ከ23 ዓመታት በፊት በ24.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዋሽ ባንክ ባለአክሲዮኖች፣ የባንኩን የተፈቀደ ካፒታል በእጥፍ በማሳደግ ስድስት ቢሊዮን ብር እንዲሆን ወሰኑ፡፡
ቅዳሜ ኅዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ካፒታል የማሳደግ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ባለአክሲዮኖች ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት የተከፈለ ካፒታሉ በእጥፍ ያድጋል፡፡ ባንኩ እስካሁን የነበረው የተፈቀደ ካፒታል ሦስት ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለካፒታል ማሳደጊያ የተጨመረውን ሦስት ቢሊዮን ብር ባለአክሲዮኖች በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሟላት ተስማምተዋል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ካፒታሉን ከ1.5 ቢሊዮን ብር ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በተወሰነው መሠረት እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ የተከፈለ ካፒታሉን 2.65 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሎ ነበር፡፡ ቀሪውን እስከ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ በማጠናቀቅ አዲሱን ካፒታል ማሰባሰብ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ ባንኩ የካፒታል መጠኑን በዚህ ደረጃ ለማሳደግ የወሰነበትን ምክንያት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታቦር ያሚ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ካፒታሉ በእጥፍ እንዲያድግ ካስገደዱ ምክንያቶች ውስጥ፣ በባንኩ የራዕይ (ቪዥን) 2025 ስትራቴጂ ዕቅድ ውስጥ የባንኩ ካፒታል 14 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተቀምጧል፡፡ የራሱን ሕንፃዎች በተለያዩ የአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች መገንባት አንዱ በስትራቴጂ ዕቅዱ ውስጥ የተያዘና ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ በግል ባንኮች የመሪነትና ትልቁን የገበያ ድርሻ ይዞ ለመቀጠል ካፒታሉን የማሳደግ አስፈላጊነት በምክንያትነት ከቀረቡት ውስጥ ተካቷል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የ16ቱ ባንኮች ጥቅል የተመዘገበ ካፒታል 42 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ ባንኮቹ ከደረሱበት 42 ቢሊዮን ብር ውስጥ የተፈቀደ ካፒታል ውስጥ የተከፈለው ካፒታል መጠን ወደ 23 ቢሊዮን ብር ገደማ ደርሷል፡፡
አዋሽ ባንክ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት፣ የባንኩ የ2009 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ለባለአክሲዮኖች ይፋ ተደርጓል፡፡ በአፈጻጸሙ ባንኩ በተቀማጭ ገንዘብ፣ በብድር መጠን፣ በትርፍ ዕድገት እንዲሁም በጠቅላላ ሀብት መጠን ከግል ባንኮች ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቁን የገለጹት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ፣ በተከፈለ ካፒታል መጠንም ከግል ባንኮች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡም በኢንዱስትሪው የግል ባንኮች ታሪክ ትልቁን እንደሆነ የጠቀሱት ሰብሳቢው፣ በ2009 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም በ2008 ዓ.ም. ከነበረው መጠን የ37 በመቶ ወይም የ364 ሚሊዮን ብር ዕድገት እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ካቻምና አንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 371 ብር ነበር፡፡ በ2009 ዓ.ም. ግን ወደ 409 ብር ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡ የትርፍ ድርሻው በኢንዱስትሪው ከተመዘገበው ከፍተኛ ነው ቢባልም፣ ከዚህ ቀደም ባንኩ ያከፋፍል ከነበረው የትርፍ ድርሻ መጠን አኳያ ዝቅ እንዳለ ያሳያል፡፡ ከዚህ ቀደም በተከታታይ ዓመታት ከ450 ብር በላይ የትርፍ ድርሻ እንዳከፋፈለ ይታወሳል፡፡
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ከ32.7 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያስመዘግብ፣ ከካቻምናው አኳያ የ35 በመቶ ወይም የ8.6 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱና በውጭ ምንዛሪ ግኝትም ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር የ18 በመቶ ዕድገት ታይቶበታል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ያበደረው የገንዘብ መጠን 22.6 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የ46 በመቶ ወይም የ7.1 ቢሊዮን ብር ዕድገት እንደታየበት ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ የባንኩ የብድር ስብጥር እንደሚያሳየው በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛውን ብድር የሰጠው ለአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ለዚህ ዘርፍ የተሰጠው ብድር ከጠቅላላ ብድር ውስጥ የ30.4 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ለዓለም አቀፍ ንግድ 30.2 በመቶ በመያዝ ሲከተል፣ ለሕንፃና ለኮንስትራክሽን ዘርፍ የሰጠው የብድር መጠን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ከጠቅላላው ብድር ውስጥ የ18.3 በመቶውን ይዟል፡፡
የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ ‹‹ባንኩ በ2009 ዓ.ም. ያስመዘገበው ገቢ በባንኩ ታሪክ ያልተመዘገበ ብቻ ሳይሆን፣ ከ2008 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ35 በመቶ ወይም የ940 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 3.76 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡ ካቻምና የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 2.82 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ፀሐይ፣ በዓምና ከተመዘገበው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ 68 በመቶ ገቢ የተገኘው ባንኩ ለብድር ካዋለው ገንዘብ የተገኘው ወለድ ነው፡፡
እንደ ገቢው ሁሉ የባንኩ ወጪም ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የ31.1 በመቶ ወይም የ575.7 ሚሊዮን ብር ጭማሪ የታየበትን የ2.4 ቢሊዮን ብር ወጪ አስመዘግቧል፡፡ ከባንኩ ጠቅላላ ወጪ ውስጥ 62 በመቶ የሚሆነው ለደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የዋለ ነው፡፡ ከካቻምናው በ232.8 ሚሊዮን በላይ ብር ብልጫ ያለው ወጪ ለደመወዝና ጥቅማጥቅም ተካፋይ ሆኗል፡፡ ለባንኩ የወጪ ዕድገት በተለይ ወለድ የሚከፈልባቸው የተቀማጭ ሒሳቦች መጠን ማደግ፣ የአዳዲስ ቅርንጫፎች መከፈትና የኪራይ ቤቶች ዋጋ መናር ለአጠቃላይ ወጪ መብዛት ምክንያቶች እንደሆኑ አቶ ታቦር ገልጸዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብትም በተመሳሳይ ሁኔታ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ 2009 ዓ.ም. የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ብር 42 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ባንኩ የደረሰበት የሀብት መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ34.8 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
ለባንኩ የሀብት መጨመር አስተዋጽኦ ካበረከቱት ውስጥ የራሱን ሕንፃዎች መገንባቱና እየገነባ መሆኑ ነው፡፡ ከባንኩ የተነገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት 20 ሕንፃዎች አሉት፡፡ በባንኩ ሪፖርት እንደታየውም በ2009 ዓ.ም. ባለአሥር ወለል የባልቻ አባነፍሶና ባለስምንት ወለል የሐዋሳ ሕንፃዎችን ያስመረቀ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በፊትም በቢሾፍቱ የባለአራት ወለል ሕንፃ ግንባታ አጠናቆ አገልግሎት አስጀምሯል፡፡ ሌሎችም ግንባታዎች በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ባንኩ በ256 ኤቲኤምና በ388 የግብይት ክፍያ ማስፈጸሚያ ወይም የፖስ ተርሚናሎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ባንኩ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 76 ቅርጫፎችን በመክፈት ጠቅላላ ቅርንጫፎቹን 316 እንዳደረሰ ለመረዳት ተችሏል፡፡
አዋሽ ባንክ የተመሠረተው በኅዳር ወር 1987 ዓ.ም. ሲሆን በወቅቱ በ486 መሥራች ባለአክሲዮኖች ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ብዛት ከ4,000 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡ የሠራተኞቹ ቁጥርም 6,770 ሺሕ እንደሆነ የባንኩ መረጃ ይጠቁማል፡፡