Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት አሥርታትን የዘለቁ የኢንቨስትመንት ፋናዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስለኩባንያዎቻቸው እንቅስቃሴ እንጂ ኩባንያቹን በባለቤትነት ስለመምራታቸው ብዙም ሲናገሩ ከማይደመጡ ባለሀብቶች መካከል አቶ ብዙአየሁ ታደለ አንዱ ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ከ35 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ የንግድ ሥራ ዘርፎችን በመፍጠር እየሠሩ የሚገኙት አቶ ብዙአየሁ፣ ከእሳቸውና ካሏቸው ድርጅቶች ብዛት ይልቅ የፈጠሯቸው ኩባንያዎች ማንነት ጎልተው ሲነገርላቸው ቆይተዋል፡፡ አቶ ብዙአየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከእሳቸው ስምና ማምነት የተሻለ ቢታወቅ ውጤት ሊኖረው የሚችለው ቢዝነሱ በመሆኑ፣ ስለራሳቸው ከመግለጽ መቆጠብን ይመርጣሉ፡፡

የጎልማሳ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸው በጋራም በተናጠልም ከ30 በላይ ኩባንያዎችን እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል፡፡ ይህን ያህል ኩባንያ የፈጠሩት እኝህ ሰው፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብም ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ባገኙት ውርስ የቢዝነሱን ዓለም የተቀላቀሉት አቶ ብዙአየሁ፣ የመጀመርያ ሥራቸው ወላጆቻው ይታወቁበት የነበረውን አነስተኛ የቡና ንግድ  ሥራ  በመጀመር ነበር፡፡ ከ35 ዓመታት በፊት ወደ ቡና ንግድ ሲገቡ ሦስት ሠራተኞችን ይዘው ሲሆን፣ ዛሬ ላይ የፈጠሯቸው በርካታ ኩባንያዎች ከ6,000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል አስገኝተዋል፡፡ ለዓመታት ስለገነቡት የቢዝነስ መጠንና ትልቅነት ይህ ነው በሚባል ደረጃ ሲገልጹ አልታዩም፡፡

 

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተሰናዳ ፕሮግራም ወቅት ግን  የአቶ ብዙአየሁ ሥራዎችንና ማንነት ለማወቅ የሚያስችል አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ስለማንነታቸው ብዙ ያልተነገረላቸው እኚህ ባለሀብት፣ ብዙ ሊባልላቸው ያበቃቸው መድረክ የተፈጠረው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ከአሜሪካው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ያገኙበት አጋጣሚ ነው፡፡ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ከዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ በመሥራት ላይ የሚገኝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ለአገር ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዜጎች ዕውቅና ለመስጠት በራሱ ተነሳሽነት ሰዎችን መልምሎ በሚያደርጋቸው ግምገማዎች አማካይነት አቶ ብዙአየሁ ታደለ አንዱ በመሆን የዓመቱ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንዲያገኙ የመረጣቸው መሆኑን፣ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና ባላደራ ቦርድ አባል ዶ/ር ጂን ሲብል ይፋ አድርገዋል፡፡

የክብር ዶክትሬቱን በዕለቱ ከተገኙት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የቦርድ አመራሮች እንዲሁም በፕሮግራሙ ወቅት በክብር እንግድነት ከተጠሩት የአርብቶ አደሮችና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን እጅ ተቀብለዋል፡፡ አቶ ብዙአየሁን ለዚህ ያበቃቸውን ተግባር የሚገልጸው የግለ ታሪካቸው ረዥም ጉዞ የጀመረው፣ ወታደራዊው ደርግ ሥልጣን ሲቆናጠጥ በተከተለው የርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ያፈሩትን ሀብትና ንብረት በመውረሱ ምክንያት ባዶ እጃቸውን በቀሩበት ወቅት እንደነበር ይጠቅሳል፡፡

በዚህ ቁጭት በመነሳሳትና የተሳካ ሥራ በመሥራት የቤተሰቦቻቸውን ጅምር ሥራ ማስቀጠል እንዳለባቸው በማመን ከአባታቸው በተሰጣቸው መነሻ ካፒታል በአፍላ የወጣትነት ዕድሜያቸው ወደ ግል ንግድ ሥራ እንደተሠማሩ ይኸው ታሪካቸው አስፍሯል፡፡

ወደ ቢዝነሱ ዓለም ሲገቡም ከአባታቸው ሲሰሙ የቆዩትን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከር እንደነበር ዶ/ር ጂን ገልጸዋል፡፡ የአባታቸውም ምክር ‹‹ንፁህ ያልሆነ ገንዘብ ይዘህ ወደ ቤት እንዳትመጣ፡፡ የማታ ማታ ይጎዳሃል፤›› የሚል እንደነበር ስለታሪካቸው ከተወሳው ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ብዙአየሁም ይህንን አባባል አስታውሰው፣ ይህ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር እስከዛሬ አብሯቸው እንደሚኖር በዕለቱ ባረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸውን በማጠናከርና በማሳደግ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ወደ ጎረቤት አገሮች ማለትም ኬንያና ጂቡቲ፣ ከዚያም አልፎ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና ወደ ሲንጋፖር ሲጓዙ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል የነበራቸው ህልም በአገራቸው በማምረቻና በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሰማራት ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ ሥልጣነ መንበሩን የተከበረው መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በውጭና በአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ያፈሩትን ጥሪት በመያዝ የረዥም ጊዜ ህልማቸው የነበረውን የማምረቻና የአግሮ ኢንዱስትሪን ለመቀላቀል አስችሏቸዋል፡፡

 በማኑፋክቸሪንግም ሆነ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ለመሰማራት መድፈር በራሱ ከባድ ውሳኔና ወኔን የሚጠይቅ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ብዙአየሁ፣ ብዙዎች ወዳጆቻቸው አላስፈላጊ ድፍረት ነው በማለት ሲተቿቸውና ሲመክሯቸው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በእርግጥም መስኩ እንደሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች የሚደፈር ባይሆንም እሳቸው ደፍረው በመግባት በኢትዮጵያ በግል ዘርፍ የመጀመርያ የሆነውን የኢንዱስትሪ መንደር በዱከም ገንብተው ለፍሬ እንዲበቃ አድርገዋል፡፡ በዚህ የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ዘጠኝ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን በመገንባት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስኬታማ ሥራ ማከናወናቸው የክቡር ዶክትሬት ለማግኘታቸው አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በወቅቱ በበርካቶች ዘንድ ባልተደፈረውና ላይ ላዩን በሚፈራው ዘርፍ ውስጥ በመግባት ታግለው ማለፋቸው አሁን ለደረሱበት ውጤት አብቅቷቸዋል፡፡

በኢንዱስትሪዎች አማካይነት ሀብትን መፍጠር በሚለው የድርጅታቸው መርኅ መሠረት ፈር ቀዳጅ ለመሆን መብቃታቸው ለዕውቅናው ሌላው አስተዋጽኦ ያደረገ መመዘኛ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከተሰጡት ውስጥ በአገሪቱ ከሚገኙ ትላልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱና ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሀብት የተቋቋመው ናሽናል ሲሚንቶ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበርን በመመሥረትና ፋብሪካውን በመገንባት፣ በአገሪቱ የመጀመርያው መሆኑ የሚነገርለትን ጨዋቃ የሻይ እርሻና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ከማቋቋም ባሻገር በማዕድናት ፍለጋና ምርት ሥራ በመሰማራትና በአገሪቱ የድንጋይ ከሰል አምራችነት በመንቀሳቀስ ረገድ ‹‹ለሌሎች ሀብትን መፍጠር›› በሚለው መርኃቸው ሠራተኞችንም ጭምር የሀብት ተጋሪ የሚያደርጉ ከ17 በላይ የጋራ ኩባንያዎችን መሥርተው ስኬታማ ለመሆን መቻላቸው ተነግሮላቸዋል፡፡ እስካሁን ከደረሱበት ስኬት ባሻገር ወደፊትም ብዙ ለመሠራት እየጣሩ ያሉ ባለሀብት መሆናቸውም ተነግሮላቸዋል፡፡  

እነዚህ ኩባንያዎቻቸው በአሁኑ ወቅት በዓመት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሽያጭ የሚያከናውኑ ሲሆኑ፣ ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ በየወሩ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ደመወዝ ለሠራተኞች መክፈል የቻሉ ኩባንዎችን የመሠረቱ መሆናቸው ሁሉ ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ዕውቅና እንዲሰጣቸው ሚዛን እንዲደፉ ካበቋቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በታክስና ግብር በዓመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ማስገባት መቻላቸውም ተጠቅሷል፡፡

በርካቶች ስለስኬታማ ኩባንያዎቻቸው ቢያውቁም አቶ ብዙአየሁ የኩባንያዎቻቸውን ያህል ታዋቂ አለመሆናቸው ለብዙዎች ግርምት ሆኖ በመድረኩ ሲነገር ተደምጧል፡፡ እሳቸው ግን ይህን መልካም ልማድ የሚከተሉት፣ ድርጅቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ እንጂ የግል ገጽታቸውን መገንባት እንደማያጓጓቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሥራን ማስቀደም፣ በጋራ መጣርና የጋራ እሴት መፍጠር ዋነኛ የኩባንያዎቹ ባህል መሆኑን ማወቅ አለብን፤›› ያሉት አቶ ብዙአየሁ፣ በጋራ ጥረት ያፈሯቸው ኩባንያዎች እንደሆኑም በአጽንኦት ተናግርዋል፡፡

የክብር ዶክትሬታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር መሳረጊያ ላይ ‹‹በውስጤ የተለያዩ ስሜቶች ይመላለሳሉ፡፡ በአንድ በኩል ያገኘሁት ማዕረግ ባለፉት ረዥም ዓመታት በስኬታማነት የደረስኩበትን ደረጃ የሚያመላክት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ዓመታት እዚህ ለመድረስ ያሳለፍኩትን እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች በትውስታ ተመልክቼበታለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ብዙአየሁን ለክብር የጠራው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ከዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 30 ተማሪዎች በዕለቱ በማስመረቅ የትምህርት ማስረጃቻቸውን ከክብር እንግዶቹ እንዲቀበሉ አድርጓል፡፡ ከአቶ ካሳ ተክለብርሃን በተጨማሪ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ይናገር ደሴን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትም በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ታድመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች