Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየባህልና የልማት መብቶች ተቃርኖ

የባህልና የልማት መብቶች ተቃርኖ

ቀን:

Anchorበውብሸት ሙላት

በፌደራሉ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አርብቶ አደሮችን የሚመለከቱ የተወሰኑ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው መሬት ያለምንም ክፍያ የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን በመግለጽ ለከብቶቻቸው እርባታም ሆነ ለሌሎች አገልግሎቶች ከሚጠቀሙበት መሬት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚፈናቀሉ ከሆነ ከቅድሚያ ካሳ የመከፈል መብት ያላቸው መሆኑን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት በልማት ወደኋላ ለቀሩ አርብቶ አደሮች ድጋፍ ማድረግ ያለበት መሆኑን የሚያሳስበው ድንጋጌ ነው፡፡ ሁለተኛውን በተመለከተ፣ ቀድሞ በቦርድ የሚመራ አንድ ተቋም የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በፌደራልና አርብቶ አደሮች ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ልዩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከላይ የተገለጹት በዋናነት የሚያያዙት ከኢኮኖሚያዊና ከልማት እንዲሁም ከማኅበራዊ መብቶች ጋር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱ በተጨማሪ፣ አርብቶ አደሮች እንደማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አንቀጽ 39 የተገለጹት መብቶች አሏቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ እየተዘዋወሩ በአርብቶ አደርነት መኖር በራሱ ባህል በመሆኑ፣ እንደ ባህል የመጠበቅና የመንከባከብ መብት አላቸው፡፡ መንግሥትም ባህልን በተመለከተ ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተደነገገው በዋናነት የባህል መብትን የሚመለከት ነው፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መግለጫዎችና ሰነዶች፣ አርብቶ አደሮችን እንደ ነባር ሕዝቦች ስለሚወስዷቸው ነባር ሕዝቦች ያሏቸው መብቶችም ጭምር አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ እነዚህ መግለጫዎችና ሰነዶች የአስገዳጅነት ኃይላቸው ነጥሮ የወጣ ባለመሆኑ አገሮች ላይ ግዴታ የመጣል አቅማቸው ውስን ነው፡፡

ይህ ጽሑፍ የሚዳስሰው የባህልና የልማት መብቶችን ግንኙነት ነው፡፡ በተለይ የሚያቃርናቸው በርካታ አጋጣሚዎች ስላሉ መፍትሔያቸውን ማመላከት ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ጉዳዮች ሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚመለከቱ ቢሆን በዚህ ጽሑፍ እንደ ቡድን የተወሰዱት በዋናነት አርብቶ አደሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ ስለባህል መብቶች ምጥን ቅኝት ይደረጋል፡፡ ቀጥሎ ስለ ልማት መብት ይቀርባል፡፡ በመጨረሻም የሁለቱን ተቃርኖ በማቅረብ፣ ለተቃርኖው መፍትሔ በመጠቆም ይጠናቀቃል፡፡ በዚህ ወቅት ለመጻፍ ገፊ ምክንያቶቹ ደግሞ የአርብቶ አደሮች ቀን በጅግጂጋ ሳምንት መከበሩ፣ ከመሬታቸው ለሚፈናቀሉ ዜጎች የሚከፈለው ካሳ የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት መሆኑና ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ለባለሀብቶች የሚሰጡት አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በመሆኑና በዋናነት አጣብቂኝ ምርጫዎች ውስጥ ከሚገቡት የቡድን መብቶች ውስጥ ሁለቱ የባህልና የልማት መብቶች በመሆናቸው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ልማታዊ መንግሥትን የሚከተል አገር አርብቶ አደርነትና ሌሎች የተወሰኑ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህሎች ተግዳሮትነታቸው የማይታበል ሃቅ በመሆኑ ነው፡፡ በአብነትም በደቡብ ኦሞ ዞን በሚከናወኑት ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ብሔረሰቦች በብሔረሰብነት ህልውናቸው ላይ እንደተጋረጠ ፈተና ተደርጎ መተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ለመዘገባቸው መነሻው የሁለቱ መብቶች ግጭት ነው፡፡

የባህል መብት

የዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት)፣ ሁሉን አቀፍ  የብዝኃ ባህል መግለጫ፣ ስለ ባህል ምንነት የሚከተለውን ይላል፡፡ ባህል ‹‹የአንድን ኅብረተሰብ ኪነ ጥበባዊ፣ ሥነ ጽሑፋዊ፣ የአኗኗር ዘዬ፣ የጋርዮሻዊ የመኖሪያ መንገዶች፣ ትውፊት፣ እምነትና ዋጋ ያላቸው ሥርዓቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ አዕምሮአዊ፣ ልባዊ (emotional) መገለጫዎችን ጠቅልሎ ይይዛል፤›› በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ይህ ጥቅል ብያኔ ነው፡፡ በጣም ዘርዘር ባለ መንገድ የሚገልጹትም አሉ፡፡ ከላይ የተገለጸውንም ብንተነትነው ወደዚያው ያደርሰናል፡፡

ባህል ከግላዊ መለያና መገለጫ ይልቅ ከማኅበረሰብ፣ ቡድን፣ ብሔረሰብ ጋር የሚኖርን ማንነታዊ ቁርኝት ያመለክታል፡፡ ባህል የአንድን ኅብረተሰብ አባል የሆነ ግለሰብ ቋንቋውን፣ ትውፊቱን፣ እንቆቅልሹን፣ እንካስላንቲያውን፣ ከብት አረባቡን፣ አስተራረሱን፣ አመራረቱን፣ አመጋገቡን፣ አለባበሱን፣ የጋብቻ ሥርዓቱን፣ ስፖርታዊ ጭውውቱን፣ ሃይማኖቱን፣ የአምልኮ ሥርዓቱንና አከባበሩን፣ ዘፈኑን፣ ጭፈራውንና የመሳሰሉትን የሚያካትት ሲሆን፣ እነዚህን መሠረት በማድረግ ለመኖሩ፣ ለሕይወቱ፣ ለዓለም ያለውን አመለካከቱን፣ ችግሮችን የሚጋፈጥበትንና የሚፈታበትን ስልትም ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ባህል የተገነጠለ፣ ስለአንድ ነገር ብቻ የሚያውጠነጥን አይደለም፤ የሰውን ልጅ ሁለመናውን አቅፎ የሚይዝ እንጂ፡፡

ሁሉን አቀፍነትን (Universalism) እንደ አንድ ጽንሰ ሐሳብ (ፍልስፍና) የሚያቀነቅኑት፣ ዓለም አቀፋዊ ባህል ያለው ሰው መፍጠር ይቻላል ይላሉ፤ የተለያዩ መስፈርቶችን በመተግበር የሰብዓዊ መብትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ሲሆን ባህል ለሰብዓዊ መብት መሰናክል ሊሆን አይገባውም፡፡ ሰውየው፣ ኢትዮጵያዊም ይሁን አሜሪካዊ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ሰብዓዊ መብት ነው የሚል ክርክር አለ፡፡

በተቃራኒው የባህል አቻዊነት (Cultural Relativism) ክርክር ደግሞ ሁሉም ባህሎች እኩል ናቸው፡፡ የአንዱን ማኅበረሰብ ባህል ሌላው መለኪያ አይሆንም፤ አንድን ባህል ከሌላ ባህል አንፃር እያስተያዩ አንዱ ትክክል አንዱ ስህተት፣ አንዱ የበለጸገ አንዱ ያነሰ አይባልም፤ የባህል መብት እንደሌሎች ሰብዓዊ መብቶችም ወጥ አይደለም፤ የትም ቦታ ቢሆን የሌላውን ባህል ማክበር፣ ማስከበርና እንዲስፋፋ ማገዝ እንጂ ዓለም አቀፋዊ የሚባል ባህል የለም የሚል ክርክር አለ፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመዘዋወር፣ በቋሚነት በአንድ አካባቢ መጠለያ ባለማበጀት፣ የኑሮ መሠረትንም አርብቶ አደር ማድረግ የባህል አካል ነው፡፡ ስለሆነም ባህልን የሚመለከቱ በርካታ መብቶች በእንዲህ ዓይነት የኑሮ ዘዬ ለሚኖሩ ሕዝቦችም ተፈጻሚነት አላቸው፡፡

የተለያዩ ባህሎች ያሏቸው ሕዝቦች የሚኖሩባቸው አገሮችን በተመለከተ የሚነሳው አንዱ ጉዳይ የብዝኃ ባህል ነገር ነው፡፡ የብዝኃ ባህል ፖለቲካዊ ፍልስፍና ከማንነት፣ አንድን ቡድን ከነልዩነቱ ከመታወቅ ፖለቲካ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በመሆኑም የባህል ውጠትን፣ መጥፋትንና ውህደትን አጥብቆ ያወግዛል፡፡ በፈረንሳይ፣ በብራዚልና ድሮ ድሮም አሜሪካም ይካሔድ የነበረውን ሁሉንም ባህሎች አጥፍቶ/አቅልጦ ጠንካራ፣ አዲስና አንድ ብቻ ፈረንሳዊ፣ ብራዚላዊ፣ አሜሪካዊ ባህል የመፍጠር ተግባርም ይሁን ዝንባሌን ይቃወማል፡፡

በአንፃሩ የባህል መከበር መሠረታዊ የሆነ መብትና የማንነት መገለጫም በመሆኑ፣ ማንነትና ባህልን በመደምሰስ አገራዊ ስሜት መፍጠር ስለሚያስቸግር ሁሉም ባህላቸውን (የኩናማውንም፣ የአማራውንም፣ የኦሮሞውንም፣ የማኦውንም ወዘተ እንደማለት ነው፡፡) እንደጠበቁ ለገበታ እንደተዘጋጀ ሰላጣ ወይም የአትክልት ቁርጥ (Fruit Punch) መታየት አለበት የሚሉም አሉ፡፡

ከላይ ከተገለጹት ማሳያዎች በመነሳት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በግዳጅ ወይም በመንግሥት ዝምታና ባህሎችን ተመጣጣኝ የሆነ እንክብካቤ ካለማድረግ የተነሳ አሁንም የባህል መብቶች ላይ ጥሰት እንዳይደረስ ነው የአንቀጽ 39(2) ዓላማ፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ባህሉን የመግለጽ፣ የማሳደግና የማስፋፋት መብት አለው፡፡ በአንቀጽ 90ም መሠረት መንግሥት ማናቸውንም ባህሎችና ልማዶች አቅሙ የፈቀደውን ያህል እንዲጎለብቱ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ የማድረግ፣ በዩኔስኮ ማስመዝገብና የመሳሰሉት፡፡ እነዚህ ግዴታዎች በሕገ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው እንደ ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶች ስምምነትም ውስጥ ተካትተዋል፡፡ በክልል ሕገ መንግሥቶችም እንደዚሁ፡፡

ሕገ መንግሥቱም ይህን ከግምት በማስገባት አንቀጽ 41(9) ላይ መንግሥት ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን የመንከባከብ ግዴታ እንዳለበት በአንቀጽ 90(2) መሠረት ደግሞ ከመንግሥትም በተጨማሪ ዜጎችም ታሪካዊ ቦታዎች የመንከባክብ ግዴታ እንዳለባቸው የደነገገው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለም የባህል ፖሊሲና ሌሎች ስለ ታሪካዊ ቅርሶች አጠባበቅና እንክብካቤ የሚደነግጉ ሕጎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ፣ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆኑት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውስጥ የተወሰኑት (ምሳሌ አፋርና ሶማሌ) አርብቶ አደርነትና ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ኑሯቸውን መምራታቸው የባህላቸው አካልና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ ያለው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የልማት መብት

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ከሚይዛቸው መብቶች አንዱ ዘርፍ የኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ራሳቸውን የማይችሉ ክልሎች ከሆኑ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ውኃ እንደሚበላው ሃቅ ነው፡፡ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕቅዶችን ለማቀድም ለማከናወንም በኢኮኖሚ ራስን መቻል ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በፌደራሉ መንግሥት ላይ ጥገኛ ሆኖ በሙሉ ነፃነት ራስን ማስተዳደር የሚቻልም አይደለም፤ የሚታሰብም አይሆንም፡፡

የራስን ዕድል በራስ መወሰን ኢኮኖሚያዊ ገጽታው የመልማት መብትና የተፈጥሮ ሀብትን በነፃነት ለሚፈልጉት አገልግሎት ማዋልን ይይዛል፡፡ ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲሆንም በተገዥዎች ላይ ተፈጽሞ የነበረው አንዱ ኢፍትሐዊ ድርጊት የተፈጥሮ ሀብትን መበዝበዝ የነበረ ስለሆነ፣ ይህ የብዝበዛ አድራጎት በድጋሜ እንዳይከሰትና ይልቁንም በተፈጥሮ ሀብታቸው የመጠቀም መብትን ማረጋገጥ ነበር፡፡

 በኢኮኖሚ የመበልጸግና የመልማት መብትና የተፈጥሮ ሀብትን ያለአንዳች ጫናና ጣልቃ ገብነት መጠቀምን በተመለከተ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ጀምሮ፣ በየአኅጉራቱና በየአገራቱ ብዙ ሕጎች አሉ፡፡ የሁሉም ይዘት ተመሳሳይና ተቀራራቢ ነው፡፡ በቅኝ ግዛትና በወረራ የሌሎች ሕዝቦችን የተፈጥሮ ሀብት መበዝበዝን ዓለም አቀፍ ሕጉ ይከለክላል፡፡ የማይዳፈሩት፣ የማይናወጥና የማይቀየር አንዱ የሉዓላዊነት መገለጫም  ጭምር ነው፡፡ ልማት፣ የሰብዓዊ መብት አንዱ አካል መሆኑም እርግጥ ሆኗል፡፡ ለልማት ደግሞ ወሳኝ ከሆኑት ግብዓቶች አንዱ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም፣ ለሕዝቡ እንዲጠቅም ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ይህ በዋናነት የሚመለከተው ሉዓላዊ አገሮችን ነው፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በተሻለ ነፃነት ለማስተዳደር የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ሲኖራቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተፈጥሮ ሀብትና በመሬት ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(3) ‹‹የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፤›› ይላል፡፡ በመቀጠል ደግሞ አንቀጽ 51(5) ላይ የፌደራል መንግሥት ‹‹የመሬት የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤›› በማለት ደንግጓል፡፡ አንቀጽ 89(5) ላይ ደግሞ ‹‹መንግሥት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን በሕዝብ ስም በይዞታው ሥር በማድረግ ለሕዝቡ የጋራ ጥቅምና ዕድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፤›› ይላሉ፡፡

እነዚህ አንቀጾችን በአንድነት ካነበብን በኋላ ከምንረዳቸው ቁምነገሮች ውስጥ አንዱ፣ እነዚህ ሀብቶች የመንግሥት፣ የሕዝብና የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት መሆናቸውን፣ ሕግ የሚያወጣው ደግሞ የፌደራሉ መንግሥት መሆኑን፣ አስተዳዳሪውም ያው መንግሥት (እንደነገሩ ሁኔታ የፌደራልም የክልልንም መንግሥት ይጨምራል) መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(3) መሠረት፣ የመሬት ባለቤትነት የመንግሥት (State) እና የሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው፡፡ ይህንን የጋራ ሀብት መስተዳደሩ (Government) በሕዝብ  ስም የማስተደዳር ግዴታ  በአንቀጽ 89(5) ተጥሎበታል፡፡  እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለው የሚገባን ቁምነገር አለ፡፡ የመሬት ባለቤትነት የመንግሥት (State) እና የሕዝብ ሲሆን እንዲያስተዳደር የተወከለው ደግሞ መንግሥት (መስተዳደሩ) (Government) መሆኑን ነው፡፡ በባለቤቱና በአስተዳዳሪው መካከል ልዩነት አለ፡፡ መንግሥት (State) አጠቃላይ አገሪቱን ሲመለከት መንግሥት (Government) የሚለው ደግሞ በምርጫ አሸንፎ አገር በመምራት ላይ የሚገኘውንና ተቋማት የሚደራጀውን ይመለከታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ከሕገ መንግሥቱ በተጻራሪ የመሬት አስተዳደር አዋጁ የመሬትን ባለቤትነት የመስተዳድሩ (Government) አድርጎታል፡፡ መንግሥት በሕዝብ ስም መሬትን ሲያስተዳድር የእንደራሴነት ግዴታ እንዳለበት አንቀጽ 89(5) ላይ ተደንግጓል፡፡ የእንደራሴነት ሥልጣን፣ የታማኝነትን፣ የታታሪነትን፣ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ብቻ መሥራትንና የመሳሰሉትን ግዴታዎች ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡  እነዚህን ግዴታዎች ከመሬት ቅርምት ጋር በማገናኘት ወረድ ብለን እንመለከታቸዋለን፡፡

መንግሥት ለሕዝቡና ለዜጎች ካሉበት ግዴታዎች አንዱ የልማት መብትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ማለትም የኑሮ ሁኔታቸው እንዲሻሻል ማድረግ ብሎም የማይቋረጥ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 43 መረዳት ይቻላል፡፡ እንግዲህ ይህንን ግዴታ ለመወጣት ይመስላል የልማታዊ መንግሥት አርዓያነትን ኢሕአዴግ እንደ መንግሥት እየተከተለ ያለው፡፡ የልማታዊ መንግሥት ዋናው ግብ ፈጣን የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማምጣት፣ ልማትን በዘላቂነት በማስቀጠልና በማስፋፋት ሕዝብን ከድህነት ማላቀቅ ነው፡፡ መርሁም ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ልማት ግንባር!›› ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት ትኩረት ከሚያደርግባቸው የልማት ዘርፎች ውስጥ አንዱ ደግሞ ግብርናን መሠረት ያደረጉ ኢንዱስትሪ ዋነኛው ነው፡፡ በተለይ  ሰፋፊ  የእርሻ መሬትና ርካሽ የሆነ የሰው ኃይል በአገሪቱ መገኘቱ ይህንን ዘርፍ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዘርፉ በሚጠበቀው መጠን ግቡን ካለማሳካቱ በተጨማሪ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም መንግሥት በጋራ ባለቤት የሆኑበት፣ ከባህላቸው ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው፣ መሬት በችግር በተተበተበ ሁኔታ እየተዳደረ ይገኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰፋፊ የእርሻ መሬት የሚገኘው አርብቶ አደሩ በሚኖርበት አካባቢ በመሆኑ ባህላቸው ላይ ከፈጠረው ሥጋት በተጨማሪ የመሬት ቅርምት አለበት የሚል ክርክር አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ስለመሬት ቅርምት ምንነትና ስለ ግብርና ኢንቨስትመንት መርሆች የተወሰኑ ነጥቦች እናንሳ፡፡

ኢትዮጵያ፣ መሬት እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ለረጅም ዓመታት አግሮ ኢንዱስትሪ ላይ በኢንቨስትመንት ለተሠማሩ ‹‹ባለሀብቶች›› ከሚሰጥባቸው አገሮች አንዷ ናት፡፡ በእርግጥ ባለሀብት የሚለው ቃል ግራ የሚያጋባ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም እዚህ ግባ የሚባል ሀብት የሌላቸው ሰዎችም በተለይም ከመንግሥት ባንኮች በርካታ ብድር ከመውሰድ በዘለለ የራሳቸው ጥሪት የሌላቸው መሆናቸውን ለታዘበ ሰው አስቀድመው ባለሀብት ያልነበሩ ነገር ግን መሬትም፣ ብድርም ከመንግሥት ከወሰዱ በኋላ ባለሀብት የሆኑ ናቸው፡፡ ይባስ ብሎ፣ መሬቱን ለታሰበው ዓላማ በማዋል ሀብት ከማፍራት ይልቅ ለግል ፍጆታና ለሌላ ዓላማ ማዋላቸው ነው፡፡

ለመሆኑ የመሬት ወረራ ወይንም ቅርምት ምንድን ነው? በርካታ ምሁራን የተለያዩ ብያኔዎች አሏቸው፡፡ ወጥ የሆኑ ግን አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ የሚጋሯቸው ነጥቦች የላቸውም ማለት ደግሞ አይቻልም፡፡ ምን ያህል ሔክታር መሬት ነው ሰፊ የሚባለው የሚለው ላይ ባይስማሙ እንኳን መጠኑ ከፍ ያለ፣ ወይንም ሰፊ መሆን እንዳለበት ግን ይቀበላሉ፡፡ ይሁን እንጂ የመሬቱ መጠንም በተመለከተ አገሮች ያላቸው የመሬት  መጠን ከግምት መግባት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ለባለሀብቶች በሊዝ  የተሰጠው መሬት ከተወሰኑ አገሮች አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ይበልጣል፡፡ ስለሆነም አንዳንዶች የመሬት ወረራ ወይንም ቅርምት ለመባል 100000 ሔክታር ወይንም 1000 ካሬ ኪሎ ሜትር መሆን አለበት የሚሉት ብዙም ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ መሬቱ የሚገኝበት መንገድም የግድ በግዥ ብቻ ሳይሆን በኪራይ ወይንም በሊዝ ሊሆን እንደሚችልም ብዙም የሚያለያይ ጉዳይ አይደለም፡፡ መሬቱን እንዳዲስ የሚወሩትን ወይም የሚቀራመቱትን ማንነት በተመለከተም የውጭ አገር ሰዎች ወይንም ኩባንያዎች ወይም የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም መንግሥታት የመሆናቸው ነገርም ብዙም አጨቃጫቂ አይደለም፡፡ በተጨማሪም የመሬት ወረራ አለ ማለት ባለሀብቶች መሬቱን ያገኙበት መንገድ ሕገወጥ ነው ማለትም አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በሕገወጥ መንገድ የተገኘም ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ነጥብ ባለሀብቶች መሬቱን የያዙበት ዓላማ ነው፡፡ ተቀራማቾቹ በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉትን መሬት የነዋሪውን ወይንም ዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን ከቁብ ያልጣፈ፣ የሰብዓዊ መብትን ስለማክበር ደንታ የሌላቸው ሲበዛም የአካባቢ ጥበቃን ቅድሚያ የማይሰጡ ናቸው፡፡

የመሬት ቅርምት ወይም ወረራ ምንም እንኳን የቆየ ክስተት ቢሆንም ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ግን በጣም ትኩረት መሳቡን ቀጥሏል፡፡ በዚህ ወቅት የምግብ ዋጋ ቀውስ መፈጠሩን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካና ላቲን አሜሪካ መሰማራታቸውን በማጧጧፍ ቀጥለውበታል፡፡ ለዚህ ድርጊታቸው ደግሞ ኩባንያዎቹ የተመሠረቱባቸው ወይም የባለሀብቶቹ አገሮች እገዛ እንደሚያደርጉላቸውና እንደሚያበረታቷቸው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ማበረታቻ ለመስጠት ደግሞ በርካታ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድሉን ማመቻቸት፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪው ግብዓቶችን ለማምረትና ከምግብ ዋጋ ቀውሱ ተጠቃሚ ለመሆን፣ ባዮፊዩል ለማምረት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ይህ የመሬት ቅርምት ነገር አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ የግብርና ኢንቨስትመንት በምን መልክ መከናወን እንዳለባቸው ዓለም አቀፋዊ መርሆች እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም መሠረት የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የግብርና ድርጅትና ሌሎች ተቋማት ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ኢንቨስትመንት ማከናወንን በተመለከተ ሰባት መሮሆችን እ.ኤ.አ. በ2010 አውጥተዋል፡፡ የመጀመሪያው መርህ በአነስተኛ ማሳ የሚተዳደሩ ገበሬዎችን፣ ከብት አርቢዎችንና ማኅበረሰቦችን ለመሬትና ለተፈጥሮ ሀብት መብቶች ዕውቅና መስጠትና ማክበርን ይመለከታል፡፡ ሁለተኛው መርህ ደግሞ ኢንቨስትመንቱ የሚከናወንበት አገር የምግብ ዋስትና በሚጋፋ ወይም በሚቃረን መልኩ መከናወን የሌለበት መሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛው መርህ፣ ከመልካም አስተደዳር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከማዕከላዊው (ከፌደራል) መንግሥት ጀምሮ እስከ ክልልና ወረዳ ወይም ከዚያ በታች ባሉ የአስተደዳር መዋቅሮች አቀናጅቶና አጣጥሞ ማስተዳደርንና ግልጽነትን ይመለከታል፡፡ አራተኛው፣ የሚፈናቀሉና ኢንቨስትመንቱ ተፅዕኖ የሚያሳድርባቸው ሕዝቦችን የማማከርና የማሳተፍ ግዴታ ነው፡፡ ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ድርጅቶችን ማቋቋም፣ የድርጅቶች የማኅበራዊ ኃላፊነት መወጣትና ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ መርሆች ናቸው፡፡

የእነዚህን መርሆች መከበር ጋምቤላን በተመለከተ መንግሥት ካቀረበው የጥናት ውጤትን በምሳሌነት በመውሰድ የተመለከተ ሰው የእነዚህ መርሆች አለመከበር፤ የመሬት ቅርምት አለ ወይም የለም ለማለት ባንጠቀምባቸው እንኳን ኢንቨስትመንቶቹ ኃላፊነት የተሞላባቸው ወይም የጎደላቸው መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ በተጨማሪም መንግሥት መሬትን በእንደራሴነት ሲያስተዳድር መወጣት ያለበትን ግዴታዎች አለመወጣቱን ያረጋግጣሉ፡፡ መሬቶቹ በአግባቡ አለማስተዳደሩ፣ በሚጠበቀው መጠን ለወካዩ ሕዝብ አለመጥቀማቸው የእንደራሴነት ተግባሩን እንደጣሰ ፍንጮች ናቸው፡፡

የመብቶቹ ተቃርኖዎች

መሬትና የተፈጥሮ ሀብት የመላው ሕዝብ የጋራ ንብረት ከሆነ አንድ ብሔር እንዳሻው ሊያዝበት አይችልም ማለት ነው፡፡ በአፋር ያለውን ሁኔታ እንውሰድ፡፡ መሬት የመንግሥት እንደሆነ በሕግ ተደንግጓል፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በአፋር የባህል ሕግ ግን መሬት የጎሳ ነው፡፡ ባልተቤቱም አስተዳዳሪውም ጎሳው ነው፡፡ አፋር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን የማይገደብ መብት ካለው፣ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ይችላል ከተባለ ከመሬቱ ተነጥሎ፣ የመሬት ሥሪቱን አብዮታዊ በሆነ መልኩ ቀይሮ ለፌደራል መንግሥት አስረክቦ፣ የፌደራል መንግሥቱ በሚያወጣው ሕግ መሠረት ብቻ እያስተዳደረ ከባልተቤትነት ወደ ባለይዞታነት ዝቅ ብሎ እንደብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት አለው ማለት ብዙም ትርጉም የለውም፡፡ መሬቱን ለባለሀብቶች ሲሰጥም እየተዘዋወረ የኑሮ ሁኔታውን መቀጠሉ ላይ እንቅፋት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚከናወኑት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መሬቱን ይዘውት በነበሩት ሕዝቦች (ማኅበረሰቦች) ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታም ለማሳየት ደፋ ቀና የሚሉ በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የሙግታቸው ማጠንጠኛም ቡድናዊ ማንነታቸውን እያጠፋ ነው፣ የአካባቢ ብክልትን ይፈጥራል፣ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ አይደለም፣ ቴክኖሎጂን እያሸጋገረ አይደለም፣ የሥራ ዕድልም ቢሆን እየፈጠረ አይደለም የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተለይም ኢንቨስትመንቱ በሚከናወንባቸው አካባቢ የሚኖሩትን ነባር ብሔረሰቦች አባላት ትርጉም ያለው ጥቅም አላበረከቱም የሚል መከራከሪያ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡

እንግዲህ ከላይ ለማየት የተሞከረው በቅድሚያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለይም በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩት ይህንን የኑሮ ዘይቤ በባህልነቱ የማስጠበቅና የመንከባከብ መብት መንግሥትም የማገዝ ግዴታ ያለበት መሆኑን ነው፡፡ በመቀጠል እነዚህ ቡድኖች የመልማት መብት እንዳላቸው መንግሥትም በተለይ በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ አርብቶ አደሮች ልዩ ድጋፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ መኖሩን ነው፡፡ ልማት ደግሞ በተለያዩ ሁኔታ የሚፈጸም ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ እነዚህን ቆላማ ቦታዎች ምርታማነታቸውን ለመጨመር ለባለሀብቶች በመስጠት ከዚህ በሚገኘው ገቢም ሆነ ራሱ ኢንቨስትመንቱ በተጓዳኝ በሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡

የሕዝቡን የመልማት መብት እውን ለማድረግ ወይንም በራሱ መወሰኑን ለማረጋገጥ ምቹ ሕግና ፖሊሲ ማውጣት፣ እነዚህም ሲወጡ ሕዝቡን የማሳተፍና ለውሳኔ የሚሆን ሐሳብ የማበርከት መብትንም ያካትታል፡፡ የመሬት ባለቤትነትንና የተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተና በልማት ጉዳዮች ላይ ቀድሞ ሕዝብን ማማከርና ማወያየት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፡፡ አርብቶ አደሩም ከባህሉ ይልቅ (በተለይም ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ከመኖር) በአንድ አካባቢ ሰፍሮ የመኖርንም ጠቀሜታ በራሳቸው አስቀድመው በመረዳት የመወሰን ዕድል ሊሰጣቸው ግድ ይላል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...