Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናመንግሥት ለፓርላማ አባላት መኖሪያ ቤት ውኃ መደጎሙ ከዓመታት በኋላ ጥያቄ አስነሳ

  መንግሥት ለፓርላማ አባላት መኖሪያ ቤት ውኃ መደጎሙ ከዓመታት በኋላ ጥያቄ አስነሳ

  ቀን:

  – የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ 500 ሺሕ ብር ውዝፍ ዕዳ ተጠይቋል

  የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የሚያስተዳድራቸውን የመኖሪያ ቤቶች በአነስተኛ ዋጋ የተከራዩ የፓርላማ አባላት፣ የውኃ ፍጆታቸው በኤጀንሲው አማካይነት በመንግሥት ወጪ መሸፈኑ አግባብ አይደለም የሚል ጥያቄ ከዓመታት በኋላ ተነሳ፡፡

  የቀድሞው የሥራ ዘመናትን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት ለተጠቀሙት የውኃ ፍጆታ፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን 500 ሺሕ ብር እንዲከፈል መጠየቁን የኤጀንሲው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው ስብሰባ፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሲሳይ የኤጀንሲውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በርካታ ጥያቄዎች ተነስተውላቸዋል፡፡ በወቅቱ የውኃ ፍጆታ ጉዳይ አከራካሪ ከነበሩት ጉዳዮች ቀዳሚው ነበር፡፡

  እንደ ኤጀንሲው ኃላፊዎች በተለይ ከ2005 ዓ.ም. በፊት በቤቶቹ ይኖሩ የነበሩት የምክር ቤት አባላት በያዙት ቤት የመኝታ ቤት ቁጥር ልክ ተሰልቶ ይከፍሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አሠራር ተቀይሮ ለእያንዳንዱ ቤት ቆጣሪ እንዲገባላቸውና እንደየፍጆታቸው እንዲከፍሉ የሚደረግ አሠራር ቢዘረጋም፣ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ግን አባላቱ መክፈል እንዳቆሙ ተገልጿል፡፡ በዚህም የተነሳ ኤጀንሲው ግማሽ ሚሊዮን ብር ውዝፍ ሒሳቡን እንዲከፍል በውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣኑ መጠየቁን፣ የኤጀንሲው የቅርንጫፍ 3 ኃላፊ ወ/ሮ አረግዋ ዓባይነህ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ከቆጣሪ ንባብ ጋር የተያያዘ ችግር አለ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ነገር ግን ያለው ችግር የቆጣሪ ንባብ ሳይሆን የክፍያ ችግር ነው፤›› በማለት ከቋሚ ኮሚቴ ለተነሳው ጥያቄ መልስ የሰጡት ወ/ሮ አረግዋ፣ የምክር ቤት አባላት ለሚጠቀሙበት ክፍያ መፈጸም እንደነበረባቸው ገልጸዋል፡፡ ቀደም ብለው የነበሩ የምክር ቤት አባላት ሳይከፍሉ የፓርላማው ዘመን ስለተጠናቀቀ፣ በጉዳዩ ላይ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ቀደም ብሎ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ውዝፍ ሒሳቡን ለመክፈል ስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ያለመተማመን በመከሰቱና ውዝፍ እየተጠራቀመ መምጣቱን አክለዋል፡፡

  ችግሩ የተከሰተው ቀደም ሲል የነበረው አሠራር በመቀየሩ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ አረግዋ፣ ቀድሞ የነበረው አሠራር ነዋሪዎች እንደያዙዋቸው የመኖሪያ ቤቶች የመኝታ ክፍሎች ብዛት ይከፍሉ ነበር ብለዋል፡፡ ክፍያውም ለስቱዲዮ 15 ብር፣ ለሁለት መኝታ 25 ብር፣ ለሦስት መኝታ 30 ብር ያህል ለረጅም ዓመታት ይከፍል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከቀድሞ አሠራር መቀየር በኋላ ግን ኤጀንሲው ከቤቶቹ ኪራይ ከሚሰበሰበው በላይ ለውኃ ፍጆታ ከፍተኛ ወጪ እያስወጣው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ይህንኑ የወ/ሮ አረግዋን ሐሳብ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙደር ሰማን በማጠናከር፣ ‹‹ዛሬ መንግሥት ለአርሶ አደሮች እንኳ ያደርገው የነበረውን የማዳበሪያ ድጎማ ባቆመበት ወቅት በከተማ የአፓርትመንት ቤቶች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ያውም ከ200 ብርና 300 ብር ከፍ ሲልም 700 ብር በሚሆን የኪራይ ዋጋ ከመደበኛው ገበያ ከ300 እና 400 በመቶ ባነሰ ዝቅተኛ ዋጋ እያከራየን፣ ውኃ መደጎም አለበት ወይ የሚለው መታየት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

  ለነዋሪዎቹ (ለምክር ቤት አባላቱ) የውኃ ፍጆታን መደጎሙ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሙደር፣ መንግሥት ግለሰቦች ለተገለገሉበት ፍጆታ መክፈል እንደማይገባው እምነታቸው መሆኑን አክለው በመግለጽ፣ ‹‹አንድ ላይ ሆነን ተወያይተን ለማቆም ብንነጋገርበት ይበጃል፤›› ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ወጪው ተሰልቶ ለህዳሴው ግድብ አስተዋጽኦ ብናደርገው አይሻልም?›› በማለት የጠየቁት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ቋሚ ኮሚቴው በዚህ ጉዳይ ሊያግዘን ይገባል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

  ነገር ግን የቤቶቹ ነዋሪ የሆኑና የቋሚ ኮሚቴው አባላት ያለባቸውን የውኃ ውዝፍ ለመክፈል ፈቃደኛ አይደሉም መባላቸውን አስተባብለዋል፡፡ ይልቁንም ችግሩ ከቆጣሪ ንባብ ጋር የሚያያዝና የኤጀንሲው የተዝረከረከ አሠራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንደ አንድ ደንበኛ ስንመለከተው ችግሩ የተከሰተው በቤቶች ኤጀንሲ ወይም በሚመለከተው አካል ትክክለኛ መረጃ ካለመያዝ መሆኑ በደንብ ሊሰመርበት ይገባል፤›› በማለት የተናገሩት ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል ናቸው፡፡

  እንደ ግለሰብ ሆነ እንደ ምክር ቤት አባልነታቸው ግለሰብ ለተጠቀመበት ፍጆታ መንግሥት መክፈል ይገባዋል ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡ አባላት ሊከፍሉ ፈቃደኛ አይደሉም መባሉን ግን ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኤጀንሲው የተጠየቀበት ውዝፍ የፓርላማ አባላት ስለማይከፍሉ አይደለም፡፡ ቀደም ብለው ይኖሩ የነበሩ የምክር ቤት አባላትም ቢሆኑ በነበረው አሠራር መሠረት እንደየመኝታ ቤቶቻቸው ብዛት ይከፍሉ እንደነበር ነው የምናውቀው፡፡ ነገር ግን ከቆጣሪ ንባብ ጋር ተያይዞ ልዩነት እየተፈጠረ ሲመጣ በወቅቱ ቆም ብሎ ማሰብ ነበረበት፤›› ሲሉ የኤጀንሲው የአሠራር ግድፈት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ‹‹ለምሳሌ ይህን መጥቀስ ካለብኝ እኔ ቤት የምጠቀምበት የቆጠረው ቁጥርና ክፍያ እንድከፍልበት የተሰጠኝ የቆጣሪው ቁጥር የማይገናኝበት ጊዜ አለ፡፡ ይህንን በመሳሰሉ ምክንያቶች የማን ቆጣሪ የቆጠረውን ሒሳብ ነው እኔ የምከፍለው የሚል ጥያቄ በእኛ በአባላቱ መካከል ይነሳል፤›› በማለት የተከራከሩት ወ/ሮ የሺመቤት፣ በወር እስከ 370 ብር ድረስ የሚጠየቅ ነዋሪ ቢስተዋልም ያን ያህል የውኃ ፍጆታ ሒሳብ በአንድ ግለሰብ ላይ ሊመጣበት ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

  ይልቁንም በተሳሳተ መረጃ ግለሰቦች ለተጠቀሙበት ሒሳብ መንግሥት ከፍሎ ከሆነ ወደኋላ ያሉ ችግሮችን በማጥራትና በመለየት፣ ለወደፊቱ ከነዋሪዎች ወርኃዊ ሒሳብ ጋር በማስላት መልሰው የሚከፍሉበትንና ወደ መንግሥት ካዝና የሚመለስበት መንገድ መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

  ወ/ሮ አዳነች ባዕናም የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል እንዲሁ መንግሥት የግለሰቦች ፍጆታ መሸፈን እንደሌለበት እምነታቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹ችግሩን ወደ ሌላ አካል ከማስተላለፍ ይልቅ መጀመሪያ የራሳችንን ችግር ብናየው፤›› በማለት ኤጀንሲው የምክር ቤት አባላት አልከፈሉም ከማለት ራሱን ሊፈትሽ ይገባው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ግለሰቦች የተጠቀሙበትን የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ ኤጀንሲው ሊከፍል አይገባውም በሚል እምነት ቀደም ብሎ በአባላቱ መጠየቁን ለማስረዳት የሞከሩት የምክር ቤት አባሏ፣ ‹‹አሁንም ቢሆን መንግሥት የግለሰቦችን ዕዳ ሊከፍል አይገባውም፡፡ ኤጀንሲው ያለበትን የመረጃ ክፍተት በማጥራት ችግሩን ሊያስተካክል ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

  የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፣ ኤጀንሲውና የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አለመቀናጀት ሌላኛው ችግር ነው ብለዋል፡፡

  አቶ ሀብታሙ ከመረጃ ክፍተት ጋር በተያያዘ የተነሳላቸውን ጥያቄ በተመለከተ ሲመልሱ ሙሉ በሒደት እንደሚያስተካክሉ ገልጸዋል፡፡ አሁን ተቋሙ አለበት የተባለውን ውዝፍ ሒሳብ እንደሚከፍል የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፣ ከተገለጸው የነዋሪዎች ውዝፍ ሒሳብ በተጨማሪ ለበርካታ ዓመታት የኦዲት ሒሳባቸው ያልተዘጋ ውዝፍ ሒሳቦች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል፡፡ ለአብነት ያህል ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ ያልተሰበሰበ ሒሳብ መኖሩን ጭምር አመልክተዋል፡፡ ይህንንም ሲገልጹ በጠረጴዛቸው ላይ ከ20 ሴንቲ ሜትር የማያንስ መጠን ያለው የውዝፍ ሒሳብ ሰነድ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

  በተያያዘም በልማት ምክንያት እየፈረሱ ላሉ ቤቶች ተገቢውን ካሳ እየተከፈለ አለመሆኑን፣ ቤቶች ከመፍረሳቸው በፊት ተገቢው የመረጃ ልውውጥ እየደረሳቸው እንዳልሆነ በቋሚ ኮሚቴው ውይይት ወቅት አስረድተዋል፡፡ በምሳሌ ሲያስረዱም በቅርቡ ከፈረሱት የመንግሥት ቤቶች አሥር ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም፣ መሰብሰብ የተቻለው ግን 1.6 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በልማቱ ምክንያት የሚፈርሱ ቤቶች መቼ እንደሚፈርሱ ቀድሞ መረጃ ስለማይሰጠው፣ ከፈረሱ በኋላም ስለፈረሱት ቤቶች መረጃ ለመሰብሰብ መቸገራቸውን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በከፋ ሁኔታ ለአንዳንድ ቤቶች ተከፍሏል ስለሚባለው የካሳ ክፍያ ባንክ የገባበትን ሰነድ እንኳ ማግኘት አለመቻሉንም ገልጸዋል፡፡    

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...