Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየተሃድሶ መድረኮቹ የክርክር ከፍታዎች

የተሃድሶ መድረኮቹ የክርክር ከፍታዎች

ቀን:

በመንግሥቱ መስፍን

መንግሥት ያልተገመተና ድንገተኛ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ካደናገጠው በኋላ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ‹‹በወታደር ማሠልጠኛ ካምፖች›› አስገብቶ ሥልጠና ለመስጠት ተገዷል፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚገመት የወደመ ሀብት የካሳ፣ የግብር እፎይታም ሆነ ተጨማሪ የማካካሻ ሥራ ለመሥራትም ተንቀሳቅሷል፡፡

ከዚሁ ባልተለየ ሁኔታ ከገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚና ከፍተኛ አመራር እስከ ታችኛው እርከን ካድሬ ድረስ ‹‹በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ›› ተጀምሯል፡፡ ባሳለፍናቸው ቀናት ደግሞ የንቅናቄ ግምገማው በሲቪል ሰርቫንቱና በሕዝብ ደረጃም እየተካሄደ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ከዚያም ለየት ባለ መስክ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ያለ ‹‹ውጤቱ የታወቀ ምክክር›› ሳይሆን፣ ይነስም ይብዛም በመርህ ለመደራደር የሚያስችል ውይይት ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ጀምሯል፡፡ ተስፋ ያለው ጅምርም መስሏል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ከአመራሩና ካድሬው አልፎ መላው የሲቪል ሰርቪሱ ተዋናይ እያደረገው ባለው ምክክር እየተነሱ ያሉ ነጥቦችን ለማየት ተሞክሯል፡፡ በተለይም ደግሞ የክርክሩ ከፍታ ጣሪያ የነካባቸውንና በብዙዎቹ መሥሪያ ቤቶች በተመሳሳይ ስሜት እየተነታረኩባቸው ያሉትን ነጥቦች በማንሳት፣ አንባቢያን እንዲፈትሹዋቸው ማድረግ ፈልጌያለሁ፡፡

ዕውን በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯልን?

የብሔራዊ መግባባት አጀንዳ አዲስ ውዝግብ የፈጠረ ነጥብ ሆኗል፡፡ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችን በዓል በማክበር ‹‹አንድነታችን ተረጋግጧል›› ማለት ይቀናዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከማንነትም ሆነ ከእምነት አንፃር ያላቸውን የሰላም ቀናዒነትና የአገር ፍቅር ስሜትና መቻቻልም ‹‹እንደ ብሔራዊ መግባባት›› መቁጠር ከጀመረ ከራርሟል፡፡ በቅርቡ በአንድ የመንግሥት ጋዜጣ ላይ የኢሕአዴጉ ቱባ ሰው አቶ ስብሐት ነጋ ግን እውነቱን ፍርጥ አድርገው ብሔራዊ መግባባት ቅርቃር ውስጥ መውደቁን ካነሱ በኋላ፣ ሁኔታው ተቀይሯል፡፡ አዲስ ውይይት (Discourse) ተቀስቅሷል፡፡

መንግሥት ‹‹ብሔራዊ መግባባት በሁሉም ጉዳዮች ላይ ሊፈጠር አይችልም›› ይላል፡፡ ያም ሆነ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ላይ ከተፈጠረ ሌሎቹ ጥቃቅን ጉዳዮች ተግባብተውም ሳይግባቡም ሊቀጥሉ ይችላሉ ባይ ነው፡፡ እንደ አቦይ ስብሐት ዓይነቶቹ ደግሞ ባለሀብቱ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል በነፃነት ተዟዙሮ የመሥራት ዋስትናና ሕዝባዊ መተማመን ካልተፈጠረ ምን ዓይነት መግባባት አለ ይባላል ይላሉ፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ሲባል በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በክልሎች የተካሄዱ መድረኮች በብሔራዊ መግባባት ጉዳይ የተነሱ ሐሳቦችን መርምሬያለሁ፡፡ በብዙዎቹ አረዳድ አሁንም ጉዳዩ አገራዊ መሠረት የያዘ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ አሁን በሥራ ላይ ካለው ባልተናነሰ የቀድሞውን ሙሉ (አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ) ሰንደቅ ብሎ የሚመርጠው ዜጋ ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ አንዳንዱም በሕግ ፀድቆ ዕውቅና ያልነበረውን የፓርቲ ዓርማ ከፍ ማድረግ ይመርጣል፡፡ ይኼ ለምን ሆነ ባይባልም በዚህ ደረጃ ልዩነቱ ለምን መጣ?! የሚለው ጥያቄ ግን ያወዛግባል፡፡

በአገሪቱ በተሠሩና እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች ላይ የተፈጠረው የባለቤትነት ስሜትና ብሔራዊ መግባባትም ጥያቄ ላይ ወድቋል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱ ዋና ዋና ክልሎች በተነሳ ሁከት ከፍተኛ ጥቃት የደረሰባቸው የአገርና የሕዝብ ሀብቶች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የአገሪቷን መዳከም የሚሹ የውጭ ተባባሪዎች ቀውሱን ቢያባብሱትም ሥራ እየፈለገ ያለ ወጣት በትልልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ የእርሻ ልማቶችና የማኀበር ኢኮኖሚ ተቋማት ላይ እሳት ሲለቅበት ስቅጥጥም አለማለቱ ይኼንኑ መጥፎ ዝንባሌ ያሳያል፡፡ ይኼ ደግሞ አንድም ‹‹ልማቱ እልጠቀመኝም›› ወይም ‹‹የኔ አይደለም›› ከሚል እምነት የሚነሳ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ‹በእኔ ሀብት ሌሎች እየበለፀጉበት ነው› የሚል ሰንካላ ሐሳብ ውስጥ በመውደቁ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ድርጊቱን ጠመንጃና ወታደር አስቆመው እንጂ ብሔራዊ መግባባትና መደማመጥ አልታደገውም?›› የሚሉ ተወያዮች ድምፅ ጎልቶ ተሰምቷል በአሁኑ ተሃድሶ መድረክ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንኳን ብሔራዊ መግባባት ፈጥረው የጋራ መተማመን ያላመጡት የዴሞክራሲ ሒደቱ ላይ ነው፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማት በሚባሉት ላይ በተለያዩ መድረኮች በስፋት እንደተነሳው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እምባ ጠባቂ ተቋም፣ መገናኛ ብዙኃን (የመንግሥት የሆኑት) መከላከያ፣ ፍርድ ቤቶች፣… ላይ የገለልተኛነት ጥያቄ ደግሞ ደጋግሞ ይስተጋባል፡፡ በተለይ ከገዢው ፓርቲ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባህሪ አንፃር መንግሥትና ፓርቲ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ እርስ በርስ ተጠላልፈው መቀጠላቸው የአማራጭ በሮችን እንደዘጉ ተደምጧል፡፡ ለቀጣዩ ጊዜም አሳሳቢ ፈተና ተብለዋል፡፡  

ገለልተኛ ሆኖ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት በሌሉበት ደግሞ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተሟላ መንገድ ማክበርም ሆነ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መካሄድ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሌላው ቢቀር ሦስቱ የመንግሥት ክንፎች (ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው) በገለልተኛነት ‹‹የቼክና ባላንስ›› ሥርዓት ሊያሰፍኑ አይችሉም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት እየተዳከመ የመልካም አስተዳደር ዕጦትም መባባሱ አይቀሬ መሆኑ ላይ ጥቅል ሙግት ተነስቷል፡፡

ከእነዚህ ዋና ዋና እውነታዎች ባሻገር በክልሎች ወሰን፣ በማንነት ጥያቄ፣ በሥልጣን አተያይ፣ . . . ዓይነት ጉዳዮች ላይ ያለው ልዩነት ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል የሚያስብል አይደለም፡፡ ወይም ጉዳዩ ገና ሰፊ ሥራ የሚጠይቅና ‹‹ብሔራዊ እርቅና መግባባት›› ወደሚል ሌላ አዲስ ዘውግ ማደግ ያለበት እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡

ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል አለ ተብሎ ይታመናል?

በዘንድሮው የትልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ውስጥ ከሹክሹክታና አሉባልታ ዘሎ አደባባይና መድረክ ላይ የወጣው ጉዳይ ‹‹ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የለም›› የሚለው አጀንዳ ነው፡፡ በሚኒስቴር ደረጃ ካሉ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚዎች እስከ ተራው ዜጋ ድረስ የትግራይ (ሕውሓት) የበላይነት አለ የሚለውን አስተሳሰብ ይዘው መቆየታቸውን ግለ ሒስ መንሳታቸው ለአባባሉ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ብሔሮች (አማራ፣ ኦሮሞ፣ . . .) ባለን ሀብት ተጠቃሚ አልሆንም፣ እንደ ብዛታችን የድርሻችንን አላገኘንም፣ . . . በሚል ቁዘማ ውስጥ መሰባሰብ ችለዋል፡፡

መንግሥት በበኩሉ አገሪቱ የምታመነጨውን ሀብት፣ የብድርና የዕርዳታ ምጣኔ ሀብት በፍትሐዊ የፌዴራል በጀት ቀመር ለክልሎች አከፋፍላለሁ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችንም (መንገድ፣ ባቡር፣ የኢንዱስትሪ፣ ፓርኮች . . .) ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ ከሕዝብ ተጠቃሚነትና ከሀብት አመቺነት አንፃር በማመዛዘን እያስፋፋሁ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በየክልሉ ባሉ አስተዳደሮችና ብሔራዊ ድርጅቶች ድክመት የተነሳ በተፈጠረ የልማት መፋዘዝና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ምክንያት ወደ ሌላ ጣት በመቀሰሩ እንጂ፣ አንዱ የበላይ ሆኖ የሚወጣበት ዕድል ዝግ ነው ሲል ይከራከራል፡፡

ያም ሆነ ምንም ዓይነት የብሔር ባርኔጣ ሳይጋርዳቸው በሙስናና በአቋራጭ መንገድ የበለፀጉ ጥገኞች በየክልሉ ተንሰራፍተዋል፡፡ ከትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ወይም ደቡብ ሳይባል ንፋስ አመጣሽ ሀብት ላይ የተቆናጠጡ ጥገኞች ሕዝብን ሊወክሉ አይችሉም፣ መጋለጥም እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ በእርግጥ ይኼን ሐሳብ ብዙኃንም ተቀብሎታል፡፡ ግን ከወሬ ያለፈ ተግባር የሚያስፈልገው ነው፡፡

ሕወሓት የኢሕአዴግ ቀዳሚ መሥራች በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በትጥቅ ትግሉም ከነበረው አስተዋጽኦ አንፃር ‹‹የበላይ እየሆነ ነው›› የሚል ወቀሳ ከ25 ዓመታት በፊትም ሲነሳበት ነበር፡፡ ገና የምርኮ መሣሪያ ከመከፋፈል አንስቶ በሥልጣን አያያዝ፣ በመከላከያና በደኅንነት መስኩ ያለው ስብጥርም በሒስ ውስጥ የዘለቀ ነው፡፡ ይኼ ‹‹ማንነት›› በተለይ (ብሔርና ቋንቋ) ማድረጊያና መፈናጠሪያ በሆነበት አገር ውስጥ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ ትልቁ ችግር ግን የተፈጠረው አሁን መንግሥት ‹‹ለየሁት›› እንደሚለው ሥልጣን አተያዩ ችግር ሲደመርበት ነው፡፡

ሥልጣን መያዝ ሕዝብ ለማገልገልና አገር ለመጥቀም መሆኑ ይቀርና ራስንና ‹‹የቅርብ ወገንን›› ለመጥቀም ሲውል የከፋ መሆን ጀምሯል፡፡ ያኔ በትግል ወቅት ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ሌላውን ነፃ ለማውጣት የተፋለሙ የሕዝብ ልጆች፣ በዚያው ሕዝባዊነት ቀጥለው ሥልጣንን ለሕዝብ ጥቅም በፍትሐዊነት እያዋሉ ነው ለማለት ይቸግራል፡፡ አንዳንድ ጠንካራ ታጋዮች አሁንም ቃላቸውን ጠብቀው ለአገርና ለሕዝብ ቢሠሩም አብዛኛው ጥቅም አጓጉቶታል፡፡ መዝብሮና አሻጥሮ ቱጃር የሆነና ለመሆን የሚሹለከለክም ትንሽ  አይደለም፡፡ ስለዚህ ተወያዩን ሁሉ እያስማማ የመጣው በሁሉም መስክ የእርስ በርስ ቁጥጥር ሥርዓት እንዲጠናከር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲበረታ፣ ብሎም የሁሉንም የአገሪቱ ሕዝቦች ስብጥር ምጣኔ እያጣጣሙ መሄድ እንደሚገባ የሚያሳስብ ነው፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ የተያዘው የተለጠጠ ፕሮፖጋንዳ ግን አፍራሽ የጥላቻ ዘመቻ ነው፡፡ በድህነት ውስጥ ሆኖ ችግርን ለማሸነፍ እየባዘነ ያለውን የሰሜን አርሶ አደር ሕይወትንም ያልመረመረ አባባል ነው፡፡ ነገር ግን ሥልጣንም ጨብጦ ይሁን ትግሪኛ ተናጋሪ በመሆን እየተሳሳበ ያልተገባውን ጥቅም ያጋበሰ ሁሉ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ መደረግ አለበት የሚለው በየውይይት መድረኩ ተደጋግሞ እየተነሳ ነው፡፡ በዚህ መንገድ መቀጠል እንደማይቻልም በማሳሰብ፡፡

ለአብነት ያህል በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ‹‹በኢንቨስትመንት›› ስም ተሠማርተው መሬት፣ ብድርና ከቀረጥ ነፃ ተጠቅመውም ሥራ መሥራት ያልቻሉ፣ ለግብርና ለኢንዱስትሪ የተበደሩትን ገንዘብ በከተሞች ቦታ ሕንፃ እየያዙ በከተሞች ኪራይ የሚሰባሰቡ ሰዎች፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ያሉ አመራሮችን እጅ እየጠመዘዙ በሕገወጥ መንገድ መሬት የሚወሩ ‹‹ወሮበሎች›› ሁሉ ሕግና ሥርዓት ሊበጅላቸው ይገባል ተብሏል፡፡

እዚህ ላይ መንግሥትም የጀመረው የማስተካከያ ዕርምጃ እንዳለ ሆኖ፣ ሕዝቡም በባለቤትነት ስሜት ሕገወጥነትን መፋለም ይኖርበታል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያለው ባለሙያና አመራር ባለመታገሉ እያቆጠቆጠ ያለውን ዝንፈት ተገንዝቦ ከአድርባይነት መውጣት እንዳበትም ተመክሯል፣ ተዘክሯል፡፡

በመንግሥት በኩል ሥልጣንና ሀብትን (ተጠቃሚነትን) በፍፁም አብዮታዊነት መነጣጠል አለበት፡፡ ዛሬ በቀላሉ የማይገኙት ቤት፣ መኪና፣ ጥሩ መብላትና መልበስ፣ ልጅን በውድ ትምህርት ቤት ማስተማር፣ . . . ወዘተ ሥልጣን በመያዝ ብቻ የሚገኙ መሆን የለባቸውም፡፡ በሥራ ትጋትና በሕዝባዊነት ጭምር ሊታገዙና እላፊ መሰብሰብንም የሚያስቆሙ መድኃኒቶች ሊበጁ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ‹ሥልጣን ወይም ሞት› ከሚል ኋላቀር ብሒል ወጥቶ ዴሞክራሲውንም ፎቀቅ ለማድረግ ይቻላል፡፡ ፍትሐዊነትም ይበልጥ ይሰፋልናል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ያልፈታቸው ችግሮች የሉም?

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዝኃነት ለሞላባቸው የሦስተኛው ዓለም አገሮች ከፌዴራሊዝም ሥርዓት የተሻለ መንግሥታዊ አወቃቀር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ላይ የሚነሱ መከራከሪያዎችም እየጠበቡ የመጡት ለዚሁ ነው፡፡ ያም ሆኖ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ትናንትም ሆነ ዛሬ (በጥልቅ ተሃድሶው) እየተነሳበት ያለው ጥያቄ ግን፣ ሥርዓቱ አሁንም ያልፈታቸው ችግሮችና ያልመለሳቸው ጉዳዮች አሉ የሚለውን ነው፡፡

አንደኛው ፌዴራሊዝሙ ይበልጡን ለቋንቋና ለብሔር በሰጠው የተለጠጠ ዕውቅና ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን በማስፋቱ ይወቀሳል፡፡ በተለይ በታሪክ አጋጣሚ እየተገባና እየተዋለደ ውህደት በፈጠረ ማኅበረሰብ ውስጥ መጠራጠርና መገፋፋት እንዲንሠራፋ አድርጓል ተብሎም ይተቻል፡፡ በዚህ ላይ በታሪክ የነበረው የሥርዓቶች መቆራቆስና ሽሚያ (ባለሥልጣናቱ በወጡበት ማኅበረሰብ ላይም እየተንፀባረቀ) ለመነቋቆር ለሴራ ፖለቲካ አመቺ መሬት ሆኗል፡፡

ይህ መንገድ ለዘመናት የብሔር ጥያቄ ለነበራቸውና ማንነታችን ተጨፍልቋል ለሚሉ ወገኖች መነቃቃትን መፍጠሩ አይታበልም፡፡ ነገር ግን ሁሉም የዚህች አገር ሕዝቦች በአንድ ሉዓላዊ ድንበር፣ ባንዲራ፣ መንግሥት ሥር እንደመሆናቸው የጋራ የሚሏቸው እሴቶች እንደ ፈርጥ እየጎመሩ መሄድ ነበረባቸው፡፡ የዚህ ፖለቲካዊ ምኅዳር አለመጠናከር ደግሞ አሁንም ድረስ ዜጎች ማንነታቸውን እየፈለጉ በብሔር መደራጀት፣ ዞንና ወረዳ ለመሆን ውሸትና መሰል ‹‹የማንነት› ድንክዬ ዕይታ እንዳይበቁ እያደረጋቸው ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚያም አልፎ የክልሎችና የወረዳ ወሰን ዜጎችን ጦር የሚያማዝዝ፣ መንግሥትንም ከሥራ የሚያናጥብ አጀንዳ እስከመሆን ደርሷል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ብሔር ተኮር መሆኑ በፖለቲካ ሥዕሉ ብቻ አይደለም የሚታየው፡፡ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው መስተጋብር ረገድም ጎልቶ መንፀባረቁ አገራዊውን መልክ እያወየበው ይገኛል፡፡ ዛሬ በአገሪቱ ያሉ የባንክ፣ የኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎትም ይሁን የእርሻ አክሲዮኖች ብሔር ብሔር ይሸታሉ፡፡ የባለሀብቱ ፍሰትም (የግሎባላይዜሽን መርህ በሚናኝበት ጊዜ) ወደ መንደሩ ማማተር ይቀናዋል፡፡ ዕድር፣ ማኅበርና ጋብቻን የመሳሰሉ የማኅበራዊ ማንነታችን አስኳሎችም ኅብረ ብሔራዊነትን እያጡ መጥተዋል፡፡ ….. ይኼ አካሄድም ያለጥርጥር የአብሮነት ማበብን አያሳይም፡፡

ከወራት በፊት የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው፣ ‹‹የፌዴራል ሥርዓቱ ያገለላቸው ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያላቸውና ኢትዮጵያዊነትን የመረጡ ዜጎች ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ ቁጥራቸውም እንደሚገመተው ትንሽ አይደለም፤›› ሲል ሸራተን አዲስ በተካሄደ የፖለቲካ ክርክር ላይ ሐሳብ ሰንዝሮ ነበር፡፡ በወቅቱም የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይኼው ሐሳብ በአሁን ጥልቅ ተሃድሶ በብዙኃኑ ጎልቶ መውጣቱ ፌደራሊዝም ያልመለሳቸው ጥያቄዎች መኖርን ያሳያል፡፡

ተሳታፊዎች እንደሚገልጹት ለምሳሌ በታሪክ አጋጣሚ አሁን አማራ ክልል ከሚባለው መስተዳደር ውጪ ያሉ የአማራ ብሔር አባላት አምስት ሚሊዮን ይደርሳሉ፡፡ በሐረር እስከ 30 ሺሕ፣ በአርሲና አካባቢው እስከ 700 ሺሕ፣ ድሬደዋ፣ ሐዋሳ፣ ናዝሬት፣ ጅማ፣ ዲላ፣ አርባ ምንጭን በመሳሰሉ ከተሞችም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪም ግንዱ ይኼው ማኅበረሰብ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ታዲያ በአንድም በሌላም ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ተዋልደውና ተዋህደዋል፡፡ ይሁንና ሥርዓቱ ‹‹ብሔራቸውን እንዲወስኑ›› ስላስገደዳቸው እንጂ ማንነታቸው ኅብረ ብሔራዊ (ኢትዮጵያዊ) ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት ሥርዓቱ እንዳገለላቸው ነው የሚቆጥሩት፡፡

አንዳንዶቹ ለዘመናት በሚኖሩበት አካባቢ በማንነታቸው ብቻ የመምረጥና የመመረጥ መብት የላቸውም (የኦሮሚያን ሕገ መንግሥት ያጤኑዋል)፡፡ ለመደራጀት፣ ብድር ለማግኘት፣ መሥሪያና መሸጫ ሼድ ለማግኘት ያለው ፈተናም የዋዛ አይደለም፡፡ በኦሮሞ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ልዩ ልዩ ማንነቶች ላይም እንዲህ ዓይነት ውህደቶች የተፈጠሩባቸው ዜጎች በየመድረኩ እየወጡ፣ አባቴ ከዚህ እናቴ ከዚያ እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ የማን ብሔር አባል ነኝ የሚል የማንነት ምስቅልቅል ላይ ሲወድቁ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ግን እስከ አሁን መልስ ያገኘ ጉዳይ አይደለም፡፡

እንግዲህ ጥልቁ ተሃድሶ ከፍ ያለ ጥያቄ እያስነሳበት ያለው የፌዴራል ሥርዓቱም ቀስ በቀስ ማስተካከያ መፈለጉ አይቀርም፡፡ ለጠባብነትና ለዘረኝነት የተለጠጠ በር የከፈቱ የሚመስሉና ለኢትዮጵያዊ ማንነት ዝቅተኛ ግምት የሰጡ አንቀጾች፣ መመርያዎችና አስተሳሰቦች ሁሉ ሊፈተሹና ሊታረሙ ግድ ነው፡፡ አገር ሊቀጥል የሚችለውም በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን አቋራጩ መንገድ ውድቀትና መንሸራተት መሆኑ አይቀርም፡፡

በአጠቃላይ አገሪቱ ከሞላ ጎደል በከፍተኛ ግምገማና ስብሰባ ላይ በወደቀችበት በዚህ ወቅት፣ በርካታ አከራካሪ ነጥቦች መመዘዛቸው አይቀርም፡፡ እኔ እንደ አንድ ዜጋ የክርክር ከፍታ ያየሁባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ብቻ በመጠቃቀስ ለመተንተን ሞክሬያለሁ፡፡ በመስማማትም ይሁን ባለመስማማት ሐሳብ ብንለዋወጥባቸው በእጅጉ ደስ ይለኛል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም ቢሆን ይኼን የሐሳብ መንሸራሸር ይጠላው አይመስለኝም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...