Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ወደ ዓለም ቅርስነት ለመመለስ የሚያስችል ግምገማ ሊጀመር ነው

  የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ወደ ዓለም ቅርስነት ለመመለስ የሚያስችል ግምገማ ሊጀመር ነው

  ቀን:

  የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አደጋ ላይ ካሉት የተፈጥሮ ቅርሶች መዝገብ ወጥቶ ወደ ዓለም ቅርስነት ለመመለስ በሚያስችል መልኩ መገኘቱ ተገምግሞ፣ ውጤቱ ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እስከ ሰኔ 2009 ዓ.ም. ድረስ እንደሚቀርብ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

  የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ሙሜ እንደገለጹት፣ በፓርኩ ላይ የተከናወኑ የማሻሻያ ሥራዎችን ገምግሞ ውጤቱን የሚያቀርበው የዩኔስኮ ገለልተኛ ልዑክ ሲሆን፣ ሥራው ተገምግሞ ሪፖርቱ እንዲቀርብ የወሰነው ደግሞ የዩኔስኮ ሄሪቴጅ ኮሚቴ ነው፡፡

  ኮሚቴው ውሳኔውን ሊያሳልፍ የቻለው፣ ብሔራዊ ፓርኩን በዓለም አደጋ ላይ ካሉት ቅርሶች አውጥቶ ወደነበረበት የዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት እንዲመለስ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የተከናወኑ ሥራዎች የደረሱበትን ደረጃ በሚገባ ከገመገመ በኋላ ነው፡፡

  ብሔራዊ ፓርኩን በአደጋ ላይ የሚገኝ መዝገብ ለማውጣት የተከናወኑት ተግባራት ዩኔስኮ ባስቀመጠው የአሠራር አቅጣጫ መሠረት መሆናቸውን ኮሚቴው ከመገንዘቡም ባሻገር፣ ከአፍሪካ ጥብቅ ቦታዎች አብዛኞቹ ከተለያዩ ዓይነት ጫናዎች የፀዱ ስላልሆኑ አገሪቱ የሄደችበት አግባብ በምርጥ ተሞክሮ እንዲቀመጥ መወሰኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

  ዩኔስኮ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከተተገበሩት ሥራዎች መካከል የሥነ ምህዳሩን መጎሳቆል ለመቀነስ የፓርኩን ድንበር የማካለል፣ ተጨማሪ ቦታን በማካተት የእንስሳትን ቁጥር እንዲጨምር የማድረግ ሥራ፣ በፓርኩ ዙሪያ የሚገኙትን የገጭ መንደር ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ማስፈርና መልሶ ማቋቋም ይገኙበታል፡፡ በዚህም መሠረት ራስ ዳሸንና ሊማሊሞ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፈው 65 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ አቅጣጫን ከነኤሌክትሪክ መስመሩ የማስቀየር ሥራ ተከናውኗል፡፡

  የእንስሳቱ በተለይ የቀይ ቀበሮ፣ የዋልያና የጭላዳ ዝንጀሮ ቁጥር እንዲጨምር የማድረጉ ሥራ ከተከናውነት ዋና ዋና ተግባራት እንደሚካተቱ፣ ከዚህ አኳያ ቀደም ሲል 250 ብቻ የነበረው የዋልያ ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ከ900 በላይ ሲሆን የጭላዳ ዝንጀሮዎች ከ26 ሺሕ በላይ መድረሳቸውንና ሌሎቹም በተመሳሳይ መልኩ ቁጥራቸው ማደጉን ተናግረዋል፡፡

  የዱር እንስሳቱን መኖሪያና አካባቢያቸውን ከተለያዩ ሰው ሠራሽ ችግሮች የመከላከል ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የግጦሽ ጫና ስትራቴጂም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

  እንደ አቶ ዳውድ የመንደሩ ነዋሪ የሆኑ 418 አባወራዎችና እማወራዎችን በደባርቅ ከተማ ሰፍረው ኑሮዋቸውን እየመሩ ነው፡፡ ለነዋሪዎቹም 257 ሚሊዮን 96 ሺሕ ብር ካሳ ተከፍሏቸዋል፡፡ ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ የሚውል በነፍስ ወከፍ 250 ካሬ ሜትር በጥቅል ደግሞ 12 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በነፃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

  የእምነት ተቋማት መሥሪያ የሚሆን ቦታም የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለመኖሪያ ቤትና ለእምነት ተቋማት መሥሪያ የሆነውን መሬት በነፃ ያቀረበው የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡

  በከተማው የአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ዋጋ 300 ብር ሲሆን  በ12 ሺሕ ሜትር ካሬ ሲሰላ 40 ሚሊዮን 200 ሺሕ ብር የከተማው አስተዳደር እንዳበረከተ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

  የመልሶ ማቋቋም ሥራው የተከናወነው በሰዎቹ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ፣ በገለልተኛ ወገን ተጠንቶና የዓለም ባንክና የአውሮፓ ኅብረት ያዘጋጁትን ዓለም አቀፍ የመልሶ ማቋቋም መመሪያ ባሟላ መልኩ መሆኑም ተገልጿል፡፡

  የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኝና ራስ ዳሸን ተራራን ጨምሮ የሰሜን ተራሮችን ያካተተ ነው፡፡ በ1951 ዓ.ም. የተመሠረተው ብሔራዊ ፓርኩ በ1970 ዓ.ም. የዓለም ቅርስ ሆኖ ቢመዘገብም፣ ከ1988 ዓ.ም. ወዲህ በአደጋ ላይ ያሉ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img