Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የስዋዚላንድ ልዑክ በኢትዮጵያ ካባ ላንቃ

ትኩስ ፅሁፎች

ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የአባል አገሮች ጉባኤ ከተገኙት ልዑካን አንዱ ከስዋዚላንድ የመጡ ናቸው፡፡ የለበሱት በወርቅ የተሸለመው ካባ ላንቃ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላገራቸው የተበረከተ መሆኑ ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡

(ፎቶ በዳንኤል ጌታቸው)

*******

የምናብ አፍቃሪ

ላንቺ ያለኝ መውደድ

ላንቺ ያለኝ ፍቅር

አንዳችም ደራሲ

ባነበብኩት መጽሐፍ

ፍፁም አልጻፈውም

በድርሰት ምዕራፍ

የኔን ፍቅር መጠን

የመውደዴን ወሰን

አንዳችም ደራሲ

አይስል በምናቡ

አይነግረውም ልቡ

በቃ..እኔ ማለት..ከተሳለ

ከምናብ ልብ-ወለድ

ከገፀ ባህሪ…በፍቅር ከሚያብድ

ከሁሉም በላይ ነኝ

በብዕር ባልጻፍ

ባይኖረኝም ምዕራፍ

ሕይወት ያለው ድርሰት

የምራመድ መጽሐፍ፡፡

  • አንዱዓለም ጌታቸው ‹‹ዮሬካ›› (2008)

*******

እንዲህም ተብሏል

በአቅማዳ ጆሮ የገባ አዝመራ አይበረክትም፡፡

ወሬኛ የሰፋው ወንፊት ባቄላ ያፈሳል፡፡

በበላህ ገብር በሰማህ መስክር፡፡

ገንፎ እፍፍ ቢሉህ ሊውጡህ ነው፡፡           

ጨረቃ ጥሶ የሚመጣ ዝናም፣ ቆብ ቀዶ የሚመጣ ሰይጣን መመለሻ የለውም፡፡

ሞት ወይስ ሕይወት ይሻልሃል ቢሉት እስቲ ላስብበት አለ፡፡

*******

‹‹ቆላ ባጠፋ ደጋ መወረሩ››

በአፄ ምኒልክ ዘመን ምንይዋብ የጨዋታ ፈላስፋ ነበሩ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን አፄ ምኒልክ›› በቆብ ላይ ልጅ ወልደሃል ሲሉ ሰምቻለሁ ልጅህ የታለ? በማለት ሲጠይቁዋቸው ምንይዋብ በማሾፍ መልክ ‹‹ዝኆን አደን ሄዷል›› በማለት መለሱላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሡ ተናደው ‹‹በጥፊ በሉልኝ›› ብለው በጥፊ አስመቷቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ምንይዋብ ‹‹ምነው የኔታ ምኒልክ ቆላ ባጠፋ ደጋ መወረሩ›› አሉ ይባላል/ብልቴ ባጠፋ ፊቴ መመታቱ ለማለት ነው/፡፡

በዚህ የተነሳ ታዲያ ንጉሡ ወህኒ ቤት አስገቡዋቸው፡፡ ትንሽ ቆይተው ‹‹በስሜ እንጀራ ይብላ›› ብለው ፈቷቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ምንይዋብ በየመኳንንቱ ቤት እየዞሩ ‹‹ስለ ቅዱስ ምኒልክ›› እያሉ ይለምኑ ጀመር፡፡ በዚህ አድራጎታቸው በድጋሚ ተይዘው እንጉሡ ፊት ቀረቡ፡፡ አፄ ምኒልክም ‹‹ምነው አንተ የመኳንንት መሳቂያ አደረግኸኝ?›› ሲሏቸው ‹‹ልማዳችን ስለማርያም ስለአቦ ነበር ነገር ግን ጃንሆይ በስሜ እንጀራ ይብላ ብለውሃል አሉኝ ከዚያ ወዲያ ምን ልበል?›› ብለው ንጉሡን አሳቁአቸው ይባላል፡፡

  • ካሕሣይ ገብረእግዚአብሔር ‹‹ኅብረ-ብዕር ሦስተኛ›› (2009)

*******

‹‹ብሽቅ!››

     ኤደንብራ ውስጥ የሚገኙ የዊቨርሊ ደረጃዎች ነፋስ ይበዛባቸዋል፡፡ ከዓመት ዓመት ያለማቋረጥ ኃይለኛ ነፋስ እንደነፈሰ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንዷ ሴት ወይዘሮ ባቡር ልትሳፈር ተቻኩላ ደረጃዎቹን እየሮጠች ወጥታ ስትጨርስ ነፋሱ ገለባት፡፡ ተናዳ ያያት ሰው መኖሩን ለማወቅ ዞር ብላ ስትመለከት አንዱ ከታች ያጮልቃል፡፡

      ‹‹ወደ ሥራህ ብትሄድ አይሻልህም?!››አለችው በተግሳጽ፡፡

      ‹‹እሺ፣ እሄዳለሁ፤ ግን ትላንትም የለበሽው ይህንኑ የውስጥ ሱሪ ነበር አይደል?›› አላት፡፡

********

አንበሳን ማን ይቀድማል?

     ስኮትላንዳዊውና እንግሊዛዊው ዱር ውስጥ እየተንሸራሸሩ ሳሉ አንበሳ ከፊት ለፊታቸው ሲመጣ አዩ፡፡ ይኼኔ ስኮትላንዳዊው ያደረገውን ትልቅ የቦት ጫማ በፍጥነት አውልቆ ቀለል ያለ ሸራ ጫማ ማጥለቅ ጀመረ፡፡

     ‹‹ይኼ ምን ይጠቅምሃል፣ ወዳጄ?›› አለ እንግሊዛዊው በመገረም፤ ‹‹መቼስ አንበሳን ሮጠህ ማምለጥ አትችልም?››

     ‹‹ልክ ነህ፣ እሱንማ አልቀድመውም፡፡ አንተን ግን እቀድምሃለሁ፤››

  • አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)

*******

አንደበትን አትለጉሚ

አንደበት፣ ነፍስ ዓለምን ለመድረስ እጇን እምትዘረጋበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ቃል ይሆን ይሆናል፤ ዝምታም ይሆን ይሆናል፡፡ በልብሽም በነፍስሽም መናገር አቁሚና አድምጪ፡፡

ምስባክ መድረኩን በቁጥጥርሽ ስር ለማድረግ አትሞክሪ፡፡ ድምፅ የተነፈጉቱ እንዲናገሩ ፍቀጂ፡፡

ነፍሶች ሁሉ እኩል ናቸው፡፡ እኩልነት ማለት፣ ሰዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጦ የልባቸውን እንዲናገሩ ማድረግ ብቻ እንዳይደለ ግን እውቂ፡፡

ይልቅ፣ ልበ-ንፁሃን የሚናገሩ፣ በአዋቂነት ማን-አለብኝነት ጉድፍ ተሸፍኖ በልብሽ ጥልቀት ውስጥ የተደበቀውን የዛ ራስሽን እውነት እንዲሁ በመረዳት፣ እነሱ እልብሽ ውስጥ እንዲቀመጡ መፍቀድ ነው፡፡ አዎን፣ የነሱ አንደበት ያንቺም አንደበት ነው፡፡ ከዚያ ሁሉም ነፍሳት በጋራ ከሚዋኙበት ውቂያኖስ የፈለቀ አንድ ጠብታ፡፡ የራስሽን እውነት የምትይዢውን ያህል ያንንም እንዱያ አጥብቀሽ ያዢው፡፡

ይህ፣ እጅግ ጥልቅ በሆነ ደረጃ ሌሎችን መድረስ፣ ሌሎችም እንዲደርሱሽ መፍቀድ፣ ውሳኔ ሆኖ ሲወለድ፣ በልብሽም በነፍስሽም አክብሪው፡፡ ያ ውሳኔ ያንቺም ውሳኔ ነውና፡፡

የገዛ ልብሽ እንዲናገር ስትፈቅጂም እንዲሁ አድርጊ፣ አዕምሮሽን ዝም አስብዩና አድምጪ፡፡

የሚናወጠውን ባህር ለመግታት ከሞከርሽ፣ በውስጡ አትዋኚበትም፡፡ ትሰጥሚያለሽ፡፡

  • ኦታም ፑልቶ ‹‹የፈላሱ መንገድ›› (2006 ዓ.ም.)
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች