በመንግሥት በእርሻ ሥራ የታወቁ አካባቢዎች ከተለመደው አሠራር ወጥተው በግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም እንዲጀምሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ የመንግሥት ዓይን ካረፈባቸው 32 የግብርና ሥነ ምኅዳራዊ አካባቢዎች ውስጥም ማኛ ጤፍ አምራቹ ጎጃም ይገኝበታል፡፡
አቶ ይልቃል አረጋና አቶ ይርሳው አያሌው በበሬ ከማረስ፣ በእጅ ከማጨድና በአውድማ ከመውቃት ተላቀው፣ በዘመናዊ ግብርና ሜካናይዜሽን እንዲጠቀሙ ከሚደረጉ አርሶ አደሮች መካከል ናቸው፡፡
አቶ ይልቃል በአማራ ክልል፣ ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ዙዬ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ ናቸው፡፡ የ42 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ይልቃል፣ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው፡፡ አቶ ይልቃል አሥር ሔክታር የሚያለሙ ታታሪ ገበሬ ሲሆኑ፣ በተያዘው የምርት ዘመን አምስት ሔክታር ስንዴ፣ ሦስት ሔክታር ጤፍና ሁለት ሔክታር በቆሎ አልምቷል፡፡
አቶ ይልቃል ከ300 ተጎራባች አርሶ አደሮች ጋር ለስንዴ ምርት ያሰቡትን አምስት ሔክታር መሬት በማዳበል ከ2008 ዓ.ም. ምርት ዘመን ጀምሮ በትራክተር አሳርሰዋል፡፡ በኮምባይነር አስወቀተው ምርታቸውን ሰብስበዋል፡፡
አቶ ይልቃል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከካቻምና በፊት ለዘመናት ያለፉበት የእርሻ ሥራቸው ጉልበት የሚጠይቅ አድካሚ ተግባር ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን የእርሻ ማሽኖች መጠቀም በመጀመራቸው ለውጡን አስደሳች ሲሉ ይገልጹታል፡፡
‹‹በዘመናዊ ማሽኖች መሥራት ጥቅም ቢኖረውም፣ ክፍያውም ከባድ ነው፡፡ በድካም የተመረተው ምርት በገበያው ጥሩ ዋጋ አያገኝም፡፡ የማዳበሪያና የኬሚካል ወጪም ከፍተኛ ነው፤›› በማለት አቶ ይልቃል ወጪና ገቢያቸው አልመጣጠን እንዳለ ይገልጻሉ፡፡
በኮምባይነር እህል አጭዶና ወቅቶ ጎተራ ለማሰንበት በአንድ ኩንታል 100 ብር ያስከፍላል፡፡ ‹‹በአንድ ሔክታር 70 ኩንታል ቢመረት፣ ማሽን አቅራቢው ድርጅት በኩንታል 100 ብር አስከፍሎ 7,000 ብር ይወስዳል፡፡ አንድ ኩንታል የምንሸጠው ግን ከ400 እስከ 500 ብር ድረስ ነው፡፡ ዘንድሮ ምናልባት 800 ብር ይገባል ብለን እንጠብቃለን፤›› በማለት አቶ ይልቃል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹የጎጃም ማኛ ጤፍ ነው የትም አገር የሚሄድ፡፡ ነገር ግን ገበያው ሩቅ በመሆኑ፣ የልፋታችንን አናገኝም፤›› ያሉት አቶ ይበቃል፣ ዋጋው ሊስተካከል እንደሚገባውም ጠይቀዋል፡፡
አቶ ይርሳውም አቶ ይልቃል ባነሱት ሐሳብ ቢስማሙም፣ ሌሎች ችግሮች እንዳሉ ያወሳሉ፡፡ አቶ ይርሳው የ67 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ዘጠኝ ልጆች አፍርተዋል፡፡ ሁለቱ ሕፃናት ሲሆኑ ሰባቱ ተገቢውን ትምህርት ባለማግኘታቸው በየቦታው ተቀጥረው የጉልበት ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡
አቶ ይርሳው፣ ቀደም ሲል አምባ ቀበሌ ውስጥ በአራት ገመድ (አንድ ሔክታር) መሬት በግብርና ሥራ ሲተዳደሩ ቢቆዩም፣ መሬቱ በመንሸራተቱና የወባ በሽታ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት በመሸኛ ወደ ልምጭን ቀበሌ ተዘዋውረዋል፡፡
በልምጭን ቀበሌ በሁለት ገመድ (ግማሽ ሔክታር) መሬት ላይ ስንዴ ያለማሉ፡፡ አቅመ ደካማ በመሆናቸው ግን ማሽኑን ለማግኘት አቅም ካላቸው ጋር መጋፋት አልቻሉም፡፡ በዚህም ተቸግረዋል፡፡
‹‹የእኔ መሬት ትንሽ ቢሆንም፣ የባሶ ሊበን መሬት ማዳበሪያ ከሰጠኸው ወቅቱን ጠብቀህ የምትሰበስብ ከሆነ፣ ጥሩ ምርት ታገኛለህ፡፡ ምርቱን ለማምረትና ለመሰብሰብ ብዙ ወጪ ቢወጣበትም ገበያው ግን እየወደቀ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ከላይ የሚወርደው የመንግሥት ሐሳብ ጥሩ ነበር፡፡ ከሥር ግን የሚተገብረው የለም፡፡ እኔም ጆሮዬ እየደከመ በስብሰባ የሚባለውን መስማት አልቻልኩም፤›› ያሉት አቶ ይርሳው፣ ‹‹መንግሥት ለአረጋውያን ቅድሚያ ይሰጥ ያለው ነገር ተግባራዊ ቢሆን ጥሩ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ይርሳው ከዚህ በላይ የሚያስጨንቃቸው ግን የልጆቻቸውና የልጆቻቸው መሰሎች ጉዳይ ነው፡፡ ለሪፖርተር ሲያስረዱም፣ ከዚህ ቀደም የእርሻ ሥራዎች በጉልበት በሚሠሩበት ወቅት፣ ወጣት ልጆች እዚህም እዚያም ተሯሩጠው በእርሻው፣ በአጨዳውና በውቂያው ሠርተው የዕለት ጉርሳቸውን ይሸፍናሉ፡፡ አሁን ግን ማሽኖቹ በበቂም ባይሆን ወደ አካባቢው ከመጡ በኋላ ወጣት ልጆች ቆመው እየዋሉ ነው፡፡ ይህ ከቀጠለም ወጣቶቹ የለመዱትን ለማግኘት፣ ለመኖር ሲሉ ተገቢ ባልሆኑ ነገሮች ውስጥ እንዲዘፈቁ ሊያስገድዷቸው ይችላል ብለው ይሠጋሉ፡፡
‹‹ቀደም ሲል ሕጉም መንግሥትም ስለረዷቸው ሥራ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ይኼ ሲቋረጥ ወደ መጥፎ ቦታ እየገቡ ነው፡፡ የእኔም ልጅ ጭምር ገብቷል፡፡ ቀደም ሲል ወጣቶች ጁቤ ከተማ (ጁቤ የባሶ ሊበን ወረዳ ከተማ ናት) ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ይቆማሉ፡፡ ሊያሠራቸው የፈለገ አርሶ አደር በጠዋት ሄዶ የፈለገውን ያህል ወጣት እየወሰደ በቀን 250 ብር ሒሳብ ያሠራቸዋል፡፡ አሁን ይኼ ሲቋረጥ ወጣቶቹ ምን ይሆናሉ?›› ሲሉ አቶ ይርሳው ይጠይቃሉ፡፡
መንግሥት ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲተገበር ያወጣው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ በአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ ውስጥ በመኸር ወቅት የሚገኘውን የሰብል ምርት በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 270.3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ያልማል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በዝርዝር እንዳስቀመጠውም፣ ‹‹የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ማዳረስ፣ አጠቃቀምንም ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ይህን በማድረግ ምርታማነትን መጨመር፣ ወጪን መቀነስና የድኅረ ምርት ብክነትን መቀነስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የዘር ፍላጎትን ሜካኒካል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከ15 እስከ 90 በመቶ መቀነስ ይቻላል፡፡
ለዚህም እንደ ዋና ተግባር የተያዘው ዘላቂ የሆነ የሜካናይዜሽን አቅርቦት ሰንሰለት መቅረፅ ሲሆን፣ ይህም የተለያዩ አርሶ አደሮችን የማዳረስ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘዴዎችን ማስፋፋትን ያካትታል፡፡ ሚኒስቴሩ ከዚህ በመነሳት በመላ አገሪቱ የሚገኙ 32 የሥነ ምህዳር ወይም የአግሮ ኢኮሎጂዎች ዞኖችን በክላስተር በማዳራጀት፣ በተበጣጠሰ መንገድ ሲካሄዱ የነበሩ ሥራዎች ተቀናጅተው እንዲተገበሩ ማድረግ ጀምሯል፡፡
ከእነዚህ አግሮ ኢኮሎጂ ዞኖች መካከል በምሥራቅ ጎጃም ዞን የተጀመረው የስንዴ፣ የጤፍና የበቆሎ ሰብሎች የልማት ክላስተር ይገኝበታል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2007/2008 የምርት ዘመን 14.3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት፣ በ2008/2009 ምርት ዘመን 15.8 ኩንታል ምርት (884, ጭማሪ ምርት) ተገኝቷል፡፡ በ2009/2010 ምርት ዘመንም 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ በተለይ በጤፍና በስንዴ ሁለት ክላስተሮች ተደራጅተዋል፡፡ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በባሶ ሊበን ወረዳ በተከበረው የሜካናይዜሽን ቀን የባሶ ሊበን ወረዳ ምክትል አስተዳደሪ አቶ ሰውነት ሹመቴ እንደተናገሩት፣ በስንዴ 17,103 አርሶ አደሮች በ58 ክላስተር ተደራጅተው መሬታቸውን አንድ ላይ እያደረጉ 16,189 ሔክታር እያለሙ ይገኛሉ፡፡
ምክትል አስተዳዳሪው እንደተናገሩት፣ በወረዳው እየሠሩ የሚገኙት ኮምባይነሮች ለብዙ ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸው በተደጋጋሚ ስለተበላሹ፣ አርሶ አደሮች በወረፋ እየጠበቁ የጊዜ ብክነትና እርስ በርስ አለመስማማት እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በቂ መሣሪያዎች እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በጨተማሪ አካባቢው ትርፍ አምራች ቢሆንም፣ ከጨሞጋ እስከ ጁቤ ከተማ ድረስ ያለው 17 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ ምርቱን ለማጓጓዝ የማያመች፣ ባሶ ሊበን ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰን በመሆኑም እስከ ኦሮሚያ የሚዘልቅ መንገድ እንዲሠራ፣ ሁለቱ ሕዝቦች (አማራና ኦሮሚያ) በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ እንዲደረግ ምክትል አስተዳዳሪው ጠይቀዋል፡፡
መንግሥት ባለፈው 2008/2009 ምርት ዘመን በ196 ሺሕ ሔክታር መሬት በሙከራ ደረጃ የጀመረው የሜካናይዜሽን ግብርና እየሰፋ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ በሙከራ የተጀመረው የሜካናይዜሽን ሥራ ውጤት እየተገኘበት በመሆኑ የበለጠ ለማስፋት ታቅዷል፡፡
ስንዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ በርካታ የዓለም ሕዝብ በቀዳሚነት የሚመገበው ሰብል እንደመሆኑ ለስንዴ ምርት የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በአጠቃላይ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም የሜካናይዜሽን ቀን ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተጋበዙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ ያሳውቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይገኙ በመቅረታቸው እስካሁን ውሳኔው አልታወቀም፡፡
ጤፍን በተመለከተ በተለይ ጤፍ የኢትዮጵያ አገር በቀል ሰብል እንደመሆኑ ለዘመናት በሰውና በእንስሳት ጉልበት ሲካሄድ የቆየ እንደመሆኑ፣ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች ሳይገኙለት ቆይቷል፡፡ ለጤፍ ምርት የተሻለ መሣሪያ ለማግኘት ሲካሄዱ የቆዩ ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርቷል፡፡
በመጨረሻ ግን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከቻይና ኩባንያ ጋር ባደረገው ምክክር የቻይናው ኩባንያ ጤፍ የሚያጭድና የሚወቃ ማሽን በማምረቱ የመጀመርያዎቹ ስምንት ማሽኖች ወደ አገር በመግባት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከዚህም በተጨማሪ ከህንድ ኩባንያ ጋር በመሆን በደብረ ብርሃን ከተማ የሜካናይዜሽን ማሽኖች ኦፕሬተሮች፣ መካኒኮችና አሠልጣኞች የሚሠለጥኑበት ተቋም ለመመሥረት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
መንግሥት የአገሪቱን 40 በመቶ በሚሸፍነው በርካታ የሕዝብ ቁጥር ይዞ በሚገኘው ከፍተኛ ቦታ ላይ (ደጋና ወይና ደጋ አካባቢ) በሜካናይዜሽን የታጀበ ግብርና በጥልቀት ለማካሄድ ሰፊ ዕቅድ ወጥቷል፡፡
ይህ አዲስና በጥልቀት ሊተገበር የታሰበ ዕቅድ ‹‹በተበጣጠሰ ማሳ ለውጥ አይመጣም!›› እየተባለ ሲቀነቀን የነበረ መከራከሪያ ደግሞ እንዲታወስ በር ከፍቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት በከፍተኛ አካባቢዎች (ደጋና ወይና ደጋ) በርካታ ሕዝብ የሚኖር በመሆኑ ሊተገበር የሚገባው ጉልበትን መሠረት ያደረገ ግብርና ነው እንጂ ጉልበትን የሚያስቀር አማራጭ አይደለም የሚል አቋም ሲያራምድ ቆይቷል፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ጉልበትን መሠረት ባደረገ መንገድ በተበጣጠሰ ማሳ ለውጥ ይመጣል ሲል፣ በሌላ ጎራ የተቀመጡ ወገኖች ደግሞ በፍፁም በተበጣጠሰ ማሳ ጉልበትን መሠረት ባደረገ ማሳ ለውጥ አይመጣም ሲሉ ይከራከሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ነገር ግን በመጨረሻ በመሬት ሥሪት ላይ ለውጥ ባይደረግም ደገኛ አርሶ አደሮች ያላቸውን አነስተኛ ማሳ ድንበር አፍርሰው እየቀላቀሉ አርሰው፣ በአንድ ላይ አሳጭደውና በአንድ ላይ አስወቅተው ምርት የሚሰበስቡበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) በሜካናይዜሽን ቀን ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ አርሶ አደሮች ይዞታቸውን ድቅድቅ በመሥራት፣ ቁልቋል በመትከልና ካብ በመገንባት ያስከብሩ ነበር፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ይህንን የቆየ አሠራር በፈቃደኝነት በመተው፣ በአንድነት በሜካናይዜሽን ማልማት ጀምረዋል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ‹‹የእርሻ መሬት እየተሸጠ ሄደ፣ የተበጣጠሱ ማሳዎች አንድ ካልሆኑ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብርና ማስፋት አይቻልም ሲባል የነበረውን የገነነ አስተሳሰብ በተግባር ውድቅ በማድረግ የሜካናይዜሽን ግብርና ተጀምሯል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጽዋል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ በሚኒስትሩ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አቶ ተስፋዬ በወቅቱ እንደገለጹት፣ የተበጣጠሰ ማሳ ተይዞ ፈጽሞ ወደ ዘመናዊነት መሸጋገር አይቻልም፡፡ በማለት ሲሞግቱ የነበሩ የኒዮሊበራል ኃይሎች ነበሩ፡፡ ‹‹ነገር ግን ዛሬ ክላስተርን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማታችንን ሜካናይዝድ በሆነ አግባብ መምራት መጀመራችንን ስንመለከት ፖሊሲያችን የቱን ያህል ትክክለኛ መሆኑን እንረዳለን፤›› ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
አቶ ይርሳው፣ አቶ ይልቃልና ሌሎች የምሥራቅ ጎጃም አርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን ግብርና ከውድነቱ በስተቀር ጉልበት በመቀነስና በምርታማነቱ ሸጋ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን አቶ ይርሳውና መሰሎቻቸው ሜካናይዜሽን በአነስተኛ ደረጃ በገባበት ወቅት እንኳ በርካታ ሰዎች ያለ ሥራ መዋል ጀምረዋል፣ ሜካናይዜሽን በብዛት ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ በነዚህ አካባቢዎች ሥራ አጥ ወጣቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ይሠጋሉ፡፡ የባሶ ሊበን ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና አቶ ሹመቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተወሰነ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በዚህ በአጨዳ ወቅት የጉልበት ሥራ እስከ 140 ብር ይደርስ ነበር፡፡ ከዚህ ረገድ በዚህ ሥራ ውስጥ ለነበሩ ዜጎች ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡
‹‹ነገር ግን ይህ ሥራ የአጭር ጊዜ ነው፡፡ እኛ ለወጣቶች እየፈጠርን ያለነው ሥራ ግን ዘላቂ ነው፤›› ሲሉ አቶ ሹመቴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ዳመነ ዳሮታ በግብርና ዘርፍ በርካታ ወጣቶች ሥራ ያገኛሉ ይላሉ፡፡
በባሶ ሊበን ወረዳ ልምጭን ቀበሌ የሜካናይዜሸን ቀን ሲከበር የተገኙት አቶ ዳመነ፣ ከተንጣለለው ማሳ ስንዴ በኮምባይነር ሲታጨድና ሲፈለፈል ሲመለከቱ ሐሴት አድርገው ነበር፡፡ ‹‹ይህን ማሳ ማን የአፍሪካ ማሳ ይለዋል፡፡ የአውሮፓ እንጂ፤›› ሲሉ አቶ ዳመነ ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡
አቶ ዳመነ፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ዘርፍን ይመራሉ፡፡ አቶ ዳመነ፣ በግብርና ዘርፍ በርካታ ሥራ እንደሚፈጠር ያምናሉ፡፡
በተለይ ደግሞ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከክልሎች እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮዎችና ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት፣ ወጣቶች በግብርና ዘርፍ በተለይ በመስኖ ልማት፣ በዶሮ እርባታ፣ በከብት እርባታና ድለባ፣ ፍየልና በግ ማሞከት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በተፋሰስ በለሙ አካባቢዎች ጭምር ወጣቶች ቦታ እየተሰጣቸው በሁለገብ የልማት ሥራዎች ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ተጠቃሚ በማድረግ እንዲሻሻሉ፣ እንዲሁም ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ጭምር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማገዝ ላይ እንደሚገኙ ከአቶ ዳመነ ቢሮ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከዚህ አንፃር በ2009 በጀት ዓመት ከ1.57 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ገጠር ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ከዚህ ውስጥ በግብርና ሥራ ላይ ብቻ 850,894፣ ከግብርና ውጪ በሆኑ የሥራ መስኮች ድግሞ 696,186 የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በቋሚነት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው 1,145,591 ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ በጊዜያዊ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው፡፡
ይህንን ሥራ በመቀጠል በ2010 በጀት ዓመትም ከ1.799 ሚሊዮን የገጠር ወጣቶችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በቋሚ ሥራ ለ1,200,365 ወጣቶችና በጊዜያዊ ሥራ ደግሞ ለ599,390 ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይህንን ዘላቂ ለማድረግ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂ ተቀርጾ መንግሥት፣ የልማት አጋሮች፣ ወጣቶች ራሳቸውና ኅብረተሰብ በአጠቃላይ የትኩረት ማዕከል የማድረግ ሥራ መጀመሩን መረጃው አመልክቷል፡
አቶ ዳመነ እንደተናገሩት በኢንዱስትሪና በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በአውት ግሮዋር ተደራጅተው ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን እንዲያቀርቡ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
የባሶ ሊበን ማኛ ጤፍ አምራች አቶ ይልቃል፣ መሰሎቹና ኢሕአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን በሜካናይዜሸን እምነት አሳድረዋል፡፡ በተለይ መንግሥት በሜካናይዜሽን ዘግይቶ በማመኑ ከጎረቤት አገሮች እንኳ ሲነፃፀር ኋላ ቀርቷል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ በዓለም አቀፍ መስፈርት በአሥር ሺሕ ሔክታር 66 ትራክተር መኖር አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር በኬንያ 26.3 እና በሱዳን 9.6 ትራክተሮች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን 2.2 ትራክተሮች ብቻ ይገኛሉ፡፡ ሚኒስትሩ የሜካናይዜሽን አብዮት ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ይህ የሜካናይዜሽን አብዮ ሲፈጠር ግን አቶ ይርሳውን ያሠጋው የሥራ ዕድል ጉዳይ ሳይዘነጋ፡፡