Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበጀት ዕጥረትና የዕዳ ጫና ፈተና ውስጥ መሆኑን ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

   –  የዕዳ ክምችቱ 102.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል

   –  የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኪሳራ 1.8 ቢሊዮን ብር ነው

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የፋይናንስ እጥረትና የብድር ግዴታ ክፍያዎች የ2009 ዓ.ም. ፈተናዎች እንደሆኑበት፣ በይፋ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደገለጸው፣ ለበጀት ዓመቱ 60.276 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ፍላጎት ውስጥ 10.5 ቢሊዮን ብር ወይም 31 በመቶው ብቻ ምንጩ እንደታወቀ ገልጿል፡፡

ለበጀት ዓመቱ የገንዘብ ፍላጎት ታሳቢ የተደረጉት 25.9 ቢሊዮን ብር ወይም 43 በመቶ ከውጭ አገር የፋይናንስ ምንጭ በብድር፣ ቀሪውን 34.3 ቢሊዮን ብር ወይም  57 በመቶ ከአገር ውስጥ ምንጮች ለመሰብሰብ ነበር፡፡

ከውጭ ብድር ይገኛል የተባለውን እስካሁን አለማግኘቱን እንዲሁም ከአገር ውስጥ ይገኛል ተብሎ የታቀደው 10.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ከየት ሊገኝ እንደሚቻል መታወቁን ገልጿል፡፡

ለተለያዩ የባቡር መሠረተ ልማት ፕሮግራሞች ከተለያዩ አገሮች የተወሰደው ብድር ክምችቱ ከፍ ማለቱንና የብድር ወለድ መክፈል መጀመሩም ጫና ውስጥ እንደከተተው ገልጿል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ የሚመሩት ተቋም ያለበትን ሁኔታ ይፋ ቢያደርጉም፣ በዚያው ልክ ከተገባበት ፈታኝ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚወጣ እርግጠኝነታቸውን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

የባቡር ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ዕዳ ውስጥ እንደሚገቡ ይታወቅ ነበር ያሉት ዶ/ር ጌታቸው፣ ‹‹እንደዚህ ያለ ፕሮጀክት ውስጥ ደፍረን የገባነው መውጫ እንፈልጋለን በሚል መርህ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የባቡር ሥራ ግም ባለ ቁጥር ችግር መጣ ብሎ የሚሮጥ ማኔጅመንት›› እንደሌለ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ፕሮጀክቱ መፍትሔ ለመስጠት የተዘጋጀ አቅም ባለው ማኔጅመንት መመራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለዚህ ዓይነት ችግር ብቻ ሳይሆን ከዚህ በላይ ለሚመጡ ችግሮች ምላሽ የመስጠት በቂ አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከውጭ አገር ባንክ የተወሰደ ብድር ክምችት ከነበረበት 71.2 ቢሊዮን ብር ወደ ብር 76.37 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡

ከአገር ውስጥ ባንክ በቦንድ ሽያጭ የተወሰደ የረዥም ጊዜ ብድር በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረበት 15.4 ቢሊዮን ብር ወደ 17.6 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱንም መረጃው ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ የኮርፖሬሽኑ የዕዳ ክምችት በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ከነበረበት 95.97 ቢሊዮን ብር ወደ 102.52 ቢሊዮን ብር ማደጉን መረጃው ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የሆነ የወለድና የግዴታ ክፍያ በየዓመቱ ለውጭ ባንኮች እየከፈለ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክትና ለተበደረው 2.5 ቢሊዮን ዶላር የወለድና የግዴታ ክፍያ መክፈል የጀመረ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ግን ወደ ሥራ አለመግባቱ ይታወቃል፡፡

በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. 35.47 ሚሊዮን ዶላር ወይም 784 ሚሊዮን ብር መክፈሉን ይገልጻል፡፡   

በጥር ወር 2009 ዓ.ም. 45 ሚሊዮን ዶላር ወይም 1.06 ቢሊዮን ብር መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ይኼንን ግዴታውን ለመወጣት የውጭ ምንዛሪውም ሆነ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች በግልጽ አለመታወቁን መረጃው ያመለክታል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትን ዕውን ለማድረግ የወሰደው 439 ሚሊዮን ዶላር ወለድና የዋና ብድር ክፍያ ከሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ መክፈል የጀመረ ሲሆን፣ 28.93 ሚሊዮን ዶላር ወይም 685.46 ሚሊዮን ብር መክፈሉን መረጃው ያስረዳል፡፡ በጥር ወር ለዚሁ ብድር ወለድና የዋና ብድር ክፍያ 29.24 ሚሊዮን ዶላር ወይም 692.7 ሚሊዮን ብር መክፈል ያለበት ቢሆንም፣ የዚህ ገንዘብ ምንጭ እስካሁን አልታወቀም፡፡

በተመሳሳይ ለአዋሽ ወልዲያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ከቱርክ ኤግዚም ባንክ፣ እንዲሁም ከክሬዲት ስዊዝ የተገኘው 1.165 ቢሊዮን ዶላር ብድር የወለድና ግዴታ ክፍያ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. መክፈል ተጀምሯል፡፡ በተጠቀሰው ወርም 18.73 ሚሊዮን ዶላር ወይም 413.66 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ሲሆን፣ በጥር ወር ውስጥ ሁለተኛው ክፍያ 22.41 ሚሊዮን ዶላር 530.92 ሚሊዮን ብር መክፈል እንዳለበት ሲጠበቅ ምንጩ ግን እስካሁን አልታወቀም፡፡

በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ በጥር ወር መክፈል የሚገባው የብድርና ዋና ወለድ ክፍያ 96 ሚሊዮን ዶላር ወይም 2.2 ቢሊዮን ብር የሚጠበቅበት ሲሆን፣ የዚህ ግዴታ የዶላርም ሆነ የብር ምንጩ ባለመታወቁ ከፍተኛ ሥጋት በኮርፖሬሽኑ ላይ መፍጠሩን መረጃው ያመላክታል፡፡

ዶ/ር ጌታቸው ለቋሚ ኮሚቴው በዕዳ ጫናው ዙሪያ በሰጡት ምላሽ መፍትሔ እንዳላቸው በእርግጠኝነት የተናገሩ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. 2017 ፈተና እንደሚሆንባቸው ግን አልሸሸጉም፡፡

‹‹የ2018 መውጫ መንገድህ ምንድን ነው ካላችሁ የባቡር መስመሩን ከቱሪዝምና ከመሳሰሉት እሴት የሚጨምሩ ቢዝነስ ሥራዎች ጋር እናቀናጀዋለን፤›› ብለዋል፡፡

በምሳሌነትም መንግሥት ፖሊሲውን እንዲቀይር በማድረግ የደረቅ ወደብ ባለቤት መሆን እንደሚቻል፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚያልፍባቸው መስመሮች ላይ ተጓዳኝ ቢዝነሶችን በማልማት መወጣት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የከፋ ነገር ቢመጣ ደግሞ የኮርፖሬሽኑን የተወሰነ ድርሻ ለውጭ ኢንቨስተሮች በመሸጥ የዕዳ ጫናውን መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ያደነቀ ሲሆን፣ ያልተጠናቀቁ ቀሪ ሥራዎች በጂቡቲ መስመርና በቀላል ባቡር መስመር ላይ በፍጥነት እንዲያልቁ አሳስቧል፡፡

ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን የገንዘብ ችግሩ መፈታት እንዳለበትም እንዲሁ አሳስቧል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች