ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅትን (ዓጤድ) በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት ለሚደረገው የመጨረሻው ውድድር ካለፉት ሦስት ዕጩዎች አንዱ ሆኑ፡፡ ከዶ/ር ቴድሮስ በተጨማሪ ዕጩ የሆኑት ብሪታኒያዊው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮና ፓኪስታናዊቷ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር ናቸው፡፡ ዓጤድ ባለፈው ረቡዕ (ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም.) ያደረገውን የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብሰባውን እንዳጠናቀቀ ይፋ እንዳደረገው፣ ከመጨረሻዎቹ አምስቱ ውስጥ የነበሩት ሁለቱ ተቀናቃኞቹ ፈረንሣዊው ፊሊፕ ዶዝ ብሌዚ፣ ጣሊያናዊው ፍላቪያ ቡስትርዮ ለፍጻሜው ሳያልፉ ቀርተዋል፡፡ ከሦስቱ ዕጩዎች አሸናፊ የሚሆነውና በዋና ዳይሬክተርነት የሚሰየመው ከአራት ወራት በኋላ በሚካሄደው የአባል አገሮቹ ጠቅላላ ጉባኤ ይሆናል፡፡