Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበሕገወጥ ደላሎች ሕገወጥ ስደት

በሕገወጥ ደላሎች ሕገወጥ ስደት

ቀን:

በዳዊት ከበደ አርአያ

እንደሚታወቀው ስደት ባላደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የምዕራባውያን አገሮች ዜጎችም በስደት ወደ ሌሎች አገሮች እንደሚሄዱ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን በየወቅቱ ከሚያወጣቸው ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የወንጀል ተግባር ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው፡፡

በተለያዩ አገሮች ያለውን የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የወንጀል ተግባር አፈጻጸም፣ በሕገወጥ መንገድ ለስደት የሚሄዱ ዜጎች የሚደርስባቸውን እንግልት፣ አሰቃቂና ኢሰብዓዊ ተግባር በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

የተለያዩ አገሮች ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ለስደት እንዲዳረጉ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ሰፊ ጥናት ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን እያንዳንዱን ቤተሰብ ያንኳኳ ነው፡፡ ብዙዎችን ለአሰቃቂ ሞትና እልቂት የዳረገ አሳዛኝ የዘመኑ ክስተት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከሰሞኑ የሰማነው ብዙዎችን ያሳዘነውና ያስደነገጠው ከሊቢያ በሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች በአነስተኛ ጀልባ ታጭቀው ወደ ጣሊያን ሊሻገሩ ከተጓዙት 190 ተጓዦች 186ቱ በባህር ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉ፣ ችግሩ ምን ያህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና ጥፋቱም የዚያን ያህል እያደገ እንደመጣ ገሃድ የወጣ ሀቅ ነው፡፡ አሁን በግልጽ የሚታየውን የሕገወጥ ስደት ዋና አቀነባባሪና ለመባባሱ ምክንያት የሆኑት የደላሎች ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው እልባት ሊደረግበት የሚገባ የወንጀል ተግባር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች አብዛኛዎቹ በደላሎች አማካይነት እንደሆነ ከስደተኞች አንደበት በተደጋጋሚ ሲነገር ተደምጧል፡፡

በአንድ ጥናት ላይ እንደተገለጸው በሞያሌ አድርገው ኬንያ በመግባት ታንዛኒያ ማላዊና ዚምባቡዌን አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሙሉ በሙሉ በሕገወጥ ደላሎች አማካይነት እንደሆነ፣ በእነዚህ ደላሎችም ሆነ በጉዞው አስቸጋሪነት ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስባቸውና አብዛኛዎቹም ኮንቴይነር ውስጥ ታሽገው እንደሚያልቁ ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡ ስደተኞች በእያንዳንዱ ሰው ለደላሎች እስከ 80 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከፈል በጥናቱ ላይ ተጠቅሶ ሕገወጥ ደላሎች ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ፣ ስደተኞቹ የኬንያን ድንበር ሲያቋርጡ በኬንያ ፀጥታ ኃይሎች ከተያዙ “የአገር ድንበር በመድፈር” ወንጀል ተከሰው ለእስር እንደሚዳረጉ ተጠቁሟል፡፡ ሕገወጥ ደላሎች ግን ወንጀል በመሥራት ያገኙትን ገንዘብ ይዘው በመሄድ ስለታሰሩ ስደተኞች ምንም ደንታ እንደሌላቸው ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ለኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ስደት የደላሎች ሚና የጎላ ሲሆን፣ ኬንያ ውስጥ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የኬንያ ደላሎች እንደሚበዙና ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ደላሎች ስማቸውን እየቀያየሩ ይኼንን ወንጀል እንደሚሠሩ ታውቋል፡፡

በአንድ ወቅት በሕገወጥ መንገድ በደላሎች አማካይነት ወደ ኬንያ ተሰደው የነበሩና የአገር ድንበር በመድፈር በሚል በኬንያ መንግሥት ተከሰው ናይሮቢ ውስጥ በእስር ላይ ቆይተው ከእስር የተፈቱ 66 ኢትዮጵያውያን፣ በድምሩ 4.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ለሕገወጥ ደላሎች መክፈላቸው ራሳቸው ስደተኞቹ አረጋግጠዋል፡፡

ወደ ኬንያ የሚደረገው ስደት በእግርና በመኪና ኮንቴይነር ውስጥ ታሽገው ሲሆን፣ ከሞያሌ በኋላ ናይሮቢ ለመድረስ ከፍተኛ ስቃይና እንግልት እንደሚደርስባቸው በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ ከናይሮቢ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋ አሶዮሎ የስደተኞች ማከፋፈያ ቦታ ስትሆን፣ ደላሎች ስደተኞቹን ተከፋፍለው በየአቅጣጫው የሚያስማሩባት ከተማ ናት፡፡

ሌላው በጣም አነጋጋሪና ዓለም አቀፍ ሥጋትና ጭንቀት እየፈጠረ የሚገኘው ሥፍር ቁጥር የሌለው የሰው ልጅ እያለቀበት ያለው በሊቢያ በኩል በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚደረገው ሕገወጥ ስደት ነው፡፡ የዚህን የስደት ጉዞ ለየት የሚያደርገው በተለይ ከምሥራቅና ምዕራብ አፍሪካ በከፍተኛ ሐሩርና በረሃ በደላሎች እየተመሩ፣ ከ10 እስከ 20 ቀናት የእግር ጉዞ ማድረጋቸውና ብዙዎቹ ያሰቡትንና ያለሙትን ሳያገኙ በየበረሃው ማለቃቸው ነው፡፡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚያሰራጩት ከሆነ በዚህኛው የስደት መንገድ ያለው ሰብዓዊ ዕልቂት የጨቅላ ሴቶች መደፈርና የሰዎች የኩላሊት ንግድ እጅግ በጣም ዘግናኝና አስከፊ ነው፡፡

 በተለይም ሊቢያ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ባለመመሥረቷ፣ ለሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ስቃዩና ችግሩ በዚህ አያበቃም፡፡ ከሊቢያ በትናንሽ ጀልባዎች ታጭቀው በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር ተጉዘው ብዙዎች ባህር ላይ አልቀዋል፡፡ የሰሞኑ የ186 ስደተኞች ባህር ላይ መሞትም የዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡

 ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ አልፈው አውሮፓ የደረሱትም ቢሆኑ፣ ያለሥራና መኖሪያ ፈቃድ በመጠለያ ተጥለውና በየበረንዳው ተበትነው ለከፍተኛ ችግርና ቀውስ ተዳርገዋል፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ በተከሰተው ከፍተኛ ብርድና ውርጭ ምክንያት ብዙዎች ያለመጠለያ ያሉት  ስደተኞች በውርጭና እርጥበት አዘል ብርድ እያለቁ ነው፡፡

በዚሁ በሊቢያ በኩል አውሮፓ ለመድረስ ለሚደረገው ሕገወጥ ስደት እያንዳንዱ ስደተኛ ለሕገወጥ ደላሎች እስከ 200 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከፈልም ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ዕድለኛ ሆነው ከሞት አፋፍ ወይም ከአንበሳ መንጋጋ የማምለጥ ያህል በሕይወት ከተረፉ ነው፡፡ ብዙዎቹ  ሠርተው መለወጥ የሚችሉበትን ገንዘብ ለሕገወጥ ደላሎች አስረክበው ሀሩር እንደ እሳት በሚለበልበው የሊቢያ በረሃ ወድቀው ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርገዋል፡፡

አውሮፓ የደረሱትም ቢሆኑ እንዳሰቡትና እንዳለሙት ሳይሆን በመቅረቱ፣ ገሚሶቹ በንዴትና ብስጭት በገዛ ራሳቸው ሕይወታቸው ሲያጠፉ ቀሪዎቹ ደግሞ ከገቡበት ድብርትና ጭንቀት ለመላቀቅ የአልኮልና የዕፅ ሱሰኞች መሆናቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የሚያወጣው መረጃ ያስረዳል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በርካቶቹ የአውሮፓ አገሮች ድንበራቸው መዝጋታቸውና በተለይም የጀርመን መንግሥት ወደ አገሮች የገቡ ሕገወጥ ስደተኞች ወደ መጡበት ለመመለስ መወሰኑን የአገሪቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር እንዳስታወቀ አልጀዚራ ቴሌቪዥን በዘገባው ገልጿል፡፡

በተለያዩ አቅጣጫዎች በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚሰደዱ ዜጎች በአብዛኛው አገር ውስጥ ባሉ አማላይ ሕገወጥ ደላሎች እየተታለሉና ድንበር እናሻግራለን በሚሉ ሕገወጥ ተቀባይ ደላሎች አማካይነት ሲሆን፣ በርካቶች በጉዞ ላይ ከሚገጥማቸው የአየር፣ የምግብና የውኃ ዕጦት ችግር በተጨማሪ ሕገወጥ ደላሎቹ ለከፍተኛ ስቃይ እንደሚዳርጓቸው የዚህ ሰለባ የሆኑ ይገልጹታል፡፡

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ የተሰማሩ ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሆነ በይፋ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ደላሎች ከአገር ውጪ መኖራቸውን ገልጾ፣ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለቀጣይ ደረጃ በደረጃ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል፡፡

ሕገወጥ የሰው ዝውውር በየትኛውም መልኩ ቀላል የማይባል ወንጀል ካለመሆኑም ባሻገር፣ ለዚህ ተግባራቸው ገንዘብ ከመቀበል በተጨማሪ ስደተኞችን በማሰቃየት፣ ልጃገረዶችንና ሴቶችን በመድፈርና በመግደል የሚፈጽሙት አሰቃቂና ከባድ ወንጀል ነው፡፡

ዛሬ በታዳጊ አገሮች ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በተለይም በአውሮፓ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይ ልዩ ትኩረት እየተሰጠው ነው፡፡ ወንጀሉን ከተቻለ ከምንጩ ለማድረቅ፣ አሊያም በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የችግሩ አሳሳቢነት በልዩ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡

የሕገወጥ ደላሎች መረብ ከአገር አገር የተሳሰረ እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አገሮች የጋራ አቋም በመያዝ ወንጀሉን ለመከላከል፣ የድርጊቱን አስከፊነት በማስረዳት ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉም በጋራ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

                                                

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...