Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎችና ጉምሩክ አራት ተከሳሽ ድርጅቶች በመንግሥት ላይ ያደረሱት ጉዳት የለም አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚሌ ላይ ተመርጠው ፍተሻ ሳይደረግባቸው እንዲያልፉ የተደረጉ አራት ድርጀቶች ማለትም የአቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ነፃ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የአቶ ከተማ ከበደ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የአቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬ ኮሜት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የአቶ ጌቱ ገለቴ ጌትአስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ያደረሱት ጉዳት እንደሌለ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በፍርድ ቤት ገለጸ፡፡

ድርጅቶቹ ጉዳት እንዳላደረሱ ወይም ሳይከፍሉ የቀሩት ታክስና ቀረጥ፣ እንዲሁም የመንግሥት ገቢ እንደሌለ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያስታወቀው ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡                        

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ቁጥር 141356 ውስጥ ተካተው በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት አራቱ ድርጅቶች፣ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከሚሌ ፍተሻ ጣቢያ ሳይፈተሹ እስከ መዳረሻ አቃቂ ቃሊቲና ለገሐር ጉምሩክ ድረስ ታክስ ሳይከፍሉ ቀርተው፣ በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ያደረሱት ጉዳት መኖር ለመኖሩን አጣርቶ ማስረጃ እንዲያቀርብ ባለሥልጣኑ መታዘዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ደብዳቤ በችሎት ተነቧል፡፡ ባለሥልጣኑ ባደረገው ምርመራ ድርጅቶቹ ያልከፈሉት ታክስና ግብር እንደሌለ ገልጿል፡፡ ባለሥልጣኑን ምላሽ ከሰጠ በኋላ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ለጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ተቃውሞ ዓቃቤ ሕግ የተጠየቀውን ማብራሪያ በሚመለከት ክስ ሳያቀርብ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠት እንደሌለበት ተናግረው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በትዕዛዙ መሠረት ድርጅቶቹ ጉዳት አድርሰዋል ቢባል እንኳን ባልተከራከሩበት ጉዳይ እንዴት ብይን ሊሰጥባቸው እንደሚችልም በማንሳት አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ለፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ ትዕዛዙ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጾ ምላሽ መስጠቱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች