– የእርሻ ዘርፍ ባለሀብቶች ማሻሻያው የሚያሠራ አይደለም አሉ
በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች የተተበተበው የሰፋፊ እርሻዎች ኢንቨስትመንት ዘርፍ፣ ከአሥር ወራት ዕግድ በኋላ በድጋሚ ብድር እንዲያገኙ ተወሰነ፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የእርሻ ዘርፍ ባለሀብቶች ብድር መለቀቁን በመልካም ጎኑ ቢያዩትም፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር አሰጣጥ ሒደት ላይ የማያሠሩ ማሻሻያዎችን አድርጓል ሲሉ ተችተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ የሰፋፊ እርሻዎች ዘርፍ ያጋጠሙት ዋና ዋና ችግሮች በሚገባ ታውቀው በሚመለከታቸው አካላት ባንኩን ጨምሮ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ፣ በባንኩና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ካለፈው መጋቢት 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በዝናብ ለሚለሙ የእርሻ ፕሮጀክቶች ብድር መስጠት እንዲቆም ማድረጉን አስታውሷል፡፡
‹‹ጉዳዩ በመንግሥት፣ በባንኩና በባለድርሻ አካላት ሲገመገም ቆይቶ፣ ለነበሩት ችግሮች የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ዘርፉን ፋይናንስ ማድረግ እንዲጀምር ውሳኔ ላይ መደረሱን የገለጸው የባንኩ መግለጫ፣ ‹‹በባንኩ በኩል የእርሻ ፕሮጀክቶችን የብድር ጥያቄ ከጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እየተቀበለ ማስተናገድ ይጀምራል፤›› ሲል አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫን መሠረት በማድረግ ለሰፋፊ እርሻዎች፣ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ለመፈብረኪያና ለከበሩ ማዕድናት፣ በተለይም የውጭ ምንዛሪ ለሚያስገኙ ፕሮጀክቶች የረጅምና የመካከለኛ ጊዜ ብድር ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በሊዝ ፋይናንስ ፖሊሲ መሠረት ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በዱቤ ግዥ ሥርዓት ማሽነሪ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ባንኩ አስታውቋል፡፡
የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ያለው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ፣ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክም የመንግሥትን የልማት አቅጣጫ በመከተል በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንቨስተሮች ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስና የቴክኒክ አገልግሎት በመስጠት የበኩሉን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
በባንኩ ፋይናንስ ከተደረጉ የእርሻ ፕሮጀክቶች ውስጥ የተለያዩ ሰብሎች በዝናብ የሚያለሙ የእርሻ ፕሮጀክቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ልማት ባንክ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ለዘርፉ ብድር ማቅረብ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ባንኩ ብድር ማቅረብ ሊጀምር መሆኑን በመልካም ጎኑ የተመለከቱ፣ ነገር ግን የተዘረጋው አዲስ አሠራር የሚያሠራ አይደለም በማለት የሚተቹ አሉ፡፡
ባንኩ ዘረጋ የተባለው አዲስ አሠራር አንድ ተበዳሪ የእርሻ መሬት መመንጠር ሲፈልግ ባንኩ ጨረታ አውጥቶ በሦስተኛ ወገን እንዲመነጠር ያደርጋል፡፡ የተለያዩ ግዢዎችን ባንኩ በራሱ ለመፈጸም ማቀዱም ታውቋል፡፡ ግንባታዎች በሦስተኛ ወገን እንዲያዙም ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሔክታር ያለው የምንጣሮ ሒሳብ ሥሌት በየጊዜው የሚለዋወጥ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል ከነበረው 45 ሺሕ ብር አሁን ከ11 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ ብር ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡
በጋምቤላ ክልል ዲማ አካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ጽጌ ሕይወት መብራቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያወጣው የአሠራር ማሻሻያ ለባለሀብቶች የሚመች አይደለም፡፡ ‹‹በፍጹም የሚያሠራ አይደለም፣ ከብድር ጽንሰ ሐሳብ ጋርም አይሄድም፤›› ሲሉ አቶ ጽጌ ሕይወት ተናግረዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስተሮች የኅብረት ሥራ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ የማነ ሰይፉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኩ በምን ዓይነት ጥናት ላይ ተመርኩዞ ይህንን አሳሪ አሠራር እንዳወጣ አልገባቸውም፡፡ በአዲሱ አሠራር ማንኛውም የልማት ባንክ ብድር ወደ ተበዳሪው እጅ አይገባም፡፡ ያለው ክፍያ በሙሉ በባንኩ በኩል እንዲከፈል የሚል አሠራር ዘርግቷል፡፡ የብድር ወለድ ምጣኔ ከስምንት በመቶ ወደ 12.5 በመቶ ከፍ እንዲልም ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ7.5 ሚሊዮን ብር በላይ ለፕሮጀክት ፋይናንስ፣ ከዚህ በታች ከሆነ ግን በሊዝ ፋይናንስ አሠራር ተዘርግቷል፡፡ የሊዝ ፋይናንስ የሥራ ማስኬጃ የለውም፡፡ ‹‹ለነባር እርሻዎች ሊያገለግል ይችላል፡፡ በጋምቤላና በአሶሳ ክልሎች ላሉ አዳዲስ እርሻዎች በፍፁም ሊያገለግል አይችልም፤›› ሲሉ አቶ የማነ ተከራክረዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል ላይ መሠረት ተደርጎ የተካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ 200 ባለሀብቶች ከልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4.96 ቢሊዮን ብር ብድር ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4.3 ቢሊዮን ብር ተለቋል፡፡
የተለቀቀው ብድር ለታለመለት ዓላማ ያልዋለ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ብድር እንዲቆም የተደረገውም በጋምቤላ ክልል በተፈጠረው የተወሳሰበ አሠራር፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ምክንያት መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከጋምቤላ ኢንቨስተሮች መካከል የተወሰኑት በጅምላ የቀረበውን ትችት መቃወማቸውን፣ የአገር ውስጥና የውጭ ፕሮጀክቶችም ተለይተው ሊገመገሙ እንደሚገባ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡