የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. በ2016 የአሜሪካ ምርጫ አሸንፈው የፕሬዚዳንትነቱን መንበር ከመቆናጠጣቸው አስቀድሞ፣ ለስደተኞች ያላቸው አቋም እዚያው በሩቁ ይቅሩብን የሚል ነበር፡፡ በተለይ አሜሪካን ይጎዳሉ፣ ሽብርና ወንጀል ይፈጸማሉ፣ ወግና ባህል ያበላሻሉ የሚሏቸውን ስደተኞች ወደ አገራቸው ከመግባት እንደሚያግዱም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል ገብተዋል፡፡ በወቅቱ ከአገራቸውና ከተለየዩ አገር ባለሥልጣናት የትራምፕ ወግ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን በያዙ በ11ኛ ቀናቸው ሙስሊሞች የሚበዛባቸው ሰባት አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ለጊዜው አግደዋል፡፡
እገዳው ጊዜያዊና ለቀጣዮቹ 90 ቀናት የሚዘልቅ ሲሆን፣ ለቀጣዮቹ አራት ወራት ደግሞ የማንኛውም አገር ስደተኛ በአሜሪካ ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ፕሬዚዳንቱ የኢራን፣ የኢራቅ፣ የሶሪያ፣ የሱዳን፣ የሊቢያ፣ የየመንና የሶማሊያ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ጊዜያዊ ዕገዳ ከመጣላቸውም በተጨማሪ፣ የአሜሪካ ወዳጆችን ጨምሮ ከ38 አገሮች ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የቪዛ እድሳት የሚያቀርቡ ሰዎች በአካል ለቃለ መጠይቅ ያለመገኘት የሚደግፈውን ፕሮግራም ለማገድ ፕሮግራሙ ላይ ክለሳ እንዲደረግ ወስነዋል፡፡ ይኼንን ውሳኔ ያስተላለፉትም የውጭ ዜጎች በአሜሪካ የሚፈጽሙትን ሽብር ለመግታትና ሕዝቡንም ከጭንቅ ለመገላገል እንደሆነ ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
የትራምፕ ውሳኔ ከአሜሪካ ውጭ ተቃውሞ፣ በአሜሪካ ደግሞ ተቃውሞም ድጋፍም ተችሮታል፡፡ ተቃዋሚዎች ተቃውሟቸውን፣ ደጋፊዎች ደስታቸውን ለመግለጽ አውሮፕላን ማረፊያዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ወጥተውም ተስተውለዋል፡፡ አብዛኞቹ የኮንግረስ አባላትም የትራምፕን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡
ለትራምፕ የጉዞ ዕገዳ ይሁንታን የሰጡ የአገሪቱ ዜጎች ለድጋፍ የወጡት፣ ስደተኛን ከመጥላት ወይም አሜሪካዊ ብቻ በአሜሪካ ይኑር ከሚል አመለካከት በመነሳት ሳይሆን፣ አሜሪካ ሰላማዊና ከሽብር የተጠበቀች እንድትሆን የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ለማውጣትና አዲስ አሠራሮችን ለመዘርጋት ጊዜያዊ ዕገዳው ዕድል ይሰጣል ከሚል አመለካከት እንደሆነ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የትራምፕ ውሳኔ ሽብርን ለመዋጋት የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው የሚሉት የ68 ዓመቱ ጡረተኛ፣ ‹‹ማንም ቢሆን ስደተኛን አይጠላም፣ በእነሱ አሜሪካ መኖርም አይበሳጭም፡፡ ሆኖም ራሳችንን መከላከል አለብን፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ድንበራችንን ማስጠበቅና የሕዝባችንን ደኅንነት መጠበቅ አለብን፤›› ያሉ የፍሎሪዳ ነዋሪ፣ ‹‹ትራምፕ ውሳኔውን ያስተላለፈው የእኛን ደኅንነት ለማስጠበቅ ነው፤›› ሲሉ ‹‹ስደተኞችን እንወዳለን፣ የምንወዳቸው ግን የሚወዱንንና ከባህላችንና ከአኗኗር ዘይቤያችን ጋር ተስማምተው የሚኖሩትን ነው፤›› ያሉም አሉ፡፡
ከላቲቪያ ወደ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1989 የተሰደደችው የ43 ዓመቷ ነርስ ሔለን ሚግዲ፣ በወቅቱ የስደተኛ መታወቂያዋን ለማግኘት ወደ ዘጠኝ ወራት እንደፈጀባት አስታውሳ፣ አሁንም ወደ አሜሪካ የሚሰደዱ ሰዎች ተቀባይነት ለማግኘት የተወሰነ ጊዜ ቢጠብቁ ምንም ማለት እንዳልሆነና የትራምፕም ውሳኔ ትክክል መሆኑን ተናግራለች፡፡ ‹‹ከላቲቪያ ወደ አሜሪካ ከረዥም ዓመት በፊት ስደተኛ ሆኜ ተመዝግቤ የገባሁት ሕጋዊ የሆኑ የስደተኛ መሥፈርቶችን አሟልቼ ነው፡፡ ሁሉም ስደተኛ ሕጋዊ መረጃዎችን ተጠቅሞ ወደ አሜሪካ እንዲመጣ እመኛለሁ፤›› ብላለች፡፡
‹አሜሪካ የአሜሪካውያን ብቻ ነች› ስደተኞች በአሜሪካ ለመኖር የሕገ መንግሥት ድጋፍ የላቸውም ያሉም አሉ፡፡ ከኩባውያን ቤተሰቦቹ በአሜሪካ የተወለደው ሮበርት ላስትራ ደግሞ፣ ‹‹በዶናልድ ትራምፕ ድርጊት ደስተኛ ነኝ፡፡ ከሌሎች አገሮች አሜሪካ የሚመጡ ሰዎች በተለያዩ ግዛቶች የሚያደርሱትን ጥቃት፣ ግድያና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ለማየት ችያለሁ፤›› ብሏል፡፡
በጀልባ አቋርጠው በሕገወጥ መንገድ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ለብዙዎች ሥጋት እንደሆኑ በሚነገርባት አሜሪካ፣ የትራምፕን የጉዞ ገደብ ‹‹ጠቃሚና ጊዜያዊ ገደብ›› በማለት ከኮንግረስ አባላቱም የደገፉ አሉ፡፡ ‹‹ትልቁ ቅድሚያችን የአሜሪካን ደኅንነት መጠበቅ ነው፤›› ሲሉ ትራምፕን የደገፉ የኮንግረስ አባላት ተናግረዋል፡፡
ሙስሊሞች አሜሪካ መግባት የለባቸውም በሚለው የትራምፕ ንግግር የሚስማማው የሚዙሪ ነዋሪ፣ ‹‹የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች ከሚመጡባቸው አገሮች ቪዛ የሚጠይቁ ላይ ጠንከር ያለ የጉዞ ምርመራ ቢደረግ እመርጣለሁ፡፡ ትራምፕ ለጊዜው ያገዳቸው የሰባት አገር ዜጎችም መሥፈርቱን ያሟላሉ፤›› ብሏል፡፡
‹‹ከአክራሪዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ገብተናል፡፡ ብሔራዊ ደኅንነታችን አደጋ ላይ ነው፤›› የሚሉት ወግ አጥባቂዎች፣ ዕገዳው ለአጭር ጊዜና መመርያዎች እስኪወጡ ብቻ የሚዘልቅ በመሆኑ ማንንም ሊያስቆጣ አይገባም ብለዋል፡፡ ሆኖም ዴሞክራቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የትራምፕን ውሳኔ ነቅፈውታል፡፡
የትራምፕን ውሳኔ ከነቀፉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የአሜሪካ ተጠባባቂ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሳሊ ያተስ አንዷ ናቸው፡፡ በፕሬዚዳንት ኦባማ ዘመን የተሾሙት ሚስ ያተስ ትራምፕ የሰባቱ አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሲያግዱ፣ የፍትሕ ዲፓርትመንት የሕግ ባለሙያዎች ዕገዳውን እንዳያስፈጽሙ ትዕዛዝ የሰጡ ቀዳሚ ባለሥልጣን ናቸው፡፡ ሆኖም የያትስ ትዕዛዝ የትራምፕን ውሳኔ ተቀባይነት ከማሳጣት ይልቅ ለእሳቸው ለሥራ መባረር ምክንያት ሆኗል፡፡ በያተስ ቦታም የምሥራቅ ቨርጂኒያ አካባቢ ዓቃቤ ሕግ የሆኑት ዳና ቦንቴ ተተክተዋል፡፡ ከዋይት ኃውስ የወጣ መግለጫም ‹‹ሚስ ያተስ ለፍትሕ ክፍሉ ያላትን ታማኝነት አጉድላለች፤›› ብሏል፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ ዲፕሎማቶችና የውጭ አገር ሠራተኞች የትራምፕን ውሳኔ የሚቃወም ረቂቅ እያዘጋጁ ሲሆን፣ ጭብጡም የትራምፕ ውሳኔ አሜሪካን የሚጎዳ፣ አሜሪካዊ ባህል ያልሆነና ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የተሳሳተ መልዕክት ያዘለ በሚሉት ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ ሆኖም የዋይት ኃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ሾን ስፓይሰር፣ ‹‹ዲፕሎማቶች ፕሮግራሙ ሊገባቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
በአሜሪካ ተሰናባች ፕሬዚዳንቶች በተኳቸው ላይ አስተያየት ከመስጠት የተገደቡ በመሆኑ ከኦባማ ምንም ዓይነት አስተያየት ባይሰማም የትራምፕን ስም ሳይጠቅሱ፣ ‹‹አሜሪካ ዋጋ የምትሰጣቸው ጉዳዮች አደጋ ላይ ሲወድቁ፣ አሜሪካውያን ለመሰብሰብ፣ ለመወያየትና የመረጡት ባለሥልጣን ድምፃቸውን እንዲሰማ ለመጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፤› ብለዋል፡፡
በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በተለያዩ ተቋማት ውግዘት የገጠመው የትራምፕ ውሳኔ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አስፈጻሚ አካላትን አወዛግቦ ነበር፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ የሚገኙ ኤርፖርቶች መመርያውን ተግባራዊ ለማድረግ ግራ ተጋብተው ተስተውለዋል፡፡ ትራምፕ ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት የአሜሪካ ቪዛ ያገኙ የውጭ ዜጎች በኤርፖርት ተይዘዋል፣ ታስረዋል፣ እንዲሁም ወደ መጡበት አገር ተመልሰው ተልከዋል፡፡
በኒውዮርክ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ዓለም አቀፍ ኤፖርት ሕጋዊ ቪዛ ይዘው የነበሩ 12 ኢራቃውያን ታስረዋል፡፡ በፊላደልፊያ ደግሞ አሜሪካ ቀድሞ በገባ ቤተሰብ ምክንያት ከሶሪያ የመጡ ስድስት የቤተሰብ አባላት ወደ ኳታር ተመልሰው ሄደዋል፡፡ የአገር ውስጥ ጉዳይ ዲፓርትመንትም ዕገዳ ከተጣለባቸው ሰባት አገሮች ቪዛ ይዘው ወደ አሜሪካ በመምጣት ላይ ያሉትም ሆኑ ያቀዱት አሜሪካ እንደገቡ ሊታሠሩና ወደ መጡበት ሊመለሱ ስለሚችሉ፣ እንዳይመጡ ጠይቋል፡፡
ትራምፕ በኤርፖርቶች በመወሰድ ላይ ያሉ ዕርምጃዎችን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹መንግሥታችን ሙሉ ዝግጅት አድርጓል፡፡ መመርያውም እንደተፈለገው ግቡን እየመታ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ትራምፕ ለአሜሪካ ይጠቅማል በማለት በስደተኞች ላይ ያሳለፉት ውሳኔ በአሜሪካ ላይ የአፀፋ መልስ አስከትሏል፡፡
ኢራቅ የአሜሪካ ዜጎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ስታግድ፣ ኢራን ዕገዳ እንደምትጥል አስታውቃለች፡፡ ኢስላሚክ ስቴትን በመዋጋት የአሜሪካ ቀኝ እጅ የሆነችው ኢራቅ፣ የአሜሪካ ዜጎች አገሯ እንዳይገቡ ማገዷ አይኤስን ለማጥፋት የተፈጠረውን ጥምረትም ያሽመደምደዋል ተብሏል፡፡ አይኤስም መልሶ ለማንሠራራት ዕድል ያገኛል ነው የተባለው፡፡
የሆላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በትራምፕ ውሳኔ ማዘናቸውንና እንደማይቀበሉትም አሳውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማርክ ሩት፣ በሆላንድ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ የትራምፕን ድርጊት እንዲያወግዙ በጠየቁት መሠረት መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹ደቾች ጦርነት ላደቀቃቸውና ጥቃት ለበዛባቸው ሕዝቦች ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ሳይለይ መጠለያ መስጠት አለብን በሚለው ይስማማሉም፤›› ብለዋል፡፡
በአሜሪካ በሰሜን ካሊፎርኒያ በሳንፍራንሲስኮ ቤይ በሚገኘው የቴክኖሎጂና የትልልቅ ኩባንያዎች መናኸሪያ ሲልከን ቫሊ የሚገኙ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች፣ የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ ተቃውሞ አዘል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በየድርጅቶቹ የሚገኙና በዕገዳ መመርያው የሚጎዱ ሠራተኞችንም እንዴት መደገፍ እንዳለባቸው ዕቅድ እያመጡ ነው፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ዋና ኮንትራክተር የሆነው ማይክሮሶፍት ገደቡን ‹‹በቅጡ ያልተመራና ወደኋላ የመመለስ ምልክት፤›› ሲለው፣ አፕል ደግሞ ‹‹የምንደግፈው ፖሊሲ አይደለም፤›› ብሏል፡፡ አማዞን ዕገዳውን እንደማይደግፈው፣ ተቃውሞውን ለማሰማትም አማራጭ ሕጋዊ መንገድ እንደሚያይ ሲገልጽ፣ ሞዚላ ደግሞ ‹‹ቅድመ ታሪክን ያላገናዘበና ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ፤›› ብሎታል፡፡
ቴስላ ፖሊሲው አሜሪካን የሚወዱና ለአሜሪካ የሚሠሩ ብዙ ዜጎችን ይጎዳል፡፡ ፖሊሲው ለእነሱ አይገባም፤›› ሲል፣ ትዊተር ‹‹የሚያበሳጭ››፣ ኢንቴል ደግሞ ‹‹አሜሪካውያን ለሰዎች ይገባል ከሚሉት በደህንነት፣ በተጠበቀና በነፃ የመኖር መብት የተቃረነ፤›› ብሏል፡፡ ኡበር ውሳኔውን ተቃውሞ፣ ከአሜሪካ ውጭ ጭምር ትላልቅ ተሽከርካሪዎችን የሚነዱ ሾፌሮቹ በፖሊሲው ተጎጂ እንደሚሆኑ ገልጿል፡፡ አትላሲያን፣ በክስ፣ ድሮፕቦክስ፣ ጉግል፣ ኢንስታካርት፣ ኒትፍሊክስ፣ ፖስትሜትስ፣ ስላክ፣ ሪዲት፣ ዋይ ከሞባናቶርና ሌሎችም ትልልቅ ኩባንያዎች የትራምፕን ውሳኔ አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡
በተለያዩ ትልልቅ ኩባንያዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ስደተኞች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ሠራተኞቹ አሜሪካን እየጠቀሙ እንጂ እየጎዱ እንደማይገኙ አሳውቀዋል፡፡ ፖሊሲው ደግሞ ከውጭ የሚገቡትን ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ያሉትን ጭምር የሚጎዳ በመሆኑ፣ በኩባንያዎቹም ሆነ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከባድ ነው ይላሉ፡፡ ለትራምፕ ግን ይህ መከራከሪያ አያስኬድም፡፡ ከመነሻቸውም ለሁሉም አሜሪካዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል ግብ በመያዛቸው፣ በክፍት የሥራ ቦታዎች ሥራ አጥ አሜሪካውያን ይገባሉ ብለው ያምናሉ፡፡
የአሜሪካ ሆምላንድ ሴኩሪቲ ዲፓርትመንት እ.ኤ.አ. በ2012 ባወጣው መረጃ 11.4 ሚሊዮን ስደተኞች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ አገባባቸውም ከአሜሪካ መንግሥት ቪዛ ሳያገኙ በድንበር፣ አልያም ደግሞ ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ለሕክምና፣ ለጉብኝትና ለተለየዩ ጉዳዮች የጥቂት ጊዜያት ቪዛ አግኝተው አሜሪካ ገብተው የቀሩና በኋላ አሜሪካ መቅረታቸውን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አቅርበው እንደ ጉዳያቸው ክብደት መኖሪያ ያገኙ ናቸው፡፡ ትራምፕ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ አይስማማቸውም፡፡ በድርጊታቸው ገፍተውበታል፡፡