Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጥጥ ምርትን በወቅቱ ኤክስፖርት ማድረግ እንዳልተቻለ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ኤክስፖርት እንዲፈቀድ ተጠየቀ

ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ግብዓት የሆነው የጥጥ ምርት ለገበያ በሚቀርብበት በዚህ ወር፣ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሠራተኞች ስብሰባ በመግባታቸውና ከተሃድሶ ከወጡ በኋላም የመመርመሪያ ላቦራቶሪው በመበላሸቱ ግብይቱ መስተጓጐል ገጠመው፡፡

ያመረቱትን የጥጥ ምርት ለገበያ ያቀረቡ ባለሀብቶች በወቅቱ መሸጥ ባለመቻላቸው፣ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ ስለሆነ ኤክስፖርት ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ ጠየቁ፡፡

በጥጥ አቅራቢዎችና በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች መካከል ያለውን የጥጥ ግብይትን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ግብይት የሚፈጸምበትን 510 ሚሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አግኝቷል፡፡

ነገር ግን ይህንን ግብይት ለመፈጸም ተዳምጦ መጋዘን የገባውን ጥጥ ደረጃ የሚያወጣለት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት ሠራተኞችን በሙሉ ይዞ ስብሰባ በመቀመጡ፣ ከስብሰባ ከተወጣም በኋላ የመመርመርያ መሣሪያዎች የቴክኒክ ብልሽት ስለገጠማቸው፣ ባለሀብቶች ያስገቡትን ጥጥ በወቅቱ መርምሮ ማቅረብ አለመቻሉ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋወሰን አለነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግብይት ለመፈጸም የግድ የኢንስቲትዩቱ የምርመራ ውጤት ያስፈልጋል፡፡

‹‹ባለፈው ዓርብ ጀምሮ የመመርመርያ ላብራቶሪው መበላሸቱ ተገልጾልኛል፡፡ ነገር ግን ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. መመርያ ማሽኑ እንደተጠገነ ተገልጾልኛል፤›› ሲሉ አቶ አስፋወሰን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዘመናዊ የመመርመርያ መሣሪያ ባለቤት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዘመናዊ መመርመርያ ማሽን የቴክኒክ ብልሽት የሚገጥመው በመሆኑና ብልሽቱን ለመጠገን በቂ ባለሙያዎች ስለሌሉ ባለሀብቶች እንደሚመረሩ ይናገራሉ፡፡

የኢንስቲተዩቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ ለሪፖርተር፣ ‹‹የቴክኒክ ብልሽት በየጊዜው ያጋጥማል፡፡ ጥገናውን ለማካሄድ የተወሰኑ ቀናት ወስደውብናል፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ችግር ያሰፋው ለስምንት ቀናት የ‹ጥልቅ ተሃድሶ› አካል ነው የተባለው ስብሰባ ላይ ስለነበሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢንስቲትዩቱ ያለው ማሽን በሚፈለገው ደረጃ ምርመራ ማካሄድ የሚችል ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ መሰለ ማሽኑ፣ ማክሰኞ ግን ተጠግኖ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

በማሽን ብልሽትና በስብሰባ ምክንያት በአግባቡ አገልግሎት አላገኘንም ካሉ ባለሀብቶች መካከል አቶ አብረሃለይ ይደግ ይገኙበታል፡፡

አቶ አብረሃለይ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ማክሰኞ ጥር  16 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ ለመሸጥ ያስገቡት 826,215 ኩንታል ጥጥ ተመላሽ እንዲሆንላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጥጡ ተመላሽ እንዲሆንላቸው የጠየቁበትን ምክንያት አቶ አብረሃላይ ሲገልጹ፣ ያስገቡት ከዛሬ ነገ ‹አልተመረመረም›፣ ‹ማሽን ተበላሸ›፣ ‹ጥልቅ ተሃድሶ› እየተባለ እሳቸው በማይመለከታቸው ጉዳይ መጉላላታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከፍተኛ እንግልትና ጉዳት ደርሶብኛል፤›› ሲሉ በደብዳቤ የገለጹት አቶ አብረሃለይ፣ ‹‹አሁን ግን ሠራተኞቼ ክፍያ ልፈጽምላቸው ባለመቻሌ የተሰበሰበውን ምርትና ካምፑን ለማቃጠል በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፤›› ሲሉ ምርቱ እንዲመለስላቸውና በርካሽም ቢሆን ለሌላ ገበያ ለማቅረብ መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅዶቹን ለውይይት ባቀረበበት ወቅት፣ የጥጥ ግብይት መመርያ እየተሻሻለ መሆኑንና ሲበላሽ የቆየው ላብራቶሪም እንደተሠራ ገልጾ ነበር፡፡

ነገር ግን ችግሩ በየወቅቱ እያጋጠመ በመሆኑ ሌሎች አማራጮች እንዲታዩላቸው ባለሀብቶቹ እየጠየቁ ነው፡፡ አገር ውስጥ በሥርዓቱ ግብይት መፈጸም ካልተቻለ ኤክስፖርት ማድረግ ሊፈቀድ ይገባል ሲሉ፣ ባለሀብቶች ለመንግሥት ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች