በሀብቶም ገብረ እግዚአብሔር
ኢትዮጵያችን ላለፉት ሦስትና አራት አመታት ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ አገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢሕአዴግም በዚህ ባለንበት ጊዜመንታ መንገድ ላይ ቆሞ የትኛውን መምረጥ እንዳለበት ግራ ተጋብቶ እያየነው ነው፡፡ ግንባሩ የሚመርጠው መንገድ የአገራችንንና የሕዝባችንን መፃዒ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው፡፡ ስለነዚህ መንታ መንገዶች ምንነት ከመግለጼ በፊት በቅድሚያ የተወሰኑ ነባራዊ ያልተደበላለቁ እውነታዎችን ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
የሕዝባችን መገለጫ
የአገራችን ሕዝብ እንደ ማንኛውም የዓለማችን ጭቁን ሕዝብ ኢፍትሐዊነትን ይጠላል፡፡ ጥላቻውንም በተግባር በመግለጽ እስከ አሁኗ ሰከንድ ድረስ ቀላል የማይባል ዕርምጃ ተጉዟል፡፡ የአብራኩ ክፋዮች የሆኑት ልጆቹ እየመሩ ኢትዮጵያ አገራችን ገነት ሆናለት መኖር አጥብቆ የሚመኝና ዛሬም ተስፋ ያልቆረጠ ሕዝብ ነው፡፡ የትናንት ኃያልነቷን ለመመለስ ዛሬም እየተጋ ነው፡፡ ማን ካልን ሕዝቡ፡፡ ነገር ግን በአብራኩ ክፋዮች ለሕዝብና ለሕዝብ ተቆርቋሪነት የመጓደል ሀልዮት ዛሬም በሚገባው መጠን ያልተካሰ ታጋሽ ሕዝብ!!!
ታሪካችን ከአሁን ወደ ኋላ – ከኋላ ወደ ፊት
አገራችን ኢትዮጵያ የአራት ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች በመሠረቱትና መጠሪያውንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መመራት ከጀመረች እነሆ ሃያ ሰባተኛ ዓመቷን አስቆጥራለች፡፡ ፓርቲው የሚከተለውን ርዕዮተ ዓለም ከግንባሩ መጠሪያ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይኼውም አንድም አብዮታዊ ሲሆን፣ አንድም ዴሞክራሲያዊ የሚለው ነው፡፡ ግንባሩ በዚህ ርዕዮተ ዓለም እመራለሁ ብሎ አገር ማስተዳደር በሚጀምርበት ወቅት ከራሱ ከፓርቲው ግለሰብ አባላት፣ ከአገራችን ምሁራን፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቀላል የማይባል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የተቃውሞው መነሻ የተለያየ የነበረ ቢሆንም፣ ዋነኛውና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ (በተለይ የምዕራቡ ዓለም ተቋማትና ግለሰቦች) ያነሱት የነበረው ጥርጣሬ፣ ግንባሩ የርዕዮተ ዓለሜ ምሰሶዎች ናቸው ብሎ መጠሪያው ላይ ጭምር ያሠፈራቸው አብዮታዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ጥምረት ነበረ፡፡ እነዚህ አካላት አብዮታዊነትና ዴሞክራሲያዊነት በተናጠል እንጂ በጋራ ሊሆኑ የማይችሉ ፍፁም በተቃራኒ የቆሙ ርዕዮቶች ናቸው ብለው ተከራክረዋል፡፡ አብዮት ብሎ ዴሞክራሲያዊነት ሊኖር አይችልም ብለው በዓለም ላይ የተደረጉ አብዮቶችን ከፈረንሣይ አብዮት ጀምረው እንደ ምሳሌ እያጣቀሱ ሞግተዋል፡፡ መሞገት ብቻ አይደለም የኢሕአዴግን ሐሳብ ለማስቀየር ትልልቅ ሚዲያዎቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ ተቋሞቻቸውን በመጠቀም ተፅዕኖ ለማሳደር ሞክረዋል፡፡
ኢሕአዴግ በበኩሉ የራሱን መከራከሪያዎች በማቅረብ ለማሳመን ጥረት አድርጓል፡፡ ይኼውም የምመራው ሕዝብ በከፍተኛ የድህነት አረንቋ ውስጥ በመሆኑ፣ ፈጥኜ ይኼንን ሕዝብ ከድህነት ማውጣት ስላለብኝ አብዮታዊ ባህሪ የግድ ያስፈልገኛል በማለት የምመራው አገር የተለያየ ማንነት፣ ቋንቋ፣ እምነትና እሴት ያላቸው ሕዝቦች መኖሪያ በመሆኑ ይኼንን ብዝኃነት የሚያስተናግድ ሥርዓት መገንባት የምችለው በዴሞክራሲያዊነት ብቻ በመሆኑ፣ ዴሞክራሲያዊነት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግድ መላበስ ያለብኝ ባህሪ ነው ብሎ ተከራክሯል፡፡ ማን ነበረ ትክክል? ሰፊ ጥናት ለሚያደርጉ ምሁራንና ለአንባቢያን ትቼዋለሁ፡፡ እዚህ ላይ ይኼንን እናቁምና ኢሕአዴግ አገራችንን ማስተዳደር በጀመረበት ወቅት የነበረውን የሕዝባችንንና የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በወፍ በረር ለማየት እንሞክር፡፡
የአገራችንን ሕዝቦች ለመጀመርያ ጊዜ የምመራበት ርዕዮተ ዓለም አለኝ ብሎ ሕዝቡን ማስተዳደር የጀመረው ከ1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት በኋላ ሥልጣን የተቆጣጠረው ደርግ ነበረ፡፡ ደርጉ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም መመርያው እንደሆነ ለሕዝቡ አውጆና ወደ ሕዝቡ የማስረፅ ሥራ ለመሥራት ጊዜ አልፈጀበትም ነበር፡፡ ነገር ግን ርዕዮተ ዓለሙን በማቀንቀን አብዮቱን አስነስቶ የዘውድ አገዛዙን የጣለው የተማረው ክፍል ሳይሆን፣ በኋላ በአጋጣሚ የመጣው የወታደሩ ክፍል ሥልጣን በመቆናጠጡ ምክንያት የርዕዮተ ዓለሙን መሠረታዊና በተነፃፃሪ ለመተግበር ቀለል ያሉ ትግበራዎችን ሳይፈጽም አገሪቱ ወደማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ገባች፡፡ በአጭሩ ርዕዮተ ዓለሙ በደም ሥራቸውና ጠንቅቀው የሚያውቁት ተገፍተው ያልገባቸው እንዲፈተፍቱና አገራችንን ወደለየለት ቀውስ አስገብተዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ለማንሳት የፈለግኩት ነጥብ ይኼንን አይደለም፡፡ ለማንሳት የተፈለገው ነጥብ ሕዝባችን በርዕዮተ ዓለም ላይ ያለው የአመለካከት ንቃት ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሊሳሳት አይችልም፡፡ ሕዝብ ተሳስቶ አያውቅም፣ ለወደፊትም አይሳሳትም፡፡ የሚሳሳተው እንመራሀለን ብሎ መንበረ ሥልጣኑን የጨበጠው የሥልጣን አካል ነው፡፡ በመሆኑም ከደርግ በፊት ለብዙ ዘመናት በአገራችን ኢትዮጵያ የገባሪና የአስገባሪ ሥርዓት እንጂ ምንም ዓይነት ርዕዮተ ዓለም አልነበረም፡፡ የነበረው ርዕዮተ ዓለም በሰፊው ሕዝባችንና በገዥዎቹ ይታይ ከነበረው ከገባሪና ከአስገባሪ ዕይታ ነበር፡፡ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን መልካም ግንኙነት ተጠቅመው አገሪቱን በርዕዮተ ዓለም የማስተዳደር ዕድል የነበራቸው የወቅቱ የአገራችን መሪ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ከእሳቸው አስቀድመው እንደነበሩት መሪዎች መጓዝ በመምረጣቸው አጨራረሳቸው ሳያምር ቀርቷል፡፡ ርዕዮተ ዓለሙን ትተን በመንግሥት መዋቅር ሊኖር የሚገባ የሥራ ክፍፍል በየዘርፉ ሚኒስትሮች መሾም የጀመሩት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ነበሩ፡፡ ከዚያ በፊት ግን አንድን አካባቢ የሚያስተዳድር ባላባት ራሱ የግብርና ኃላፊ፣ ራሱ የፀጥታ ኃላፊ፣ ራሱ ዳኛ፣ ወዘተ. የነበረበት እውነታ ነው የነበረው፡፡ ሄዶ ሄዶ ንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ፡፡
ደርግ ከ1966 እስከ 1983
ስለዚህ ደርግ በገባው መጠን የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምን በሕዝቡ ውስጥ ለማስረፅ ማስተማር ሲጀምር፣ የነበረው ኅብረተሰብ ምን ዓይነት ነበረ የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ መልሱ ባጭሩ አይደለም ሰብዓዊ መብቱን ይቅርና ማወቅ ያለበትን በገዥዎቹ መልካም ፈቃድ እያገኘ እንዲኖርና እንዲገዛ ተፈርዶበት የኖረ ሕዝብ ነበር፡፡ ታዲያ ደርግ በገባው መጠን የሶሻሊዝም/ኮሙዩኒዝም ርዕዮተ ዓለም ኅብረተሰቡን ማስተማርና ማስረፅ ሲጀምር ሕዝባችን ከኖረበት እሳቤ ፍፁም የተለየ ነገር በመሆኑ፣ ለማስረፅ ከፍተኛ ልፋትና ያላሰለሰ ጥረት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ደርግ ግን ርዕዮተ ዓለሙ መጀመርያም ቢሆን የራሱ ውጥን ያልነበረ በመሆኑ (አብዮቱን ያስነሱ ምሁራንና ተማሪዎች ነበሩ) ከሕዝቡ ቅራኔ ሲገጥመው ለማፈን በሚያደርገው ጥረት፣ የሕዝቡን ተቃውሞ አባብሶ አገሪቱን ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ዳርጎ አልፏል፡፡ በአጠቃላይ የደርግ ባለሥልጣናት ሶሻሊዝም ለሕዝባችን መልካም ነው ብለው አስበው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ መልካም የሆነን ነገር ማወቅና መተግበር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ደርጎች መልካም ያሉትን ርዕዮት ለመተግበር በሚያደርጉት ጥረት የገጠማቸውን ተቃርኖ የሚቋቋም፣ ወይም ደግሞ ታላቁን የአገራችንን ሕዝብ ለመምራት ብቃቱም ሆነ ዝግጁነቱ ስላልነበራቸው እጃቸውን በሕዝብ ደም አጨማልቀው አልፈዋል፡፡ ሕዝብን በማስተዳደር ሒደት መልካም መመኘትና መልካም መተግበር እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ መልካም መመኘትህን ለሕዝብህ የማሳመንና የማሰለፍ ችሎታ ሲጎልህ፣ እንዴት መልካም እያሰብኩለት አይረዳኝም ወደሚል ጥሬ ንዴት ገብተህ ወገንህን በአደባባይ መጨፍጨፍ ትጀምራለህ፡፡ መልካሙን ነገር ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ወደ መሬት ማውረድ ስለማይቻል ኅብረተሰቡን ማሳመን ምንም አማራጭ የለውም፡፡ የማንን ሕይወት ለመቀየር ነው ሕዝቡን ከጎንህ ሳታሠልፍ የምትዋትተው? ዕውቀት፣ ብስለትና ጥልቅ ሕዝባዊነት ያልተካተተበት መሪነት መጨረሻው ልክ እንደ ደርግ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ከ1983 ጀምሮ – አጠቃላይ ቅኝት ከኢሕአዴግ ሥርዓት ጋር በማዋሀድ
ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር በሚጀምርበት ወቅት ደርግ ከገጠመው ኅብረተሰብ የሚለየው፣ እንኳን ደርግ ኢሕአዴግ ራሱ ዛሬም ድረስ ሊደመስስ ያልቻለው የገባሪና አስገባሪ ፊውዳል አስተሳሰብና ያልጠራና ድብልቅልቁ የወጣው፣ ደርግ ለማስረፅ የሞከረው ኮሙዩኒዝም ቀመስ የሆነና ሚናውን ያለየ ኅብረተሰባዊ እሳቤ ነው፡፡ አሁን 2010 ዓ.ም. ላይ በአንድ ጎልማሳ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካዊ ንግግር ውስጥ ሦስት ዓይነት ነገሮችን በተለያዩ አጋጣሚዎች መስማት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በሙስና የተቸገረ አንድ ዜጋ ስለሌብነት አምርሮ ሲናገር ትሰማውና አንድ ቤተሰቡ ወይም የቅርብ የሚለው ሰው የመንግሥት ሹመት ሲያገኝ ሰርፆ አልነቀል ካለው የፊውዳል መንፈስ አጣቅሶ፣ የድርሻውን እንዲወስድ መክሮ ‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› ብሎ ያስረግጣል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሌላ ብሔር ወይም እምነት ተከታይ በመሆኔ መድልኦ ተደርጎብኝ የሚገባኝን አገልግሎት ሳላገኝ ቀረሁ ሲል ልትሰማው ትችላለህ፣ ያው አንድ ግለሰብ፡፡
የሆነ ሆኖ ደርግ ሊያሰርፅ ከሞከረው አዲስ ርዕዮተ ዓለም በተጨማሪ፣ ኢሕአዴግ የተረከበው ሕዝብ በባሰ የድህነት አረንቋ፣ ጭቆናና ውርደት ውስጥ የተዘፈቀ ነበረ፡፡ መንበረ መንግሥቱን የጨበጠው ኢሕአዴግ ደግሞ በምታምነው እመን፣ በቋንቋህ እደር፣ ራስህን አስተዳድር የሚል አዋጅ በማወጅ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮቴን ጀምሬያለሁ ብሎ ከሽግግር መንግሥቱ በኋላ በይፋ ሥራውን ጀመረ፡፡ በእነዚህም ዓመታት ልክ እንደ ደርግ ባይሆንም ሥልጣን የሰጠው ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ርዕዮተ ዓለሙን አስታጥቋል ማለት አንችልም፡፡ ዓላማውን ለሕዝቡ አስታጥቆ በማዝምትና ውጤት በማስመዝገብ ደረጃ እንደማይታማ ከመግለጽ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ለምን ቢባል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንኳ የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ተብለው የተያዙ ነጥቦችን በማሳካት ዕውቅና ያገኘ ግንባር ነው፡፡ ይኼንን ደግሞ ተማምኖና አሳምኖ ሕዝቡን ከጎኑ ማድረግ ባይችል ኖሮ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ከላይ በጠቀስነው ለአገራችን መልካም ማሰብና በመተግበር መካከል በሚኖረው ክፍተት ምክንያት ታስበው ያልተሞከሩ ውጥኖችን ሁሉ ኢሕአዴግ ለማሳካት ችሏል፡፡
እንደ ምሳሌ ዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማንሳት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ስለመልካም እሳቤና ተግባር ልዩነት በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዓባይ ላይ ግድብ የመገንባት ዕቅድና ፍላጎት አልነበራቸውም ማለት ታላቅ ታሪካዊ ክህደት ነው፡፡ ሁለቱም ሥርዓቶች ይኼንን መልካም ህልም ለመፈጸም ዕቅድ ነበራቸው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት መልካም ነገር ለወገንህ ተመኝተህ ማቀድና ያንን ዕቅድ መተግበር እኩል ክብደት የላቸውም፡፡ ጥልቅ የሆነ ማሰብና አገራዊ፣ አኅጉራዊ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍዊ ሁነቶችን ወደ ግንዛቤ ያስገባ ፖለቲካዊ አመራር መስጠት ያስፈልግ ነበር፡፡ አልቻሉም እንጂ አልፈለጉም ማለት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን መፈለግ ሌላ መቻል ሌላ፡፡ ለማንኛውም ኢሕአዴግ ስላሳካቸው መልካም ነገሮችና ስለፈጠራቸው ድፍርሶች ማውራት ዓላማዬ አይደለም፡፡
የሆነ ሆኖ ኢሕአዴግ በተነፃፃሪ ስላሳካው አብዮታዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ለማወደስ እኔም እናንተም ጊዜ የለንም፡፡ ለዚያ ቢበላ ቢበላ እንደ ቀጨጨ ወይም አልጠረቃ ላለው የመንግሥት ሚዲያ በቂ ይመስለኛል፡፡ ዕውቀት እንዲገበይ ዕድል እያለው ዕውቀት የማይገባውን እንደዚህ ነው የማየው፡፡ የቀረፃ ስቱዲዮ እንጂ የአዕምሮ ብቃትን መኮረጅ የማይችሉ የሚዲያ ተቋማት ባለቤት ነው ግንባሩ፡፡ እዚህ ላይ ርዕስ ለቀሀል አትበሉኝና የኢሕአዴግ ሚዲያዎች የሠሩትን ለሕዝቡ ከማስረዳት ይልቅ፣ ከነሱ በተቃራኒ ቆመው የሐሰት ወሬ የሚያስወሩባቸውን ፕሮፓጋንዳ በመከላከል የተጠመዱ መሆናቸውን ሳላነሳ ማለፍ አልፈልግም፡፡
የዛሬው ሁኔታ – ኢሕአዴግ ያለበት መንታ መንገድና የአገራችን ዕጣ ፈንታ
ወደ ፊት አራማጅ መንገድ ብለን መውሰድ የሚገባን የተሳኩ ነገሮችን ማወደስ ሳይሆን በላቀ ሁኔታ ማጎልበት፣ በተፈጠሩ ችግሮች መብሰልሰል ሳይሆን እየቀረፉ መሄድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ዋናው ነገር አገራችን ቀውስ ውስጥ ናት፡፡ ያ ቀውስ በምን መጣ? አገሪቷስ ከዚህ ቀውስ እንዴት ትውጣ? ማንስ ነው የሚያወጣት? የሚሉት ጥያቄዎች በአግባቡ መነሳት ይኖርበታል፡፡
አሁን አገሪቱ ያለችበት ቀውስ እንዴት መጣ?
ኢሕአዴግ የ1993 ዓ.ም. የውስጥ ክፍፍሉን ተከትሎ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የበላይነት በተረጋገጠበት ሁኔታ፣ በሕዝባዊና ዴሞክራሲያውያን የበላይነት ተጠናቋል በማለትና የተለያዩ ሴክተሮች የሚመሩበት ራሱን የቻለ መሪ ሰነድ (የግብርና ፖሊሲ፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ሌሎች) አዘጋጅቼ ወደ ሥራ ገብቼያለሁ በማለት ለሚያስተዳድረው ሕዝብ አወጀ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ መሪ ሰነዶች የተባለው ለውጥ ሕዝቡ ማጣጣምና ማየት ሳይጀምር ቀጥሎ የመጣው ምርጫ 97 ግንባሩ ፈጽሞ ያልጠበቀው ኪሳራ አመጣበት፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ፡፡ የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ አገሪቷ ወደ አለመረጋጋት ምህዋር እንድትገባ ሆነ፡፡ ተቃዋሚዎችም በተለይም ቅንጅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘውን መቀመጫ እንደማይገባበት በማወጅ ለተለያዩ የተቃውሞ ዓይነቶች ሕዝቡን መጥራት ጀመረ፡፡ በስተመጨረሻም በርከት ያሉ ወገኖቻችንን ሕይወት በመቅጠፍና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እስር ምርጫው ያመጣው ማዕበል እንዲቆም ተደረገ፡፡ እዚህ ላይ ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ አንድ የሚቆጨኝን ነገር ሳላነሳ ማለፍ አልፈልግም፡፡ ያገኙትን መቀመጫ አንወስድም ያሉት ፓርቲዎች በተቃራኒው ቢያደርጉ ኖሮ ለአገራችን የዴሞክራሲ ዕድገት ያደርጉት የነበረው አስተዋፅኦ ሳስበው ያንገበግበኛል፡፡ የሆነ ሆኖ ዋናው መነሻችን አሁን ያለንበት ቀውስ ነውና ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ እስካሁኑ አገራዊ አለመረጋጋት የመጣበትን መንገድ በወፍ በረር ለመቃኘት እዚያ ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ፡፡
ከምርጫ 97 ማግሥት ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት አገር ከማረጋጋት ባለፈ የሕዝቡን ልብ ለመመለስ ከምርጫው በፊት ከነበረው ብዙ እጥፍ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ የዚህ ሥራ መሪ የነበሩት ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በ1995 ዓ.ም. ፀድቀው ወደ ትግበራ የገቡ መሪ ሰነዶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሥራዎች በዋነኝነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነበረ፡፡ በተለይ ግንባሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የቀድሞውን የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሩ በስፋት እንዲሠራው የተደረገው ኅብረተሰቡን በቅርብ የማወያየት ተግባር ከፍተኛ ፖለቲካዊ ድል አስመዝግቦበታል፡፡ ድሉን ያፈጠነው ደግሞ የፖለቲካ ሥራውን ያጀበው በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መታየት የጀመረው የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ነበር፡፡ ይኼ ኢኮኖሚያዊ ስኬት ግንባሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ፖለቲካዊ ድል እንዲያስመዘገብ አድርጎት ምርጫ 2002 በተረጋጋ ሁኔታ በድል እንዲወጣ ረድቶታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ለዛሬው ቀውስ ከፍተኛ የሚባለውን ስህተት የሠራው ከዚያው ምርጫ 97 ማግሥት ነበረ፡፡ ይኼውም በየደረጃው የአባላት ምልመላ ማድረግ ጀመረ፡፡ ጭራሽ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት በይፋ ማወጅ ጀመረ፡፡ በወቅቱ ከአገራችን ሕዝብ ቁጥር ወደ አሥር በመቶ የሚጠጋ ሕዝብ አባሌ ነው እንደ ማለት ነበረ፡፡ ይኼ ደግሞ ላይ ላዩን ሲታይ ትልቅ ስኬት መስሎ ታይቶ ነበረ፡፡ ክፋቱ ገና ነው ወይም ደግሞ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‹‹The Worst Yet To Come›› በሚል ንግርት ብዙዎቻችን በትዝብት አልፈነዋል፡፡ ትዝብቱ የሚመነጨው ከሌላ ሳይሆን ከፓርቲ አባልነት መርህ፣ ሥነ ምግባርና ሒደት የሚመነጭ ነበረ፡፡
በመሠረቱ በብዛት አባላትን መመልመል በራሱ ችግር አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ጥያቄው ሊሆን ይገባ የነበረው አመላመሉ ምን ዓይነት ሒደትን የተከተለ ነው የሚለው ነው፡፡ ከዓለም የፖለቲካ ታሪክ መረዳት እንደምንችለው የፓርቲ አባልነት እንዲሁ በቀላሉ ከጎዳና የሚገኝ ዳረጎት ሳይሆን፣ በጥብቅ ሥነ ምግባርና መርህ የሚመራ መሆኑን ነው፡፡ ኢሕአዴግም ከምርጫ 97 በፊት ባለው ታሪኩ በዚህ አካሄድ ብዙም የሚታማ ግንባር አልነበረም፡፡ ከምርጫው በኋላ የሕዝቡ ምላሽ በፈጠረበት መደነባበር ሊሆን ይችላል መርህን ባልተከተለ መልኩ ያደረገው፡፡ የአባላት በገፍ ምልመላ የራስን ምቹ ሜዳ (Comfort Zone) ከመፍጠር ባለፈ ዘላቂ አገራዊ ውጤት እንደማይኖረው የብዙዎች ልሂቃን ግምት ነበረ፡፡ ይኼ ምቹ ሜዳ የመፍጠር ሒደት ለጊዜው እንጂ የሚዘልቅ ጠቀሜታ እንደማይኖረው የብዙዎቹ የአገራችን ምሁራን ቢገነዘቡትም ኢሕአዴግ ሊያምን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
አንድ ርዕዮተ ዓለም አለኝ የሚል ፓርቲ ከየትኛውም የማስፈጸም ሥራ በፊት የፖለቲካ ፕሮግራሙን በአባላቱ የደም ሥር እንደሚከተሉት ሃይማኖት ሊያሰርፅ ይገባል፡፡ ርዕዮተ ዓለሙን አምኖ ለመሞት የተዘጋጀ እስኪሆን ድረስ አንድ ግለሰብ የዚያ ፓርቲ አባል ሊሆን አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡ አለበለዚያ መርህና አመክንዮ (Principle And Logic) ተጥሰው ላልተገባ ዓላማ ውለዋል ማለት ነው፡፡ በኢሕአዴግ ሁኔታ ደግሞ ምርጫ 97 የፈጠረበት መወናበድ ለዚህ መርህና አመክንዮ መጣስ ዳርጎታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢሕአዴግ እንዳደረገው ከላይ በተጠቀሱት የአባልነት መሥፈርቶች በሁለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ አባላትን መሰብሰብ የማይቻልና ተደርጎ የማያውቅ ነው፡፡ ግንባሩም ለዚህ ታሪካዊ ስህተቱ የሚገባውን ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡ ለዚህም ምስክራችን ባለንበት ወቅት ከፓርቲው ርዕዮተ ዓለም ጋር ፈጽሞ የማይገናኙ መግለጫዎች ሲሰጡ የሚውሉት፣ ከፍተኛ የፓርቲውና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በቂ ምስክራችን ናቸው፡፡ በተለይ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ለምናውቅ ሰዎች፡፡ ማንኛውም ዜጋ የፈለገውን ርዕዮት ዓለም የማራመድ መብት አለው፡፡ ነገር ግን አባልነቱ ሌላ ርዕዮቱ ሌላ ሲሆን፣ የዚያን ፓርቲ የንቅዘት ደረጃ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ አባል የሆነበትን እንጂ የርዕዮተ ዓለሙን ባለቤት ፓርቲ ንቅዘት እንደማያሳይ ሳንዘነጋ፡፡
ጭቁኑ የአገራችን ሕዝብና ኢሕአዴግ ከዚህ የተደናበረ የአባላት ምልመላ ምን ተረፋቸው ብለን ስንጠይቅ ወደ ዛሬው የቀውስ ምንጭ በቀላሉ ይመራናል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በተቀመጠው የፓርቲ አባልነት የሥነ ምግባር ደረጃ የአባላት ምልመላ ሳያደርግ ኢሕአዴግ የአባላት መጠኑን ሰባት ሚሊዮን እንዳደረሰ ሲገልጽልን ለራሱ የደገሰው አሜኬላ ገብቶት አልነበረም፡፡ ከነበረው የዕድሜ ደረጃ በሚጠበቀው መጠን የመለመላቸውን አባላት ለርዕዮተ ዓለሙ ታማኝና ሕይወታቸውን የሚሰው የማድረግ ልምድና መዋቅራዊ ብቃት ነበረው ለሚለው ጥያቄ መልሱ አልነበረውም የሚል ነው፡፡ የኢሕአዴግ ቀደምት መሥራቾች ሕወሓትና ኢሕድን (ኢሕድን በኋላ ኦሕዴድንና ድኢሕዴን የመሠረቱ ነባር ታጋዮችን በመለየት ብአዴን ሆኗል) ከአምስት መቶ ሺሕ አባላት በላይ አስተዳድረው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በአባልነት አይያዙት እንጂ ሕዝቡን ከጎናቸው አሠልፈው እንደነበረ ግን መካድ አይቻልም፡፡ በአባል ምልመላ ግን ያልተገባ ሒደት ከምርጫ 97 በኋላ ይቅር የማይባል ስህተት ኢሕአዴግ እንደሠራ ማመን አለብን፡፡ የቀደመ ታሪኩን መርሳት ያስከፈለው ዋጋ ነው፡፡ ካላመነ እንኳን ሰባት ሚሊዮን አባል፣ 20 አባልን የፖለቲካ ትምህርት አስተምረህና አንፀህ ማሠለፍ ራሱ ለምን ያህል ድል እንደሚያበቃ ስለዓለም የፖለቲካ ታሪክ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ከግንባሩ መሥራቾች መካከል ሕወሓት በዚህ የምልመላ ሒደት ተካፋይ እንደ መሆኑ፣ ምሥረታው በአምስት ያመኑ አባላት መጀመሩን መረሳቱ ራሱ አስገራሚ ነበረ፡፡
ኢሕአዴግም ያንን ያህል አባላት መለመልኩ ብሎ ሲያበቃ እንኳን ርዕዮተ ዓለሙን ሊያሳምናቸው ይቅርና መረጃቸውን በተሟላ ሁኔታ ማጠናቀር በሚችልበት ደረጃ አልነበረም፡፡ አይጠጌ አይነኬ አመራሮቹ እንኳን የአባሎቻቸውን ሁኔታ ሊከታተሉት ይቅርና ርዕዮተ ዓለሙ ላይ ያላቸው የራስ ቁርጠኝነት በተለይ በዚህ ወቅት ለሰፊው የአገራችን ሕዝብ ግልጽ ሆኗል፡፡
የአባላት ምልመላ ለዛሬው ቀውስ ያደረገው አስተዋጽኦ ምንድነው?
እንግዲህ አባላቱን በዚህ መንገድ ያጋበሰው ኢሕአዴግ በሒደት መንግሥታዊ መዋቅሩን በዚህ ሁኔታ ለተፈበረኩ አባላቱ በብዛት ለማስረከብ በቃ፡፡ እንኳን እንደዚህ ለበዙ አባላቱ ሪዕዮተ ዓለም በብቃት ሊያስታጥቅ ይቅርና መላው አባላቱ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑበት ደረጃ ላይ መድረስ የጀመረው ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ነበረ፡፡ በትንሹ እንኳ ወርኃዊ የአባልነት ክፍያ በጥብቅ ዲሲፕሊን ማስፈጸም የማይችልበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡ በእንደዚህ አኳኋን የመጡ አባላቱ ናችው እንግዲህ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል መንግሥቱ ያሉ መዋቅራት ውስጥ በሒደት አብላጫ እየወሰዱ የመጡት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ይኼ አካሄድ እንደማያዋጣ የተረዱ እውነተኛ የርዕዮተ ዓለሙ ታማኞች አባልነታቸውን እየተው ፓርቲውን በብዛት መልቀቅና ከፖለቲካው መራቅ ጀመሩ፡፡ በፅናት እንታገላለን ያሉት ደግሞ በፍጥነት ሥልጣን በሥልጣን ላይ እየደረቡ በመጡት እነዚህ ሰርጎ ገቦች፣ የተለያየ ምክንያት እየተፈለገ በስፋት እንዲመነጠሩ ተደረገ፡፡ አስቀድሞ ይጠበቅ እንደነበረው ርዕዮተ ዓለምህን አስቀድመህ ያላስታጠከው አባል ርዕዮተ ዓለምህን ሊያስፈጽምልህ አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሁ ብዙ ፖሊሲዎች ማውረድ ቢጀምርም፣ የሚያስመስል እንጂ የሚፈጽምለት አባል በስፋት ሊባል በሚችል ደረጃ ማግኘት ተሳነው፡፡ ጭራሽ በግንባሩ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ የፓርቲው መርህ የሆነው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እየተጣሰ ሁሉም በየፊናው በስሜት ወደ መነዳት የተገባበትን እውነታ መመልከት ከጀመርን ውለን ማደር ጀምረናል፡፡
ይኼኔ ነው እንግዲህ ለመጀመርያ ጊዜ በታሪኩ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል እያየ የነበረው ሕዝባችን ወደ ምሬትና የለየለት ጭቆና ውስጥ መግባት የጀመረው፡፡ ተወደደም ተጠላም ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ ሕዝቡ በግልጽ የተመለከተው የተለያየ ኢኮኖሚያዊ ድሎች ማስመዝገብ ችሎ ነበር (ግንባሩ እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ድሎች መመዝገብ የጀመሩት ከ1995 ዓ.ም. ከፓርቲው ተሃድሶ በኋላ ነው ይላል)፡፡ እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች በስፋት ሀብት መፍጠር ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ይኼ ሀብት ፈጠራ በመጀመርያዎቹ ዓመታት እየሄደበት የነበረው ፍጥነት እንዲቀዘቅዝና ጠፍቷል የሚባልበት ደረጃ ላይ ያደረሱ ሁኔታዎች ተፈጠሩ፡፡ የሥራ ዕድልና የሀብት ፈጠራ ሲቆም ደግሞ አገር በሰላም ውላ ታድራለች ማለት አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ አርቆ ማየት አቃተው እንጂ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የፈጠረው የሥራ ዕድል በምርጫው ወቅት በሥራ አጥነትና በመልካም አስተዳደር ምሬት ብጥብጡ ውስጥ ሲሳተፍ የነበረና ሳይሳተፍም የሐሳቡ ደጋፊ፣ እንዲሁም ኢሕአዴግን ምንም ጠብ ሳያደርግለት ግን ይደግፈው ለነበረው ወጣት ነው፡፡ በዓለም ላይ ሕይወት እስከቀጠለ ድረስ ሁልጊዜ ወጣት ይፈጠራል፡፡ የአገራችን እውነታ ከዚህ የማይሻር ሕግ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በአሥር ዓመት ውስጥ ሊገጥምህ የሚችለውን የወጣት ኃይል ማሰብና ለዚህም በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተህ መጠበቅ እንደ ኢሕአዴግ ላለ ራሱን በተራማጅነት ለሚቆጥር ፓርቲ ነጋሪ የማያሻው የሞት ሽረት ኃላፊነት ነበር፡፡ ነገር ግን ይኼን ማድረግ ይቅርና በሌቦች (ይኼንን ሌቦች የሚል ቃል የምጠቀመው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የሚጠቀምበት ኪራይ ሰብሳቢ የሚል ቃል እጅግ ለዘብተኛና ያለንበት ሁኔታ ይገልጻል ብዬ ስለማላምን ነው፡፡ ካሁን በኋላም ይኼንን ሌቦች የሚል ቃል መጠቀሜን እቀጥላለሁ) የተጥለቀለቀውን መዋቅሩን በቁርጠኝነት ለማፅዳት ዳተኛ የሆነ ፓርቲ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ የአገሪቷ አለመረጋጋት ከተከሰተ ጀምሮ በዋነኝነት ተሳታፊ የሆኑት በአብዛኛው በአሥራዎቹ መጨረሻና በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ ያሉ ወጣቶች ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በ1997 ዓ.ም. ገና ሕፃናት የሚባሉና ነገር ዓለሙን ያላዩ ታዳጊዎች ነበሩ፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለትምህርት በሰጠው ትኩረትና ከዓለም ነባራዊ ሀልዮት በፈጣን ሁኔታ መለዋወጥ፣ በተለይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋት ምክንያት አሁን በአገራችን ያሉ ወጣቶች በብዙ መንገድ ከአሥር ዓመት በፊት ከነበሩት ወጣቶች በአመለካከትም ሆነ በፍላጎት እጅግ የተለዩ እንደሚሆኑ አስቀድሞ በሳይንሳዊ መንገድ መተንተንና መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደገለጽኩት ከምርጫ 97 በኋላ የተጀመረው የጅምላ አባላት ምልመላ በአግባቡ እንኳን ርዕዮተ ዓለሙን ሳይሰርፅ እከተለዋለሁ ከሚለው ለሰፊው ሕዝብ የወገነ ርዕዮተ ዓለም፣ በተፃራሪ ሕዝቡን በስፋት የሚበድሉ የሥልጣን ባለቤቶች እንደ አሸን መፈልፈል ጀመረ፡፡ የታቀደው የልማታዊ ፐብሊክ ሰርቫንት ወደ ሌባዊ ፐብሊክ ሰርቫንት ቀላል በማይባል ደረጃ ተዋጠ፡፡ ለአርሶ አደሩ አንደኛ ጠበቃ ነኝ የሚል ግንባር አርሶ አደሩን በስፋት እያፈናቀለ ተገቢውን የማቋቋምና የካሳ በአግባቡ ሳይፈጽም አርሶ አደሩን በገዛ መሬቱ ባለሀብቱ በገነባው የሆነ ነገር (መጋዘን፣ ፋብሪካ ወይም ታጥሮ የተቀመጠ) ላይ ዘበኛ ሲደረግ በዝምታ መመልከት ጀመረ፡፡
የነገዱ ሳይሆን በመንግሥት ሥልጣን የከበሩ ሌቦችን በየአካባቢው የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ የሕግ ያለህ ቢልም፣ ምንም ዕርምጃ እንደማይኖር በማወቁ ቀላል የማይባል የኅብረተሰብ ክፍል ብቸኛ የመክበሪያ መንገድ ወይ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ወይ ከመንግሥት ባለሥልጣን መጠጋት ወደሚል እሳቤ እንዲገባ የመንግሥት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የእሳቤ መንቅዝ ነበረ፡፡ ለዚህም ሙሉ ኃላፊነቱን ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት መውሰድ አለበት፡፡ የኮንትሮባንድና የጥቁር ገበያ ንግድ በስፋት የመንግሥት መዋቅር በመጠቀም ጭምር ይከናወኑ ጀመር፡፡ አገሪቷ እየፈጠረች በመጣችው ሀብት ምክንያት በራስ አቅም የተወጠኑ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የታለመላቸው ግብ ሩቡን እንኳ ሳይመቱ፣ አንድ ፕሮጀክት የተመደበለት የአገሪቱና የሕዝቡ ሀብት እንደጉም ተኖ ሲጠፋ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚጠየቅ አለመኖሩና መቀጣጫ አለመሆኑ፣ ብዙ ፕሮጀክቶች ተመሳሳይ ጎዳና እንዲከተሉ አድርጓል፡፡ በዚህ ወቅት ያልተጓተቱ የመንግሥት ፋብሪካዎች፣ መንገዶችና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች በጀታቸው ባክኖ እንኳ የሚጠይቅ አካል የለም፡፡ የዚህ ምንጭ ደግሞ በስፋት የመበስበስ ውጤት ነው፡፡ አንድ የሕዝብ ፕሮጀክትን የሚመራ ዜጋ በራሱም ሆነ በሌላ ምክንያት የተሰጠውን ሕዝባዊ አደራ መወጣት ካልቻለ፣ ሌላው ቢቀር በራሱ ኃላፊነቱን የማስረከብ ባህል ሊኖር ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መስመር ይልቅ፣ የሌቦች ፍላጎት የፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት በማሳየቱ ይኼ ሕዝባዊ መስመር የበላይነት ተወስዶበት መላወስ አቅቶት በመንፈራገጥ እንዲወሰን ተደርጓል፡፡ ለምን ቢባል በምርጫ 97 ቤተ ክርስቲያን ሄዶ የኢሕአዴግን መውረድ እንዲያይ ሥዕለት አስገብቶ የነበረ ግለሰብ በአግባቡ ርዕዮተ ዓለሙን ሳያስታጥቅና ሳያሳምን የኢሕአዴግ አባል ከሆነ፣ በኋላ በሥልጣን ላይ ሥልጣን እየደረበ ምን ያህል የዘቀጠና የሌባ ኔትወርክ የዘረጋን ግለሰብ እኔ ጥሩ ምስክር ነኝ፡፡
ይኼን ስል ለዛሬው የመዝቀጥና የሌቦች ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማገንገን ሊጠየቅ የሚችለው፣ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ግንባሩን በስፋት የተቀላቀለው አርትዖት ያልተደረገለት የሰፋ የአባላት ምልመላ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ የሰፋ ሀብት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በፈጸሙት ሌብነት መቀጣታቸው የሚረሳ ታሪክ አይደለም፡፡ ቀጣይ ያልሆነበት ሁኔታ ግን የአቶ ታምራት ላይኔን የስኳር ታሪክ በሕዝባችን እንዳይረሳ ሆኖ አልፏል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ኢሕአዴግ ሀብት በአገሪቱ መፍጠር ከቻለ በኋላ እንኳ የመዘበሩትን ቱባ ባለሥልጣናቱን ግለ ሂስ አድርጎ ታርሟል በሚል፣ ትንኝ ወሮት የበሽታ ምንጭ እንደሆነ ኩሬ ፀረ ተባይ ተረጭቷል በሚል ተራ ምክንያት ለፈጸሙት ስህተት ሕዝባዊና የማያዳግም ዕርምጃ ሳይወሰድ ባሉበት የሥልጣን እርከን እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ ‹ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም› እንዲሉ የኢሕአዴግ አባላትን ያለምንም አስተማማኝ ወንፊት መመልመል ሲጀምር ለእነዚህ ቂም ለቋጠሩና ግለ ሂሳቸውን አጎንብሶ ለማለፍ የተጠቀሙበት አባላት ለሕዝቡ ሳይሆን ለራሳቸው በስፋት የሚጠቀሙበት መረብ ለመዘርጋት ችለዋል፡፡ ይኼን ስል ከእነዚህ መሥራች አባላት በኋላ የበሰበሰ መሥራች አባል የለም ማለት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ኢሕአዴግም ሕዝብ ሕዝብ ከመሽተት ወደ ሌቦችና ወደ ንቅዘት ምንጭነት፣ ወደ ማይነኩና የማይጠጓቸው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የጡት አባትነት፣ ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ወደ ሌባ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማዕከላዊነት የዕዝ ሰንሰለት ወደ መሸጋገር መጣ፡፡ ያውም በእነዚህ ሌቦች ዕቅድ ያለመርህ ተመልምለውና የመንግሥትን መዋቅር በተቆጣጠሩት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት፡፡ የአገራችን ሕዝብ አንድ የሚያውቀው እውነታን ልንገራችሁ፡፡ ጀግንነትም ሆነ መፍራት የአንድ ሕዝብ መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ሕዝብ ለመልካም ይመራል እንጂ ለሌብነት ሊመራ አይቻልም፡፡ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ይኼን የመሰለ ፖለቲካዊ ምዕራፍ አጓጉቶ አያውቅም፡፡
አሕአዴግን በመሠረቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ በሌባውና በዴሞክራሲ ኃይሎች መካከል የሞት ሽረት ትግሉ ውስጥ ተገብቷል፡፡ ለአገራችን ሕዝብ በሚገባው ቋንቋ አይገለጽለት እንጂ፣ የኢሕአዴግ የውስጥ ትግል ከሕዝባዊነትና ከፀረ ሕዝባዊነት የሚመነጭ ነው፡፡ በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ኢሕአዴግ በአራት የአገራችን ክልሎች የተመሠረቱ ፓርቲዎች የመሠረቱት ግንባር ነው፡፡ በዚህም ያለ ብሔር ልዩነት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ኃይሎች እንደ ሌቦቹ ባይሆን እንኳ፣ አሁንም ሕዝባዊ ተቆርቋሪነታቸውን በፅናት ይዘው የሌቦችን ግብዓተ መሬት ለማረጋገጥና ዛሬ አርሶ አደሩን ነገ በሚኖረው የኢንዱስትሪ ሽግግር የላብ አደሩን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ እየተጉ ነው፡፡ ግን አንሰዋል፡፡ በሌባው ተበልጠዋል፡፡ ለሕዝቡ ተቆርቋሪነት በሌብነት ተበልጧል፡፡ የሌቦችና የሰርጎ ገቦች ፖለቲካል ኢኮኖሚ (ለጊዜውም ቢሆን የበላይነቱን ያረጋገጠበት ሁኔታ ተስተውሏል) ሕዝባችንም መሮታል፡፡ ርዕዮተ ዓለሙ ሳይነቅዝ የማያውቁት ግለሰቦች በተዘበራረቀ የሪዕዮተ ዓለም ዝቅተት ውስጥ ሲዋልሉ በሺሕ ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ተስፋ የተጣለበት ግንባር ላይ እንደማየት የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡
ሌቦቹም አልተኙም ወይም አይነኬ ሆኑ፡፡ ሌብነቱ የተረጋገጠበት ኃይል ከነባር እስከ ጥርቃሚ (በገፍ ሒደቱን ሳይከተል የገባውና መዋቅሩን በስፋት የተቆጣጠረው ምልምልን ጨምሮ) የበላይነቱን አረጋግጦ ይገኛል፡፡ እንደሚባለው ሌቦች በየትኛውም የሕዝብ ዋጋ ራሳቸውንና ከእነሱ ጋር ያለውን የመከላከል ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነሱን ከሚነካ በስተቀር ጥቅማቸውን ለማስከበር የትኛውንም መስዋዕትነት እንዲከፈል ያደርጋሉ፡፡ ደኅነታቸውን ለማስጠበቅ የትኛውንም አስቀድሞ የተቋቋመ የመንግሥት ቢሮክራሲ እንደአስፈላጊነቱና እንደሚያገኙት ጥቅም ይጠቀሙበታል፡፡ ሌቦች በየትኛውም ዋጋ እንዳይነኩ እንጂ ሕዝባዊነት የሚባል ነገር ከነ ንድፈ ሐሳቡ የማያውቁት የጭቁኖች ርዕዮት ነው፡፡ ድል ለሰፊው ሕዝብ ሞት ለሌቦች ሳልል ማለፍ አልፈልግም፡፡ የአርሶ አደሩ ዘለዓለማዊ ዘቦች ነን ብለው በንፅህና የሚኖሩት ደግሞ በሚከፍሉት አብዮታዊ ዋጋ የሚታገለውን የበሰበሰ እሳቤና ድርጊትን እንጂ፣ ሕዝቡ እንዳይነካ ወይም እንዳይጎዳ ይተገሉ፡፡ ሕዝብ ምንጊዜም ከሕዝባዊነት ጋር እንጂ ከግለሰባዊ ጥቅም ጋር ጉዳት እንዲደርስበት ፈጽሞ አይፈቅዱም፡፡ ስለዚህ በአገራችን በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ በሕዝባዊነትና በፀረ ሕዝብነት ከፍተኛ ትግል ውስጥ ተገብቷል፡፡ የአርሶ አደሩና የላብአደሩ አሸናፊነት የሰፊውን ሕዝብ ድል ያረጋግጣል፡፡ አሁንም ሞት ለሌቦችና ያላግባብ ለከበሩ ነቀዞች፡፡
ቀውሱ በምን መጣ የሚለውን ከመለስን ዘንዳ አገሪቷስ ከዚህ ቀውስ እንዴት ትውጣ? ለሚለው የመፍትሕ አቅጣጫ ለማስቅመጥ እሞክራለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ብዙ ስኬቶችን በአገራችን ማስመዝገብ የቻለ ፓርቲ ነው፡፡ የአገራችን ሕዝቦች እነዚህ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲቀጥሉ ይፈልጋል፡፡ የአገራች ገበሬ እንደሚለው ‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ› ነውና ኢሕአዴግ በስፋት የወረረውን አረም መንቀል መጀመር አለበት፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ሌቦቹን በስፋትና በቁርጠኝነት ጠርጎ የጠራና የተስተካከለ ቁመና ሊይዝ ይገባል፡፡ ግንባሩ ሁለት መንታ መንገዶች ላይ ይገኛል፡፡ በሌብነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ዘቅጦ መጥፋት ወይም በአብዮታዊነት አገሪቷን ለላቀ ድል ማዘጋጀት፡፡ ስለዚህ እኔም እንደ አንድ ዜጋ የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች ኢሕአዴግ ቢተገብር ቶሎ የመዳን ዕድል ይኖረዋል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ወይ መጥረግ ወይ መጠረግ የሚለው ሰዓት ላይ ተደርሷል
- ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነቱን በየትኛውም ዋጋ ማረጋገጥና የግንባሩን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ፡፡ ይኼን ማድረግ ጊዜ የማይሰጥና ሌቦችን በማባበል ለማስቀረት ከታቀደው ቀውስ መፃዒው የሚያስፈራ ነውና በአፋጣኝ ሥርዓቱ ባሳደጋቸው ሌቦች ላይ መብረቃዊ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡
- የአገሪቱን ሚዲያዎች በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በማዋል ሌቦችን የመታገሉን ሒደት ሕዝቡን እስካሁን ባለው ሳይሆን የእውነት በስፋት በማሳተፍና ሌቦችን አጋልጦ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ፡፡ በዚህም ትክክለኛ ለሕዝብ የወገኑ አባላቱን ለይቶ ዋነኛ ተዋናይ ማድረግ፡፡ በእስካሁኑ ሒደት በሌብነት የሚታወቁ በየደረጃው ያሉ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጥልቅ ተሃድሶ ተብሎ የተጀመረውን ማልያ ገልብጠው ሲመሩት እያየን ነው፡፡
- የግንባሩን አባላት በአንድ ሚሊዮን መገደብና የአባልነትን ክብር ወደ ነበረበት መመለስ፡፡ እያንዳንዱ የግንባሩ አባላት ፓርቲዎች 250 ሺሕ እንዲሆኑና ሌላውን በደጋፊነት መያዝ ይቻላል፡፡ በዚህም ሒደት አባልነት አጓጊ ማድረግና ክብሩን መመለስ፡፡
- በአባላቱ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ መሥራትና እነዚህን አባላቱ በተለይ ወጣት አብዮተኞችን መፃዒ የአገሪቷ መሪዎች እንዲሆኑ ማድረግ ሰይውል ሳይታደር ኃላፊነቱን መስጠት፡፡ የወጣቱን ችግር በወጣት አብዮተኞች ለመፍታት መመረሽ
- ያለንበትን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ቀምሮ አገራችን ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በመቀመር አቶ መለስ ዜናዊ ካለፉ በኋላ ለሕዝቡ መስጠት ያቃተውን አዲስ ራዕይ ለሕዝቡ ማስታጠቅ፡፡ ራዕይ ሁልጊዜ መታደስ ስላለበት፡፡ ለምሳሌ በቻይና የሲልክ ሮድ (Silk Road) ፕሮጀክት የአገራችን ተጠቃሚነት እስከምን መሆን እንዳለበትና የሚኖረንን ድርሻ ኢሕአዴግ እስካሁን የነገረን የለም፡፡ ይኼ ለእኔ አሳፋሪ ነው፡፡ የመካከላኛው ምሥራቅ የጂኦ ፖለቲካል ሁኔታ በፍጥነት ተቀያይሯል፡፡ ስለዚህም ምንም እየሰማን አይደለም፡፡
እንግዲህ ኢሕአዴግ ያለበት መንታ መንገድ ከሞላ ጎደል ይኼንን ይመስላል፡፡ የሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የበላይነት ተረጋግጦ ኢትዮጵያን ለላቀ ስኬት ማብቃት፣ ወይም የሌቦች የበላይነት ባለበት የኃያልነት ደረጃ አሸናፊነቱን አረጋግጦ አገራችንን ወደማያባራ ቀውስ መክተት፡፡ ለሁሉም ሁላችንም አብረን የምንታዘበው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ› ሳልል ማለፍ አልፈልግም፡፡ በአጠቃላይ ቆራጥ አመራርነት መስጠት ግንባሩን ከሚመሩ አካላት ይጠበቃል፡፡ አለበለዚያ የሚፈጠረውን ለመገመት ጠንቋይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ድል ለሰፊው ሕዝብ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡