እነሆ መንገድ እነሆ ጉዞ! ከወሎ ሠፈር ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። መንገድ አልቆ መንገድ ልንጀምር፣ ዕድሜ ጨርሰን ዕድሜ ልንቀጥል እንራመዳለን። ወያላው፣ “የሞላ ሁለት ሰው! ከእነ ሰርተፊኬቱ፤” ብሎ ይጮሃል። “የምን ‘ሰርተፊኬት’ ነው የሚያወራው?” ሰው ይደናበራል። “ምነው ኢሕአዴግ ብቻ ነው ለጥቅም ብሎ ለሚሰበሰብለት ታዳሚው ‘ሰርተፊኬት’ መስጠት ያለበት? እኛስ ከማን እናንሳለን?” ወያላው የሰውን መደናገር ግልጽ አደርጋለሁ እያለ ነገር ያወሳስባል። “አብዷል እንዴ ይኼ?” ከመካከላችን አንዱ ይጠይቃል። “መቼ እሱ ሆነና? የትንኙን ርቢ፣ የዝንቡን ቁጥር መጨመር ሳይቀር ከመንግሥት አምባገነናዊ አገዛዝ ጋር ካላዛመዱ የማይሆንላቸውን እያየ እኮ ነው የሚቀባጥረው. . .” እያለ ይመልሳል ሌላው። እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣ የእንካ ስላንትያ ቅብብሎሽ ወጪ ወራጁ ይናከሳል። የሆነውን ሁሉ በመልካምና በክፉ ትውስታ ጉያ ውስጥ ደብቀን በዘመን መለዋወጥ የምናምን ፍጥረታት፣ በዘመን መለወጫ ዋዜማ ስንታይ ልዩ ስሜት እንፈጥራለን።
ሰው በደሉን ረስቶ በነገር ጉሽሚያ ወዲያና ወዲህ ተከፍሎ ያሳለፋቸውን ወራት ዘንግቶ በአንድ እንቅብ ተሰፍሮ ያደመ ይመስላል። እንደፈለገውና እንደወረደ ከሚያወራው ወያላ በቀር ዛሬ የሁሉም ሰው ቀልብ ያረፈው ራስን ለመለወጥ ተስፋ የሰነቀበት የሚለወጥ ዘመን ላይ ነው። በአሮጌ በሬ እያረሱ የፊትን ሩጫ በትዕግሥት መሮጥ ስለማይቻል፣ ባለመሆን ጥላሸት የከሰለን ዕድል በሚያንፀባርቅ ሳሙና ለማጠብ ተስፋ ስለሚያሻ ሁሉም ጥቂት ማንነቱን ረስቶ፣ ጥቂት ኑሮውን ችላ ብሎ ከአቅሙ አምሮቱን አስቀድሞ ስለሚሸኘው ዓውደ ዓመት ይንደፋደፋል። ዓለም አሮጌ ጆንያዋን እንደ ወትሮው ሁሉ አራግፋ በአዲስ ጅማሮ በአዲስ ዓመት ልታስሮጠን ፍቅረኛዋን እንደምታታል ዘማዊት የዓመት ግብሯን ታገባለች። ከዕወቀት ሐዘን፣ ከጥበብም ብዛት ተስፋ ቢስነትን ያተረፈ ሁሉ መስሎ በማስመለስ የመኖር ጥበብ ይህችን አታላይ ዓለም የናቃት ይመስላል። የመሆንና ያለመሆን መንገድ እንዲህ ቅዠት ባየለበት ስሜት ይጀመራል። እነሆ መንገድ!
“ስማ አንተ! ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” አንድ አፉን ያዝ የሚያደርገው ኮስታራ ጎልማሳ ወያላው ላይ አፈጠጠበት። “ምን አልኩ ጋሼ?” ወያላው ጎልማሳው ስለምን እየጠየቀው እንደሆነ ስላወቀ ከሸረኛ ሳቅ ጋር ጥያቄ አቀረበለት። “ያልሰማሁ መስሎህ እንዳይሆን! እንኳን ይኼንን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን፤” አለ ጎልማሳው። ወያላው ቀነጣጥቦ ካከማቸው ጫት ጥቂት ቆንጠር አድርጎ ሲያበቃ፣ “ጉድ እኮ ነው! ‘የፌስቡኩን’ አደን ሳትጨርሱ ደግሞ ታክሲ ተራ ገባችሁ?” ብሎ ያስነሳውን አቧራ ደንበኛ ማዕበል አድርጎት አረፈ። “ስለሰርተፊኬቱ እየጠየቅከኝ ከሆነ ግን ላንተ በቃ ሁለት እናደርግልሃለን!” አለ። “ታዲያ ይኼንንም በጉልበት ከምትወስዱት በፀባይ፣ በመልካም ሁኔታ ከሰው ጋር በማደርና አገር በማስተዳደር ቢሆን ይመረጣል፤” አለው። ‘የመረቀነ ማንን ይፈራል?’ የሚል ይመስላል ወያላችን። ጎልማሳው ተንቆራጠጠ።
“በማን ላይ ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ’ አሉ! አሁን አንተ በማን ላይ ሆነህ ነው እኛ፣ እናንተ እያልክ የምተዘባርቀው?” ብሎ ጎልማሳው ሲያፈጥ ወያላው፣ “ስንፈልገው በምናረክሰው ስንፈልገው በምንዘክረው ሕገ መንግሥታችን ላይ ቆሜ ነዋ። ዛሬ እኮ መሬቱም የሕዝብ አልሆነ፤” ብሎ ከራሱ ከጎልማሳው ጎን የተቀመጠ ተሳፋሪ ወያላውን በይፋ በመደገፍ መለሰ። “አቦ በቃህ ነገር አብርድ! ዓመት በዓል በምጥ ደርሶ በምጥ እየሸኘን ደግሞ ሌላ ጣር ልታመጣ ነው?” በጎርናና ድምፁ ሾፌራችን በገላጋይነት መሀል ገባ። ምጥ ሲባል የነቁት አዛውንት ተሳፋሪ ጮክ ብለው፣ “እህ በይ ግዴለም ግፊው ይወለዳል፣ ሽል ይፀነስ እንጂ አጥንት ሆኖ ያድጋል’ ይባላል ይኼውልህ!” ብለው ፈገግ አሉ። ገና ጉዞው ከመጀመሩ ከወዲህ ወዲያ የተነሳውን አለመግባባት ስናስተውል፣ ቀሪዎቻችን በግርምት ፈዘን ቁጭ። እስከ መቼ በማንግባባት ጎዳና ፈዘንና ግራ ተጋብተን እንደምንኖር ብቻ እንጃ!
ጉዟችን ቀጥሏል። በታክሲያችን የሙዚቃ ማጉያ በኩል ኤፍሬም ታምሩ ‘አንቺ ልጅ. . . አንቺ ልጅ. . .’ ይላል። መጨረሻ ወንበር ላይ ከተመቀመጥነው ተሳፈሪዎች ሁለቱ ስለዓመቷ የመጨረሻ ቅዳሜ ምሽት ሲጨዋወቱ ይሰማሉ። “እኔ ድሮም ስድስት ገዴ አይደለችም እኮ” ይላል አንደኛው። “እንዴት?” ይለዋል ወዳጁ። “ሰባትን ትቼ ስድስት ቁጥር ማሊያ ለብሼ መጫወት እንደጀመርኩ እኮ ነው ያኔ እግሬ የተሰበረው። ያኔ ትዝ ይልሃል በ2006 ዓ.ም. በመጨረሻዋ ቅዳሜ ቡድናችን በሜዳው መሸነፉ ሳይንስ፣ ማታ እንዳያሃት ያች ልጅ ነካክታኝ አጫውታኝ ነገሩን መስመር ሳታስይዘው ልቤን ሰብራው ሄደች፤” አለ በቁጭት። ከቁጥር ተጣልቶ በቁጥር ተስፋ አድርጎ። “እንዲያው ሰውን ግን አይተኸዋል? ዋልያ ያሸንፋል ብሎ ለመስከርና ለመዝለል ቋምጦ ውሎ ሲያበቃ ድል ፊቷን ስታዞር ቅዳሜን የዓመቱ የመጨረሻዋ ቅዳሜ ብሎ ሰይሞ እንዳይሆን ሲሆን ይደር?” ጠየም አጠር የሚለው ነው የሚገረመው። ይኼ ሁሉ ትዝታ በአፍሪካ ዋንጫ ሰሞን ሲታወስ ወይ ጉድ አያሰኝም?!
“ታዲያስ! ‘ሰበቡ ነጠላ ለብሼ’ የሚል ዘፈን የተዘፈነው ለምን ይመስልሃል? ‘ሳታማሃኝ ብላ’ የተባለውስ ያለአንድ ይመስልሃል? ሐበሻ ዘመኑን በሙሉ ሰበብ አስባብ እየፈለገ መሠረት ለሌለው ነገር ለመጥፋትና ለመጠፋፋት የሚያክለው ስለሌለ እኮ ነው፤” አለ ነገሩን የጀመረው ልጅ። “ኤድያ ጀመረህ ደግሞ እዚህ የፈረደበት ሕዝብ ላይ እንደ ሐምሌ ዶፍ መውረድ። ይልቅ ምናለበት ሁሉን በአንድ መውቃት ትተህ ስለዚያች ቀሽት ልጅ መጨረሻ ብትነግረኝ?” ይላል የወዲያኛው። ይኼው ልጅ በአደባባይ ሙግት ነፍሱ የዛለች በኩሽና ጨዋታ ቀልቡ የተመሰጠ ግዴለሽ እንደሆነ ያስታውቃል። መሰልቸት ስንቱን ከሚጠበቅበት ሥራውና ኃላፊነቱ አዘግይቶት ይሆን?
ከመጨረሻ ወንበር ጥጋቸውን ይዘው፣ መስኮት ተከፍቶባቸው የሚነፍስባቸውን ንፋስ እየታገሉ በአሳር የሚጠበሱ አዛውንት ጨዋታ ያነሳሉ። “አዳሜ እንዲህ የሆድሽን አውጥተሽ እያራገፍሽ የመናገር ነፃነት ታፍኗል እያለሽ አሳይለም ትጠይቂያለሽ! ወዬውልሽ እያንዳንዳሽ! በፍርድ ቀን የምትመልሽውን አዘጋጂ!” አሉ። “እኔ የሰማሁት ግን የመጻፍ እንጂ የመናገር ነፃነት ችግር አለ ሲባል አይደለም፤” አለች እዚያው ቅርባቸው። “የተጻፈ ሕይወት እየኖራችሁ ማነው አትጻፉ ያላችሁ በእስጢፋኖስ?” አዛውንቱ ነገሩን ማጠጠርና ማዋዛት ይዘዋል። “ምነው አባት ሕገ ሰማይና ሕገ መንግሥት ከተለያዩ ቆዩ እኮ?” ሲላቸው ደግሞ ያ አጭሩ ነገር ጫሪ፣ “እሱንማ መርጣችሁ ነዋ። የሰው መንግሥት ድሮም ወጉ የሰው ነው። ምነው ግን የዛሬ ልጆች ይኼ ይኼ ማስተዋል ርቋችሁ ከእባብ እንቁላል የዶሮ ጫጩት ትጠብቀላችሁሳ? ደግሞ ይኼንንም ፌስቡካችሁ ላይ ለቅልቁና አነካኩኝ አሉዋችሁ፤” ሲሉ ተሳፋሪዎች ሳቁ፡፡
ጎልማሳው ዘወር ብሎ፣ “ዘመኑ የመነካካት ነው አባት። ሳይነካኩ መኖር ከብዷል፤” ሲላቸው ደግሞ “ኧረ እኔስ የከበደኝ ሌላ ነው?” ብለው ልብ አንጠልጥለው ዝም አሉ። “ይንገሩና!” ጎልማሳው ወተወታቸው። “አትኖረው ይመስል ምኑን ልነገርህ?” አሉት። “እሱን እኮ ነው የምልዎት፤” ሲላቸው፣ “ምን ይላል ሰውዬው? የራሴን ሐሳብ መልሰህ እየነገርከኝ ነው ‘እሱን እኮ ነው የምልዎት’ የምትለኝ? አዲስ ሐሳብ ሳታፈልቁ አዲስ ራዕይ ሳትቀርፁ ነው ታዲያ ማይኩ የጥቂቶች ብቻ ሆነ ብላችሁ የምትጮሁት? ለመቃወም ለመቃውምማ ሰይጣንም ይቃወማል እኮ። ቀናነትን በጠማማነት ለማሸነፍ የመረጠው የትግል ሥልት ግን የት አደረሰው? የትም!” እያሉ ያሻቸውን ነካክተው ጠያቂና ሞጋቾቻቸውን ዝም አሰኙ። መቼም ዕድሜ የጠገበ ሰውና ሥርዓት ዝም የሚያሰኝበት ነገር አያጣም!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አዛውንቱ በአንዱ ጥግ ያወጋሉ። ወጣቶች ልብ ብለው ያደምጣሉ። “አንድ ሰውዬ በግ ሊገዛ ገበያ ወጣ. . .” ያቋርጣቸዋል ቆብ የደፋው ወጣት። “መቼም በዛሬ ገበያ ባልሆነ?” “ቆይ ትደርስበታለህ። ምናለበት ለነገር ከምትቸኩሉ ጨዋታ ብታስጨርሱ?” አዛውንቱ ወሬያቸውን ስላቁዋረጡዋቸው ደህና እንዳልተግባቡዋቸው ወጣቶቹን ማማረር ጀመሩ። አጠገቤ የተቀመጠው ላጤ፣ “መጨረስ ምንድነው? ያስጨረሰስ ማን ነው? የጨረሰን እንጂ የጨረሰልንስ አለ እንዴ?” ሲለኝ ለካ ሰምተውታል። “እሱንስ ስታጨርሰኝ ታገኘው መስሎኝ? የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ አሉ. . .” ተረቱ አዛውንቱ። “ተቀይሯል አባት። ለዛሬዎቹ አይሠራም፤” አለቻቸው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠችው ወይዘሮ። “እኮ ምን ተተረተባቸው?” አዛውንቱ ሳያስቡት መስመራቸውን ሳቱ። “እነማን ላይ?” ወይዘሮዋ ጠየቀች። “ስለነማን ነው የምናወራው? ስለዛሬ ልጆች ነዋ፤” ቁጣ ቁጣ አላቸው። ወይዘሮዋ፣ “ዛሬ ደግሞ ምን ልጅ አለ? ገና ሳይወለዱ እየሸበቱ፤” ማባዘት ወደ ፈለገችው ነገር ስትንደረደር አዛውንቱ፣ “በይ ተይው. . .” ብለው ወደ በግ ገበያቸው ተመለሱ። “እና ምን እያልኳችሁ ነበር? . . . አዎ፣ በግ ሊገዛ ገበያ ሄደ። አንዱን የሰባ ያለተለተ በግ አይቶ ወደ ባለበጉ ጠጋ አለ ‘ስንት ነው?’ አለው። ‘60 ብር’ ሲለው ነጋዴው፣ ‘60 ብር? በ20 ብር አህያ አልገዛም እንዴ?’ እያለ ተነጫነጨበት። ታዲያ በግ ነጋዴው ምን አለው መሰላችሁ? ‘የሚጣፍጥህን አንተ ታውቃለህ. . .” ጥልቅ ዝምታ ሰፈነ። ወያላው ‘አማሌሌሌሌን’ ያፏጫል።
ወጣቶቹ አዛውንቱ ያመጡት ምሳሌ አንድምታ ሰፍቶባቸው ያወጣሉ ያወርዳሉ። ወይዘሮዋ አንዴ ረብሸኛ ልጇን አተኩራ እያየች ታገነግናለች። መውረጃችን ደርሶ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ሲከፍተው አዛውንቱ ወደ ወጣቶቹ ዞረው፣ “የዛሬን አያድርገውና ይህቺ አገር ስንት ባለቅኔ፣ ስንት ነገር ፈቺ፣ ተፍጥሮን መርማሪ እንዳላማጠች ይህቺ ምሳሌ ቋጥኝ ትሁንባችሁ?” ብለው እያዘኑ ተነሱ። “ብቻ ጊዜው አጭበርባሪ ነው። የትኛዋም አገር የወጣቶች ናት። ቢያጣምሙዋትም ቢያቀኑዋትም ኃይሉ አላቸው። ዋጋ መክፈል እየፈራችሁ ርካሽ ነገር አትምረጡ አደራ። ኤድያ የእኔ ነገር። ለካ ጊዜው የዴሞክራሲ ነው። የሚጣፍጣችሁን እናንተ ታውቃላችሁ። ብቻ. . . ብቻ. . .” እያሉ ወርደው በእግራቸው ተጓዙ። ‘ልፋ ያለው ገበላ ይወቃል’ ያለው ማን ነበር? መልካም ጉዞ!