Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ገበያ አለመናበብ ለአገሪቱ የቡና ኤክስፖርት ንግድ አለማደግ አንዱ ምክንያት ነው››

 አቶ ሳኒ ረዲ፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

አቶ ሳኒ ረዲ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ አቶ ሳኒ ረዲ ከኮተቤ ኮሌጅ በሒሳብ በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል፡፡ በሥራው ዓለም በደቡብ ክልል ከወረዳ ጀምሮ ባሉ መዋቅሮች በአመራር ደረጃ ሠርተዋል፡፡ የወረዳና የዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የስልጤ ዞን አስተዳዳሪ፣ በደቡብ ክልል የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ፣ ከዚያም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን እየሠሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የቡና ልማትና ግብይት በተለይም ቡናን በሚመለከቱ መንግሥታዊ መዋቅሮችና የባለሥልጣኑን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አሁን እንደ አዲስ እንዲቋቋም ከመደረጉ ቀደም ብሎ የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ነገር ፈረሰ፡፡  አሁን ደግሞ መልሶ እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ ይህ ባለሥልጣን መጀመርያ ለምን ፈረሰ? አሁንስ እንደ አዲስ እንዲቋቋም ለምን ተፈለገ?

አቶ ሳኒ፡- ታሪካዊ አመጣጡን ስናየው ቡና ቀድመን ወደ ዓለም ገበያ የገባንበት ምርት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የቡና መገኛ አገር ከመሆናችን ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና በጣዕሙም ተወዳጅነት ያለው ነው፡፡ ተፈላጊም ነው፡፡ ቡና ለማልማትና ለማገበያየት የሚያስችል ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ተቋም በንጉሡ ጊዜ በቦርድ ደረጃ የተቋቋመ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ባለሥልጣን ደረጃ ከፍ አለ፡፡ በኋላም የደርግ የዕዝ ኢኮኖሚ በገነነባቸው ዓመታት ከባለሥልጣን ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትነት ደረጃ ተሸጋግሮ ሲመራ የነበረ ተቋም ነው፡፡ በኋላም ቡና ልማቱንና ግብይቱን ከሌሎች የግብርና ምርቶች ጋር አንድ ላይ መምራት ተገቢ መሆኑ በወቅቱ ስለታመነበት፣ በግብርና ሚኒስቴር ሥር እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ በግብርና ሚኒስቴር ሥርም በተለያዩ አደረጃጀቶች ያለፈ ነው፡፡ በመጨረሻ በ2001 ዓ.ም. አካባቢ ኤክስቴንሽኑ ከሌሎች ልማት ዘርፎች ጋር ተዋህዶ ሲመራ ነበር፡፡ ግብዓቱና ግብይቱ በሚኒስቴር ዴኤታ ደረጃ በግብርና ምርቶች ግብይትና ግብዓት ዘርፍ ተደራጅቶ ሲመራ ነበር፡፡ በ2003 ዓ.ም. ደግሞ የበለጠ ውጤታማ የሆነ የግብርና ምርቶች የግብይት ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ በመሆኑና ከሌሎች የንግድ ሥራዎች ጋር መቀናጀት አለበት ተብሎ ስለተወሰነ፣ የግብርና ምርቶች ዘርፍ ሆኖ ወደ ንግድ ሚኒስቴር ተዛወረ፡፡ ልማቱም በግብርና ሚኒስቴር እንዲቆይ ተደረገ፡፡

አሁን ደግሞ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ሲገመገም በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ያለውን አቅም በተሻለ ደረጃ በማልማት በዚህ ዘርፍ ያሉትን አርሶ አደሮችንና የግብይት ተዋንያኑን ተጠቃሚ በማድረግ፣ ለግብርናውም ሆነ ለሌሎች የኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዕድገት የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ በማመንጨት ረገድ የተሻለ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም በግብይት ሒደቱ የነበሩ ተዋናዮችም የግብይት ሥርዓቱን በመምራትና ከልማቱ ጋር በማስተሳሰር የሚደግፍ አካል ያስፈልጋል የሚል ጥያቄም ነበራቸው፡፡ ይህ ጥያቄም እንደ ግብዓት ተወስዷል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከዘርፉ የሚጠቀበውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የማመንጨትም ይሁን በዘርፉ ያሉ ተዋንያን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል፣ ልማቱንም ግብይቱንም የሚመራ አንድ ተቋም ማደራጀት እንደሚገባ ስለታመነበት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 364 በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. ሊቋቋም ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለሥልጣኑ ከተቋቋመ በኋላ በዘርፉ ምን ለውጥ አመጣ የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዋናነት ግን በቡና ልማት ግብይት ውስጥ ትልቁ ችግር ሆኖ የሚነሳው ቡናን  የሚመለከቱ መሥሪያ ቤቶች መብዛት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንና ንግድ ሚኒስቴር እያለ ሰባት ስምንት መሥሪያ ቤቶችን መጥራት ይቻላል እናንተም አላችሁ፡፡ ይህ ቡናን የተመለከተ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መብዛት ዘርፉን ጎድቶታል ይባላል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን አስፈለገ? አንድ ተቋም አይበቃም?  

አቶ ሳኒ፡- በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ አንድ ዘመን በአጠቃላይ የግብርና ምርቶች ግብይትን ይመራ የነበረው ንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ አንተ እንዳነሳኸው ከአርሶ አደሩ የመጀመርያ ግብይት ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት መዳረሻ ድረስ ያለው የግብይት ሒደት ይመራ የነበረው በንግድ ሚኒስቴር ሥር ባሉ ተቋማትና በንግድ ሚኒስቴር በራሱ ነው፡፡ ከአርሶ አደሩ እስከ ግብርና ምርቶች የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት ድረስ ያለውን ግብይት ሲመራ የነበረውም ንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ በአቅራቢዎች የተዘጋጀውን ቡና ተረክቦ ደረጃ አውጥቶ ለኤክስፖርተሮች ያስረክብ የነበረው የግብርና ምርቶች የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ እንዲሁም አቅራቢዎችና ላኪዎችን በአንድ የግብይት መድረክ በማገናኘት ሕጋዊና ዘመናዊ የግብይት ሥራ እየሠራ የቆየው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነው፡፡ እሱም ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ ሁለቱን ተቋማት እንደተቆጣጣሪ ሆኖ የሚመራው ደግሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ነው፡፡ ይህም ባለሥልጣን ቢሆን ለተወሰነ ጊዜ ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር ነበር፡፡ በኋላ ላይ እንደ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲያድግና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እንግዲህ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኋላ ያለውን ኤክስፖርት ማዘጋጀትና ኤክስፖርቱን የመምራቱን ሥራ የሚወስደው የንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ በእርግጥ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሽኝትና የቁጥጥር ሥራውን ይሠራል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁ ኮንትራት የመመዝገብና የማስተዳደር ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በኋላ የመጣው ሐሳብ የቡና ልማቱና ግብይቱ ተሳስረውና ተመጋግበው ባለመመራታቸው ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ እያደጉ አይደለም የሚል ግምገማ ላይ ተደረሰ፡፡ ለምሳሌ በቡና ልማት ረገድ ከዓለም ትልቋ አምራች ብራዚል ናት፡፡ ሁለተኛዋ ቬትናም ነች፡፡ ከእነሱ አንፃር ሲታይ ገና ነን፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን ቬትናም ከኢትዮጵያ በኋላ ቡና መላክ ጀምራ ነው እዚህ የደረሰችው፡፡

አቶ ሳኒ፡- አዎ፡፡ ቬትናም በዓመት 1.5 ሚሊዮን ቶን ነው ኤስክፖርት የምታደርገው፡፡ የኢትዮጵያ ወደ ሁለት መቶ ሺሕ ቶን ነው፡፡ በኢትዮጵያ በእርግጥ ካመረትነው ቡና ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን እዚሁ እንጠቀማለን፡፡ የቡና ልማቱ የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም በውጭ ምንዛሪ ላይ ግን የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ይህንን ያህል አቅም እያለን ለምንድነው ልማቱ ያላደገው? ስንል ግብይቱ ያበረከተው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ አርሶ አደሩ በአንድ በኩል ባለቤት ሆኖ የሚደግፈው ተቋምና አደረጃጀት ባለመኖሩ ምክንያት ተደራሽነት ያለው ተገቢ የሆነ የኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ ጥራት፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦት አላገኘም፡፡ በዚህም ምክንያት ምርታማነቱ አነስተኛ ነው፡፡ ሁለተኛ ለተመረተው ቡና ፍትሐዊ የሆነ ዋጋ በማግኘት ረገድም ችግሮች ነበሩ፡፡ ስለዚህ አምራቹ ምርታማነቱን እንዲያሳድግና የማሳ መጠኑን እንዲያሰፋ የሚያበረታታው የግብይት ሥርዓት፣ ለላቡና ለወዙ የሚከፈለው ግብይት ሥርዓት ፍትሐዊና ሕጋዊ በመገንባት ረገድ በበቂ ደረጃ አልሄድንበትም፡፡ ስለዚህ ልማቱና ግብይቱ እየተመጋገቡ የሚሄዱ እንደመሆናቸው መጠን ቡና ካለው ተፈጥሯዊ ባህሪ አኳያ ልማቱንና ግብይቱን አንድ ላይ የሚመራ ተቋም አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዘመናዊ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት እንዲያረጋግጥ በዚህም ምርታማነቱን፤ ጥራትንና ዘመናዊ ግብይትን ለማረጋገጥ ተልዕኮ ወስዷል፡፡ ሁለተኛ ዘመናዊ፣ ፍትሕዊና ሕጋዊ የግብይት ሥርዓትን መገንባት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዘመናዊና ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት መገንባት የሚለው ጉዳይ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ዘመናዊና ፍትሐዊ ሲባል እንዴት የሚሠራ ነው? ምንስ ያጠቃልላል?

አቶ ሳኒ፡- ዘመናዊ ስንል ሰንሰለቱ አጭር መሆን አለበት፡፡ አሁንም ከአሥር በላይ የሚሆኑ በቡና ግብይት ሒደት ላይ የሚሳተፉ አካላት አሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከምርት እስከ ኤክስፖርት ድረስ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ማለት ነው?

አቶ ሳኒ፡- አዎ፡፡ እነዚህ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ድርሻ ይወስዳሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ሰንሰለት መቀነስ አለበት፡፡ ሁለተኛ ወጪ ቆጣቢና በአነስተኛ ጊዜና ወጪ የሚካሄድ ግብይት መኖር አለበት፡፡ ከአርሶ አደሩ እስከ ኤክስፖርት መዳረሻ ያለው  የማጠብ፣ የመቀሸር፣ የማገበያየትና የማጓጓዙን ሒደት ስናየው ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪም የሚያስከትል ነው፡፡ ይኼም መስተካከል አለበት፡፡ ሦስተኛ ከግብይቱ አኳያ ፍትሕዊ መሆን አለበት፡፡ ከአምራቹ እስከ ኤክስፖርተሩ ድረስ ባለው ሒደት የሚሳተፉ አካላት እንደ አስተዋጽኦዋቸው ቡና ከሚያስገኘው ገቢ ሊደርሳቸው ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ የቡና ቀጣይነት ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ በእኛ አገር ደረጃ አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጎጂ ነው፡፡ እኛን የሚወዳደሩት እንደነ ብራዚል፣ ኮሎምቢያና ቬትናም ያሉ አገሮች የውጭ  ገበያ ከሚከፍለው ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ ይደርሳል፡፡ እኛ ጋ ግን አነስተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለቡና የውጭ ገበያ ከሚከፍለው ዋጋ የኢትዮጵያ አምራቾች ምን ያህል ይደርሳቸዋል?

አቶ ሳኒ፡- ከ35 እስከ 40 በመቶ ቢሆን ነው፡፡  ሌላው በሙሉ ከአርሶ አደሩ በላይ ያሉት የግብይት ሰንሰለቱ ተሳታፊ አካላት የሚቀራመቱት ነው፡፡ ዋናውን ለግብርና (ለቡና) ልማት ዕድገትም ሆነ ለቀጣይነት አርሶ አደሩ ትልቅ ድርሻ የሚገባውና የተጠቃሚነቱን ድርሻ መውሰድ የሚገባው አርሶ አደሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ከፍትሐዊነት አንፃር ብዙ መሠራት የሚጠብቀው ነው፡፡ ሌላው በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በግብዓት ተዋንያን ዘንድ መተማመን መፈጠር አለበት፡፡ እርስ በርስ መተሳሰብ መኖር አለበት፡፡ በእኛ ሁኔታ ሲታይ የቡና ዘርፍ ለበርካታ ሕገወጥ ንግድና ዝውውር የተጋለጠ ነው፡፡ ይኼም የሆነበት ምክንያት ወጥ በሆነ መንገድ ሒደቱን ተከታትሎ ራሱን ችሎ የሚመራ ተቋም ባለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ምክንያት ታምኖበት ቡናና  ሻይ ባለሥልጣን ተደራጅቷል፡፡ እንግዲህ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሲደራጅ የግብይት ሥርዓቱንም የመገንባት ተልዕኮ ወስዷል ማለት ነው፡፡ ሦስተኛ እሴት ለሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎች የግብርና ምርቶችን ማምረት ብቻ ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ እሴት ጨምሮ በተሻለ ዋጋ በመሸጥ የዘርፉ ተዋንያንን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል፡፡ አገሪቷንም ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህንን ሥራ በማከናወን ሒደት ላይ አሁን ያሉት ተቋማት አሉ? የሉም? ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይህንን ሁሉ ተልዕኮ ይወስዳል? አይወስድም የሚለው ጥያቄ ይደመጣል፡፡ ቀድሞ የነበሩት ተቋማት አሉ፡፡ በጋራ እየሠራን ነው፡፡ እነዚህን ሥራዎች የሚሠሩ ተቋማት ተጠሪነታቸው በሚኒስቴር ደረጃ ለሦስት አካላት ነው፡፡ ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ለንግድ ሚኒስቴርና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ እነዚህን ተቋማት ለማቀናጀት የሚያስችል ወደፊት የሕግ ማሻሻያ ተጠንቶ እስኪካሄድ ድረስ፣ የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ተደራጅቶ እየሠራ ነው፡፡ የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት አገልግሎት የሚሰጠው ለቡና ብቻ አይደለም፡፡ ለሰሊጥ፣ ለጥራጥሬና ለሌሎችም ነው፡፡ ወደፊትም የሚጨመሩ ይኖራሉ፡፡ የምርት ገበያውም ቢሆን የሚያገበያየው ቡና ብቻ አይደለም፡፡ ወደፊት ግን ቡና ራሱን ችሎ በእነዚህ ተቋማት እንዴት ሊመራ ይችላል? የሚለው በጥናት እስኪወሰን ድረስ የማስተባበር ተልዕኮ የተሰጠው ጊዜያዊ ኮሚቴም አለ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመ የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላ ኮሚቴ ማለት ነው? ይህንንስ ኮሚቴ የሚመራው ማነው? 

አቶ ሳኒ፡- የንግድ ሚኒስትሩ ይመሩታል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አባል ናቸው፡፡ የምርት ገበያ ባለሥልጣንና የምርት ገበያውን የመጋዘን አገልግሎት ድርጅትን የሚመሩት የቦርድ ሰብሳቢዎች አባል ናቸው፡፡ የእነዚህ ተቋማት ኃላፊዎችም አባል ናቸው፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በጸሐፊነት ያገለግላል፡፡ ስለዚህ የቅንጅት ሥራውን የሚያቀላጥፍ የሚያደርግ ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴው እስከ መቼ እንደሚቀጥል በሒደት አሠራራችን ግልጽ አድርገን ቡና ከልማት እስከ ግብይት ራሱን ችሎ እንዲመራ በተወሰነው አግባብ ይሄዳል? ወይስ አሁን ባለው አደረጃጀት የተሻለ ቅንጅት ፈጥሮ ይሄዳል? የሚለው ይታያል፡፡ በነገራችን ላይ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም የዚህ ኮሚቴ አባል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ አሁንም ቡና ጉዳይ የሚረግጥበት ቦታ መብዛቱን ነው የሚያሳየው፡፡ ከቡና ጋር የተያያዙ መሥሪያ ቤቶች እዚህም እዚያም አሉ፡፡ በቡና ግብይቱ ላይ እንዳለው ረዥም ሰንሰለት ሁሉ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም በቡና ጉዳይ የሚወስኑ ወይም ያገባናል የሚሉ መሥሪያ ቤቶች ስለመብዛታቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከሚሆን ቡናን የተመለከተ አንድ ተቋም መፍጠር ለምን አልቻለም?

አቶ ሳኒ፡- እንግዲህ የግብይት ሥርዓቱን ከማሳጠር፣ በአነስተኛ ወጪና ጊዜ እንዲሠራ ከማድረግ አኳያ ተቃኝቶ ወደፊት በጥናት ይመለሳል፡፡ እስከዚያ ድረስ የቅንጅት አሠራር ያስፈልጋል ነው የተባለው፡፡

ሪፖርተር፡- የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያስፈልጋል ተብሎ ከተቋቋመ በኋላ በተጨባጭ የተሠራው ሥራ ምንድነው? በእርግጥ  ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በቡና ግብይቱ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮች አሉና ችግሮቹን ከመቅረፍ አኳያ ምን አድርጋችኋል?

አቶ ሳኒ፡- የባለሥልጣኑን ተልዕኮ በሁለት መንገድ ማየት እንችላለን፡፡ ራሱን እስከ ቀበሌ ድረስ የማደራጀቱ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ተመሳሳይ ባለሥልጣኖች ተደራጅተዋል፡፡ እስከ ወረዳ ድረስ ራሳቸውን ችለው ጽሐፈት ቤቶች አደራጅተው እየሠሩ ነው፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራና በጋምቤላ ክልሎች ቡና አምራችና አብቃይ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የቡናን ጉዳይ የሚመለከት በሥራ ሒደት የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ለመዋቅሩ የሚያስፈልግ የሰው ኃይል የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የቡና ልማቱን ምርታማነትና ጥራት ማሻሻል ወሳኝ በመሆኑ፣ ቀድሞ የነበረውን የቡና ስትራቴጂ የማሻሻል ሥራ ተሠርቷል፡፡ የቡና ምርምር ስትራቴጂ ከምርምር ተቋማትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካለት ጋር ሆኖ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጀማሪና ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ካላቸው አገሮች ጋር የሚወዳደር በመሆኑ፣ እነዚህ አገሮች ቀድመው የደረሱበትን የምርታማነት ደረጃ መድረስ የግድ ነው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ አገሮች ተሞክሮ ወስደናል፡፡ በተለይ የብራዚልና የኮሎምቢያን ወስደናል፡፡ በቅመማ ቅመም ውጤታማ የሆኑ አገሮችን ተሞክሮ ወስደን ፓኬጁን አዳብረናል፡፡ ምርታማነቱንና የምርት ጥራቱን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ፓኬጅ ጉድለቱን አሟልተን ለእያንዳንዱ ቀበሌ ለሚመደብ ባለሙያ በአማርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች ተሰራጭቷል፡፡ በዚህ ፓኬጅ ላይ ለፌዴራል፣ ለክልልና ለወረዳ ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት እንሰጣለን፡፡ ሁለተኛው የተሠራው ነገር ገበያውን ማዘመን፣ ፍትሐዊና ሕጋዊ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለሥልጣኑ ከተቋቋመ በኋላ ሁለት ዙር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ ከአምራች አርሶ አደሮች፣ ከወረዳ ባለሙያዎች፣ ከአቅራቢዎች፣ ከቡና ላኪዎች፣ ቡና ከማገዙ የውጭ ኩባንያ ተወካዮች፣ እንዲሁም በቡና ምርምር ሥራ ላይ ከነበሩ ተመራማሪዎችና የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በሁለት ዙር መድረክ ፈጥረን ተነጋግረናል፡፡

ሪፖርተር፡- በእነዚህ መድረኮች ላይ በአገሪቱ የቡና ልማትና ግብይት ውስጥ ያሉት ችግሮች ቀርበው እንደነበረ ይታወሳል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ተችሏል? በአጠቃላይ ምክክሩ ያስገኘው ውጤት ምን ነበር?

አቶ ሳኒ፡- በቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች ምን ዕድል አለ? ምንስ ተግዳሮቶች አሉ? እነዚህን ተግዳሮቶች በምን መንገድ ነው ልንፈታ የምንችለው? ከእያንዳንዱ ባለድርሻ ምን ይጠበቃል? የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተወያይተን በጋራ የተስማማንባቸውንና መሠረታዊ ናቸው ያልናቸውን ማነቆዎች ለይተን፣ ለማነቆዎቹ ደግሞ መፍትሔና ባለቤት አስቀምጠን ወደ ተግባር ገብተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት መፍትሔ?

አቶ ሳኒ፡- ከባለቤቶቹ አንደኛ አርሶ አደሩ ነው፡፡ ከዚያም አቅራቢዎች፣ የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት፣ ምርት ገበያ፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ እንዲሁም ጉዳዩ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥን የሚመለከት በመሆኑ ንግድ ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኤስክፖርተሮች፣ የኤክስፖርት ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ከእያንዳንዳቸው ጋር በተልኳቸው ላይ ውይይት አድርገን ተግባብተንና የሚፈምበት የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠን ወደ ተግባር እያመራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ ምን ነበር? ተግባብተን እየሠራንበት ነው ያሉትስ ምንድነው?

አቶ ሳኒ፡- ከአርሶ አደሩ አኳያ የምርት ጥራት ችግር መኖሩ አንዱ ነው፡፡ ልማቱ በራሱ ጊዜ የሚሄድ ነው፡፡ ከግብይት አኳያ የቡና ጥራት የሚጀምረው ከአርሶ አደሩ ነው፡፡ ከለቃሚው ነው፡፡ ለገበያ ከሚያቀርብበት ዕቃ ጀምሮ ነው፡፡ እነዚህን በማሻሻል ጥራት ያለው ቡና አቅርቦት በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ ማድረግ ነው፡፡ ተግባብቶ ነው የሚሠራው፡፡ ቡና አዘጋጅ ኢንዱስትሪዎችም የሚያዘጋጁት ቡና በምን ዓይነት የጥራት ደረጃ ማዘጋጀት እንዳለባቸው፣ የክህሎትና የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው ግንዛቤ ተወስዶ ሥልጠና የሰጠ ነው፡፡ ለባለሙያዎችም ለባለሀብቶችም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የጥራት ግብ አስቀምጠንላቸው በዚያ ደረጃ እየሠሩ ናቸው፡፡ ይህም የቡናውን ጥራት በማሻሻል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ የመጋዘን አገልግሎት ድርጅቱ ጥሩ ሆኖ በመጋዘን አያያዙ፣ በደረጃ አወጣጡና በመሳሰሉት አገልግሎቶች ላይ ያሉበትን ችግሮችን ለይተን፣ ከጊዜና ከወጪ አኳያ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለይተን፣ ተልዕኮ ሰጥተነው በየጊዜው እየገመገምነው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ሌላው ጥያቄ የሚነሳበት ተቋም ነው፡፡ ለምርት ገበያውስ ምን ተልዕኮ ሰጣችሁት?

አቶ ሳኒ፡- ምርት ገበያውም የወሰዳቸው ተልዕኮዎች አሉት፡፡ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ገበያ አለመናበብ ለአገሪቱ የቡና ኤክስፖርት ንግድ አለማደግ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ የሚናበብበትን ሥርዓት እንዲያጠና የቤት ሥራ ተሰጥቶት፣ አሁን ባለድርሻ አካላት ተግባብተውበት ዕለታዊ የዋጋ ገደብ ሥርዓት እየተገበረ ነው፡፡ አሁን ይህ አሠራር በቦርድ ፀድቆ ሥራ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ባሻገር በምርት ገበያው አገናኝ አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አቅራቢዎችንና ኤክስፖርተሮችን የሚያገናኙት አገናኝ አካላት የአገልግሎት አሰጣጥ በራሱ ቀልጣፋና በአነስተኛ ወጪ የሚካሄድ ካልሆነ፣ በኤክስፖርቱ ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ለዚህ ክፍተትም የአገናኝ አካላትን የሚገመግምበትንና የሚመራበትን ሥርዓት ፈጥሯል፡፡ ቡና አቅራቢዎች ቡናቸው እንዲሸጥላቸው ሲያዙ የመልዕክት መቀበያ ሥርዓቱን እየገነባ ነው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ወንበሮችን በመጨመር ተጨማሪ ወጣቶች በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ የማድረግ፣ አቅራቢዎችም በማኅበር ተደራጅተው በአገናኝነት እንዲሳተፉና ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር የማድረግ ሥራዎችን ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር– በቡና ግብይት የሚሳተፉ ላኪዎችና ሌሎች ተዋንያኖች ብቃታቸው ታይቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡ የፈቃድ አሰጣጡም የተለየ እንዲሆን እየተፈለገ ነው? ሊያብራሩልን ይችላሉ?

አቶ ሳኒ፡- የግብይት ሥርዓቱን ከማዘመንና ከማቀላጠፍ አኳያ ተግባራዊ ሊደረጉ  ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ብቃት ያላቸው ተዋንያንን ማፍራት ነው፡፡ ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ፈቃድ ከመስጠት አኳያ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ አስተዋጽኦ የሌላቸውና ልምድ የሌላቸው ሰዎች የሚገቡበትና ራሳቸውም ችግር ውስጥ የሚወድቁበት፣ ግብይቱንም የሚያበላሹበት ሁኔታ ነበር፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ እንዴት  ነው የቡና ኤክስፖርት ፈቃድ መስጠት ያለብን? የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጠው ደግሞ የእኛ ባለሥልጣን ነው፡፡ የብቃት ማረጋገጫችንስ ምን ላይ መመሥረት አለበት? የሚሉ በቅብብሎሽ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከተቋቋመ በኋላ በግብይት ሒደቱ ውስጥ የነበሩ አካላት የግብይት ሥርዓቱን በመገንባት ድምፅ እንዲኖራቸው፣ ሐሳብ እንዲያካፍሉ ጭምር ተደርጓል፡፡ የግብይት ሒደቱ አጭር፣ ወጪ ቆጣቢና ፍትሐዊ እንዲሆን ለማድረግ የሚያነሱዋቸውን ሐሳቦች ወስደን ሥራ ላይ እንዲውልና ለሚመለከተው አካል ተልዕኮ በመስጠት ትልቅ መድረክ ፈጥረናል፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ አሁን የለየናቸው ችግሮችና ማነቆዎች ከተፈቱ አቅራቢውን፣ ኤክስፖርተሩን፣ አርሶ አደሩንም ሆነ ሌላውን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ መሠረታዊ ችግሮች እንፈታለን ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከእነዚህ ተቋማት የተውጣጣ ቡድን አቋቁመናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን የሚሠራ ቡድን?

አቶ ሳኒ፡- ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ከምርት ገበያ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአርሶ አደሩና፣ ከመጋዘን አገልግሎት ድርጅት የተደራጀው ይህ ቡድን ከአርሶ አደር የመጀመርያ ገበያ ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ገበያ መዳረሻ ድረስ ባለው ሒደት ላይ ከሕጋዊነት አኳያ ምን ችግሮች አሉ? ገበያውን ፍትሐዊ ከማድረግ አኳያ ምን ችግሮች አሉ? ገበያውን ለማዘመን መቆረጥ ያለባቸው ሰንሰለቶች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ደግሞ የሚያጠና ቡድን አደራጅተን እያጠናቀቅን ነው፡፡ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ውይይት ይደረግበታል፡፡ በጋራ ያመንበትን ወስደን ወደ ተግባር እንገባለን፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ በቡና ግብይት ውስጥ ብዙ ብልሹ የሚባሉ ተግባራት የሚፈጸሙ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ በተለይ የላኪዎች አፈጻጸም ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ በግብይቱ ውስጥ በሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትም ላይ የሚነሳ ጥያቄ አለ?

አቶ ሳኒ፡- እንግዲህ በግብይት ሒደት ውስጥ ወደ ስድስት ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ግማሾቹ የማጠቢያና የመቀሸሪያ ኢንዱስትሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ግማሾቹ ደግሞ ተከራይተው የሚሠሩ ናቸው፡፡ አሁን ካለው ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት አንፃር ምን ያህል ብቃት አላቸው? ቡናን በጥራት አዘጋጅተው አገራዊና ዓለም አቀፍ ዋጋውን ተከታትለው የሚሠሩት ምን ያህል ናቸው? የሚለውን ለመገምገምም፣ የብቃት ማረጋገጫና ማሻሻያ ለማድረግም ቡድን አደራጅተን እየሠራን ነው፡፡ መነሻው የብቃት ማረጋገጫ ነው፡፡ ለዘርፉ ተዋናይ የንግድ ፈቃድ ለመስጠት መጀመርያ በዘርፉ ሥራ በመሥፈርት ደረጃ የተቀመጡትን አሟልቶ ብቁ ነው ወይ? የሚል ምላሽ ከተቆጣጣሪ አካሉ መሄድ አለበት፡፡ የእኛስ ብቃት ራሱ ብቁ ነው? የሚለውን መፈተሽ አለብን፡፡ ስለዚህ የአቅራቢዎችን የብቃት ማረጋገጫ እየተፈተሸ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ፍተሻው ምን ላይ ያነጣጠረ ነው?

አቶ ሳኒ፡- የክህሎትና የፋይናንስ አቅም፣ ለገበያው ታማኝነት፣ ቀጣይነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አስተሳሰብ አለው ወይ? የኢንዱስትሪ ብቃትንም እየፈተሽን ነው፡፡ ይህንን ስንጨርስ ከአቅራቢዎች ጋር ተወያይተን ሊሻሻል የሚገባውን አሻሽለን ወደ ሥራ እንገባለን፡፡ ሁለተኛው ደረጃ የምርት ገበያው ውስጥ የሚሳተፉ የአገናኝ አባላት ብቃትና ታማኝነት ነው፡፡ እነዚህ አባላት የትምህርትና የክህሎት ደረጃቸውን ማሻሻል አለባቸው ብለን የትምህርት ደረጃቸውን ከፍ አድርገናል፡፡ አሁን ቡና ከነባሩ የግብይት ሥርዓት ወደ ኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት ተሸጋግሯል፡፡ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ በሐዋሳና በነቀምት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት አገልግሎት እንጀምራለን፡፡ ስለዚህ በአገናኝ አባልነት የሚሠሩት የተማሩ ወጣቶች የሚቀላቀሉበት፣ ለዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት አሠራር እንዲዘረጋ ብለን ወጣቶችን የማደራጀት፣ ሥልጠና የመስጠትና የማሰማራቱ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በላኪዎች በኩልስ ምን ለማድረግ ታስቧል?

አቶ ሳኒ፡- ትልቋ ቡና ላኪ አገር ብራዚል 230 ኤክስፖርተሮች ናቸው ያሏት፡፡ እኛ ከ400 በላይ ኤክስፖርተሮች አሉን፡፡ ሁሉም ብቃት አላቸው ልንል አንችልም፡፡ አንዳንዱ ቡናን እንደ ዋናው ሥራው አድርጎ የሚሠራ አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ቡናንና ሌሎች የንግድ ሥራዎችን አዳብሎ የሚሠራ አለ፡፡ አንዳንዱ የቡና ገበያ ጥሩ መስሎ ሲታየው  የሚሠራ፣ ሳይሆን ደግሞ የሚያፈገፍግ ነው፡፡ ይህንን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ምርምሩን መደገፍ አለበት፡፡ የግብይት ተዋንያኑ ልማቱን መደገፍ አለባቸው፡፡ የሚመጣ ቡና መጠን እንዲያድግና የጥራት ደረጃው እንዲሻሻል መደረግ አለበት፡፡ በዚያ ደረጃ ያሉ ሰዎች ናቸው ወይ እዚህ ቢዝነስ ውስጥ ያሉት? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ስለዚህ በወጪ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥ የብቃት ማረጋገጫችንን ከዚህ አኳያ ቃኝተን እየጨረስን ነው፡፡ ያሉትን በዚህ ቅኝት ውስጥ አስገብተንና ገምግመን የሚያሟሉትን እናስቀጥላለን፡፡ ለማያሟሉት ደግሞ የማብቃት ሥራ እንሠራለን፡፡ የማብቃት ሥራ ተሠርቶባቸው የማያሟሉትን ደግሞ ከግብይቱ ውስጥ እናስወጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለላኪዎች ይወጣል በተባለው የብቃት ማረጋገጥ ሥራና የፈቃድ አሰጣጥ፣ በቡና የወጪ ንግድ ለመሰማራት ከተፈለገ በቡና ወጪ ንግድ ብቻ መሰማራት አስገዳጅ ይሆናል?

አቶ ሳኒ፡- አይደለም፡፡ ይኼ ችግር ያለው ነገር አይደለም፡፡ ዋናው አስተሳሰቡ ነው፡፡ ቡናን ኤክስፖርት እያደረገ ሰሊጥ ኤክስፖርት ሊያደርግ ይችላል፡፡ አቅሙ ነው የሚወስነው፡፡ ለሰሊጥም ለቡናውም የብቃት ማረጋገጫ ይወስዳል፡፡ ሌላም ምርት ኤክስፖርት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ለዚህም የብቃት ማረጋገጫ ሊወስድ ይችላል፡፡ አስገዳጅ አይደለም፡፡ ዋናው ለቡና የሚያስፈልገው ሥነ ምግባር ምንድነው? አቅምና አስተሳሰብ ምንድነው? የሚለው ነው ወሳኙ ነገር፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የሚያስችል የብቃት ማረጋገጫ ክለሳ ላይ ነን፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ክለሳው በግሉ ዘርፍ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በመጋዘን አገልግሎት ድርጅቱ ቡናን ለማቆየት የሚያስችል ብቃት አለ ወይ? የቡና ጥራት ሳይጓደል ለማቆየትና ለኤክስፖርተሩ የማስረከብ ብቃት አላቸው ወይ? የመሳሰሉትን እንደ ተቆጣጣሪ እንፈትሻለን፡፡ የኤክስፖርት ማደራጃ ኢንዱስትሪዎችም የአገሪቷን የቡና ጥራት ደረጃ ጠብቀው አስተሳሰቡና ብቃቱ አላቸው ወይ? ሳይችሉ ሲቀሩ ደግሞ የምንቀማበት የሕግ ሥርዓት አለ ወይ? የሚለውን እየፈተሽን ነው፡፡ ይህንንም አልፈን የአገሪቱን የቡና የጥራት ደረጃ የሚያረጋግጥ ተቋም አለን ወይ? የቡና ጥራት ደረጃ ሰርቲፊኬሽን ማዕከል አለን ወይ? ብለን ይኼንንም የማጎልበትና የማሻሻል ሥራ ከተወዳዳሪ አገሮች አኳያ ፈትሸን ጉድለቱን የማሟላት ሥራ ይሠራል፡፡ ይህንን ማድረግ ስንችል ነው የሚፈለገው ውጤት የሚመጣው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጪ በመላክና የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ረገድ ቀዳሚ ነች እየተባለ፣ ከዚያ በኋላ የመጡት እንደ ቬትናም ያሉ ቡና ላኪዎች ቀድመዋታል፡፡  በአጭር ጊዜ ውስጥ የቡና የወጪ ንግድ እንዲሁ እየዋለለ ነው፡፡ እንዲያውም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከቡና የወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ ነው፡፡ በእርግጥ ዓለም አቀፉ ገበያ ተፅዕኖ ቢኖረውም ካለው አቅም አንፃር ግን ቡና የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ ለቡና የተቀመጠውን ግብ ማሳካት ይቻላል? በእርግጥ በግልጽ የተቀመጠውን ግብና ኢትዮጵያን ከብራዚል ቀጥሎ ሁለተኛዋ የቡና ላኪ አገር እናደርጋለን የሚለው ዕቅድ ይሳካል?

አቶ ሳኒ፡- የቡና ኤክስፖርት ሥራችን ከልማቱ የሚመነጭ ነው፡፡ ሁለተኛ እኛ ከዓለም ቡና አምራች አገሮች የተለየ የሚያደርገን አንድ እውነት አለ፡፡ እኛ ቡና አምራች ብቻ ሳንሆን ተጠቃሚም ነን፡፡ ብራዚል ከምታመርተው ቡና ለአገር ውስጥ ፍጆታዋ የምትጠቀመው አሥር በመቶውን ብቻ ነው፡፡ ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ቡና ተጠቃሚ አገር ነች፡፡ እኛ ግን ከምናመርተው ቡና ከ50 እስከ 60 በመቶውን የሚሆነውን ቡና ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንጠቀማለን፡፡ ይህ የሚያመለክተው የቡና ኤክስፖርት ዕድገት  ዓለም አቀፍ ገበያውን ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ የመግዛት አቅማችን ጭምር ይወስነዋል፡፡ የአገራዊ ኢኮኖሚው እያደገ በሄደ መጠን የቡና ፍላጎታችንም እያደገ መጥቷል፡፡ ለቡና የመክፈል አቅማችንም እያደገ መጥቷል፡፡ የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከዓለም አቀፍ ዋጋው የሚበልጥበት ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ የቡናው ዘርፍ አላደገም ማለት አንችልም፡፡ ዕድገቱ አዝጋሚ ነው፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ የቡና አጠቃቀም ባህላችን ለቡናው ዕድል እንጂ ሥጋት አይደለም፡፡ ብዙዎችም በዘርፉ ያጠኑ እንዳረጋገጡትም የኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ዕድል አለው፡፡ ችግሩ ከፍጆታ በላይ ማምረት ያለመቻል ነው፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ ችግር ውስጥ ቢወድቅ የአገራችን ኢኮኖሚ አሁን ባለው ደረጃ እንኳን እያደገ ቢሄድ፣ የኢትዮጵያ ቡና ዕድገቱን አያቆምም፡፡ ገበያ አለው፡፡ ይኼ መንደርደሪያ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ቡና ዘርፍ ዕድገት አዝጋሚ ነው፡፡ እንዴት ነው የምናስተካክለው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ይህንን ለማሳካት ሦስት ነገሮች ነው የተደቀኑብን፡፡ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ፣ በአርሶ አደር ደረጃ የምርት ጥራት ማሻሻል፣ በተጓዳኝ የግሉ ዘርፍ በዚህ ዘርፍ እንዲሰማራ የመመልመል፣ የማሰማራትና ድጋፍ የማድረግ አንዱ ተልዕኮ ነው፡፡ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ደግሞ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ምርት አደገ ተብሎ ዋጋው የሚወርድ ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ስለዚህ የገበያ ዕድልን ማስፋት፣ ለሚመረተው ምርት የተሻለ ገበያ መፈለግና በተሻለ ዋጋ መሸጥ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ገበያ በማፈላለግ ረገድ ውለታ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ውለታ?

አቶ ሳኒ፡- የኢትዮጵያ ቡና ከሌላው የተሻለ ነው፡፡ የእኛን ቡና የሚፈልጉ አገሮችና ደንበኞች አሉ፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ካቀረብን የተሻለ የሚከፍሉንና ለመክፈል የተዘጋጁ አካላት አሉን፡፡ እነዚህን የመፈለግና የማስተዋወቅ ሥራው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀናጅተን የምንሠራው ይሆናል፡፡ ይህንን ለመሥራት በንግድ ሚኒስቴርና በእኛ መሥሪያ ቤት አደረጃጀት ተፈጥሯል፡፡ አሁን የግሉ ዘርፍ ያዋጣኛል ባለውና ባገኘው ዋጋ ነው እየሸጠ ያለው፡፡ የተሻለውን ገበያ ከተፈጠረለት ተቀናጅተን እንሠራለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የተሻለ ገበያ መፍጠር አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ሁሌ ግራ የሚያጋባ ነገር አለ፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸምን የሚያሳይ ሰንጠረዥ እየተመለከትኩ ነበር፡፡ ቡና የሚላክባቸው አገሮች ከአሥር የማይበልጡ አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ ይኼ ችግር በቡና ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የወጪ ንግድ ምርቶች የሚታይ ነው፡፡ የገበያ መዳረሻ  ቦታን ማስፋት ግድ ይላል፡፡ ግን የለም፡፡ አገሪቱን የመሸጥ ነገር የለም፡፡ በእርግጥ አሁን ያነሱልኝ ሐሳብ ጥሩ ቢባልም በተጨባጭ ሥራው ምንድነው?

አቶ ሳኒ፡- ዋና ዋና የሚላክባቸው አገሮች አሥር ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን 52 አገሮች ይላካል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአሥሩ ሌላ ለቀሪዎቹ አገሮች የሚላከው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የገበያ መዳረሻዎቹ ትንሽ ናቸው፡፡

አቶ ሳኒ፡- ለዚህም ዓለም አቀፍ በሆነ ደረጃ ቡናችንን ማስተዋወቅ መሸጥን እንደ አንድ ሥራ ወስደን አደረጃጀት ፈጥረናል፡፡ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤታችን የፕሮሞሽንና የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ተፈጥሯል፡፡ በንግድ ሚኒስቴርም እንደ አገር የኤክስፖርት ምርቶቻችንን ፕሮሞሽንና ማርኬት ሊንኬጅ የሚሠራ ኤጀንሲ ለመፍጠር አደረጃጀቱ እያለቀ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ተቋማት በማቀናጀት ለቡናችን የተሻለ ዋጋ በሚከፍሉ አገሮች ላይ ትኩረት አድርገን ለመሥራት ነው፡፡ ቁጥሩን ሳይሆን የተሻለ ዋጋ በሚከፍሉ አገሮች ላይ እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአምና አፈጻጸማቸውን ስናይ በአንድ ቶን 6,300 ዶላር አግኝተዋል፡፡ አምራች ላኪዎች ደግሞ በአንድ ቶን ያገኙት በአማካይ 5,400 ዶላር ነው፡፡ ሌሎች ቡና ላኪዎች በአንድ ቶን ያገኙት 3,600 ዶላር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንድ አገር የሚሄደው ቡና በዚህን ያህል ደረጃ ለምን ተለያየ? በሦስቱ ላኪዎች መካከል ያለው ልዩነት ምክንያት አለው?

አቶ ሳኒ፡- የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ቡና የተመዘገበ ነው፡፡ ብራንድ ነው፡፡ የዚያች ቀበሌ ቡና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተወዳጀ መሆኑ የተመዘገበ ነው፡፡ በእነዚህ ማኅበራት በኩል የተላከው የቡና መጠን ስምንት በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ቡና የሚፈልጉ አሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውን ቡና ለማሳደግ እንሠራለን ማለት ነው፡፡ የአምራች ባለሀብቶቹ ዋጋ 5,400 ዶላር ለምን ሆነ? የከፋ የዚህች ቀበሌ ቡና ከተባለ የዚህች ቀበሌ ባለሀብት ነው፡፡ ያንን ቡና ቀምሶ የመጣው ገዥ ያቺን ቡና ድገሙኝ ይላል፡፡ ስለዚህ ያቺን ቡና የሚፈልጉ ከፍተኛ የሆኑ ገዥዎች አሉ፡፡ በዚህ አካባቢ ያሉትን እነዚህን ልማታዊ ባለሀብቶች በዙሪያቸው ካሉት አርሶ አደሮች ጋር የገበያና የልማት ትስስር ከፈጠርን ኤክስፖርት የሚደረገው ያድጋል፡፡ ሌላው እሴት መጨመር ነው፡፡ የገበያ ስትራቴጂያችንን በአንድ አቅጣጫ ሳንወስን ለመሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ሲገለጽ እንደነበረው ባለሥልጣኑም እየዋጣቸው ካሉ መረጃዎች ዘንድሮ የቡና ምርት ማደጉን ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምን? ባለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸማችሁስ ምን ይመስላል?

አቶ ሳኒ፡- የቡና ምርትን በዚህ ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ነው ግብ የያዝነው፡፡ ከሚመረተው 241 ሺሕ ቶን ደግሞ ኤክስፖርት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ የስድስት ወራት አፈጻጸማችን ሲታይም ከወር ወር እያደገ መጥቶ ከዕቅዳችን 86 በመቶ አሳክተናል፡፡ በቀረበው የምርት መጠን ካለፈው ዓመት አፈጻጸማችን ጋር ስናይ 2.7 በመቶ ያንሳል፡፡ በገቢ ደረጃ ግን በስድስት ወራት የተገኘው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከተገኘው በሰባት በመቶ ይበልጣል፡፡ በመጠን ቢያንስም በገቢ ጭማሪ አለው፡፡ ይህ የሆነው ከጥቅምት ጀምሮ የዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋው ከፍ እያለ ስለመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ዓመታት ምርቱ እየጨመረ ነው ተብሎ ገቢው ግን እየነቀሰ ነበር፡፡ ዘንድሮስ ይህ ያጋጥማል?

አቶ ሳኒ፡- በዚህ ዓመት ግን በጣም ምቹ እንደሚሆን እየታየ ነው፡፡ ለምርቱም በጣም ምቹ ነው፡፡ በቅድመ ምርት አሰባሰብ የመረጃ ትንተና መሠረት ወደ 26 በመቶ የቡና ምርት ዕድገት እንደሚኖር እንገምታለን፡፡ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚያወጣው መረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኛ ባሰባሰብነው መረጃ ወደ 702 ሺሕ ቶን ቡና እናመርታለን ብለን እንገምታለን፡፡ ይህም ለበጀት ዓመቱ ያስቀመጥነው ዕቅዳችንን እናሳካለን የሚል ግምት አለን፡፡ አሁን ያለው የእሸት ቡና አቅርቦትም በጣም ጥሩ ነው፡፡ ወደ 406 ሺሕ ቶን እሸት ቡና ኢንዱስትሪዎች ገዝተዋል፡፡ የ63 ሺሕ ቶን ደረቅ ቡና ግብይት ተፈጽሟል፡፡ ይኼ ካለፉት አፈጻጸም ጋር ሲታይ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የቡና ምርት ዕድገትን ገበያውም እየተናገረ ነው ማለት ነው፡፡ ኤክስፖርቱም እየጨመረ መጥቷል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...