Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊአቶ አስፋው ተፈራ ወልደመስቀል (1921 - 2009)

አቶ አስፋው ተፈራ ወልደመስቀል (1921 – 2009)

ቀን:

ኢትዮጵያ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን (1928 – 1933) በድል ከቀለበሰች በኋላ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማቆም፣ አገሪቱን በየዘርፉ ለማጠናከር በተደረገው የመጀመሪያዎቹ የ15 ዓመታት ጉዞ ውስጥ በተለይ በትምህርት መስክ አስተዋጽኦ ካደረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በ1948 ዓ.ም. ያወጣው የተሻሻለው ሕገ መንግሥት ከመተግበሩ በፊት በነበሩት ዓመታት፣ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር የአገሪቱን ኦፊሲያል ቋንቋ አማርኛን በትምህርትና በሥነ ጽሑፍ ለማበልፀግ እንዲያመች ሲንቀሳቀስ ከተሰለፉት አንዱ፣ በ1945 ዓ.ም. በአማርኛ ትምህርት የበሰሉ በተለይም በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን በብዛት ማግኘት ባልተቻለበትና በአማርኛ ትምህርት አሰጣጥ ችግርን ለማስወገድ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ልዩ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎችን በመመልመል ለማስተማር ከተመደቡትና ለፍሬ ካበቁት መካከል አንዱ አቶ አስፋው ተፈራ ነበሩ፡፡

በ1942 ዓ.ም. በመምህራን ማሠልጠኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት አቶ አስፋው፣ በደብረ ብርሃን ኃይለማርያም ማሞና በአዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተማሪነታቸው በተጨማሪ ለሦስት ዓመታት በተከታታይ የክረምት የማሻሻያ የአማርኛ ኮርስ ለመምህራን ሰጥተዋል፡፡

በጣሊያንኛና በፈረንሣይኛ ቋንቋዎች የተከበበው አማርኛ በአገር ልጆች ጎልቶ እንዲወጣ፣ የመማርያም የሥራ ቋንቋም ሆኖ እንዲገኝ ይጥር የነበረው የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴርን ተግባር ያከናውኑ ነበር፡፡

- Advertisement -

በ‹‹እኔ ማን ነኝ?›› እንደተጻፈው በአገር ፍቅር ስሜት ቀስቃሽ መዝሙሮችም የታጀበ ነበር፡፡

‹‹ለእምዬ ኢትዮጵያ ለውድ አገራችሁ፣

ተግታችሁ ተማሩ ልጆች እባካችሁ

ያልተማረ ዜጋ ደንቆሮ ሆናችሁ

የሌላ አገር ዜጋ እንዳይወስዳችሁ፡፡››

አቶ አስፋው ከአስተማሪነታቸው በተጨማሪ የብሔራዊ ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት) የድርሰት ክፍል በኃላፊነት መሥራታቸው ለደራሲነትም ለተርጓሚነትም በር ከፍቶላቸዋል፡፡

በሀገረ እንግሊዝ በትምህርት አስተዳደር ከፍተኛ ትምህርት (1948-50 ዓ.ም.) ከተከታተሉ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ክፍል በሕዝብ አስተዳደር ዘርፍና ከዚያም በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በመዘዋወር አጫጭር ኮርሶችን ሰጥተዋል፡፡

በ1951 ዓ.ም. በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ በባሕር ክፍል የወደብ አስተዳደር የሠራተኛ ማስተዳደሪያና ማሠልጠኛ ክፍል ሹም በመሆን፣ ከሦስት ዓመት በላይ በዋናው መሥሪያ ቤትና በምፅዋና አሰብ ቅርንጫፎች ያገለገሉት አቶ አስፋው፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የነበራቸው የአገልግሎት ቆይታ ያበቃው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥረው በሌጎስ (ናይጄሪያ) የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሦስተኛ ጸሐፊ በመሆን እስከ 1956 ዓ.ም. ካገለገሉ በኋላ ነበር፡፡

ከሦስት ዓመት ተመንፈቅ የዲፕሎማሲ ሥራ ቆይታ በኋላ በልጅነት ተጀምሮ ወደነበረው የንግድ ሥራ ሲመለሱ የጽሕፈት መሣሪያ መደብር፣ ቼምበር ማተሚያ ቤትንና ኢምፔሪያል ሆቴልን በማቋቋም ከ50 ዓመታት በላይ ስኬታማ ሕይወት መምራታቸው ይወሳል፡፡

አቶ አስፋው የግል ማተሚያ ቤት ለማቋቋምና ወደ ሙያው ለመግባት ከገፋፉዋቸው ምክንያቶች መካከል ሥነ ጽሑፍ መውደዳቸው፣ ለንደን በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ በትርፍ ሰዓት ዩናይትድ ፕሬስ ውስጥ መሥራታቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በዘመነ ዲፕሎማትነታቸው በሌጎስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አጠገብ የነበረው ሪብዌይ ፕሪንተርስ “Africa’s March to Unity” የተባለው መጽሐፋቸው የታተመበት ሲሆን፣ ወደ ኅትመት ሕይወት እንዳቀረባቸው በግለ ታሪካቸው ገልጸውታል፡፡

የግላቸው የሆነው ማተሚያ ቤታቸው መጀመሪያ በ1958 ዓ.ም. የተቋቋመበትና ሥራውን የጀመረው በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት (ኢትዮጵያን ቼምበር ኦፍ ኮመርስ) ሕንፃ ምድር ቤት ውስጥ ሲሆን፣ ስሙንም ‹‹ቼምበር›› ያሉት ንግድ ምክር ቤቱ ማተሚያ ቤቱን ለማቋቋም ባደረገላቸው ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር የተነሳ ስሙን በታሪካዊ ማስታወሻነቱ ለማሰብ መሆኑን በግለ ታሪካቸው ጠቅሰውታል፡፡

አቶ አስፋው በማኅበራዊ ሕይወታቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሙያና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ በአባልነትና በኃላፊነት መሥራታቸውን ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ከግማሽ ክፍለ ዘመን ባለፈ ጊዜ በአንጋፋ የብዕር አዛውንቶች በእነ አቶ አበበ ረታ፣ ራስ ቢትወደድ መኰንን እንዳልካቸውና ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት በተቋቋመው የኢትዮጵያ የድርሰት ማኅበር የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል፣ በ1972 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ደራስያን አንድነት ማኅበር (ኢደአማ) ተብሎ በአዲስ መልክ ሲቋቋም ገንዘብ ያዥና ንብረት ጠባቂ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባና በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶችም በአመራር ቦርድ ውስጥም አገልግለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የላየንስ ክለብ በማቋቋምና በመምራት ለኬንያ፣ ለኡጋንዳ፣ ለታንዛኒያ፣ ለሲሼልስና ለኢትዮጵያ ላይንስ ክለብ በምክትል ገዢነት ለ15 ዓመታት መሥራታቸውም ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በካቶሊካዊትና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በጋራ የተቋቋመው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አሰፋው፣ ለቤተ ክርስቲያን ካበረከቱት አገልግሎት በመነሳት የአዲስ ዓለም ርዕሰ አድባራት ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ‹‹ብላታ ጌታዬ›› የሚል የክብር ስም ከካባው ጋር ሰጥታቸዋለች፡፡

በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ውስጥ የሚጠቀስ ‹‹ዕድሜ›› የተሰኘ መጽሔት በዋና አዘጋጅነት በየጊዜው ያሳትሙ የነበሩት አቶ አስፋው፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ለትምህርት የሚሆኑ ግለ ታሪክና በኢትዮጵያና በአፍሪካ ታሪኮች ላይ የተመሠረቱ 14 መጻሕፍትን ደርሰውና ተርጉመው ለንባብ አብቅተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል መክስተ ሰዋስው (የአማርኛ ሰዋስው)፣ ሰንደቅ ዓላማችን፣ ዶን ኪሾት አንደኛ መጽሐፍ፣ እኔ ማን ነኝ? የዕድሜ ውሎ ማስታወሻ፣ “Africa: Past, present and Future Development Panorama of Historical Revolution” ይገኙባቸዋል፡፡ ለኅትመት የተዘጋጁ ‹‹ዳንቴ አልጊሪ››ን ጨምሮ አሥር መጻሕፍት አሏቸው፡፡ ለዚህም 75ኛ ዓመት ልደታቸውን ባከበሩበት ወቅት ከቀረበው ግጥም አንዱ አንጓ ለጥቅስ ይበቃል፡፡

‹‹ሆኛለሁ ደራሲ ታሪክ ጂኦግራፊ፣

እንዲሁም ከታቢ ልቦለድ ጸሐፊ፡፡

ነበርኩኝ አርታኢ ገጣሚ ተርጓሚ፣

ለሀገሬ ልጆች በሚሆን ተስማሚ፡፡››

ከስድስት ዓመት በፊት እንደጻፉትም፣ ‹‹የሰው ልጅ ጥሮ ግሮ እንዲበላ ወደዚህች ዓለም ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የሚያጋጥሙትን ውጣ ውረዶች እያሳለፈ ያልፋል፡፡ የዕድሜው እርከን እስከሚቋጭበት ድረስ ዘመኑ ሁሉ የድካምና የፈተና ነው፡፡ በመሆኑም የምድሩን ሩጫ ፈጽሞ የኑሮ ምዕራፉን ከመዝጋቱና ወደ ፈጣሪው ከመጓዙ በፊት ለሚተካው ትውልድ ታሪኩን ጽፎ መተው ተገቢ ስለሆነ፣ እኔም ለቤተሰቤና ለወዳጆቼ ለሚያውቁኝም ጭምር ይህንን የሕይወት ጉዞዬን ማስታወሻ አዘጋጀሁ፤›› ብለው ሞትን ቀድመውት ግለታሪካቸውን ለኅትመት ብርሃን አብቅተውታል፡፡

ይሁን እንጂ ባደረባቸው ሕመም ረዘም ላለ ጊዜ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በሕክምና ሲረዱ የቆዩት አቶ አስፋው፣ ሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በተወለዱ በ88 ዓመታቸው አርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው በቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል በሁለተኛው ቀን ተፈጽሟል፡፡

ከአባታቸው ከአቶ ተፈራ ወልደመስቀልና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብዙነሽ ካብትይመር ቅዳሜ ሚያዝያ 12 ቀን 1921 ዓ.ም.፣ በቀድሞ አጠራሩ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት፣ ጨርጨር አውራጃ በጭሮ ወረዳ፣ ጎርቆሬ በተባለ መንደር የተወለዱት አቶ አስፋው፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰበ ተፈሪ (ጭሮ) ከተማ በደጃች ወልደገብርኤል አባሰይጣን፣ በአዲስ አበባ ሊሴ ገብረማርያም፣ በተግባረ ዕድ ትምህርት ቤቶችና በመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ሲከታተሉ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በለንደን የምሥራቅ አፍሪካ ትምህርት ቤት በ1951 ዓ.ም. በትምህርት አስተዳደር ተመርቀዋል፡፡ በዚያው ዓመት ከካናዳ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአፍሪካ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪን በመላላክ ትምህርት አግኝተዋል፡፡

አቶ አስፋው ተፈራ በ1953 ዓ.ም. ከወ/ሮ ጥሩወርቅ መንግሥቱ ወልደ ጻድቅ ጋር ሕጋዊ ጋብቻ በመፈጸም፣ ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ከማፍራታቸውም በላይ አምስት የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...