Wednesday, October 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለሁለንተናዊ ዕድገት የማይጠቅሙ ከንቱ ውዳሴዎች ገደብ ይኑራቸው!

የአሁኗ ኢትዮጵያ ሁለት ገጽታዎች አሏት፡፡ አንደኛው በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ የተቸረው የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሸን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ ጥላሸት የተቀባ ስም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዕድገት ከኢኮኖሚያዊው ምልከታ አንፃር ብቻ እየተጨበጨበለት፣ በጣም መሠረታዊ የሚባለው የዴሞክራሲ ጉዳይ ግን አሁንም እንደተዳፈነ ነው፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ለዘለቀው ደም አፋሳሽ ሕዝባዊ አመፅ መነሻ ምክንያቶች ምን መሆናቸው እየታወቀ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አሁንም ተጠምደው ያሉት ከንቱ ውዳሴ ላይ ነው፡፡ አገሩ ስታድግ፣ ስትለማ፣ ስትበለፅግና ከድህነት ማጥ ውስጥ ተስፈንጥራ ስትወጣ ማየት የሚጠላ ዜጋ የለም፡፡ ነገር ግን ኢፍትሐዊነት፣ ሕገወጥነትና ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚፃረሩ ድርጊቶች አሁንም እየታዩና ምሬት እየተቀሰቀሰ፣ ከንቱ ውዳሴዎች ላይ ብቻ መጣድ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ይልቁንም ካለፉት ስህተቶች ተምሮ ለአገር የሚጠቅም ጉዳይ ላይ ማተኮር ይሻላል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶውን ወደ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ካሸጋገረ ወዲህ አስገራሚ ነገሮች እየተስተዋሉ ነው፡፡ በፈረቃ ይካሄዳሉ የተባሉ የመንግሥታዊ ተቋማት የተሃድሶ ስብሰባዎች ሠራተኞችን ሥራ እያስፈቱ ተገልጋዮችን እያማረሩ ነው፡፡ አንድ ሳምንት ሙሉ ሥራ በፈታ መንግሥታዊ ተቋም ምክንያት እያደረሰ ያለው ኪሳራ እየተሰላ ይሆን? የሚባክነው ጊዜስ አያሳዝንም? ግብር ከፋዩ ሕዝብ ያለጥፋቱ ለምን ይቀጣል? በተሃድሶ ስብሰባ ሰበብ ቢሮአቸውን እየዘጉ የሚጠፉ ሹማምንትን የሚቆጣጠራቸው ማን ነው? እንዲህ ዓይነቱን የምንቸገረኝ ድርጊት በትዝብት ከሚመለከቱ ሠራተኞችስ ምን ዓይነት ውጤት ይጠበቃል? ከግለሰብ እስከ አገር ድረስ ለኪሳራ ሲዳረጉ የሚጠየቀው ማን ነው? ስብሰባና ሥልጠና እየተባለ ያላግባብ የሚረጨው ገንዘብ ለስንት ቁም ነገር አይውልም? በርካታ ፕሮጀክቶች እየተጓተቱ የአገር ሀብት ሲባክን ከተደጋጋሚ ስብሰባዎችና ሥልጠናዎች ምን ተገኘ? በሐሰተኛ ሪፖርቶች እየተዝናኑ ማጣፊያው ሲያጥር ሰበብ ከመደርደር ይልቅ ቀድሞ መገኘት ባለመቻሉ ብዙ ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ማስፈን ያቃተው እኮ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ድርጊቶች ስለበዙ ነው፡፡ ስለዚህ ከንቱ ውዳሴ ማብዛቱ ትርፉ ትዝብት ብቻ ሳይሆን ጥፋት ጭምር ነው፡፡

የአገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት እያዘቀዘቀ ነው፡፡ በዓለም ገበያ መጣበብ እየተመካኘ የአገሪቱን ምርቶች መሸጥ ባለመቻሉ፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅዱ መሠረት የሚጠበቀው ገቢ እየተገኘ አይደለም፡፡ በመስኩ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ክፍተቱን ከመሙላት ይልቅ ሰበብ ለመደርደር ሲሯሯጡ ነው የሚታዩት፡፡ የመጀመሪያ ዕቅድ በታሰበው መንገድ ካልተሳካ በተለዋጭ ዕቅድ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል በርካታ ልምዶች ያስተምራሉ፡፡ የአገሪቱን የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በዓይነትና በጥራት በማሳደግ የገበያ መዳረሻዎችን በጥልቀት መፈለግ ሲገባ፣ የዓለም ገበያን መቀዛቀዝ ምክንያት አድርጎ መተኛት ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ለላኪዎች የተለያዩ ማትጊያዎችን በማቅረብ ገበያዎችን እንዲያስሱና ጥቅም እንዲያስገኙ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም፣ አሳሪ የሆኑ ደንብና መመርያዎችን ደንቅሮ ውጤት መጠበቅ ከማስገረም በላይ ያስከፋል፡፡ ዘመኑ የውድድር፣ ውድድሩን የሚያሸንፉት ደግሞ ብርቱዎች ናቸው፡፡ ይህ በሌለበት በባዶ እየተኮፈሱ ባለፉ ስኬቶች መኩራራት ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር ይቃረናል፡፡ ለአገርም አይጠቅምም፡፡

ከኤክስፖርት ከሚገኘው በተጨማሪ በሐዋላ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በብድርና በዕርዳታ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ ገቢ ዕቃዎች ወሳኝ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ በአስተማማኝ መገኘት ካልቻለ የአገሪቱ መጠባበቂያ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ፍሰት አስተማማኝ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነው ያለነው፡፡ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ለመስጠት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ባሉበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስተዋሉ ያሉ ለውጦች ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ተጋፍጠው የተሻለ ነገር ለማምጣት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? እነ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምንም ነገር በፊት አሜሪካ በሚሉበት ዘመን፣ ሌሎችም የራሳቸው የውስጥ ጉዳይ ላይ ሲያተኩሩ አማራጭ ፍለጋው ምን ይመስላል? ከአሁኑ ዓለም መለወጥ ጋር እኩል መራመድ ይቻላል? ወይስ በዘልማዳዊ አሠራር ታስሮ የሚመጣውን መጠበቅ? ይህ እንግዲህ ውዳሴ ላይ ውሎ ከማደር የሚያላቅቅ አዲስ የቤት ሥራ ይሆናል፡፡

ከመልካም አስተዳደር ዕጦትና ከፍትሕ መዛባት ጋር ስሙ አብሮ የሚነሳው ሙስና አሁንም ትልቁ የአገር ፈተና ነው፡፡ በተለይ መንግሥት በገነነባቸው የአገሪቱ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈሰው መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብና በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ግዥዎችና ንብረት አወጋገድ ላይ ያለው ዝርፊያ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ እንደምንም ተብሎ የመንግሥት ሥልጣን ላይ መንጠላጠል ራስንና ቢጤዎችን የማበልፀግ እኩይ ዓላማ ያነገበ በመሆኑ፣ ገዥው ፓርቲ ጭምር ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ እንዲገባ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ሰሞኑን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ያወጣው የሙስና ሪፖርትም አገሪቱን ከ176 አገሮች 108ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ በዕድገት መሰላል ላይ በስኬት እየተራመደች ነው ለሚባልላት ኢትዮጵያ ይኼ ውርደት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በአቋራጭ የሚበለፅጉ የዘመኑን ቱጃሮች ያውቃቸዋል፡፡ በሙስና የከበሩ ባለሥልጣናትን ለማጋለጥ ማስረጃ አልተገኘም ቢባልም፣ ከሕዝብ ዓይን ግን የተደበቀ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ በጥልቅ ተሃድሶው አማካይነት ሙስና ስለመቀነሱ የወጣ ሪፖርት ባይኖርም፣ ሙስና አሁንም አገሪቱን እንደ ሰደድ እሳት የሚበላ ነውረኛ ተግባር መሆኑን ማን ይክዳል? ኢኮኖሚው ውስጥ ተሰግስገው የገቡ የሙስና ደላሎች ሰንሰለታቸው ከሚበጣጠስ ይልቅ ይበልጥ እየተጠናከረ ነው፡፡ ከመሬት ዝርፊያ እስከ ባንክ የውጭ ምንዛሪ የኮሚሽን ሌብነትና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ድረስ ያለው ዝርፊያ፣ ከስኬትና ከውዳሴ ይልቅ ቆፍጣና ዕርምጃ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ቢያንስ ታዳጊውን ትውልድ ከጥፋት ለመታደግ ያገለግላል፡፡

በአጠቃላይ አገራችን ኢትዮጵያ ሰላሟ የተጠበቀ፣ አንድነቷ የተጠናከረ፣ ወደ ቀድሞ ገናናነቷና ዝናዋ የምትገሰግስ ስኬታማ እንድትሆን ከልባቸው የሚመኙና ለዚህም የሚተጉ ዜጎችን ትፈልጋለች፡፡ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ ሆና ‹በዕድገትና በብልፅግና እየተጓዘች ነው› ብሎ መለፈፍ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ይልቁንም ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባት፣ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል የሚደረግባት፣ ዜጎች በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹባትና የሚደራጁባት፣ የመሰላቸውን አመለካከት ያለምንም ገደብ የሚያንፀባርቁባት፣ በአገራቸው ዙሪያ መለስ ጉዳዮች ባለቤት ሆነው በነፃነት የሚሳተፉባት፣ ማንም ማንንም የማያስፈራራበትና የሕግ የበላይነት የሚከበርባት፣ ወዘተ ልትሆን ይገባል፡፡ ሰላሟን የሚያደፈርሱ፣ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር የሚሻረኩ፣ ከሥልጣን በስተቀር ምንም የማይታያቸው፣ ራስ ወዳዶች፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞች፣ የአገር ፍቅር ስሜት የሌላቸውና ይህንን ኩሩና የተከበረ ሕዝብ የማያከብሩ በፍፁም ለዚህች አገር አይጠቅሙም፡፡ ነገር ግን ለአገራቸው ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያስቡ ዜጎች ይፈለጉ፡፡ ይህ በተግባር ሲረጋገጥ ያኔ ከውዳሴ ይልቅ የበለጠ ለመሥራትና አገሪቱን ለመጪዎቹ ትውልዶች ለማሸጋገር መደላድሉ ይስተካከላል፡፡ እስከዚያው ግን በአንድ ወገን ስኬት ላይ በመንጠልጠል ብዙኃኑን የማይወክል ዲስኩር ይቁም፡፡ ለሁለንተናዊ ዕድገት የማይጠቅሙ ከንቱ ውዳሴዎች ገደብ ይኑራቸው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...

የመከፋት ስሜት!

ከቤላ ወደ ጊዮርጊስ ልንጓዝ ነው፡፡ መውሊድና መስቀልን በተከታታይ ቀናት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግጭቶች በሙሉ ሁሉን አሳታፊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተገቶ የተስፋ ጭላንጭል መታየት ሲጀምር፣ በአማራ ክልል ሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት ሊያደርስ የሚችል ግጭት መነሳቱ ብዙዎችን ያሳስባቸዋል፡፡ በአማራ...

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...