– በሚድሮክ ወርቅ ልማት ላይ ጥቆማ ቀርቧል
በማዕድን ዘርፍ የተሠማሩ ኩባንያዎች የማምረት ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ የማምረት ሙከራ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ለዓመታት እያጭበረበሩ እንደሚቆዩ እንደተደረሰበት በመግለጽ፣ ክትትል እንዲደረግ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. የማዕድን፣ ተፈጥሮ ጋዝና ፔትሮሊየም ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ባቀረበበት ወቅት ነው ይኼንን ማሳሰቢያ የሰጠው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ ጀምበርነሽ ለንፉ ለሚኒስቴሩ አመራሮች ማሳሰቢያውን በሰጡበት ወቅት፣ ቋሚ ኮሚቴው የማዕድን ዘርፉን በአካል በየቦታው በመዘዋወር እንደጎበኘ አስታውሰዋል፡፡
‹‹ሕገወጥ የማዕድን ዝውውር እናንተ ከምትሉትና እኛም ከምንገምተው በላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የማዕድን ፈቃድ ወስደው ለዓመታት የመንግሥትን ጥቅም የሚያሳጡ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ወደ ሻኪሶ አቅንቶ ሻኪሮ በሚባል አካባቢ ያለውን የወርቅ ልማት ለመመልከት እንደሞከረ የተናገሩት ወ/ሮ ጀምበርነሽ፣ በዚህ ሥፍራ ያለው የሚድሮክ ወርቅ ልማት ገና በሙከራ ላይ ቢሆንም እውነቱ ከዚህ በተቃራኒ እንደሆነ ለሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና ለባልደረቦቻቸው አሳስበዋል፡፡
በወርቅ ልማት ክልል ውስጥ ገብተው እንዳዩ የተናገሩት ምክትል ሰብሳቢዋ ‹‹እዚያ ያለ ባለሙያ ጭምር የገለጸው ከ21 ካራት በላይ የሆነ ጥራት ያለው ወርቅ እየተመረተ ከሻኪሮ ወደ ዋናው ሚድሮክ እየመጣ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ሚድሮክ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሙከራ ላይ መሆኑን ቢገልጽም፣ በተጨባጭ ግን እየተመረተ ስለመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመከታተል የመንግሥትን ጥቅም እንዲያስከብር አሳስበዋል፡፡
በሌሎች ማዕድናት ላይ ሙከራ ላይ መሆናቸውን እየገለጹ ለዓመታት የሚቆዩትን ኩባንያዎች መመርመር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ በአጠቃላይ የማዕድን ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ በመሆኑ በጥልቀት ሊመረመር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በተለያዩ የማዕድን ልማት አካባቢዎች ቱሪስት መስለው የሚንቀሳቀሱ የውጭ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ የከበሩ ማዕድናትን እያወጡ መሆኑን፣ በተለይም ኦፓል የተሰኘውን ማዕድን የራሳቸው አድርገው በድረ ገጽ ጭምር የሚለቁ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የግል ባለሀብቶች ከውጭ ዜጎች ጋር አቅደው የማጭበርበር ተግባር የሚፈጽሙ መኖራቸውን ኮሚቴው እንደደረሰበት በመጠቆም ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ መልስ የሰጡት ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቀሳ የተሰጡዋቸውን ማሳሰቢያዎች ተቀብለው እንደሚመረምሩ ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ ግን ሙሉ ለሙሉ ለሙስና ተጋላጭ መሆኑን፣ ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ የውጭ ኩባንያዎች በቀላሉ ሁሉንም በገንዘባቸው እንደሚጠመዝዙ አክለዋል፡፡ በሚድሮክ ወርቅ ላይ የቀረበውን ጥቆማ አስመልክቶ ሪፖርተር ከሚድሮክ ወርቅ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡