Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ማን ነው ተረኛ?

ሰላም! ሰላም! ምን ሰላም አለ ዋጋ እያሻቀበ? አትሉኝም። ባለፈው እህል ቅጠል የማይል ፍርፍር ማንጠግቦሽ ሠርታ ብታቀርብልኝ ማላመጥ እንኳ እስኪያቅተኝ አፌ ውስጥ ሳንገዋልለው ነበር። ማንጠግቦሽ ዓይታኝ፣ “እንግዲህ ቻለው! ቲማቲሙም የባለሀብት መሬቱም የመንግሥት ሆኗል!” አለችኝ። የቲማቲሙ ገብቶኛል የመሬቱ ግን ግር ስላለኝ “የመንግሥት ስትይ ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?” አልኩና ጠየቅኳት። “እንደ ድሮው ቢሆን ጓሮ ኖሮን ቲማቲሙን ቤታችን ባበቀልነው ነበር። አሁን ሊዝ ከመጣ ወዲያ እንኳ ለቲማቲም ለሰው የሚበቃ ምን ቦታ ተረፈ ብዬ ነዋ?” አለችኝ። በሌላ አባባል ለጓሮ አትክልት መትከያ መሬት በሊዝ መግዛት ይጠበቅብሀል ነው ነገሩ። ‘የምትለብሰው የላት የምትከናነበው አማራት’ ማለት ይኼ አይደል ታዲያ? ተደራጅተን ቆጥ ላይ መኖር አቅቶናል ማንጠግቦሽ ሆዬ ጭራሽ ስለጓሮ እርሻ ታስባለች።

እንግዲህ ይህን ሁሉ የሚያስወራን የቲማቲም ዋጋ ከሞባይል ካርድ እኩል መሆን አይደል? (ካርዱንስ ኔትወርክ የሚባል  ስለሌለ ባትሞሉት ግድ የለም፣ ሆድ ግን እንዴት?) ምን አሉ መሰላችሁ አንዲት በጡረታ ገንዘባቸው የሚተዳደሩ ሴት አዛውንት። “እስኪ አንድ ኪሎ ቲማቲም መዝንልኝ?” ይሉታል አሉ ባለአትክልት ቤቱን። “ዋጋውን ሰምተዋል አይደል?” ይላቸዋል ኋላ ሁለቴ እንዳይደክም ፈርቶ። አዛውንቷም፣ ‹‹የዘመኑ ሥራ ግሽበት ነው! ያው ጨምሯል ልትለኝ አይደል? በልማ መዝንልኝ፤›› አሉት ቆጣ ብለው። “እሺ! ለማንኛውም 25 ብር ሆኗል፤” ሲላቸው ያን ያህል ጭማሪ ስላልጠበቁ በተዘበራረቀ ስሜት አካባቢውን በዕልልታ አቀለጡት። “ምን ተገኘ?” ሲሏቸው፣ “‘የሞት መድኃኒት ተገኘ!’ ብዬ ነዋ!” አይሉ መሰላችሁ? ይህንን እንደሰማሁ የሳቅኩትን ያህል እየቆየሁ ከቲማቲም ዋጋ መናር አንፃር የአዛውንቷን ግነታዊ ማነፃፀሪያ ሳብላላው ሳግ አነቀኝ። ኧረ! ኧረ! እስከ መቼ ይሆን እንዲህ በኑሮ እያሾፍን ሳንኖር ሞት የሚቀድመን?!

አዎ! ስለኑሮ ሸክም አወራለሁ ብዬ ሌላ ሸክም ቁለላ ውስጥ ተደነጎርኩ። መቼስ ወግ አይደል። ወግ ደግሞ በዓይን ይገባል። አሁን እንኳ በቴክስት፣ በቫይበር፣ በፌስቡክና በትዊተርም እየገባ ነው። ማን ዓይን ለዓይን ይተያያል? እውነቴን ነው። ስንተያይም የራሳችንን ምሰሶ ሳንነቅል የሰው ጉድፍ ካላወጣን እያልን አገር ይያዝልን ሆኗል ሙያችን። ይኼው ያልነው አልቀረልንም፡፡ እማማ ኢትዮጵያ ይህቺ የሆሜር ድርሰት አድማቂ፣ የሦስት ሺሕ ዓመት ተጀምረው ያልተጨረሱ ሥልጣኔዎች ባለቤት፣ እርስ በርስ በመነቋቆርና በመጠዛጠዝ ግርግር ተይዛልን አረፍነው። እሰየው አይባል አገር፣ እንቢየው አይባል ፍቅር ነስቶን በ‘ምን አባህ! የት አባሽ! ምን ታመጣለህ?! ምን ታመጫለሽ?!’ ግልምጫ ማን አለብኝነታችን ፋፋ። “ምነው ግን በልጅነታችን የበላነው ፋፋ ደግ ደጉ ባህላችን ላይ አላፋፋን አለ?” ብዬ የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው፣ “ከጥያቄህ በፊት የሚቀድመው ‘ስንት ፐርሰንቷ ኢትዮጵያ ናት ይኼን ምግብ እኩል ተመግባ የፋፋችው?’ የሚል ጥያቄ አለ፤” ብሎኝ አረፈው። እሱ ደግሞ እንዴትም እንዴትም ብሎ ‘ፐርሰንት’ እና ‘ዕድገት’ የሚባሉ ቃላት ንግግሩ መሀል መደንጎር ይወዳል። ኤድያ!

እኔም ቆርጦ አይቆርጥልኝ ዞሬ ዞሬ ለእሱው ነው የሆዴን የማጫውተው። ሆዴ ከሞላና ጨዋታ ‘ኤክስፖርት’ የማድረግ አቅም ካለው ነው ታዲያ። ለነገሩ ተመስገን ነው! እኛ እኛ ምንም አንልም። ለእነሱ ለእነሱም በልማታዊ ብልፅግና ጎርፍ በሥልትና በጥበብ (ጥበብ የሚለው የፀደቀ ስለመሰለኝ አቋራጭ ማለቱን ትቻለሁ) ተሽለው ለሚታዩትም አገሩ አማን ነው። ግን ደግሞ አሉ ወዲያ። ከአደባባዩ ባሻገር፣ ፍሳሽ እያስመለሰ ከተማችንን ከፊል ጎርፋማ ከሚያደርገው ፉካ ሥር የሚያድሩ። መጠለያና ንፁህ ምግብ ማግየት፣ መንግሥተ ሰማይ ‘ቪአይፒ’ ቦታ ከማግኘት እኩል የሆነባቸው ደግሞ አሉ። ‘እንዴት ይረሳል?’ እንዳለው የትዝታው ንጉሥ!

ታዲያ በቁሜ የማየው የዚህች ዓለም ትዕይንት በሐዘን እያፈዘዘኝ በቁሜ ላንኮራፋ ‘ሲንግል ዲጂት’ የሮሮ ዕድገት ሲቀረኝ እባንንና እጄ ላይ ያሉትን ሥራዎች ለመጨራረስ እቃብዛለሁ። እዚያ የሚከራይ ቤት አለኝ። ወዲህ ወደ 12.8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቪላ ቤት፣ ተከራይና ገዥ የሚፈልጉ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎችማ አልቆጥርላችሁም። ግን መምረጥ ይከብደኛል። ‘የቱን ቅድሚያ ልስጥ? ማን ደውሎልኝ ነበር? ምን ፈልጎ?’ ስል የሚታዘበኝ አንድ የሙያ ባልደረባዬ “አይ አንበርብር አንተም ብለህ ብለህ እንደ ሰፊው ሕዝብ ግራ ተጋባህ?” ይለኛል። እንደምታውቁቱን ባልተጻፈው የጠቅ ጠቅ ፎርሙላችን እገዛ መናገር የምንፈልገውን ቀጥታ ተናግረን አናውቅም። መናገሩን ትታችሁትን መንገድም ቀጥ ብለን አንራመድም። ለምሳሌ፣ ከቤት ወጥተን ጎረቤት ቤት ገብተን፣ ከጎረቤት አውርተን ደግሞ ዕቃ ረሳን ብለን ቤታችን ተመልሰን ገብተን፣ ከዚያ ተመልሰን የሠፈራችን ሱቅ ወይም ከአንድ ባለሻይ ቤት ወዳጅ ጋር አቶክቱከን፣ ከዚያ ነው ሊመሽ አካባቢ ሠፈር የምንለቀው እንጂ ከፈረንጅ እኩል 24 ሰዓት ተሰጥቶን ይኼን ያህል የኑሮና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዴት ይመጣል? ደግሞ ይኼን ልናጣራ ነው ብላችሁ ዙሩን አክሩት አሉዋችሁ። ሆሆ!

አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ መግዛት የሚፈልግ ደንበኛዬን አንጋግሬ ሳበቃ ሳይውል ሳያድር ላሳየው ቀጠርኩት። ያው እንደምታውቁት በአገራችን መቅጠር እንጂ መድረስ ከባድ ነው። ማቀድ እንጂ ማሳካት ህልም ነው። ማፈንዳት እንጂ ማምከን እንዴት ጭንቅ እንደሆነ ለኖረ አይነገረውም። “. . . ዳሩ ትናንትን ዛሬ እያሰከረው ብዙ ነገር የገባን መስሎን ሳይገባን እየዘለለን ነው። ከታሪካችን አስታውሰን ልንማርበት የሚገባንን ሁሉ እንደምንዘለው ለጤናችን አስበን ገመድ እንኳ አንዘልም፤” ይሉኛል ባሻዬ የሰሞኑን አጥንት ሰርሳሪ ብርድ ቁርጥማት ጨምድዶ ቤት እያስቀመጣቸው ልጠይቃቸው ስሄድ። መቼም እሳቸውን ታውቋቸዋላችሁ። ሲያመሩም ሲቀልዱም ወግ ይችሉበታል። ደግሞ መቼ ዕለት ነው፣ “አንተ ተው እንጂ? ምነው ወጣት ካልተሆነ በረደኝ ተብሎ ሚስት አይፈለግም እንዴ? እስኪ ሚስት ፈልግልኝ፤” አሉኝ።

“አይ ባሻዬ በፍለጋ ቢሆን ነፋስ እስከዛሬ ስንት ሚስቶች ይኖሩት ነበር?” ስላቸው ከት ብለው እየሳቁ፣ “እኔ እኮ ገለባ ስለማንገዋልል አልጠየቅኩህም? ከአጨዳና ከጉልጓሎ የቱ እንደሚቀድም የተምታታበት ትውልድ በ‘ኢንተርኔት’ የትዳር አጋር ሲጎለጉል ይውላል ሲባል ስለሰማሁ ለምን ይቅርብኝ ብዬ እንጂ። በላ ምን ይጎድለኛል?” ብለው ሳቃቸውን እስኪጨርሱ አጀብኳቸው። ባሻዬ ለቀልድ ነገሩን አነሱት እንጂ እንኳን ትዳር ወገባችንን ታጥቀን የተያያዝነው የአገር ልማት በጎደለ ተሞልቶም አልሞላ ብሏል። እናላችሁ ከሕዝብ ተቀላቅዬ ወደ ደንበኛዬ ስገሰግስ አንዱ፣ “በቅርቡ ሳተላይት እናመጥቃለን የሚሉን መጀመርያ መቼ ምድር ለምድር መጠቅን? የታለ ራዕያችን? ወሬ ከመደራረብ ምናለበት ከሥር ከሥሩ ጫና ብናቀልና የዋልንበትን አረም ባይበላው?” እያለ ሰውን ሲያስጨንቀው ሰማሁ። ተጨንቆ አስጨናቂ ብቻ ይሙላው መንገዱን?!

በሉ እንሰነባበት። ሆድ ስለባሰኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ደወልኩ። የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተገናኝተን አንድ አንድ ስንል አመሸን። ብርዱ በአጥንት ይገባል። ብንጠጣ ብንበላ አልሞቀን ብሏል። “ዘንድሮ ደግሞ በንፋስ ሊያጥበን ነው መሰል ሐሳቡ?” ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ይኼን ሲል አንዱ ከሩቅ ሰምቶት፣ “ንፋስ ምን አለን? ከሕግ በላይ የሚወበራውና አላስቆም አላስቀምጥ ያለን አልጠግብ ባይ ጉቦኛ የሚያጥበን አይብስም?” አለው። “ነገር መጣልህ!” አልኩና የካፖርቴን ኮሌታ ወደ ላይ ቀስቼ ጠንቀቅ ብዬ ተቀመጥኩ። ተጠንቅቀንም መዳናችንን እርግጠኛ አይደለንም እንዳትሉ ብቻ። ወይ እናንተ!

“እና ምን ይሻላል?” አለው አንዱ ተናግሮ አናጋሪ ከወዲያ በኩል የተቀመጠ። “ማጥራት ነዋ። ማፅዳት ነው መፍትሔው። ሳይታክቱ መጥረግ፤” አለው። እኔ ብርዱን አልቻልኩም። የባሻዬን ልጅ ተሰናብቼ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ስደርስ ቤቱ ተተራምሷል። “ምንድነው እሱ?” ስላት ማንጠግቦሽን፣ “ቤት እያፀዳሁ!” አለችኝ። ወገቧ እስኪቆረጥ ጎንበስ ቀና ትላለች። “በዚህ በሌሊት እንደ ዕብድ? ደግሞስ ከላይ ከላይ አፅድተሽ ሲነጋ በደንብ አታፀጂም?” ብላት “ ‘ሱፐርፊሺያል’ ፅዳትና ሥራ ነው አንድ ወደፊት አስኪዶ ሦስት ወደ ኋላ እየሳበ ያስቸገረን፤” ብላኝ እርፍ። ብርዱ ላይ የማንጠግቦሽ እንግሊዝኛ አጠቃቀም ሲጨመርበት አዞረኝ። ዘልዬ አልጋዬ ላይ ወጣሁ። ለማለት የፈለገችው ግን ገብቶኛል። ጥልቀትና ጥራት የሌለው፣ የታይታ፣ ከአንገት በላይ ፅዳት በዛ ማለቷ ነው፡፡ ዛሬ ከትናንት እንደማይሻል ሁሉ አንገት እያስደፋን እባቡን፣ ጊንጡን፣ አይጡንና ምስጡን አደላድሎ አስተኝቶብናል። እኮ እስከ መቼ በታይታ ሥራና በአገም ጠቀም አካሄድ እንታሻለን? እስከ መቼ ከላይ ከላይ? ይኼን ጊዜ ነው እኔ አለሁ የሚል ትጉህ የሚፈለገው፡፡ ማን ነው ተረኛ? መልካም ሰንበት!       

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት