Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትምህርት ያለመጽሐፍ የሆነበት አገር!ትምህርት ያለመጽሐፍ የሆነበት አገር!

የትምህርት ዘመን ሲጀመር ወላጆች ከሚጠየቁት የመመዝገቢያና የወርሃዊ ክፍያዎች በተጓዳኝ፣ ለልጀቻቸው ትምህርት አጋዥ መጻሕፍት ግዥ እንዲፈጽሙ ይጠየቃሉ፡፡ እንደ ተማሪዎቹ የክፍል ደረጃ የመማሪያ መጻሕፍቱ ዋጋም ስለሚለያይ፣ ወላጆች በሚቀርብላቸው ዋጋ መሠረት ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡

መጻሕፍቱ በዓመቱ ለተማሪዎች ቢታደሉም፣ ዘንድሮ ግን በተለመደው መርሐ ግብር መሠረት ለተማሪዎች ማቅረብ ሳይቻል፣ የትምህርት ዘመኑ ከተጀመረ ሦስተኛው ወር ተቆጥሯል፡፡ ከዛሬ ነገ መጻሕፍቱ ይቀርባሉ ቢባልም እስካሁን ድረስ በአብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ ይህም በመማር ማስተመሩ ተግባር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ጥቂት መጻሕፍትን በቤተ መጻሐፍት ቢያኖሩም፣ መጽሐፍ ያልደረሳቸው የበርካታ ተማሪዎችን ፍላጎት እንዳላሟሉ እየተገለጸ ነው፡፡ አንዳንዴም  መምህራን መጻሕፍት እንዳልደርሳቸው እያወቁ በሌላቸው መጻሕፍት እንዲያጣቅሱ ማድረጋቸው ተማሪዎችን ሲያስጨንቅ ታዝበናል፡፡

መጻሕፍቱን ለተማሪዎች በአግባቡ አለማዳረስ በተማሪዎቹ ላይ ብቻም ሳይሆን፣ በመምህራንና በወላጆች ላይም ጫና ያሳድራል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የመማሪያ መጻሕፍቱ እስካሁን ያልቀረቡበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ ተማሪዎች፣ ወላጆችና መምህራን ግን ከዛሬ ነገ እናገኛለን በማለት እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በርካታ ተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ ሳያደርሳቸው የሴሚስተር አጋማሽ ፈተና ወስደዋል፡፡

በመጻሕፍቱ መጥፋት ሳቢያ ተማሪዎች የሚፈጠርባቸውን ጫና ማንም የሚገነዘበው ቢሆንም፣ ለችግሩ አፋጣኝ ዕርምጃ አለመሰጠቱ ግን እጅግ ያሳዝናል፡፡ መጻሕፍቱን ለየትምህርት ቤቶቹ ማድረስ የነበረበት ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የትምህርት ቢሮዎች፣ ለተፈጠረው ችግር ተገቢውን መፍትሔ መስጠት አለመቻላቸው፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባብ እንደማይወጡ አሳይቷል፡፡ ለተማሪዎቹ መድረስ ያለበት መጽሐፍ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት መሰራጨት ሲገባው ይህ ባልሆነበት ወቅትም   ምክንያቱን በአግባቡ ማብራራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ችግሩ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅዕኖና መጻሕፍቱ ባለመገኘታቸው በልጆቸቸው ውትወታ የተቸገሩ ወላጆች፣ አቅማቸው እንደቻለ ‹‹በጥቁር ገበያ›› የመማሪያ መጻሕፍት ገዝተዋል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ይገኛል ያሉ አንዳንዶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ደጋግመው ቢናገሩም ሰሚ አላገኙም፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ለመፍትሔ የሚሆን ዕርምጃ ባለመወሰዳቸውም በመማር ማስተማሩ ላይ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ ወላጆች በቅድሚያ የከፈሉበት መጽሐፍ ትምህርት ቤቶቹ ሊሰጧቸው ባለመቻላቸው፣ ዳግመኛ በተጨማሪ ወጪ ከገበያ ለመግዛት ወጥተዋል፡፡ ነጋዴዎች ግን በ20 ወይም በ25 ብር የሚሸጠውን መጽሐፍ እስከ 150 ብር ሲሸጡ መታየታቸው የጉድ አገር ያሰኛል፡፡ ግራ የሚያጋባው የመጻሕፍቱ በተጋነነ ዋጋ መሸጥ ብቻ አይደለም፡፡ አስገራሚ የሚሆነው ትምህርት ሚኒስቴር ባለጉዳይ የሆነባቸው እነዚህን መጻሕፍት ትምህርት ቤቶች ማግኘት ተስኗቸው ነጋዴዎቹ ግን እንዳሻቸው ማግኘታቸው ነው፡፡ እንዴት የነጋዴ ሲሳይ ሆኑ? መልስ የሌለው ጥያቄ ቢመስልም፣ መንግሥት በራሱ ንግድ ውስጥ የገባበት አካሄድ ሲታይ ግን ነገሩ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡  ይኸውም በውጭ አገሮች ዕርዳታ ያውም በነፃ ለተማሪዎች እንደሚታደሉ የተጻፈባቸው መመሪያ መጻሕፍት እኮ እስከ 300 ብር እያወጡ የሚሸጡት በራሱ በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ነው፡፡ ይህን ለመመልከት አራት ኪሎ በሚገኘው ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ጎራ ማለት በቂ ነው፡፡

መጻፍቱን የማሳተም መብት ያለው ትምህርት ሚኒስቴር ከሆነ፣ በገበያው የምናያቸው መጻሕፍት ምንጫቸው የት ነው? ትምህርት ሚኒስቴር የሌለውን መጻሕፍት በየመንገዱ የሚሸጡት ከየት የአምጥተው ነው ተብሎ የሚጠይቀው ማነው? ማን ያውቃል ለትምህርት ቤቶች ይታደሉ የተባሉ መጻሕፍት በጎን እንዲሾልኩ መንገድ ተመቻችቶላቸውስ ቢሆን? ምክንያቱም ምንም ይሁን ተማሪዎች ያለመደበኛ የመማሪያ መጻሕፍት እየተማሩ፣ በሌላ በኩል መጻሕፍቱ ገበያ ላይ የመገኘታቸው ጉዳይ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የቱንም ያህል ምክንያት ቢደረደር አሁን ያለመማርያ መጻሕፍት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ተማሪዎች እየደረሰባቸው ያለውን ተፅዕኖ ሊያባብስ አይችልም ወይ?

እርግጥ በአንድ ወቅት የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች አንድ መጽሐፍ ለአምስት ለስድስት ተማሪ እንዲያቀርቡ ሲደረግ ነበር፡፡ ይህ መደረጉ በወቅቱ የነበረውን ችግር ያሳያል፡፡ አሁን ግን ለየትምህርት ክፍሉ በተማሪዎች ልክ በቂ መጽሐፍ እንዲታተም በጀት ተይዞ፣ ይህም ታሳቢ ተደርጎ ወላጆች ለመማሪያ መጻሕፍቱ ክፍያ ፈጽመው ሳለ በወቅቱ ያላገኙበትን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ ምነዋ እንዲህ ቸገረሳ? ያደላቸው መንግሥታት ልጆቻቸው በዘመናዊ የትምህርት ቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እያቀረቡ ነው፡፡ ሩቅ ሳይኬድ በአፍሪካ ምሳሌዎች አሉልን፡፡ በወረቀት መጻሕፍት ወደ ዲጂታል መጻሕፍት በመሻገር ልጆችም የዚሁ ተቋዳሽ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ባትበቃ ለወረቀት መጻፍሕት ያውም በዕርዳታ የሚታተሙ መጻሕፍትን ማዳረስ ይሳናታልን?

ከዚህ በኋላ ባለው የትምህርት ጊዜ ውስጥ እንኳ መጻሕፍቱ በቶሎ እንዲቀርቡ በማድረግ ችግሩ የሚቃለልበትን መንገድ ማበጀት ቢቻልም ማለፊያ በነበር፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት