ዘገባ እያዘነበለ ነው፡፡ በተግባር ባይታይም በመርህ ደረጃ በፍትሐዊ የሀብት ሥርጭት ፍልስፍና ከሚያምነው የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ አመራር ወደ ገበያው ያውጣህ የሊበራል ኢኮኖሚ ፍልስፍና ውስጥ ገብተናል፡፡
ከድንግል መሬትና ርካሽ ጉልበት አለን ቀጥሎ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠቀሙት ማስታወቂያ፣ በቅርቡ መካከለኛ ገቢ ውስጥ የሚገባው ሸማች ሕዝባችን ቁጥር በእጅጉ ይጨምራል የሚል ነው፡፡ ይሳካል እንበልና ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ አሥር ወይም ሃያ ሚሊዮኑ ወደ መካከለኛ ገቢ ውስጥ ቢገባ፣ ለዚህ ሸማች ምርት ለማቅረብ ከአሁኑ ዝግጅት እያደረጉ ያሉ የውጭ ኢንቨስተሮች እነማን ናቸው የሚለውን እንመለከት፡፡
የምግብ ምርት ኢንዱስትሪው ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተተወ ይመስላል፡፡ በውጭ ኢንቨስተሮች የሚመረተው የአልባሳት ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ እንደሆነ በይፋ ተነግሯል፡፡ የማዕድን ምርቱም ተጭኖ ወደ ውጭ የሚሄድ ነው፡፡
በውጭ ኢንቨስተሮች ለአገር ውስጥ ገበያ ከሚቀርቡት የገበያ ሸቀጦች አምራቾች ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዙት ጠንካራ ዳቦአችንን ወደ ፈሳሽ ዳቦነት የቀየሩት የቢራ አምራች ድርጅቶች መሆናቸውን የማያውቅ የለም፡፡ የዚህ ኢንዱስትሪ ዕድገት ፍጥነት ወደ ፊትም ሌሎቹን ሁሉ እንደሚቀድም ሁኔታዎች ይመሰክራሉ፡፡
አንዳንድ ምልክቶችን ወስደን መመልከት እንችላለን፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ባለቤት የራያ ቢራን አክሲዮን ከፊት ገጽታ ዋጋው ሰባት እጥፍ በሆነ የገበያ ዋጋ ለመግዛት ሐሳብ ማቅረቡ፣ ለወደፊት ኢንዱስትሪውን በሞኖፖል ለመቆጣጠር ማሰቡን የሚያመለክት ነው፡፡ መንግሥት በቢሊዮኖች እያወጣ የምግብ ስንዴ ከውጭ በሚያስገባበት ወቅት የባሌና የአርሲ ገበሬዎች የቢራ ገብስ እንዲያመርቱ በቢራ አምራቾቹ የሚሰጠው የድጋፍ ማበረታቻና የሥራ ትስስር፣ ሌላው የኢንዱስትሪው ፈጣን ዕድገት ምልክት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚታየው ጠጪ አሽከርካሪዎች በትራፊክ አደጋ ሕዝቡን እየፈጁት ባሉበት ወቅት፣ የቢራ ማስታወቂያ ከምግብና ከአልባሳት ምርቶች ማስታወቂያ የእጥፍ እጥፍ መብለጡ ሌላው የፈጣን ዕድገት ምልክት ነው፡፡
አገሪቱ በልማታዊ መንግሥትና በኒዮ ሊበራሊዝም ፍልስፍናዎች መንታ መንገድ ላይ እየተዋከበች ከአንዱ ወደ ሌላው እየሮጠች ነው፡፡ የልማት ኢኮኖሚውን በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መምራት ይቻል ይሆናል፡፡ በውጭ ገበያ ላይ የተመሠረተውን የኒዮ ሊበራል ኢኮኖሚ ግን ፍላጎትና አቅርቦትን በማጣጣም በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መምራት አይቻልም፡፡
ማዕከላዊ መንግሥቱ የመንታ መንገድ ሩጫውን በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ሚና ለሁለት ከፍሎታል፡፡ ለራሱ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትን ከኒዮ ሊበራሎች ጋር ተደራድሮ ወደ አገር ውስጥ መሳቡን እንደ ዋና ሥራው አድርጎ ሲወስድ፣ ለክልሎች ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ሥራ አጣሁ ብሎ ለሚጮኸው ወጣት ጊዜያዊ ሥራም ቢሆን ፈጥራችሁ አፉን ባታዘጉልኝና ምንም ዓይነት ረብሻ ቢፈጠር ወዮላችሁ ብሏቸዋል፡፡
አንድ ሰሞን እንደ ሀብታም ልጅ ፋፍቶ የነበረው ከባለሥልጣናት አፍ በቁልምጫ መልክ ጠፍቶ የማያውቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአሁኑ ጊዜ እንደ ደሃ ልጅ ቀንጭሯል፡፡
ይህ የፌዴራል መንግሥቱና የክልሎች የውጭ ምንዛሪና ሥራ አጥነትን ማስወገድ የሥራ ክፍፍል አገሪቱን አንድ የተቀናጀ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳይኖራት ከማድረጉም በላይ፣ የወጣቶች ሥራ ማግኘት ዕድልም እንደ ክልላቸው ባለሥልጣናት ሥራ የመፍጠር አቅምና ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት የሚለያይ አድርጎታል፡፡
አገሪቱ በልማታዊ መንግሥት መፈክር ፖሊሲ የገበያ ኢኮኖሚ መርህ ሥር በነበረችበት ጊዜም የሥራ አጥነት፣ የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የመሳሰሉት የፖሊሲ ድክመት ችግሮች ይሳበቡ የነበሩት በገበያ ጉድለት ነበር፡፡ አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ በተያያዘችው ግማሽ የልማታዊና ግማሽ የሊበራል ገበያ ኢኮኖሚ መስመር፣ ከዋጋ ንረትና ከሥራ አጥነት በተጨማሪ ወደ ፊት ከፍተኛ የሀብት ይዞታና የገቢ ክፍፍል ልዩነት ይፈጠራል፡፡
የፖለቲካ ሥልጣን ለመጋራት የቋመጡት የኢሕአዴግ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም የዋጋ ንረት ሲከሰትና የሥራ አጥ ቁጥር ሲበዛ በዓይን ያዩትን በአፍ ለመናገር ባይሰንፉም፣ የዋጋ ንረትም ሆነ የሥራ አጥነት ምክንያቶች ከመከሰታቸው በፊት አውቀው ለማስጠንቀቅ ወይም ከተከሰቱም በኋላ የተከሰቱበትን ምክንያት ለመተንተን አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡ ፓርላማ ሲገቡ ለመናገር እየቆጠቡ እንደሆነም አይታወቅም ብቻ፣ ትግላቸው ሁሉ የፓርላማ ወንበር ለማግኘት ሆኗል፡፡ ይህ የእነርሱ ድክመት ለኢሕአዴግ እንደ ጥንካሬ እየተቆጠረ በብዙዎች ዘንድ ኢሕአዴግን የሚተካ ኃይል በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደማይፈጠር እየተገመተ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው g[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡