አቶ ሞላ ዘገዬ፣ የሕግ አማካሪና ጠበቃ
አቶ ሞላ ዘገዬ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው፡፡ አቶ ሞላ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ በውትድርና፣ በፖለቲካና አስተዳደር የመንግሥት ሥራ ያገለገሉም ናቸው፡፡ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ የ‘ውይይት’ መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተርም ናቸው፡፡ በቅርቡም በሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ላይ አነስ ያለ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በመጽሐፋቸው ባነሱት ሐሳብና ተዛማጅ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን መቶ በመቶ ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ እንደ ኢሕአዴግ ገለጻ፣ ይህ ውጤት የሚያሳየው ከእሱ ውጪ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን ሕዝቡ እንደማይፈልግ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በገዥው ፓርቲና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞና አመፅ ታይቷል፡፡ በሁለቱ ሁነቶች መካከል ያለውን ተቃርኖ እንዴት አዩት?
አቶ ሞላ፡- በ2007 ዓ.ም. የተደረገውም ሆነ ከዚያ በፊት የተደረጉትን ምርጫዎች ከምርጫ 97 ውጪ ኢሕአዴግ በአሸናፊነት ተወጥቷል፡፡ ግን ከእነማን ጋር ተወዳድሮ ነው ያሸነፈው? የመወዳደርያ ሜዳው ለሌሎች ተወዳዳሪዎች በእኩልነት የሚያገለግል አልነበረም፡፡ ብቻህን ተወዳድረህ አሸንፈህ ሕዝቡ ሌሎች ተወዳዳሪዎችን አይፈልግም ልትል አትችልም፡፡ መርጦኛል ያለው ሕዝብ እኮ ነው መልሶ የተቃወማቸው፡፡ ይኼ ምን ያመለክታል? ለኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳልነበር ያረጋግጥለታል፡፡ ከተቃውሞ አልፎ አመፅ ነክ ድርጊቶች ከተፈጸሙ አገር ጤና ያጣል፡፡ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ወታደር የምትልክ ከሆነ የፖለቲካ ሥርዓቱ መውደቁን ያሳይሃል፡፡ የምርጫው ውጤትና ውሎ ሳያድር ሕዝቡ ያቀረበው ተቃውሞ የሚያሳየው ይኼንኑ ነው፡፡ እስካሁን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባበትን ዕድል ማመቻቸት አልቻለም። ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚደረግበት፣ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት የሚመሠረትበትና ዓይነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባበትን ዕድል መፍጠር አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- የሕዝቡ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚያሳየው ሥርዓቱ በኃይልም ቢሆን መወገድ እንዳለበት ነው በማለት የሚገልጹ ኃይሎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል እርስዎን ጨምሮ በርካቶች መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ይከራከራሉ፡፡
አቶ ሞላ፡- ሕዝባዊ አመፁ እጅግ ከፍተኛ ቀውስና ትርምስ ከማስከተሉም በላይ የአገሪቱ ህልውናም አደጋ ላይ ወድቋል። ኢትዮጵያ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ለአንዳንዶች መፍትሔው ኢሕአዴግን ከሥልጣን ማስወገድ ነው፡፡ ይህ ወገን ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ችግሮቹ አይቀረፉም ብሎ ያምናል፡፡ ችግሩን የፈጠረው ኢሕአዴግ የመፍትሔው አካል መሆን አይችልም ይላሉ፡፡ እኔን ጨምሮ አብዛኛው ድምፁን ያላሰማው ሕዝብ ግን የሚያስብ የሚመስለኝ ከአመፅ ይልቅ መሠረታዊ ለውጥ የተሻለ እንደሆነ ነው፡፡ ለውጡ ግን እውነተኛ፣ ዴሞክራሲያዊና መሠረታዊ መሆን አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ካለፈ ስህተቱና ከኢትዮጵያ ታሪክ ተምሮ ይሻሻላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሁልጊዜ እኛ የምንለው ብቻ ነው የእውነት መንገድ እያሉ ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ ለውጡ መጀመር ያለበት መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ነው፡፡ አሁን ባለው አስተሳሰብ ከቀጠለ እንኳን የለውጡ መሪ የለውጡ አካል መሆንም አይችልም፡፡ ነገ ምን እንደሚሆን አላውቅም፡፡ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በእጃቸው ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከፈለጉ መለወጥ ይችላሉ፡፡ ይኼ ጥልቅ ተሃድሶ የሚሉት ነገር መቼ እንደሚያልቅ አላውቅም፡፡ ስንት ጊዜ ነው የሚታደሱት? ውጤቱ ሰው ማባረርና መሾም ነው፡፡ የሚያባርሩበት መሥፈርትም ግልጽ አይደለም፡፡ የሚቃወሟቸውን ሰዎች ነው የሚያባርሩት?
ነፃ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በሌሉበትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ሲቪክ ማኅበራት ባልዳበሩበት ተሟጋች የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የመብት ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ፣ በሕዝባዊ አመፅም ይሁን በሌላ አብዮታዊ መንገድ በሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል ማስወገድ የሚፈይደው በጎ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም የከፋ መዘዝ ይዞ ሊመጣ ይችላል። ‹‹ከመንግሥት ለውጥ በኋላስ?›› የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ በቂና ተግባራዊ መልስ ሳያገኝ፣ ሁሉም ‹‹ከለውጥ በኋላ›› በሚል መንፈስ መንጎዱ መዘዘኛና ውድ ዋጋ የሚያስከፍል አካሄድ ነው። በግብፅ ኢዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ መመሥረት ስለሚኖርበት የፖለቲካ ሥርዓት በበቂ ሳይመክሩና ሳይደራጁ አብዮት በማካሄዳቸው፣ ተደራጅተው ሲጠብቁ በነበሩ ጽንፈኛ ድርጅቶች ተጠልፎ ሥልጣን በሠራዊቱ እጅ ገብቶ ተኮላሸ። እኛም ከመንግሥት ለውጥ በኋላ የተከሰተውን የፖለቲካ ሕዋ ሊሞሉ የሚችሉ ድርጅቶች ስለማቋቋማችን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡
ከኢሕአዴግ በኋላ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሥርዓት ያስፈልጋታል? ምን ዓይነት ተቋማት መገንባት አለባቸው? የአገሪቱ ህልውና እንዴት ይጠበቃል? ወዘተ. በሚሉት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ሳንመክር፣ ከስምምነት ላይ ሳንደርስና ሽግግሩን ሊመሩ የሚችሉ ተቋማትን ሳናደራጅ የኢሕአዴግን አገዛዝ ለማስወገድ ዕርምጃ ብንወስድ የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት የምንችል አይመስለኝም። መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፡፡ እኔ በእሱ አላምንም፡፡ ከዘመን ዘመን ሲንከባለሉ የመጡትና በየጊዜው የሚጨመሩት የአገራችን ችግሮች ይበልጥ እየሰፉና እየተወሳሰቡ በመሄድ ላይ ናቸው። ችግሮቻችንን ለመፈተሽና መፍትሔዎችን ለማመንጨት የሰከነና ሀቀኛ የሆነ ውይይት ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለም ባይ ነኝ። የገጠሙንን አገራዊ ችግሮች ስፋትና ጥልቀት ለመገምገምም ሆነ መፍትሔዎችን ለማመንጨት ከመወያየት የተሻለ መላ የለም። ሕዝብ በተለያየ መንገድ እየተሰባሰበ የሚወያይባቸውና ሐሳብ የሚለዋወጥባቸው፣ እንዲሁም በሙያና በጥቅም ማኅበራት በነፃነት እየተደራጀ ኅብረትና አቅም ፈጥሮ መብቱን ሊያስከብር የሚችልባቸው ልዩ ልዩ ሲቪክ ማኅበራት እንዳይንቀሳቀሱ ዕቀባ ሲደረግ ሌላ መንገድ መፈለጉ አይቀርም። ሃይማኖታዊና ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎችና ህቡዕና ጽንፈኛ የሆኑ ቡድኖች የበለጠ ጉልበት የሚያገኙት እንደዚህ ባለ የታፈነ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ መሆኑ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው።
ሪፖርተር፡- በኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለምና በሕገ መንግሥቱ መካከል ግልጽ የሆነ ተቃርኖ አለ፡፡ እርስዎ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን በተግባር ላይ የሚያውሉት ዴሞክራቶች እንጂ አብዮተኞች አይደሉም ይላሉ፡፡ ይህ ውጥረት በምን መንገድ መፈታት ይችላል?
አቶ ሞላ፡- በመሠረቱ የዚህ አገር አብዛኛው ችግር የሚመነጨው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሚከተለው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከፈጠረው የፓርቲና የመንግሥት አደረጃጀት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ እንደሚናገረው አብዮታዊና የግራ ፓርቲ ነው፡፡ የግራ ፓርቲዎች ደግሞ ጠቅላይና አምባገነናዊ ናቸው፡፡ በባህሪያቸው ከእነሱ ውጪ ያሉ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን አይታገሱም፣ አያስተናግዱም፡፡ ኢሕአዴግን ከጊዜ በኋላ የተቀላቀሉት አባላት ጭምር አብዮታዊ ናቸው፡፡ እኔም እኮ አብዮታዊ ነበርኩ፡፡ ያሳለፍነውን ሒዴት ከገመገምኩ በኋላ ነው ችግሩን የተገነዘብኩት፡፡ ነገር ግን እነሱ እያንቋሸሹ የሚጠሩት የሊበራል የፖለቲካ እሴቶች በተለይ ዴሞክራሲ ላይ ማመን አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ስታነበው በርካታ የሊበራል የፖለቲካ እሴቶችን ታገኛለህ፡፡ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ ብዝኃነት፣ ወዘተ የሚባሉት የሊበራል የፖለቲካ እሴቶች ናቸው፡፡ እርግጥ አብዮታዊ አስተሳሰብን የሚያንፀባርቁ ድንጋጌዎችም ተካተዋል፡፡ ለምሳሌ መሬት የመንግሥት ነው የሚለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሊበራል የፖለቲካ እሴቶች የታጨቁበትን ሕገ መንግሥት እናስፈጽማለን የሚሉት አብዮተኞች ናቸው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያትቱና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ አንቀጾች ቢኖሩትም፣ የተደነገጉትን መብቶችና ነፃነቶች ወደ መሬት በማውረድ ረገድ ከፍተኛ ችግር እንዳለ የሚያጠያይቅ አይደለም። ብዙዎቹ ድንጋጌዎች መሬት ላይ አልወረዱም። ከእነዚህ መሬት ላይ ካልወረዱትና በሕዝቡ ውስጥ ትልቅ ቅሬታን ከፈጠሩት ጉዳዮች መካከል ነፃ የዳኝነት አካል፣ ነፃ ዓቃቤ ሕግ፣ ነፃ ፖሊስና ነፃ ማረሚያ ቤትን፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ወገንተኛነት የተላቀቀ የአገር መከላከያ ሠራዊትና የደኅንነት ተቋምን የሚመለከተው ነጥብ ተጠቃሽ ነው። ተወደደም ተጠላ ሕገ መንግሥቱን ሥራ ላይ ሊያውሉ የሚችሉት ቁርጠኛ የሊበራል የፖለቲካ እሴቶችን የሚያራምዱ ዴሞክራቶች ብቻ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ሁለት ምርጫ አለው፡፡ የፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም ከመረጠ ለአብዮተኞች የሚመች ሌላ ሶሻሊስት ሕገ መንግሥት ማርቀቅ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በዋነኛነት የመንግሥትንና የዜጎችን ባህሪ እንደሚገዙ ይጠበቃል፡፡ ገዥው ፓርቲ ግን ካድሬዎቹም ሆኑ ዜጎች ይበልጥ እንዲያውቋቸው በስፋት የሚያሠለጥነው ከሕገ መንግሥቱ ጋር ብዙም ስምሙ እንዳልሆኑ የሚተቹት የፖሊሲ ሰነዶችን ነው የሚባለውስ?
አቶ ሞላ፡- እውነተኛ የሕግ ሰዎች ሕግ የፍትሕ ማስገኛ መሣሪያ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ተፅዕኖ በሚሳድሩበት አገር ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ይፈጠራሉ፡፡ በርካታ ፈታኝ ችግሮች ከፊት ለፊታችን የተደቀኑ ቢሆንም፣ የችግሮች ሁሉ መቋጠሪያ ሕዝብ በነጻነት የመከረባቸውና የሚያምንባቸው ነፃ ተቋማት አለመኖር ይመስለኛል። ስለሆነም ከሁሉ አስቀድሞ ነፃ፣ ሕዝብ የመከረባቸውና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ዘመን ተሻጋሪ ሊሆኑ ስለሚችሉ አገራዊ ተቋማት ግንባታ መነጋገር ያስፈልጋል። በአገራችን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሆኑ ነፃ፣ ጠንካራና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማት እንዳልተገነቡ የሚያከራክር አይደለም። ጠንካራ የሠራተኛ ማኅበራት፣ በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የሙያና የጥቅም ስብስቦች፣ በነፃነት የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበራት፣ ወዘተ. እንደሌሉም ግልጽ ነው። በዚህ ላይ መንግሥት ራሱ በተደጋጋሚ እንደገለጸው ሙስናውና የመልካም አስተዳደር ችግሩ ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ያማረረው ሲሆን፣ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች በየአካባቢው የሚቀሰቀሱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ እያሉ ቀጥለዋል። ብሔረሰባዊና ሃይማኖታዊ ቅርፅ እየያዙ የመጡበት የሚረብሽ አዝማሚያም እየታየ ነው። ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ዕድል በጣም ዝቅተኛ ነው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር እንዲደረግ ገለልተኛ አገራዊ ተቋማት ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ እንደተባለው ሥልጠናዎቹ የሚያተኩሩት የፓርቲ ፖሊሲዎች ላይ ነው፡፡ ሕጎቹም የሚቀዱት ከእነዚህ ፖሊሲዎች ነው፡፡ ፓርላማው ደግሞ የአንድ ፓርቲ ፓርላማ ነው፡፡ ተቃራኒ አስተሳሰብ የለም፡፡ ነገር ግን ወደ ሕገ መንግሥቱ መመለስ አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ድርድር ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ተስማምቷል፡፡ እርስዎ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትክክለኛ የሕዝብ ድጋፍ እንደሌላቸው በመጠቆም የለውጡ ዋነኛ አካል መሆን የለባቸውም ይላሉ፡፡ ይህ አቋምዎ ከምን የመጣ ነው?
አቶ ሞላ፡- ተቃዋሚ ኃይሎች እርስ በርሳቸውም የቀለጠ ጦርነት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ቡድኖቹ በልዩነት ላይ የቆሙ በመሆናቸውና ልዩነቱን ወደማይታረቅ ደረጃ ስለሚያከሩት ተቃዋሚ ኃይሎችን ያቀፈ ቅንጅት ለመፍጠር ሲደረግ የቆየው ጥረት ፍሬ ማፍራት አልቻለም። በአገራችን በአብዮቱ ዘመን የተቋቋሙትም ሆኑ በኋላ የመድበለ ሥርዓት ተፈቅዷል ከተባለ ጊዜ ጀምሮ የተመሠረቱት አብዛኞቹ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ስለዴሞክራሲ እየሰበኩ ነገር ግን በውስጣቸው የዴሞክራሲ ሽታ የሌለባቸው፣ ስለፍትሕና የሕግ የበላይነት እየዘመሩ ራሳቸው ፍትሕን የሚደፈጥጡና ከሕግ በላይ የሚሆኑ፣ ሕዝብ ሳይወክላቸውና ሳይመርጣቸው ራሳቸውን በሥልጣን ላይ የሚያስቀምጡና ለማስቀመጥ የሚፈልጉ፣ በአጠቃላይ ከዴሞክራሲና የሕዝብን መብት ከማስጠበቅ አንፃር ተፈትነው የወደቁ፣ የወደቅን ነን፡፡ ከዚህም በላይ እስካሁን ልንሻገረው ያልቻልነው በጠላትነት የመፈላለግ አደገኛ ሁኔታ፣ ቂሙና ቁርሾው፣ ጥሎ ማለፉ፣ በትውልድ፣ በድርጅት፣ በብሔረሰብ፣ ወዘተ. መከፋፈሉ ሁሉ አሁንም ገና ያልጠራና መድኃኒት ያልተገኘለት ትልቅ በሽታ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራ ላይ ባለው ብሔር ተኮር የፌዴራል ሥርዓት ላይ ተቃውሞ አለዎት፡፡ አንዳንዶች ግን ሥርዓቱ ችግር ውስጥ የገባው የዴሞክራሲ ዕጦት ስላለበት ነው እንጂ በራሱ የሚነቀፍ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ሞላ፡- የእኛ ፌዴራላዊ አደረጃጀት በቋንቋና በዘውግ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የዚህ መሠረትም ሌኒን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከወጣ በኋላ መገንጠል የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፡፡ ኦነግ መገንጠል ነው የሚፈልገው፡፡ የ1960ዎቹ ንቅናቄ አካል የነበረው ትውልድ አገሩን ወደ ውስጥ በማየት በአገሩ ባህል፣ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ላይ የአገሩን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ አስተሳሰብ አላዳበረም፡፡ ከቻይና፣ ከቬትናም፣ ከሩሲያና ከመሳሰሉት ሐሳብ ሲሰበስብ ነው የነበረው፡፡ እየተነሱ የነበሩትን ከአስተዳደር፣ ከፍትሐዊነትና ከዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ ዘውጌ ብሔርተኞች የእኔ የሚሉትን አካባቢ ገንጥለው ለመግዛት ስለፈለጉ፣ የመገንጠል ንቅናቄ ጀምረው ብዙ መስዋዕትነት አስከፍለዋል፡፡ በሥራ ላይ ባለው ፌዴራላዊ አደረጃጀት ወደ አንድነት እየሄድን አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ልሂቅ ዘውጌ ብሔርተኛ ኑሮውን ለማሻሻል ነው አካባቢውን መቆጣጠር የሚፈልገው፡፡ የብሔረሰቦች ጥያቄ በአገራችን ላለፉት አርባ ዓመታት ሲነሳ ሲወድቅ ቢቆይም ከጊዜ ወደጊዜ ይበልጥ አከራካሪ እየሆነ በመሄድ ላይ ይገኛል። የፖለቲካ ልኂቁ ‘ብሔረሰብ’፣ ‘ነገድ’፣ ‘ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ’፣ ‘ዘውግ’፣ ‘ጎሳ’፣ ወዘተ. እያለ በጽንሰ ሐሳቡ ስያሜ ላይ ሳይቀር መስማማት እንዳልቻለም ግልጽ ነው። ከኢትዮጵያና ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ሊባል በሚችል ሁኔታ በብሔረሰባዊ ማንነት መደራጀትን በቀጥተኛ መንገድ በሕግ ወይም በተግባር ከልክለዋል፤ ‹‹በብሔረሰባዊ ማንነት መደራጀት ይበልጥ ክፍፍልን የሚጋብዝ በመሆኑ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰናክል ይፈጥራል፡፡ ለአገራችን ህልውናም አደገኛ ነው›› የሚሉ ወገኖች ያሉትን ያህል፣ በብሔረሰባዊ ማንነት መደራጀትን አጥብቀው የሚደግፉ ኃይሎች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይም የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተያየቱን እንዲሰጥበት ዕድል ማግኘት አለበት። ጉዳዩ ከልኂቃኑ መሻኮቻነት ወጥቶ፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት እንደሚፈልግ ሊጠየቅ ይገባል። ከዚህ ጋር የመንግሥት አወቃቀሩ አሃዳዊ ይሁን ፌደራላዊ፣ ፌደራላዊ ከሆነስ ምን ዓይነት የፌደራላዊ ሥርዓት? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያገኛል።
ሪፖርተር፡- በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦሮሚያ ክልልና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የአማራ ክልልም በተወሰነ ደረጃ አንድነትን ከልዩነት በማጣጣም አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ እያራመዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንቅስቃሴው ኢሕአዴግን ከውስጥ ለመለወጥ ያለመ አንድ አካል ተደርጎ ይወሰዳል ተብሎ የሚቀርበውን አስተያየት እንዴት አዩት?
አቶ ሞላ፡- በእኔ እምነት ኦሮሞ ትልቅ ሕዝብ ቢሆንም የሚመጥኑትን ፖለቲከኞች አግኝቶ አያውቅም ነበር፡፡ ኦነግ በሻዕቢያ፣ ኢሕዴድ ደግሞ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር ነበሩ፡፡ አሁን የእውነት ከሆነ ትክክለኛ አቅጣጫ ይዘዋል፡፡ የሚፈለገውም ይኼ ነው፡፡ ለውጥ በአንድ ምሽት አይጠናቀቅም፡፡ እኔ እነአቶ ለማና አቶ ገዱን የምደግፈው ከልባቸው ለለውጥ የተዘጋጁ ከሆነ ነው፡፡ ይኼ ትውልድ አገሩን በምክንያት እንዲወድ ማድረግ አለብን? የብሔር ማንነት ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ተጣጥሞ ሊሠራበት ይገባል፡፡ አቶ ለማ ስለኢትዮጵያዊነት ሲያወራ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የሕገ መንግሥታዊ ‘ሪፎርም’ ወቅታዊነት ላይ በቅርቡ አነስ ያለ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ብዙዎች ስለሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ የእርስዎ ሐሳብ ዋነኛ ጭብጥ ምንድነው?
አቶ ሞላ፡- ኢሕአዴግ ከፈለገ ሕገ መንግሥቱን መለወጥ ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥቱን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለመፍጠር ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፃነት የመከረበት፣ ያመነበትና ሊንከባከበው የሚችለው ሕገ መንግሥት የመኖሩ ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ተግባር ነው። አሁኑ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰነዘሩ የቆዩ የተለያዩ አስተያየቶች አሉ። አንዳንዶች ሕገ መንግሥቱ ተቀዶ መጣል አለበት የሚል አቋም ያራምዳሉ። አንዳንድ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት ሲሉ፣ ሌሎች የተወሰኑ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች በማሻሻል ሰነዱን መጠቀም ይቻላል የሚል አቋም ያራምዳሉ። ብዙዎቹ ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ አልዋለም በማለት ቅሬታ ቢያቀርቡም በይዘት ደረጃ የሚቃወሙት ነገር የለም። እኔ ተቀዶ ይጣል ከሚሉትም፣ እንዳለ ይቀጥል ከሚሉትም እለያለሁ። የቱንም ያህል ስለሕዝብ ተሳትፎ ቢነገር፣ የቱንም ያህል ስለዴሞክራሲያዊነቱ ቢሰበክ፣ ሕገ መንግሥቱ እንደ ቀደሙት ሕገ መንግሥቶች ከላይ ወደ ታች የወረደ ሰነድ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም። ሕገ መንግሥቱ ተቀዶ መጣል አለበት የሚለውን አስተያየት አልደግፍም። ሕገ መንግሥቱ በርካታ ውስንነቶች ያሉበት ሰነድ በመሆኑ እንዳለ ይቀጥል የሚለውን አስተያየትም አልደግፍም። የመንግሥት ሥልጣንን በሆነ አጋጣሚ የያዘው ኃይል የሕዝቡን ሕገ መንግሥት የማፍለቅ ወይም የማውጣት መብት ከሕዝብ ነጥቆ፣ በሕዝብ ስም ሕገ መንግሥት አርቅቆ የሚያፀድቅበት አካሄድ ከመነሻው ሰነዱ የቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ የሚያደርግ መሆኑ አያጠያይቅም። ጉዳዩ በአገራችን ተደጋግሞ የታየ ያልተሻገርነው ዓቢይ ችግር ነው። ቀደም ሲል ንጉሠ ነገሥቱ ቀጥለውም ደርግንና ኢሕአዴግን የሚመሩ ውስን ልሂቃን በእናውቅልሃለን መንፈስ ሕገ መንግሥት ‹‹ይሰጡታል›› እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ነፃነቱ ተከብሮለት፣ ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ መክሮ ዘክሮ ያፀደቀው ሕገ መንግሥት አግኝቶ አያውቅም። ሰነዱ ውስንነቶች ቢኖሩበትም ሙሉ በሙሉ ከመወርወር ለአዲስ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ዝግጅት እንደ መሸጋገሪያ ሆኖ ሊያገለግል ስለሚችል በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ መንግሥት እንዳለ መቀጠሉ አግባብነት ያለው ይመስለኛል። ለጠንካራ ተቋማት መገንባትና መጠናከር መሠረት የሆነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነፃነት አስተያየቱን የሰጠበትና የሚንከባከበው ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ሳይኖረን ወደፊት መራመድ እንደማንችል ግልጽ ነው። የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ አስፈላጊም ወቅታዊም የሚሆነው ይህንን ለሌሎች አገራዊ ተቋማት መገንባትና መጠናከር የማዕዘን ድንጋይ የሆነውን ተቋም በፅኑ መሠረት ላይ ለመትከል ነው።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚመለከቱ 30 አንቀጾችን ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን ቃል በቃል ያካተተ ሰነድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት እንዳለ ከማስቀጠልም ሆነ እንደገና ‘ሀ’ ብሎ ከመጀመር ‘ሪፎርም’ የተሻለ አማራጭ ነው። በሌላ አገላለጽ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻለው በመቃብራችን ላይ ነው፤›› የሚሉት አካላት ሰነዱ ከነጭራሹ ሊወገድ የሚችልበትን ሁኔታ እያመቻቹ ስለሆነና ይህ ደግሞ ያው የተለመደው የ‹‹እየገነቡ ማፍረስና እያፈረሱ መገንባት›› በሽታ በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ከዚህ በሽታችን የምንፈወስበትን መድኃኒት የሚሰጠን የተሻለው አማራጭ ነው።
የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ የሚያስፈልግበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ክፍፍልን የፈጠሩ፣ በፖለቲካ ልኂቁ አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ የተራገቡና አጨቃጫቂ ሆነው የቀጠሉ አገራዊ አጀንዳዎች እንደገና መታየት ስለሚገባቸው ነው። ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሬት ጥያቄ ላለፉት 50 ዓመታት ማዕከላዊ ቦታ ይዞ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው። ለንጉሣዊ ሥርዓት መገርሰስ ምክንያት ከሆኑት አጀንዳዎቸ አንዱ የሆነው የመሬት ጥያቄ በዚህ በያዝነው ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች ለተቀሰቀሱትና የሰው ሕይወት ለጠፋባቸው ተቃውሞዎች ምክንያት መሆኑ ጥያቄው አሁንም ወቅታዊ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው። የመሬት ጥያቄ እንዳልተመለሰ፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደርና የከተማ ነዋሪ የመሬቱ ባለቤት እንዳልሆነ፣ የሕዝቡ የመሬት ባለቤትነት ባለመረጋገጡ ምክንያት አሁንም በሥልጣን ላይ ባለው ኃይል ቁጥጥር ሥር በመሆኑ የፈለገውንና ያመነበትን የፖለቲካ አመለካከትና የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ እንደማይችል፣ ስለዚህም የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ አስተማማኝ ምላሽ ሳያገኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንደማይቻል አጥብቀው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ።
ከዚህ በተቃራኒ በተለይ በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት አካባቢ የመሬት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱንና በሕገ መንግሥት ደረጃ መረጋገጡን፣ ከዚህ ውጪ መሬት በግለሰቦች ይዞታ ሥር መሆንና ባለይዞታው በፈለገ ጊዜ መሸጥ መለወጥ መቻል አለበት የሚለው አስተያየት፣ የአገራችንን ደሃ አርሶ አደር እንደገና በከበርቴዎች ቁጥጥር ሥር ጭሰኛ የሚያደርግ ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። በአጠቃላይ ሁሉም ጎራ በመሬት ጉዳይ ላይ የየራሱን አስተያየት ቢያቀርብም፣ አሁንም የመሬት ጥያቄ ከኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ከሙስና፣ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ወዘተ. ጋር ጥብቅ ዝምድና ያለው አንገብጋቢና ወቅታዊ አጀንዳ ሆኖ የቀጠለ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ጥያቄ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ መደረግ ይኖርበታል። በአጠቃላይ ሕገ መንግሥቱ በየጊዜው ራሱን እያደሰ የሚሄድ ትልቅ አገራዊ ተቋም እንዲሆን የሕገ መንግሥት ሪፎርም በጣም አስፈላጊ ነው።
ነገር ግን ኅብረተሰቡ ያለምን ተፅዕኖ አስተያየቱን እንዲሰጥና በነፃነት የመሰለውን መወሰን እንዲችል ግን ከሁሉ አስቀድሞ ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ሕዝብ ሳይሸማቀቅና ሳይፈራ አስተያየት እንዲሰጥና እንዲወስን ከተፈለገ፣ እነዚህ ተቋማት ራሳቸው ነፃና በሕግ ብቻ የሚሠሩ እንዲሆኑ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር ሕዝቡ ከመፍራትና ከመሸማቀቅ ነፃ ሆኖ አስተያየት መስጠትና መወሰን የሚችለው ተቋማቱ ተጠሪነታቸው ለሕዝብ መሆኑ ሲረጋገጥና የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ ነው። አሁንም ቢሆን ገለልተኛ የሆኑ፣ ነፃና በሕግ ብቻ የሚሠሩ አገራዊ ተቋማት ችግር አለ። እነዚህ ተቋማት ነፃ፣ ከፖለቲካ ወገንነኝነት የራቁና በሕግ ብቻ የሚሠሩ መሆናቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ደግሞ በሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም። የተቋማቱ አሠራር የገለልተኛነት ጥያቄ የሚነሳባቸው መሆኑን ስንጠቅስ፣ ይበልጥ ሕዝባዊ እንዲሆኑና እየተጠናከሩ እንዲሄዱ፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው እንዲሠሩ መግለጻችን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
በብዙ አገሮች ተደጋግሞ እንደታያው የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ በሚካሄድበት ወቅት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይ በሥልጣን ላይ ያሉት ወገኖች ሠራዊቱን፣ ደኅንነቱንና ሌሎች የፍትሕ ተቋማትን ተጠቅመው ሒደቱን ለመጥለፍና እነሱ የሚፈልጉትን አጀንዳ ለማስፈጸም ብርቱ ትግል ስለሚያደርጉ ‘ሪፎርሙ’ የሚፈለገውን ውጤት ማስገኘት አይችልም። ስለሆነም በአገራችን የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ወቅታዊና አስፈላጊ በመሆኑ ላይ ግንዛቤው ካለ፣ ሒደቱን የሚመሩት አካላት ከፖለቲካ ድርጅቶች ውጪ መሆን ይኖርባቸዋል። የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ከተለመደው የገንብቶ ማፍረስና አፍርሶ መገንባት የማንኮራበት ታሪካችን ይገላግለናል፡፡ ይልቁንም የአንድ ቡድን ሳይሆን የጋራ ሰነድ ያደርገዋል፡፡ ተቀባይነት ያጎናፅፈዋል፡፡ የጋራ ማንነት የሚገነባበት ሰነድ እንዲሆን ዕድል ይከፍታል፡፡ ከዚህም በላይ ‘የሪፎርም’ ሒደቱ ዋና ዋና አገራዊ ችግሮቻችንን በነፃነት የምንወያይበትን፣ የታሪክ ቁርሾዎችን የምናርምበትንና የምንቀራረብበትን ዕድል ይፈጥርልናል፡፡ የዴሞክራሲ እሴቶችን ማለትም ውይይትን፣ ክርክርንና ሰጥቶ መቀበልን እንማርበታለን፡፡ በአገራችን አከራካሪ ስለሆኑና ክፍፍልን ስለፈጠሩ ጉዳዮች ለምሳሌ ስለመሬት ጥያቄ፣ በብሔረሰባዊና ሃይማኖታዊ ማንነት መደራጀትን በሚመለከት፣ ስለመንግሥት አወቃቀር፣ ስለምርጫ ሥርዓታችን፣ ስለሲቪል ሰርቪስ ነፃነትና ገለልተኛነት፣ የርዕሰ ብሔሩንና ርዕሰ መንግሥቱን የሥልጣን ዘመን ስለመወሰን፣ ወዘተ. የምንወያይበትን፣ የምከራከርበትንና መቋጫ የምናበጅበትን ዕድል ይሰጠናል፡፡
‹‹የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርሙን’ ማን በባለቤትነት ይምራው? እንዴት ይምራው? ተጠሪነቱ ለማን ይሁን?›› የሚሉት መሠረታዊና አከራካሪ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ለጥያቄዎች አንድ ሁሉንም የሚያስማማና ያለቀለት መልስ መስጠትም ያስቸግራል፡፡ በብዙ የሕገ መንግሥት ምሁራን አካባቢ ሪፎርሙ ውጤታማ ይሆን ዘንድ፣ ለሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ብቻ ተብሎ የተቋቋመ ገለልተኛ አገራዊ ተቋም መመሥረት አለበት በሚለው ሐሳብ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ስለሆነም በእኛም አገር የሕገ መንግሥቱ ‘ሪፎርም’ አገራችንንና ሕዝባችንን ወደፊት የሚያራምድ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ሒደቱ መመራት ያለበት ለሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ብቻ ተብሎ በተቋቋመ ገለልተኛ አገራዊ ተቋም መሆን ይኖርበታል፡፡ በእኔ አስተያየት ይህ ገለልተኛና አገራዊ ተቋም ከፖለቲከኞች ይልቅ ልዩ ልዩ የሙያ፣ የጥቅምና ሲቪክ ማኅበራት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች፣ ወዘተ. የተሰባሰቡበት ቢሆን ተመራጭነት ይኖረዋል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕገ መንግሥት ሪፎርም ሒደቱ ላይ ቢሳተፉ፣ ጠባብ የሆነ ድርጅታዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሻኮቱ ሒደቱን ራሱን በተለመደው የመጠላለፍ ኢዴሞክራሲያዊ መንገድ ማኮላሸታቸው ስለማይቀር፣ የፓርቲዎች ሚና ዜሮ ይሁን ባይባልም በጣም ዝቅተኛ ቢሆን ውጤቱ ያማረ ይሆናል፡፡
ሒደቱን ከልዩ ልዩ የሙያ፣ የጥቅምና ሲቪክ ማኅበራት የተወከሉ አካላት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወዘተ. የተሰባሰቡበት ገለልተኛ አገራዊ ተቋም ይምራው የምንልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ይልቅ እነዚህ ተቋማት ኅብረተሰቡን በስፋት ስለሚደርሱና ስለሚያቅፉ፣ ይልቁንም ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገሉ አካላት ባለመሆናቸው የተሻለ ገለልተኝነት ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚገመት ነው፡፡
የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርሙን’ የሚቋቋመው ገለልተኛ አገራዊ ተቋም በበላይነት ይምራው በሚለው ነጥብ ላይ ስምምነት ካለ፣ ይህ ተቋም ሒደቱን እንዴት ይምራው የሚለው ጥያቄ የቴክኒክ ጉዳይ ስለሆነ ብዙም የሚያሳስብ አይሆንም፡፡ የተለያዩ ዘዴዎችን መከተል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል በብዙ አገሮች የሚተገበረውን አሠራር ብንጠቅስ፣ የተመሠረተው ገለልተኛ ተቋም አባላቱን በሕግ፣ በባህል፣ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣ ወዘተ. ቡድኖች ካዋቀረ በኋላ፣ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት በሚመለከት (ቢቀነሱ ወይም ቢጨመሩ የሚላቸውን ድንጋጌዎች በተመለከተ)፣ ቀደም ሲል በጠቀስናቸው አከራካሪ በሆኑና በኅብረተሰቡ መካከል ክፍፍል በፈጠሩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ፣ ወዘተ. ሁሉም 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነው ዜጋ አስተያየቱን እንዲሰጥ ይጠየቃል፡፡ ሁሉም ዕድሜው የሚፈቅድለት ዜጋ አስተያየቱን በነፃነት እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላ፣ በሕዝቡ አስተያየት መሠረት የተለዩትን አንኳር ጉዳዮች ያካተተ ሰነድ ይዘጋጅና በሥራ ላይ ካለው ሕገ መንግሥት ጋር ተመሳክሮ/ተናቦ ሲያበቃ፣ አዲስ ሰነድ ተዘጋጅቶ መልሶ ለሕዝበ ውሳኔ ይቀርባል፡፡ ይህ አንዱ መንገድ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ ከላይ እንደተጠቀሰው ጉዳዩ ቴክኒካዊ በመሆኑ፣ ባለሙያዎች የተለያዩ አማራጮችን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ቁም ነገሩ ሁሉም ዕድሜው የሚፈቅድለት ዜጋ እንዴት መተዳደር እንደሚፈልግ መጠየቁ፣ ሐሳብ ማመንጨቱና አስተያየት መስጠቱ፣ ይልቁንም በሕዝብ ጉዳይ ላይ የሚወስነው ራሱ ሕዝቡ እንጂ ሌሎች አለመሆናቸው መረጋገጡ ነው፡፡ ዋናውና አከራካሪው ጥያቄ የዚህ ገለልተኛ አገራዊ ተቋም ተጠሪነት ለማን ይሁን የሚለው ነው፡፡ ኢዴሞክራሲያዊ በሆኑ ሥርዓቶች ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር መሆኑ ቢታወቅም፣ በርካታ አገሮች የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርሙን’ የሚመራው ተቋም ተጠሪነት ለምክር ቤት እንዲሆን ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ የተቋሙ ተጠሪነት ለርዕሰ መንግሥቱ (ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዚዳንት)፣ ከዚያም አልፎ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛው እንዲሆን ያደረጉ አገሮችም አሉ፡፡ ሁሉም መንገዶች አከራካሪዎች ናቸው፡፡ የተቋሙ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆን ተመራጭነት ይኖረዋል፡፡
ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ሳይኖር፣ ወይም ምንም ዓይነት ሕዝባዊ ግፊትና አስገዳጅ ሁኔታ ሳይፈጠር፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሕገ መንግሥት ሪፎርም እንዲደረግ ይፈቅዳል፣ ከዚያም አልፎ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ማለት ተምኔታዊ (utopian) ነው ሊባል ይችላል፡፡ መንግሥት በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋሙን የሚቆጣጠሩት ከሆነ፣ እንደፈለጉ አያሽከረክሩትም ወይ የሚል ጥያቄም ሊሰነዘር ይችላል፡፡ ተገቢም አስፈላጊም አስተያየት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ እንዲደረግም ይሁን አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲዘጋጅ ያደረጉበትን በርካታ አጋጣሚዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ መንግሥታት የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹት፣ ወይም ሒደቱን በበላይነት የሚመሩት፣ ሥልጣናቸውን ይበልጥ ለማጠናከር፣ በሥልጣን ላይ ያለው ፕሬዚዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር እንደገና በምርጫ የሚሳተፍበትን መንገድ ለማዘጋጀትና የፕሬዚዳንቱን ወይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥራ ዘመን ለማራዘም ነው፡፡
በርካታ አገሮች ችግር ከመከሰቱ በፊት የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ማድረግና በሪፎርም ሒደት ለዋና ዋና አገራዊ ችግሮቻቸው መቋጫ ማበጀት ባለመቻላቸው ወደ አመፅና ትርምስ ውስጥ ገብተው በርካታ ዜጎች ከሞቱና መጠነ ሰፊ ንብረት ከወደመ በኋላ የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ለማድረግ ወይም አዲስ ሕገ መንግሥት ለማዘጋጀት ይገደዳሉ፡፡ ለምሳሌ ኬንያ ውስጥ ስለሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ መነገር ከጀመረ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ በሥልጣን ላይ ያሉት አካላት ጉዳዩን የምር ስላላደረጉት በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ዘር ለይተው ከተጨፋጨፉ በኋላ ነው አዲስ ሕገ መንግሥት ወደ ማዘጋጀት የተገባው፡፡ የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ ለብዙ ዘመናት ሲንከባለሉ ለመጡና በየጊዜው ለሚጨመሩ አንገብጋቢ አገራዊ ችግሮቻችን መላ የምንፈልግበትን ዕድል ይሰጠናል፡፡ ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን በሰከነ ሁኔታ ገምግመው ሒደቱን ቢመሩት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ባለውለታ ይሆናሉ፡፡ በአገራችን ታሪክም አኩሪ ቦታ ይኖራቸዋል፡፡