– የግንቦት ሰባትን የትጥቅ ትግልን ሊቀላቀሉ ሞክረዋል የተባሉ ተከሰሱ
ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው አክራሪ የሽብር ቡድን ጋር ከተገናኙና ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የጅሃድ ጦርነት ለማወጅ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ እንደነበር በማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል የተባሉ ተከሳሾች ከአራት ዓመት በላይ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡
ፍርደኞቹ ጃፋር መሐመድ፣ መሐመድ ኑር፣ ሐጂ መሐመድ ታሚ፣ አንዋር ቲዳኔና ሼህ ጀማል ያሲን፣ መሐመድ አባቢያና ሼህ ጀማል አባ ጨቦ ናቸው፡፡ የአክራሪነት ሥልጠና ለመውሰድ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው አክራሪ ቡድን በተጨማሪ ወደ ሶማሊያ በመሄድ ከአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋርም መሠልጠናቸውን፣ የቅጣት ውሳኔ የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ገልጿል፡፡
ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ የአክራሪነት ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ሌሎች አባላትን መመልመላቸው፣ ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በሰው ማስረጃዎች ማረጋገጡን ውሳኔው ያሳያል፡፡ ፍርደኞቹ በጅማ አካባቢ በሚገኙ ጫካዎች አዲስ ለተመለመሉ አባላት ሥልጠና ከሰጡ በኋላ፣ ለተጨማሪ ወታደራዊ ሥልጠና ወደ ሶማሊያ በመሄድ አልሸባብን ለመቀላቀል የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በማዘጋጀት ላይ እያሉ በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም፣ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃው ማረጋገጡን ውሳኔው ይጠቁማል፡፡
ፍርደኞቹ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ስላስረዳባቸው እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ ቢሆንም፣ ባቀረቡት ማስረጃ ሊያስተባብሉ ባለመቻላቸው ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው የውሳኔው ሰነድ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም መሐመድ ኑር፣ ሙዲን ጀማልና ሼህ ጀማል አባ ጨቦ እያንዳንዳቸው በአራት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ጃፋር መሐመድ፣ መሐመድ አባቢያና አንዋር ቲዳኔ ደግሞ እያንዳንዳቸው በአራት ዓመታት ከአምስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆነው አቶ መልካሙ ገበየሁና ምሥራቅ ጐጃም እንደሚኖሩ የተገለጸው አቶ አንሙት ታሞ፣ አቶ ሲመሽ አስማሴና አቶ ባዬ ደሱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል በመሆን የድርጅቱን የትጥቅ ትግል ለመቀላቀል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ በአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን ተመልምለውና ሌሎችን በመመልመል በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ሌሎች ነዋሪዎችን ለመቀስቀስና ድርጅቱ የሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ይዘው እንዲቀርቡና ጠበቃ ለማቆም አቅም የሌላቸው መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ለጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጥሮአቸዋል፡፡