Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርጥልቅ ተሃድሶው ውኃ ሲወስድ አሳስቆ ነገር ሲወስድ አራርቆ

ጥልቅ ተሃድሶው ውኃ ሲወስድ አሳስቆ ነገር ሲወስድ አራርቆ

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ጥልቅ ተሃድሶው ለመረረውና ሆድ ለባሰው ሰው እንደሚፈልገው ፈጣን ባይሆንም የተደበቀውን ገሀድ እያወጣ፣ የካዱትን እያሳመነ፣ የዋሹትን ዋሽተናል እያሰኘ አዝጋሚ ጉዞ እያደረገ ነው፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን መርህ ሳይገነዘብ ሃያ አምስት ዓመታት በተጓዘው ሥርዓት ላይ ሰዎችን እንደ ውኃ እያሳሳቀም እንደ ነገር እያራራቀም ነው፡፡

እንደ ውኃ እያሳሳቀና እንደነገር እያራራቀም አንዱን በሌላው እያስበላ የሥርዓቱን ልብስ እየገፈፈ እርቃን እያስቀረ ነው፡፡ እንደ ዶፍ ዝናብ ባይረግጥም እንደ ሰደድ እሳት በቀስታ በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ሥር እየሰደደ ነው፡፡ እንደ ማዕበል እንዲነጉድ የሚፈልጉ አንዳንዶች ዱብ ዕዳ እንዲሆንም የሚመኙ ቢኖሩም እኔ ግን አልመክርም፡፡ በደንብ ያልበሰለው በደንብ Anchorይብሰል እላለሁ፡፡

- Advertisement -

ስለኪራይ ሰብሳቢነት ትርጉም ሳያውቅ በቀን አሥር ጊዜ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት እያወራ ደመወዙን የሚበላው የመንግሥት ሠራተኛና ሹመኛ ነጭ ላብ አልቦታል፡፡ አጎብድዶ ደጅ ጠንቶ ሰብቆ ያለውድድር የተሾመ ሰው ለኢኮኖሚስት እንኳ ረቀቅ የሚለውን የውድድር ጉድለት ጽንሰ ሐሳብ አመልካች ቃል ጠቅሶ ሌላውን ኪራይ ሰብሳቢ ሲል፣ ስለራሱ አሳፋሪ የሆነ ቃል እየተናገረ ነው፣ አለማወቁን እየለፈፈ ነው፡፡

እስከ ዛሬ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ብቻ ‘ይኼ ኪራይ ሰብሳቢነት ምንድን ነው? እኔም እኮ አንድ የማከራየው ቤት አለኝ’ ብሎ መጠየቁን ነው የማውቀው፡፡ የማያውቁትን ጠይቆ ለመረዳት በመድፈርም ተከታይ ቢያጣም ኃይሌ ሪከርድና ዝምታ ሰብሯል፡፡

ሰሞኑን የነጋዴዎች ተሃድሶ የሚመስል በኑሮና ቢዝነስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በርበሬ ውስጥ ሸክላ የጨመረውን፣ ዘይት በእግሩ ያቦካውን፣ እንጀራ ውስጥ ጀሶ የጨመረውን፣ ወዘተ እያነሱ ሰዎች ስለንግድ ሥነ ምግባር ሲወያዩ ሰምቼ ነበር፡፡ 

ከኢንቨስትመንት ባለሥልጣን የተጋበዙ ባለሙያ ከአፍሪካ ለመጡ ኢንቨስተሮች፣ ‘ሥልጠና ስንሰጥ እናንተ እኛን ኢንቨስት አድርጉ ብላችሁ ትሰብኩናላችሁ፣ የእናንተ ሰዎች ለምን እኛ ጋር መጥተው ኢንቨስት አያደርጉም?’ አሉን አሉ፡፡

‘የእኛ ሰዎች ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ወዘተ ሄደው የጉልበት ሥራ ሠርተው ይኖራሉ፡፡ የእናንተ ሰዎች ለምን እኛ ጋር መጥተው የጉልበት ሥራ ሠርተው አይኖሩም?’ ብለው ለምን አልመለሱም ብዬ አሰብኩ፡፡ ‘ለእናንተስ መቼ በቃና?’ የሚል መልስ ሰጥተው እንዳያሳፍሯቸው ፈርተው ሊሆንም ይችላል ብዬም ገመትኩ፡፡

እንጀራ እጠግብ ብለው እጃቸውን ለሙስናም ሆነ ለምን ቸገረኝነት የአዕምሮ ዝቅጠት ከሰጡ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ ጥቂት ሺዎች በጥልቅም ሆነ ላይ ላዩን በመታደስ ወዲያው የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ቢመጣም ‘ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል’ ይሆናል፡፡ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት ሳያገኙ፣ ሕዝብን ቀድመው ሳያነቁ፣ አመፅ በታየ ቁጥር ለሥልጣን ቋምጠው ቤንዚን የሚያርከፈክፉ የፖለቲካ ሰዎች ፋይዳ ቢስ ናቸው፡፡ ሕዝብ ለትንንሽ ሰዎች ሥልጣን ደሙን አያፈስም፡፡

ፖለቲከኞችና አብዮታውያን ወይም የዴሞክራሲያዊ መብት ታጋዮች ሕዝብ ለማስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት፣ በድብቅና በግልጽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች ፍልስፍናዎችን፣ ፕሮግራሞችን፣ ታሪኮችን፣ ለውጦችን ይተነትናሉ ይጽፋሉ፡፡ ሕዝብን ያሳምናሉ፣ ያነቃሉ፣ ኅብረ ብሔር ድርጅት ይፈጥራሉ፡፡

የግል ታሪኩን ወይም ልብወለድ ተረት የጻፈና የተረጎመ ወይም በምርጫ ሰሞን የተሰጠውን ጥቂት ሰዓታት ተጠቅሞ በቅጡ የማያውቀውን ነገር የቀባጠረ ሁሉ ሕዝብን ያነቃ ይመስለዋል፡፡ የቢሮ ማኅተምና ቁልፍ ተሰራርቀው ከዛሬ ጀምሮ ሊቀመንበር፣ ፕሬዚዳንት፣ ዋና ጸሐፊ እኔ ነኝ የሚባባሉ ብሎላቸው ለሥልጣን ቢበቁም በጎሳና በጓደኝነት ሥልጣንን ለኔ ለኔ ብለው መልሰው ይጣላሉ፡፡

እያረጀ ያለው የመገነጣጠል መጥበብ ስብከትና ስሜት ከነጀብደኝነቱ ሳይከስም፣ በኢትዮጵያ ስም ከመታገልና ከማታገል ከመታደስና ንቃተ ህሊናን ከማሳደግ በፊት ሁሉም በእኩል ዓይን የሚታይበት የጋራ አገር መገንባት አይቻልም፡፡ መንግሥት ተጥሎ መንግሥት ቢመሠረትም እንኳ የኋለኛው የቀድሞው ግልባጭ (ፎቶ ኮፒ) ይሆናል፡፡ የነፃነት ታጋይ የነበረው ኢሳያስ ወደ ጨቋኝ ኢሳያስነት እንደተለወጠ እንሰማለን፡፡

በልማዳችንና ከአያት ቅድመ አያት በወረስነው ወግ ድህነቱ ዕጣ ፋንታው ስለሆነ ነው እያልን፣ የፈረንጆቹ አልበቃ ብሎ ልጆቻችንን የአጎራባቾቻችን ሎሌና ገረድ ለማድረግ እያሰብን ሳለን በተሃድሶ ጥቂቶች ቢገማገሙ ምን ለውጥ ይመጣል?

እንደ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አስተምህሮት ሰዎች ከምርጫ የሚገኝን ጥቅም የላቀ ለማድረግ አዋቂ እንዲሆኑ፣ ሁሉም ሰው በቂ አዎንታዊ መረጃዎችን መጨበጥ አለበት፡፡ (Acquire Positive Information to be Rational Enough to Optimize Benefits from Choice) ወደን በምርጫችን ሳይሆን ሁኔታው ገፍቶ መጥቶ ምቾቱና ድሎቱ ቀርቶ ለምን እንደተፈጠርንና ከሌሎች ለምን እንደምናንስ ማወቅ ተስኖናል፡፡ እኛ ሁኔታውን አንቆጣጠርም፣ ሁኔታው እኛን ይቆጣጠረናል፡፡

 

በዚህ ሰሞን በጋዜጣ በወጣ ዜና ያለፈቃድ ሄደው በሰው አገር ሲንከራተቱ እስር ቤት ለገቡት ምህረት እንዲደረግላቸው ተማፅነውና በመንግሥት ዕውቅና የተሰጣቸው፣ ገረድና ሎሌ ለመላክ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዓረብ አገር ባለሥልጣናት ጋር ተዋውለው መጡ ተባለ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ‘ሌሎች አገሮች በእኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በነበሩ ጊዜ የሴቶቻቸውን ፀጉር ሽጠው ነበር፡፡ የእኛም የወደፊት ተስፋችን በሀዋላ የሚላክ ገንዘብ ከፍ እንዲል መትጋት ነው’ አሉ፡፡ ተገርደን ሁለመናችንን ሽጠን ነው ለአገራችን በሀዋላ ገንዘብ መላክ የምንችለው፡፡ ዕውን እኛ የተፈጠርነው ለዚህ ብቻ ይሆን እንዴ? ዕጣ ፈንታችን ግርድናና ሎሌነት ነው እንዴ? ሌላ ምርጫ የለንም እንዴ፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው መሆን የነበረበት ስለዚህና መሰል ጉዳዮች እንጂ፣ የራበው ወይም በዚህ መሰል ኅብረተሰብ ውስጥ ኖሮና ተኮትኩቶ ስርቆትን ዓመል ስላደረገው ሰው አልነበረም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአንድ ጆሮ ተሰምቶ በሌላ ጆሮ የሚፈስ የቴአትር መድረክ ቀልድ አይደለም፡፡ የአዋጅና የሕግ ያህል ሊቆጠር ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በግልጽነታቸው እውነቱን ሳይደብቁ በመናገራቸው ሊደነቁ ይገባል፡፡ ኢኮኖሚስቶቻችንማ እንደ ሮኬት በዕድገት ወደ ሰማይ ተተኩሰናል ነበር ያሉት፡፡

የፖለቲካ ሰዎች በዓይናቸው ባዩት እርሻው፣ ሕንፃው፣ መንገዱ፣ ወዘተ ሊረኩ ይችላሉ፡፡ የዚህ ዘመን ዕውቀት ያለው ኢኮኖሚስት ግን የሚያምነው ዛሬ ሆኖ በሚታየው ብቻ ሳይሆን፣ ነገ ይሆናል በሚባለው ተስፋም (Expectation) መሆኑን ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ የኢኮኖሚክስ መጽሐፍ አንብበው የማያውቁ ኢኮኖሚስቶች እንዲያነቡ ምክር ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፓርላማ አባል፣ ሚኒስትር፣ አምባሳደር፣ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ጳጳስ፣ ሼህ፣ ወዘተ ነገን ፈርቶ ለሥራ በተላከበት ውጭ አገር የዘበኝነትና የፅዳት ሥራ ፈላልጎ ሲቀር፣ እዚህ የቀረው ምን ነገ አለ ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡

አዳም ስሚዝ ነፃ ገበያን ሲተነትን ከካፒታሊዝም ሥርዓት በፊት የነበሩት የፊውዶ ቡርዧ ሥርዓተ ማኅበርና የዘመነ-ንግድ (Mercantalism) ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን ልማዶችና አመሎች፣ በአጠቃላይ ማኅበራዊ ሥነ ምግባሮች ለነፃ ገበያ ካፒታሊዝም ስለማይስማሙ ነቅፎ በመንግሥት ጥረት መወገድ እንደነበረባቸው ጽፏል፡፡

በእኛ አገር የፊውዳሉም፣ የሶሻሊስቱም፣ የካፒታሊዝሙም፣ የዱር ቤቴ ፖለቲካውም ልማዶችና አመሎች እንዲሁም ማኅበራዊ መስተጋብሮች ተቀላቅለው ባሉበት ሁኔታ፣ የተዘበራረቀ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንጂ ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የተመቻቸ የኢኮኖሚ ሥርዓት ሊኖር እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ከገባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ታክሲ ልሳፈር ስል ሾፌሩ በእጄ ለያዝኳት በጣም ትንሽ ፌስታል ያስከፍልሀል አለኝ፡፡ እንዴት ይሆናል ብለው ነፃ ገበያ ነው ካልተስማማህ ውረድ አለኝ፡፡ ታክሲው የእርሱ ቢሆንም መንገዱ ግን የተሠራው በሕዝብ ሀብት እንደሆነ ባውቅም፣ ታክሲ የማሽከርከር ፈቃዱንም ያገኘው በሥነ ሥርዓት ሕዝብን ለማገልገል እንደሆነ ባውቅም ልመልስለት አልፈለግሁም፡፡

ይኸን ባለኝ ወቅት እኔ በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ አራተኛ ዓመት ተማሪዎችን ኢኮኖሚክስ ሳስተምር ቆይቼ የመጣሁ ከመሆኔም በላይ፣ ስለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መጽሐፍ ጽፌ አሳትሜ ነበር፡፡ ሙያዬን የታክሲ ሾፌር ሊያስተምረኝ መሞከሩ ቢያናድደኝም፣ ያንኑ ሰሞን ‹‹ጊዜ ያነሳው ቅል ድንጋይ ይሰብራል›› የሚል ጽሑፍ በየግድግዳው ላይ ተጽፎ ስላየሁ በዚህ ተጽናናሁ፡፡ ዛሬም ያው ነው፡፡ ጊዜ ያነሳው ቅል ድንጋይ እየሰበረ ነው ያለው፡፡ ነገ ይለወጣል እያልን እየተጽናናን ነው ያለነው፡፡

ብዙ ዓመታት የለፋሁበትን የኢኮኖሚክስ ሙያዬን ጋዜጠኛው ላስተምርህ ይለኛል፡፡ ፖለቲካኛው ላስተምርህ ይለኛል፡፡ ነጋዴው ላስተምርህ ይለኛል፡፡ ለመሆኑ ይህ የኢኮኖሚክስ ሙያ መቼ ይሆን የሚከበረው? እስከ መቼ ይሆን ቅል ሁሉ እየተነሳ ልስበርህ የሚለው? ኢኮኖሚክስ የማንም ሰው የኑሮ ዘዴ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል ቢባልምኮ፣ የኑሮ ዘይቤ ምህንድስና የሆነውን ሙያ የተማረውን ድንጋይ የሰበረ ቅል መንገደኛ ሁሉ ተነስቶ ላስተምርህ ይለዋል ማለት አይደለም፡፡

ምን ያድርጉ እውነታቸውን ነው፡፡ ኢኮኖሚክስን የሚያወቁት በተሰበከላቸው ልክ ነው፡፡ ኢሕአዴጎች ሥልጣን በያዙ እስከ አሥረኛው ዓመት ቢሆን ኖሮ ሊገባኝ ይችል ነበር፡፡ ሳይንሱን ከጣሪያ ላይ የሚያወርድላቸው ሰው ስለሌለ ነው ሊባል ይችላል፡፡ አሁን ግን ዕድሜ ለዚያ ምሁር ማምረቻ ዩኒቨርሲቲ ሁሉም ባችለር፣ ማስትሬት፣ ዶክትሬት የሚለውን የምሁርነት መታወቂያ ሠርተፊኬት ይዘውታል፡፡

የፖለቲካን ችግር ጥቂት ሰዎችን ገንዘብ አጉርሶ ወይም ታምራት ላይኔ ላሱ የተባለውን ነገር አልሶ ዝም በማሰኘት ይወጡታል፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሆዱን ያመመውን የኢኮኖሚ ችግር ለማን አጉርሰው ማንን አልሰው ይወጡታል፡፡

ጥልቅ ተሃድሶውን ጥቂት ሰዎች ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በማለት በጅምሩ እርስ በእርሳቸው በታሸገ ውኃ እየተሳሳቁ ተነቃቅፈው በመጨረሻው በነገር ተወነጃጅለው፣ እንግሊዞች አቅም ያለው አቅም በሌለው አጽም ላይ ቆሞ ይኖራል ‘Survival of the fittest’ አንደሚሉት ከፊሉ ከፊሉን በልቶ የሚያበቃ ሳይሆን በጊዜ ብዛት በማየት፣ በመገንዘብ፣ በማጤን፣ በመናገር፣ በመስማት፣ በመጻፍ፣ በማንበብ፣ የሕዝብ ሁሉ ንቃተ ህሊና የሚያድግበት ያድርግልን፡፡ ያኔ የጠላነውን ሁሉ በአንድ ጣታችን ብቻ ገፍተር አድርገን አንገዳግደን ራሱ አውቆ እንዲወድቅ አድርገን እንጥላለን፡፡ ለአገራችን ከዚህ ውጪ ምንም መፍትሔም የለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...