Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብርሃንና ሰላም 600 ሚሊዮን ብር የወጣባቸውን ፕሮጀክቶች ለሥራ ዝግጁ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ደርጅት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበቸውን ሦስት ፕሮጀክቶች ቅዳሜ ጥር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሥራ ማብቃቱን ይፋ አረገ፡፡

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በዕለቱ ተገኝተው ፕሮጀክቱን መርቀዋል፡፡ የ95ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በዕለቱ ያከበረው ማተሚያ ደርጅት ለኅትመት ቴክኖሎጂ አካዴሚው ያስገነባቸውን ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃን ጨምሮ በሚስጥራዊ ኅትመት ዘርፍ በአገራችን ቀዳሚ ያደረገውን የቼክ ፐርስናላይዜሽን ፕሮጀክት እንዲሁም ቀደም ብሎ ያስተከለውን ባለስምንት ዩኒት የኅትመት ማሽን አስመርቋል፡፡

በዕለቱ ፕሮጀክቶቹን የመረቁት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ‹‹ድርጅቱ እያደገ የመጣውን  የደንበኞቹን ፍላጎት በማሟላት ለኅትመት ቴክኖሎጂ አካዴሚው ቅድሚያ በመስጠት ኢንዱስትሪውን ማስፋት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም የደንበኞቹን ፍላጎት በበለጠ ለማርካት በዘርፉ ተወዳዳሪ በመሆን መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ አገሪቱ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚጓዝና ጥራት ያለው ኅትመት የሚሰጥ ማተሚያ ቤትም ሆነ ባለሙያ ክፍተትን ለመሸፈንና እንዲሁም ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ ለመድረስ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የኅትመት ቴክኖሎጂ አካዴሚ የድርጅቱን የሰው ኃይል ችግር ከማቃለሉ ባሻገር፣ ለአገራችን ኅትመት ኢንዱስትሪ አልፎም ተርፎ ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሥልጠና ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተካ አባዲ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ተካ ገለጻ፣ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት የቼክ ፐርሰናላይዜሽን ፕሮጀክት የውጭ ምንዛሪ ወጪ ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተመሠረተበትን 95ኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት ለረዥም ዘመን ደንበኞቹና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሠራተኞች ሽልማት አበርክቷል፡፡

ወደ 1,000 የሚሆኑ ሠራተኞች ያሉት ማተሚያ ቤቱ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና መስክ ከደረጃ አንድ እስከ ሦስት ባለው እርከን የኅትመት ቴክኖሎጂ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ እስካሁንም 125 ሠልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም 80 ሠልጣኞችን ተቀብሎ እያሠለጠነ ይገኛል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅታቸውን በቅርቡ በኅትመት አገልግሎት ዋጋ ላይ ቅናሽ ማድረጉን ጠቁመው፣ በተለይ በጋዜጣና በሌሎችም የኅትመት አገልግሎቶች ላይ በየደረጃው ተመሳሳይ ቅናሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

አቶ ተካ ጨምረው ባለፈው ቅዳሜ የተመረቀው የቼክ ፐርሰናላይዜሸን ፕሮጀክት የግዙፉ የሚስጢራዊ ኅትመት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ንዑስ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይኽም ፕሮጀክት በአገር ውስጥ የሚገኙት 19ኙም ባንኮችን ተግባራዊ የተደረገውን አዲሱን ቼክ ፐርሰናላይዝ የማድረግ ሥራ እንደሚያከናውን አስረድተዋል፡፡ ይኽም ሥራ ሙሉ ለሙሉ ኮምፒውተራይዝድ በሆነ ዲጂታል ኅትመት ቴክኖሎጂ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥራውንም ሙሉ ለሙሉ ለመጀመር የብሔራዊ ባንክን እየጠበቁ መሆኑን አቶ ተካ ገልጸዋል፡፡ የመጀመርያው ወጥ ቼክ ኅትመትና ፐርሰናላይዜሽን ከአገር ውጭ እንደተሠራ ጠቁመው፣ በዚህኛው ንዑስ ፕሮጀክት የፐርሰናላይዜሽን ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ መሥራት ያስችላል ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች