Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሩስያ ኩባንያን ጨምሮ ለተቋራጮች ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበላቸው መንገዶች ሊገነቡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሩስያ ሥራ ተቋራጭን ጨምሮ አገር በቀልና የቻይና ኩባንያዎች የተሳተፉባቸው አምስት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከ5.07 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለማስገንባት የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈረሙ፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር የመንገዶቹ ግንባታ ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ውለታ ሲመፈጸም፣ አንደኛውን የመንገድ ሥራ በመውሰድ ለመገንባት የተስማማው ኢንቨስትስትሮይ ፕሮኤክት የተባለው የሩስያ ኩባንያ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ በዕለቱ ከተፈራረማቸው የአምስት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሩስያው ተቋራጭ በጨረታ አሸንፎ የተረከበው የጭዳ ሶዶ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት (ሦስተኛ ክፍል) ሲሆን፣ ግንባታውን ለማካሄድ አሸናፊ የሆነበት ዋጋም 1.17 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ጭዳ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገነባ ሲሆን፣ በዳውሮ ዞን ውስጥ የሚኙትን የጭዳ፣ አባ፣ ጎርኬ፣ ወራ እና ላላ ከተሞችን ለማገናኘት ያስችላል፡፡ ኩባንያው ከተረከበው መንገድ በተጨማሪም ሁለቱን የቻይና፣ ቀሪዎቹን ሁለቱን ደግሞ የኢትዮጵያ ተቋራጮች በመረከብ ኮንትራት ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ እንደገለጹት፣ በዕለቱ የተፈረሙትን አምስት ፕሮጀክቶች ጨምሮ በ2009 ግማሽ ዓመት ብቻ 13.7 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 18 ፕሮጀክቶችን ካሸነፉ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ተካሂዷል፡፡ በዚህ ተጓዳኝ በአሁኑ ወቅት 29 ፕሮጀክቶች በጨረታና በግምገማ ሒደት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በቅርቡም ውለታቸው እንደሚፈረም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡  

በዕለቱ የተፈረሙት አምስት መንገዶች በጥቅሉ 357 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ናቸው፡፡ ገምሹ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በሐሙሱ የኮንትራት ስምምነት ወቅት ከአገር በቀል ተቋራጮች አንዱ በመሆን ፕሮጀክት ተረክቧል፡፡ ገምሹ ኩባንያ በጨረታ በማሸነፍ የተረከበው የግንጪ – ካቺሴ – ጩሊቲ የመንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሎት አንድ ጊንጪ – ሺኩቴ ኪሎ ሜትር 59+000 የመንገድ ክፍልን ለመገንባት ነው፡፡ መንገዱ 59 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ነው፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የሚገነባው ይህ መንገድ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙትን የደንዲ፣ ጀልዱና ካቺሴ ወረዳዎችን የሚያገናኝ እንደሆነ አቶ አርዓያ በዕለቱ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ነባሩን የጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት ኮንክሪት ደረጃ የሚያሳድገው በመሆኑ፣ በአካባቢው የሚገኙትን ምርቶች ከቀድሞው በተፋጠነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ ለማድረስ እንዲያስችል ታስቦ የሚገነባው ይህ መንገድ ዕውን እንዲሆን ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 846.2 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡  

ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን በዕለቱ ከተረከበው የመንገድ ሥራ ቀደም ብሎ ከባለሥልጣኑ ጋር በመዋዋል የድሬዳዋ ደዋሌና የድሬዳዋ ሐረር፣  የማይፀብሪ ዲማ – ዲማ ፍየል ውኃ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ አስረክቧል፡፡ በቅርቡም የሐረር ባይፓስ የተባለውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አጠናቆ ከማስረከቡም ባሻገር፣ በጎንደር የአዘዞ – ጎርጎራ መንገድ ፕሮጀክትን ግንባታም 98 በመቶ በማጠናቀቁ በቅርቡ እንደሚያስረክብ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከመሐል ሜዳ ዓለም ከተማ ድረስ የሚዘልቀውን የመንገድ ፕሮጀክት 60 በመቶ በማጠናቀቅ አፈጻጸሙ በጥሩ ታይቶ ተጨማሪ አዲስ ሥራ እንደተሰጠው ተጠቅሷል፡፡

በዕለቱ ስምምነት የፈረመበትን የመንገድ ፕሮጀክት ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋም 887.7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ከአራት ፕሮጀክቶች በላይ ተረክቦ ማከናወኑም አይዘነጋም፡፡

ሌላው በዕለቱ የተፈረመው የፓዊ መገንጠያ – ህዳሴ ግድብ (ጉባ) የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አካል የሆነው የፓዊ መገንጠያ – ኪሎ ሜትር 69 የመንገድ ክፍል ነው፡፡ በቤንሻንጉል ክልል የሚገነባው ይህ መንገድ፣ ማንቡክና የጉባላክ ከተሞችን አቋርጦ የሚያልፍ ነው፡፡ ይህ መንገድ ወደ ህዳሴ ግድብ የሚያደርሰውን የጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት ኮንክሪት የሚያሳድግ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ለመገንባት ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ሥራውን ተረክቦ የተፈራረመው ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የተባለው ተቋራጭ ነው፡፡

ከአምስቱ ፕሮጀክቶች የሁለቱን የመንገድ ሥራዎች ከተረከቡት የቻይና ተቋራጮች መካከል የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ይገኝበታል፡፡ የጨሪቲ – ጎሮበክሳ – ጉራዳሞል የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በሦስት ኮንትራት ተከፋፍሎ የሚገነባ ነው፡፡ ሎት አንድ ከጨሪቲ – ሀገረመቆር (90 ኪሎ ሜትር) ድረስ ያለው መንገድ የሚሸፍን ሲሆን፣ ይህንን መንገድ ለመገንባት ኩባንያው ተዋውሏል፡፡ በሶማሌ ክልል የሚገኙትን የጨሪቲ፣ የጎሮበክሳና ጉራዳሞል ወረዳዎችን ያገናኛል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፣ 12 ቀበሌዎች አቋርጦ ያልፋል፡፡ ቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ይህንን መንገድ ለመገንባት የተዋዋለበት ዋጋ 1.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ውስጥ በብዛት በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ በዋናነት የሚታወቅበት ፕሮጀክት የመጀመርያውን የአዲስ አበባ አዳማ የክፍያ የመንገድ ግንባታው ሲሆን፣ ከአራት ያላነሱ የመንገድ ግንባታዎች ላይም ተሳትፏል፡፡

ማክሮ ጄኔራል ኮንትራክተር የተባለው አገር በቀል ተቋራጭ ደግሞ የፊቅ ሐመሮ ኢሚ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የፊቅ ኪሎ ሜትር 81 የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ለመገንባት ውለታ ገብቷል፡፡ በሶማሌ ክልል የሚገነባው ይህ መንገድ፣ የፊቅና የጎዴ ዞኖች ውስጥ የሚገኙትን የፊቅ፣ የሐመሮ፣ የጊሳንጊስና የመራበልሚ የሚባሉ ከተሞችን አቋርጦ የሚያልፍ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ለመገንባት ያሸነፈበት ዋጋ 819.1 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡

በ36 ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አሥር ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ በወረዳ ከተሞች ደግሞ 19 ሜትር ስፋት ኖሮት የሚገነባ ነው ተብሏል፡፡ ማክሮ ጄኔራል በመንገድ ግንባታ ከባለሥልጣኑ ጋር ተስማምተው ከሚሠሩና ቤተኛ ከሆኑ ተቋራጮች አንዱ ነው፡፡ ከአዳባ አንጋቱ የሚዘልቀውን የመንገድ ፕሮጀክት በ1.24 ቢሊዮን ብር በማሸነፍ ሥራውን ተረክቦ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

አቶ አርዓያ በዕለቱ ኮንትራት ስምምነት ስለፈረሙት ተቋራጮች ብቃትና ተሞክሮ ተናግረዋል፡፡ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ግሩፕ፣ የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ እንዲሁም ማክሮ ጄኔራል ኮንትራክተር የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በመረከብ በጥራትና በጊዜ የማስረከብ ልምድ ያላቸው ድርጅቶች ናቸው ብለዋቸዋል፡፡ እንደዚሁም ኢንቨስትስትሮይ ፕሮኤክት ናቸው ብለዋል፡፡ ኢንቨስትስትሮይ ፕሮኤክት  ከዚህ ቀደም በሠራቸው ሥራዎች በቂ ልምድ እንዳለው በጨረታ ግምገማ ወቅት ለማየት በመቻሉ አሸናፊ የሆነበት የመንገድ ግንባታ ሥራ እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡  

አሸናፊዎቹ ኮንትራክተሮች ጥራቱን እንዲያረጋግጡ የተመደቡት የአማካሪ መሐንዲሶች መንገዶቹ በከፍተኛ ጥራት፣ ሙያው የሚጠይቀውን ከፍተኛ ሥነ ምግባር በመላበስና በፍጥነት በመጨረስ ወሳኝ ሚና እንደምትጫወቱም አቶ አርዓያ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአሁኑ ወቅት የ339 የመንገድ ግንባታና ጥገና ፕሮጀክቶች እንዲሁም የ94 የመንገድ ፕሮጀክቶችን የአዋጭነት፣ የዲዛይንና የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹም በአጠቃላይ 118.3 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ከነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ የ32 ፕሮጀክቶች ግንባታ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጡ ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡ የ2009 በጀት ዓመት ስድስት ወራት አፈጻጸም በምናይበት ጊዜ የ6627 ኪሎ ሜትር የዋና ዋናና የአገናኝ መንገዶች ግንባታ፣ ማጠናከርና ማሻሻል፣ የመደበኛ፣ የከባድ እንዲሁም የወቅታዊ ጥገናዎችን ማከናወን እንደተቻለ የሚያመለክተው መረጃው፣ ይህም ከአጠቃላይ የስድስት ወራት ዕቅድ አንፃር የ88 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉንም ጠቅሷል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ከአምስቱ ኮንትራክተሮች ጋር በተገባው ውል መሠረት ለመንገድ ግንባታው የሚውለውን ወጪ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹን የሚቆጣጠሩ አማካሪ ድርጅት መረጣም ወደፊት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች