የኢትዮ ቴሌኮም ከሚገዛቸው ተሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ በመንግሥት ላይ ኪሳራ እንዲደርስ አድርገዋል በሚል በሙስና ተጠርጥረው ከ15 ቀናት በፊት ታስረው የነበሩት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ምክትል ሥራ አስፈጻሚና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ዋስትና ተፈቀደላቸው፡፡
ምክትል ሥራ አስፈጻሚና ሶርሲንግና ፋሲሊቲ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ አብርሃም ጓዴና የሥራ ባልደረቦቻቸው አቶ ፍስሐ ሹመት፣ ፍሬዘር በኃይሉ፣ ልዑል መንበሩ፣ ሰለሞን ግርማ፣ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ዓለማየሁ ግርማና ዮሐንስ አውግቸውን ጠርጥሮ ለእስር ያበቃቸው ፌዴራል ፖሊስ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከከረዩ ቱር ኤንድ ትራቭል ድርጅት ጋር 67 ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ከተፈጸመ ውል ጋር በተያያዘ ሙስና ፈጽመዋል በማለት ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የምርት ዘመናቸው እ.ኤ.አ. 2000 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ከከረዩ ቱር ኤንድ ትራቭል ለመግዛት ውል የፈጸመ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዎቹ ከአቅራቢው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ሐጐስ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የምርት ዘመናቸው እ.ኤ.አ. ከ2000 በታች የሆኑ ተሽከርካሪዎች እንዲያልፉ በማድረጋቸው፣ በመንግሥትና በተቋሙ ላይ ከ343 ሺሕ ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ለጥር 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶት ነበር፡፡
ፖሊስ በዕለቱ ቀርቦ የሠራውን ካስረዳ በኋላ የሚቀረው ምርመራ እንዳለው በመግለጽ ተጨማሪ 14 ቀናት ጠይቆ ነበር፡፡ የጊዜ ቀጠሮውን የፈቀደው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ግን የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ለተጠርጣሪዎቹ ዋስትና በመፍቀድ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ በመሆኑም የከረዩ ቱር ኤንድ ትራቭል በ50,000 ብር፣ የኢትዮ ቴሌኮም ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በ20,000 ብርና ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው በ10,000 ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ሲሰጥ መርማሪ ፖሊስ ይግባኝ እንደሚል በማመልከቱና በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓት የማስረጃ ሕግ 434 አንቀጽ 5(2) መሠረት መርማሪው በአምስት ቀናት ውስጥ ይግባኝ ያለበትን ማስረጃ እስከሚያቀርብ፣ ተጠርጣሪዎቹ በእስር ቆይተው የይግባኝ ማስረጃው ካልቀረበ ጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. 8፡00 ሰዓት ላይ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡