Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበራስ ጉዳይ ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ ለምን?

በራስ ጉዳይ ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ ለምን?

ቀን:

በቅርቡ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት ሲጠበቅ የነበረው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ እንደማይካሄድ ድንገት ሲታወቅ ግራ ከማጋባት አልፎ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በራሱ ጉዳይ ባዕድ የሆነበትና ፊፋ በኢትዮጵያ ሊያካሂድ ያቀደው ስብሰባ ተሰርዞ በደቡብ አፍሪካ እንዲካሄድ የተወሰነበት ምክንያት ደግሞ ይበልጡን አነጋጋሪና አስተዛዛቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ከየካቲት 13 እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ለፊፋ ጉባኤ ታዳሚዎች ማረፊያና የጉባኤ ማካሄድ እንዲሆን የታቀደውን ሸራተን አዲስ፣ ጉባኤው በሚካሄድባቸው ቀናት በአንደኛው ዕለት ሌሎች እንግዶች ስላሉበት የፊፋውን ጉባኤ ለማስተናገድ እንደሚቸግረው በማሳወቁ ምክንያት ፊፋ የስብሰባው ቦታ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲቀየር መደረጉ የሆቴሉ የመስተንግዶ ክፍል ኃላፊ አቶ ጌታቸው መለሰ ይናገራሉ፡፡ እንደ ኃላፊው ፊፋ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ለማካሄድ ሲያቅድ ኅዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሸራተን አዲስ የመጀመርያውን የኢሜይል መልዕክት መላኩንና ሆቴሉም ከተጠቀሱት ቀናት መካከል የካቲት 14 ቀን ጉባኤውን ማካሄድ የተመረጠው የላሊበላ ሬስቶራንት ቅድሚያ በጠየቁ ሌሎች እንግዶች የተያዘ መሆኑን በመግለጽ መልስ ሰጥቷል፡፡ ከዚያ በኋላም ፊፋና ሸራተን አዲስ አማራጮችን ለማመቻቸት ተደጋጋሚ የኢሚይል መልዕክቶችን እንደተለዋወጡ ያከሉት አቶ ጌታቸው፣ ይኼ ሁሉ ሲሆን በቀጥታ የሚመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሸራተን አዲስ ጋር ተገናኝቶ በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ሙከራ አለማድረጉን ነው ያስረዱት፡፡

ከፊፋ ጋር የዕለት ተዕለት ግንኙነት እንዳለው የሚታወቀው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፊፋ ላከልኝ ያለውን ማብራሪያ ‹‹ፊፋ የአዲስ አበባውን ስብሰባ ያዛወረበትን ምክንያት አስታወቀ›› በሚል እንዳስታወቀው፣ በፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋትማ ሳሙራ ተፈርሞ በላከው ይፋዊ ደብዳቤ መሠረት የፊፋው ስብሰባ ወደ ጆሀንስበርግ እንዲዛወር የተወሰነው የፊፋ ምርጫ በሆነው ሸራተን አዲስ ስብሳበውን ለማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ፣ ፊፋና ሸራተን መግባባት ላይ ሊደርሱ ባለመቻላቸው ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ፊፋ በአዲስ አበባ ሊያካሂደው የነበረው ይህ ስብሰባ መሰረዙን አስመልክቶ ሪፖርተር  በጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕትሙ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ጠቅሶ ፊፋ የአዲስ አበባውን ጉባኤ ለምን እንደሰረዘ ለፌዴሬሽኑ ያሳወቀው ነገር እንደሌለ መናገራቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ይሁንና የስብሰባው ትልቅነት ግን ይህንን ምክንያት ‹‹አያያዙን አይተህ የያዘውን ቀማው›› የሚለውን የአበው ብሂል ያስታውሳል የሚሉት አንድ ባለሙያ የጉዳዩ ባለቤት እንደሆነ የሚታወቀው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሁሉ ነገር ካበቃ በኋላ ሸራተንና ፊፋ ስላልተስማሙ የስብሰባው ቦታ ተቀይሯል የማለቱ ተገቢነት የተቋሙን መሪዎችና የመሪነት አቅማቸውን ጭምር ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለስብሰባው የሚመጡት ዓለም አቀፉን እግር ኳስ የሚመሩ ትልልቅ እንግዶች መሆናቸው እየታወቀና በተጨማሪም የስብሰባው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለቱሪዝም ዘርፍና ለሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰጠው ፈርጀ ብዙ ጥቅም ሆኖ ሳለ፣ ስብሰባው በሸራተን ምክንያት ‹‹ሊካሄድ አልቻለም›› መባሉ ‹‹የጉዳዩ ባለቤት ነኝ›› ከሚል ተቋም የማይጠበቅ ስለመሆኑ ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሸራተን ጉዳይ ሌሎችን ተጠያቂ ማድረጉ ያልተዋጠላቸው የሸራተን አዲስ የመስተንግዶ ክፍል ኃላፊ አቶ ጌታቸው፣ ፊፋና ሸራተን አዲስ ጉባኤው የሚካሄድባቸውን ቀናት አስመልክቶ በተለዋወጡባቸው በእያንዳንዱ የኢሜይል መልዕክት የአንዷ ቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሆቴሉ ሌሎች አማራጮችን ጨምሮ የፊፋን እንግዶች ለማስተናገድ ሙሉ ፍላጎት እንደነበረውም ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው አያይዘውም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለዚህ ጉዳይ ‹‹ባይተዋር›› መሆን እንዳልነበረበት ይልቁንም ‹‹ጉዳዩን ጉዳዬ ነው›› ብሎ ሸራተን አዲስ የቢዝነስ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን በፊፋና በሆቴሉ መካከል በነገሮች አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን ሌሎች አማራጮች እንዳሉ የመጠቆምና  የማግባባት ሥራ መሥራት የፌዴሬሽኑ ብቻና ብቻ  መሆኑን ጭምር ነው ያስረዱት፡፡

ፊፋ በአዲስ አበባ ለማካሄድ አቅዶ የነበረውን ጉባኤ ለምን እንደሰረዘ ፌዴሬሽኑ ፊፋ አሳወቀኝ ከማለቱ በፊት የጉዳዩ ባቤት እንደመሆኑ ሒደቱን መከታተል አልነበረበትም ወይ? ፊፋና ሸራተን የሆቴሉን ጉዳይ አስመልክቶ ግንኙነት የጀመሩት አስቀድሞ መሆኑ ሁለቱ አካላት ከተለዋወጧቸው የኢሜይል መልዕክቶች መረዳት ተችሏል፡፡ በዚህ መሀል ፌዴሬሽኑና ፊፋ የጉባኤውን ሒደት አስመልክቶ መልዕክት እንዴት ሳይለዋወጡ ቆዩ? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ምንም ዓይነት መግለጫ እንደማይሰጥ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ አቶ ወንድምኩን ሁለቱ አካላት በየበኩላቸው እየሄዱበት ነው ብለው ዝርዝሩን ከመናገር ግን ተቆጥበዋል፡፡

ስለጉዳዩ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ፊፋ ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ለማከናወን ዕቅድ እንዳለው ፌዴሬሽኑ የሚያውቀው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ጉባኤው እንዴትና በምን አግባብ ሊካሄድ እንደታሰበ ተከታታይነት ያለው መረጃ መለዋወጥ የተቋሙ የቅድሚያ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ መታወቅ ነበረበት ብለው አሁን ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂነቱን ፌዴሬሽኑ ሊወስድ እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...