Tuesday, February 27, 2024

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ራሱን ያየበት መነጽር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ35 ቀናት የግምገማ ስብሰባ ላይ ከርሟል፡፡ በግምገማውም የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር ክልላዊና አገራዊ ተልዕኮውን ከመወጣት አንፃር ያለበትን ቁመና ለማየት የሚያስችል ሥር ነቀል ግምገማ ማካሄዱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ለአንድ ወር የቆየውን የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በተመለከተ በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ማዕከላዊ ኮሚቴው ወደ ስብሰባ ሲገባና ስብሰባውን አጠናቆ ወደ ሂስና ግለ ሂስ ሲሸጋገር በሰጣቸው መግለጫዎች የተዘበራረቁ አስተያየቶች ሲሰሙ ነበር፡፡

አንዳንዶቹ ከተለመደው የግምገማ ውጤት የተለየ ነገር ይዞ አልመጣም ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ጥሩ እንደነበር ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ስብሰባው ሲጠናቀቅ የወጣውን መግለጫ ግን በበጎ ጎኑ ያዩ አሉ፡፡ እንደ ምክንያት የሚያነሱትም ከዚህ በፊት ከነበረው በተቃራኒ ራሱን የችግሮች ሁሉ ምንጭ አድርጎ ማቅረቡን ያወሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ በፊት የነበሩ አሰልቺ አገላለጾች መቅረታቸውንም ያስረዳሉ፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ከፍተኛ የሚባል ቀውስ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ አገሪቱ በተለመደበው የፀጥታ ሥርዓት መመራት ተስኗት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ይኼን ቀውስ በተመለከተ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐሙስ ኅዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ስትራቴጂካዊ አመራሩ እየተዳከመ ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመናው፣ አመለካከቱና አደረጃጀቱ በየጊዜው እየተሸረሸረ፣ ሕዝባዊነቱ እየቀነሰ፣ የሕዝብን ችግር በማያወላዳ መልኩ ሳይፈታ በትንንሽ ድሎች የሚረካ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ መሆን የጀመረበት ሁኔታ በስፋት መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹በዚህ ቁመናም መስመሩን ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ በግልጽ አሳይቷል፤›› በማለት መግለጫው አስታውቋል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ከገባበት አዙሪት ለመውጣት ያለው ብቸኛ አማራጭ በድርጅቱ የቆየ ሳይንሳዊ የትግል ባህል መሠረት፣ በቁጭት ተነሳስቶ ጥልቀት ያለው የአመራር ግምገማ ማድረግ ብቻ እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ቀውሶች ዋነኛው ምክንያት የመንግሥት አመራር እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ቀውሶች ዋነኛ ምክንያቱ የመንግሥት አመራሮች ዘንድ ባለ ክፍተት እንደሆነ ጠቁመው ነበር፡፡ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በክልሉ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮችም ዋና ምክንያቱ አመራሩ እንደሆነ አስምሮበታል፡፡

ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጥሞና መርምሮ ድርጅቱን በማያዳግም ሁኔታ ወደ ትክክለኛው መስመሩና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ ለመመለስ በሚያስችለው ደረጃ ራሱን በጥልቀት መፈተሹን ገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት ይደረጉ ከነበሩ ግምገማዎች በዓይነቱ የተለየ እንደነበርና ችግሮቹን በሚገባ ለመለየት ያስቻለ ውስጣዊ ትግል እንዳካሄደ የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ይጠቁማል፡፡  

አሁን በሥራ ላይ ያለውና ተተኪው አመራር ከገባበት አዙሪት ለመውጣት በተለመደው መንገድ መሄድ እንደሚያዋጣ መገምገሙንም ጠቁሟል፡፡ ይኼን ለማስተካከልም ስፋትና ጥልቀት ያለው ክርክር ለማድረግ የሚያግዝ ሰነድ እንዳቀረበና ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጎበት የአመራሩን ድክመት ለመለየት እንደተቻለ መግለጫው አትቷል፡፡

በሰነዱ ላይ ተመሥርቶ በተደረገ ውይይትና ክርክርም የሕዝቡንና የመላው አባሉን ተደጋጋሚ ጥያቄ መመለስ ያልቻለበትን ምክንያት ጠቅሷል፡፡ ይኼም ስትራቴጂካዊ አመራሩ ከገባበት አዙሪት ውስጥ መውጣት አቅቶት ሲዳክር በመቆየቱ ምክንያት የፈተጠረ ችግር እንደሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴው መገምገሙን አስረድቷል፡፡

አመራሩ የሐሳብና የተግባር አንድነት እንደጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቲክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ እንደተነከረ፣ በተልዕኮ ዙሪያ በመታገል በመርህ ላይ የተመሠረተ አመራር እንደማይሰጥ፣ ሕዝብንና ዓላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርና ጥቅም እንደሚያስቀድም መታየቱንም አትቷል፡፡

ከኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ሕወሓት አመራሩ የሕዝብ ወገንተኛነቱ እየተሸረሸ መምጣቱን አስምሮበታል፡፡ በመግለጫው፣ ‹‹ለሕዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከአገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ እየቆጠረ፣ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የሕዝብ ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴዎች ከመጠመድ ይልቅ በድምር ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዥ መደብ የማሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን በትክክል አስቀምጧል፤›› ሲል መግለጫው ያብራራል፡፡

የስትራቴጂካዊ አመራሩ ድክመት በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦችና አፈጻጸሞች ላይ እጅግ ከባድ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ጠቁሟል፡፡ የተመዘገቡ ለውጦችን ማስቀጠል ያልተቻለበት፣ አንዳንዴም ወደኋላ መመለስ የጀመረበት ሁኔታ እንደነበረ በጥልቀት መታየቱን መግለጫው ጠቅሷል፡፡ ‹‹ሁሉንም የልማት ኃይሎች በተደራጀ መንገድ በመምራት ረገድ የነበረውን ሰፊ ክፍተትም እንዳሳየ ተጠቁሟል፤›› ሲል መግለጫው አስረድቷል፡፡

‹‹ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶችና ሌሎችም የሙያ ማኅበራትና መሰል አደረጃጀቶች የለውጥ ባለቤት ሆነው የሚወጡበትን ዕድል በማምከን፣ ድርጅቱን በቀጣይነት የሚመራ ብቁ ኃይል እንዳይፈጠር እንቅፋት የሆነ አመራር መሆኑንም በሚገባ ተረድቷል፤›› ሲል መግለጫው ያትታል፡፡

አራቱ የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ አባላት እንዳሏቸው ይነገራል፡፡ በአገሪቱ እየከሰቱ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ የድርጅቶቹ አባላት ብዙ ጥያቄዎችን ሲያነሱና ችግሮች እንዲስተካከሉ እየጠየቁ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴም ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ‹‹የሕዝቡ በድርጅቱ ላይ የነበረውን እምነት እንዲሸረሸርም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በአመራሩ ዘንድ የታየው ድክመት በሕዝብ ዘንድ ካስተከተለው ከፍተኛ የአመኔታ መሸርሸር ችግር በተጨማሪ፣ በከተማም ሆነ በገጠር በጀመርናቸው ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ሥራዎች ለአደጋ ያጋለጠ ነበር፤›› ብሏል፡፡

በገጠርም ሆነ በከተማ የተቀረፁ ፖሊሲዎችና የተቀየሱ ስትራቴጂዎች ትክክለኝነት ላይ ችግር እንደሌለ የጠቆመው መግለጫው፣ አፈጻጸሙ በታቀደው ልክ አስተማማኝ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለና በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ማድረጉን ማዕከላዊ ኮሚቴው እንደለየ ጠቁሟል፡፡

‹‹በገጠር የእርሻ ትራንስፎርሜሽን፣ በከተማ የአነስተኛና ጥቃቅን ልማት፣ የከተሞች ዕድገት፣ የወጣቶችና ሴቶች ሥራ ፈጠራ፣ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት ባቀድነው ልክ ላለመመዝገቡ የስትራቴጂካዊ አመራሩ ድክመት ዋናውን ድርሻ እንደሚወስድ ገምግሟል፤›› በማለት መግለጫው አብራርቷል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ከገመገመ በኋላ ለተፈጠረው የአመራር ችግር ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት በማመን፣ በኮሚቴው አባላት ሒስና ግለ ሒስ ማካሄዱን ጠቁሟል፡፡ የተፈጠረውን ችግር ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥልቅ የሒስና ግለ ሒስ መድረክ ማከናወኑን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች በተለያየ ጊዜ በሚያደርጉት ስብሰባ ሒስና ግለ ሒስ በማካሄድ ችግሮችን ለመቅረፍ ተዘጋጅተናል የሚል መግለጫ ቢያወጡም፣ ብዙዎች እምነት እንደሌላቸው ሲናገሩ በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡ ሕወሓት ባካሄደው ሒስና ግለ ሒስ አመራሮችን ከኃላፊነት ከማውረድ ጀምሮ ሌሎች አዳዲስ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት አምጥቷል፡፡ የሒስና ግለ ሒስ ዓላማም በግለሰብ አመራር አባላት ላይ ያተኮረ እንዳልሆነ፣ ድርጅቱ ካለው ስትራቴጂካዊ ፖለቲካዊ ተልዕኮ አንፃር እያንዳንዱ አመራር ኃላፊነቱን የተወጣበትን ደረጃና ልክ በትክክል ለመገንዘብና አስፈላጊውን የዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ያለመ እንደነበር አብራርቷል፡፡ ‹‹ሒደቱም በግልጽነት በሙሉ ተሳትፎና በቁጭት መንፈስ የተከናወነ ሲሆን፣ በመጨረሻም በመላው አመራር ዘንድ በተደረሰበት ድምዳሜ የጋራ መግባባት የተያዘበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤›› በማለት አስታውቋል፡፡

የሒስና ግለ ሒስ ሒደቱ ከተከናወነ በኋላም በድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር ዘንድ ይስተዋል የነበረውን የሐሳብና የተግባር አንድነት ችግር ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱንና የአመራር ሽግሽግ መደረጉን መግለጫው አብራርቷል፡፡

ድርጅቱ ፈተናዎች ሲገጥሙት ከሕዝብና ከአባላቱ ጋር በመሆን ችግሮችን ለበርካታ ዓመታት ሲፈታ እንደቆየ የጠቆመው መግለጫው፣ ጥያቄዎችን በመፍታት ረገድ የሕወሓት አመራር ድክመት አሳይቶ እንኳን ሕዝቡ በትዕግሥትና በተስፋ ሲጠብቅ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

የሕዝቡንና የአባላቱን ጥያቄዎች እንደሚፈታ፣ ተሸርሽሮ የነበረውን አመኔታ እንደሚያድስ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊኖር የሚገባውን ሚና ለማስቀጠል እንደተዘጋጀና ቀጣዩን ጉባዔ አሳታፊ በሆነ መልኩ ለማከናወን የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚያከናውን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

‹‹አመራሩ በጊዜ የለም መንፈስ ከመላው አባላችንና ሕዝባችን ጋር በሚደረገው ጥልቅ ውይይት ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች በበለጠ ለማበልፀግ የሚያስችል ሥራ ይሠራል፤›› በማለት በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔን በቅርቡ እንደሚያካሂድና ጉባዔውም መላው አባላት፣ ምሁራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ብዙኃን ማኅበራትን በማሳተፍ እንደሚካሄድ ጠቁሟል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው በክልሉና በአገሪቱ ጉዳይ ሕዝቡን በሚገባ እንዳላሳተፈ ጠቁሞ፣ ጥያቄዎችን ለመመለስና የተሟላ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምሁሩና ባለሀብቱ በመሰላቸው አደረጃጀት ውስጥ ሆነው፣ ተዋናይ የሚሆኑበት ተቋማዊ መሠረት በማስቀመጥ የሚሠራ እንደሆነ በመግለጫው ገልጿል፡፡

የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሕዝቡን በተገቢው መንገድ አዳምጠው ምላሽ ከመስጠት አኳያ ክፍተት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ ሕወሓት ይህን እንደሚያስተካክልም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

‹‹በክልላችን ልማትም ሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላችሁ ተሳትፎ ለአገራችን ዕድገትና ህዳሴ መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ ከምንም በላይ የተጠቃሚነትና የተሳታፊነት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ ድርጅታችሁ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ቃል ይገባል፡፡ እናንተን በጥሞና ለማዳመጥና ለማታገል የሚያስችሉ መድረኮችንም ያመቻቻል፤›› ብሏል፡፡

ለድርጅቱ አባላት፣ ለአርሶ አደሮችና ለከተማ ነዋሪዎች፣ ለወጣቶችና ለሴቶች፣ ለኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና ለአጋር ድርጅቶች ጥሪ አቅርቧል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተፈጠረ ላለው ቀውስ ዋነኛ ምክንያቱ የአመራሩ ድክመት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ በአመራሮች ድክመት የተነሳም በአገሪቱ በተለይም በእህት ድርጅቶች መካከል መተማመን ባለመፍጠር ችግሮች መከሰታቸው ይነገራል፡፡ በጠገዴና በፀገዴ ወረዳዎች መካከል የነበረው የአስተዳደራዊ ወሰን ዋነኛው ችግር በሕወሓትና በብአዴን አመራሮች መካከል ተፈጥሮ በነበረ አለመግባባት እንደነበር ይወሳል፡፡

ሕወሓትም ይህን በተመለከተ፣ ‹‹የአመራር ድክመት በሕወሓት ውስጥም ሆነ በክልላችን በሚደረጉ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥረቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ፣ በእህትና በአጋር ድርጅቶች መካከል ለበርካታ አሥርት ዓመታት የነበረውን በመርህና በትግል ላይ የተመሠረተ ውህደት፣ ለዙሪያ መለስ ስኬት ያበቃን የአመለካከትና የተግባር አንድነት በየጊዜው እየሸረሸረ እንዲመጣና በጋራ ዓላማ ዙሪያ በአንድ ልብና መንፈስ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በንትርክና በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርጓል፤›› በማለት መግለጫው አብራርቷል፡፡

‹‹የሕዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ፖሊሲዎች ላይ ስኬታማ አፈጻጸም ከማድረግ ይልቅ፣ የፌዴራል ሥርዓት ጠላቶች ባጠመዱልን ወጥመድ ውስጥ ገብተን የአገራችንን ኢትዮጵያ ህልውና ፈተና ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ረገድ በሕወሓት አመራር ዘንድ የታየው ድክመት የማይናቅ ሚና እንደነበረው በግልጽ ይረዳል፤›› ብሏል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱን ለመናድ ከውስጥም ከውጭም የተሰባሰቡ ጥገኛ ኃይሎችን በጋራ የመመከት አቅም እየተመናመነ፣ በተመሳሳይ ፕሮግራምና ልማታዊ መስመር ዙሪያ የተሠለፉ ኃይሎች የጋራ ትግላቸው መደነቃቀፍ የጀመረበት ሁኔታ መፈጠሩን መግለጫው አክሎ ገልጿል፡፡

‹‹በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ለሚታዩ ችግሮች ዋነኛው ተጠያቂነት ለየድርጅቱ አመራር የሚተው ቢሆንም፣ በሕወሓት አመራር ውስጥ ይታዩ የነበሩ አዝማሚያዎች ለብዙ አሥርት ዓመታት በእሳት ጭምር ተፈትኖ የመጣውንና ለአገራችን ኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ ዕውን መሆን ምክንያት የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በመሸርሸር ረገድ የማይናቅ ድረስ እንደነበረው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ባደረገው ግምገማ አረጋግጧል፤›› ሲል መግለጫው አትቷል፡፡ ሕወሓት ከእህትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት በመርህና በእርስ በርስ ትግል ላይ በመመሥረት፣ መጠራጠሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚከተል እንደሚሆን በመግለጫው አስረድቷል፡፡

‹‹ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚቃጡ አፍራሽ ጥቃቶችን ለመመከት ከመላው የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር በቅርበት ይሠራል፤›› በማለት የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ መግለጫው በመጨረሻም፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ አንድነታችሁን አጠናክራችሁ፣ አፍራሽ አጀንዳዎቻቸውን ለማሳካትና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚዳክሩ ጠላቶችን በጋራ እንመክት›› በማለት ከላይ ለተጠቀሱት አካላት ጥሪ አስተላልፏል፡፡  

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከአንድ ወር በላይ ሲያካሂድ የነበረውን ግምገማዊ ስብሰባ አዳዲስ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመምረጥ አጠናቋል፡፡ በዚህም መሠረት የመገናኛና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን (ዶ/ር) ሊቀመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርን ምክትል ሊቀመንበር  አድርጎ መርጧል፡፡

ከግምገማው በኋላ በሒስና ግለሒስ የማጥራት ዕርምጃ በመውሰድ ዘጠኝ አባላት ያሉት የድርጅቱን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማካሄዱን ጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ ዓለም ገብረ ዋህድ፣ አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር)፣ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሒምና አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አድርጎ መርጧል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በማውረድ ያገደ ሲሆን፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ዓባይ ወልዱን ደግሞ በማንሳት ከሥራ አስፈጻሚ አባልነታቸው ዝቅ አድርጎ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ገድቧቸዋል፡፡ ለአዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) እና ለአቶ ዓለም ገብረ ዋህድ ማዕከላዊ ኮሚቴው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -