Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የስያሜ ያለህ!

   ዛሬ በየመንደሩ መደብሮች ደጃፍ ላይ ተስጣጥተው የምናያቸው የታሸጉ ውኃዎች ከሃያ ዓመታት በፊት በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ሆቴሎች ዘንድ ብቻ የሚገኙ ነበሩ፡፡

እንደ ዛሬው በየደጃፉ የሚደረደሩ፣ በየመንደሩ ለሚቸረችሩ ነጋዴዎች የሚታደሉ አልነበሩም፡፡ መገኛቸው ብዙዎች ከማይደፍሯቸው ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ፣ ያውም ውድ ከሚባሉ መጠጦች ተርታ በቄንጥ የሚደረደሩ ቀበጥ ውኃዎች ነበሩ፡፡

ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ሆቴሎችም የታሸገ ውኃን ከውጭ በማስመጣት ከውድ መጠጦች ጎራ የሚያስቀምጡ ስለነበሩ፣ የታሸገ ውኃ አለን ለማለት በየመደርደሪያቸው ላይ ያኖራሉ፡፡ የውኃው ዋጋም ቢሆን በዚያን ጊዜ ቢራና ሌሎች የአልኮል መጠጦች ይሸጡበት ከነበረው ዋጋ በላይ ቢሆን እንጂ እንደማያንስ የነበረ ያውቀዋል፡፡

በዚያን ወቅት በውጭ ዜጎች ወይም በጥቂት ኢትዮጵያውያን እጅ ብቻ እንደብርቅዬ የቅንጦት ዕቃ ይታይ የነበረው ውኃ፣ በአገር ውስጥ የማይመረትና የውጭ ምንዛሪ ተጠይቆበት ተከፍሎበት ከውጭ የሚመጣ እንደነበር መዘንጋት የለብንም፡፡

ታሪክ ተለውጦ ዛሬ ከ50 በላይ የታሸጉ ውኃዎች በአገር ውስጥ መመረት ጀምረዋል፡፡ ባማሩ መደርደሪያዎችና ባንኮኒ ላይ ይሰየሙ የነበረበት ጊዜ አክትሟል፡፡ ከውጭ የሚገቡ የውኃ ምርቶች የሉም ባይባልም፣ ገበያው ግን አገር ውስጥ ውኃዎች ሆኗል፡፡ ጥቂት ቄንጠኞች ይቀናጡበት የነበረው አልያም በአገሪቱ የባንቧ ውኃ እምነት ጥራትና ንፅህና ላይ ሥጋት ያላቸው ሰዎች፣ የታሸገ የውኃ ይዘው የሚሽከረከሩበት ጊዜ ዛሬ አክትሞ፣ ውኃው ለሁሉም ተዳርሷል፡፡

በፕላስቲክ መያዣ ውኃ በአገር ውስጥ ተመርቶ ለገበያ የዋለው የመጀመሪያው  የታሸገ ውኃ ስያሜ ‹‹ሃይላንድ›› እየተባለ የሚጠራውና ዛሬም ድረስ የወል ስም የሆነው ምርት ነው፡፡ ይህን ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብዬ እንዳስታውስ ያደረገኝ ከሃላይንድ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ገበያውን እየተቀላቀሉ ያሉት የታሸጉ ውኃዎችን ስያሜ አገርኛ ቅኝትና ቃና ያጡበት ምክንያት ግራ ስላጋባኝ ነው፡፡

የታሸገ ውኃ ስያሜዎችን ብትመለከቱ ከአገራችን ምድር የወጣው ውኃ በቱቦ ወደ ፋብሪካ ገብቶ በፕላስቲክ ታሽጎ ለገበያ ሲቀርብ በአንዴ ፈረንጅ ሆኖ ዜግነቱን ይቀይራል፡፡ በማስታወቂያ እንደምነሰማው ከእከሌ ተራራ ሥር የመነጨ ውኃ ተቀድቶ በፕላስቲክ ታሽጎ የቀረበው ውኃ እንደሆነ ነበር፡፡ መጠሪያው ግን ከአገራችን ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ የፈረንጅ ስም የመሆኑ ነገር ምነዋ ለገዛ ውኃችን የሚሆን የእኛ ስም ጠፋሳ? ያስብላል፡፡

‹‹ሃይላንድ›› ተብሎ መጀመሩ ተፅዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌሎች ንግድ ሥራዎችም ቢሆን ቀድሞ አገልግሎት የጀመረ አንድ ዘርፍ ሌሎች ሲገቡበት በቀድሞው ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡ ለምሳሌ ባንክን ብንወስድ አንድ ባንክ ኢንተርናሽናል ብሎ ከጀመረ በኋላ የሚቋቋሙት ሁሉ ኢንተርናሽናል የምትለውን አክለው ሲቀጥሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ኢንተርናሽናል መባሉ ፋይዳው ብዙም ባለመሆኑ ጀማሪው ባንክ ራሱ አያስፈልግም ብሎ ኢንተርናሽናል የሚለውን አውጥቶቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት ተፅዕኖዎች ይኖራሉ፡፡

ከ50 በላይ ከሚሆኑ የታሸጉ ውኃ ምርቶች ውስጥ በአዲስ አበባ ገበያ ላይ ከ26 ያላነሱ የውኃ ምርቶችን ታዝቤያለሁ፡፡ ከእነዚህ ምርቶች አንዱ ብቻ አገራዊ ስያሜ ያለው ነው፡፡ አንዱ ጉራማይሌ ነው፡፡ 24ቱ የታሸጉ ውኃዎች ግን አገራዊ ስም የላቸውም፡፡ ከ26ቱ አራቱ ብቻ ስያሜያቸውን በአማርኛ ቋንቋ ሲጽፉ የተቀሩት  ምርቶቻቸው ላይ የተለጠፉት መረጃዎች በሙሉ የተጻፉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፡፡ ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነውን ምርቶቻቸውን የምንጠቀመው ግን አገሬው እኛው ነን፡፡ እርግጥ ጎብኝዎችንና ቱሪስቶችንም አስበው ይሆናል፡፡ መልካም ነው፡፡ በሁለቱም ቋንቋዎች መጠቀም ይቻል አልነበር ወይ?

ነገሩን ካነሳን ሌላም እንጨምር፡፡ ብዙም ባይሆን አንዳንድ በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ላንሳ፡፡ መድኃኒቶቹን የሚገልጸው ማብራሪያ በሙሉ በእንግሊዝኛ ይጻፋል፡፡ መቼም እነዚህን መድኃኒቶች የሚጠቀምባቸው እዚህ የሚኖር የውጭ ዜጋ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ቢሆንም ስንቱ ነው ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ የተመረቱት ለአገሬው ዜጋ ከሆነ መረጃውን ሙሉ በሙሉ በእንግሊዝኛ ከማድረግ ቢያንስ በአማርኛና በሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ጋር ማድረጉ ምን ነበረበት?  አንዳንድ ጊዜ አሁን የሚመጡ መድኃኒቶች የሚመረቱበት አገር ቋንቋን አስቀድመው ከአምስትና ከስድስት በላይ ቋንቋዎችን በማካተት ስለመድኃኒቱ መረጃ ይሰጣሉ፡፡ እኛ ግን ሾላ በድፍን እየሆንን ነው፡፡

ቻይና ወደዚህ የምትልክልን ምርቶች ላይ በትላልቁ በቻይንኛ የሚጻፈውን ጽሑፍ ትክ ብለን ብንመለከት ፊደሉ መልሶ ይመለከተናል እንጂ ብዙዎቻችን አንረዳውም፡፡ ቻይናውያን ምርቶቻቸው ላይ የአገራቸውን ፊደል ሳይጽፉ አይልኩም፡፡ ካሻቸው እንግሊዝኛ ያክሉበታል፡፡ እኛ ግን ለቻይናና ለሌሎች አገሮች በምንልከው መያዣ ቀረጢት ላይ እንኳ የእኛ መሆኑን የሚገልጽ ነገር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በገዛ ምርታችን ላይ በቋንቋችን ብናሰፍር ምናለ? ለአምራቹም ቢሆን በአገር ቋንቋ መጠቀም ጥሩ ነው፡፡ የገባቸው አንዳንድ ኩባንያዎች ከውጭ የሚመጣ ምርት ቢሆን ምርቱ ላይ በአማርኛ መጻፋቸው ምንኛ እንደጠቀማቸው መረዳት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል ጽሑፍ ተለጥፎበት ሊወጣ የሚችል ምርት የቱ ነው ቢባል እውነት አለው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ጫማና ሸሚዝ በኢትዮጵያ የተሠራ የሚል የእንግሊዝኛም ሆነ የአማርኛ ጽሑፍ አይሰፍርበትም ነበር፡፡ ይኸውም ምርቱ በቀጥታ ለገዥዎች ሳይሆን ለሦስተኛ ወገን ይቀርብ ስለነበር እንደሆነ ይነገራል፡፡

አሁን እየታየ ባለው ሁኔታ ግን አገርኛ ቋንቋን ለመጠቀም የሚጋብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ ገበያው እየመጣ የኢትዮጵያ ምርትም እየተፈለገ መጥቷል፡፡ ከስያሜ ጀምሮ በምርቶቻችን ላይ በራስ ቋንቋ የመጠቀም ባህል እንዲኖር አስገዳጅ ሕግ ቢኖር መብት መጋፋት ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡

እዚህ ላይ ግን በፍፁም ልንስተው የማይገባ ብርቱ ጉዳይ አገራዊ የንግድ ስሞችን ለመጠቀም የአገራችን ሕግ ራሱ ክፉና ንፉግ መሆኑን ነው፡፡ የንግድ ስያሜን የተመለከተው ሕግ በወል ስሞች እንዳንጠቀም የሚገድብ በመሆኑ፣ ይህ ካልተስተካከለ ጣታችንን የምንቀስረው በባህር ማዶ ስም የተለከፉት ላይ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ላይ ነውና ሕጉን ይፈትሽ፡፡ እንደ ሸማች እኛን የሚገልጹ ምርቶችን የመጠቀም መብታችን ይከበር፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት