Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአካል ጉዳተኛው ጉዳይ ልናስታምመው የሚገባ ፖለቲካ ነው››

አቶ ዮሴፍ ኃይለማርያም፣ የመረጃና ግንዛቤ ስለአካል ጉዳተኞች ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት

መረጃና ግንዛቤ ስለአካል ጉዳተኞች ማኅበር፣ የአካል ጉዳተኛውን ችግር ግንዛቤ በመፍጠር ለመቅረፍ የተቋቋመው ከ11 ዓመታት በፊት ነው፡፡ በአምስት አባላት የተመሠረተው ማኅበር ዛሬ ላይ 82 አባላትን አፍርቷል፡፡ የማኅበሩ መሥራችና ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ዮሴፍ ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡ ጋዜጠኛ ዮሴፍ፣ ‹‹ዮሴፍ ምርኩዝ›› በሚል መጠርያ መጣጥፎች በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በቀድሞው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣና ለገዳዲ  ሬዲዮ ላይ ሠርተዋል፡፡ አሁን ላይ በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ይሠራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ በሚዲያ ሕግ ማስተርስ ዲግሪያቸውን በኖርዌይና በስዊድን አግኝተዋል፡፡ ቲዎሎጂም ተምረዋል፡፡ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር በመሠረቱት ማኅበር ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹አካል ጉዳተኞች ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በቀዳሚነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራት አለበት›› በሚል በግንዛቤ ዙሪያ የሚሠራ ማኅበር አቋቁማችኋል፡፡ የአካል ጉዳተኛውን ችግር ያባባሰው ምንድነው ይላሉ?

አቶ ዮሴፍ፡- እንደ መረጃና ግንዛቤ ስለ አካል ጉዳተኞች ማኅበር፣ አካል ጉዳተኛውን ከኅብረተሰቡ፣ ከመንግሥትና ከራሱ ጋር እንዲጣላ ያደረገው የመረጃና የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ አንድ ተቋም ወይም ግለሰብ በአካል ጉዳተኛ ዙሪያ መረጃ ከሌለው አብሮ መሥራት አይችልም፡፡ ይህንን መሠረት አድርገን ከ11 ዓመታት በፊት ፕሮጀክት ቀረፅን፡፡ ማኅበሩ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ግንዛቤ ይሰጣል፣ መብት ላይም ይሠራል፡፡ የሕግ ክፍተቶችን ያሳያል፣ ሕጎች ያስተዋውቃል፡፡ የሕክምና፣ የትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸውን ተደራሽነት ችግሮች ነቅሶ በማውጣትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር፣ የአካል ጉዳተኞችን ችግር ግንዛቤ በመፍጠር ለመፍታት ይሠራል፡፡ መጀመሪያ ላይ መጽሔት እናዘጋጅ፣ በራሪ ወረቀትም እንበትን ነበር፡፡ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ሕግ ጋር ተያይዞ ግን ዕርዳታ ሰጪዎች ወደኋላ ስለተጎተቱብን በሕግ፣ በጋዜጠኝነት በሌሎችም ዘርፎች የተማርነው የማኅበሩ አባላት በበጎ ፈቃደኝነት ‹‹ትኩረት›› የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም የመጀመሪያው ኤፍኤም በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲጀመር ጀምሮ እያስተላለፍን ነው፡፡ በትንሽ ዕርዳታም መሥራት ከባድ ስለሆነ፣ በመንግሥት ሚዲያ ውስጥ ገብተን በአዲስ ቲቪ፣ በኤፍኤም 96.3፣ በአካል ጉዳት ላይ ግንዛቤው እንዲኖር እንሠራለን፡፡ አካል ጉዳተኛውም የሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ እየገባ መሥራት ጀምሯል፡፡ ዓባይ፣ ሸገር፣ ዛሚ፣ ብሥራት ላይ የአካል ጉዳተኛውን ችግር ለማስገንዘብና ችግሮችን ለመቅረፍ እየተጋገዝን እንሠራለን፡፡ የጋራ ገቢ ግን የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- የተማሩና ገንቢ ሐሳብ ሊያመነጩ የሚችሉ ብዙ አካል ጉዳተኞች ቢኖሩም በየማኅበራቱ ተሳትፈው ለመብታቸው ሲሟገቱ አይስተዋሉም፡፡ ለምን ይመስልዎታል?

አቶ ዮሴፍ፡- የኛ ማኅበር አባላት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ ኖርዌይ ለትምህርት በቆየሁባቸው ዓመታት የተማርኩት ስለአካል ጉዳተኛ አካል ጉዳተኛ ያልሆነውም ጭምር የሚሟገት መሆኑን ነው፡፡ የአካል ጉዳተኛ ጉዳይ ሁሉንም ያሳተፈ መሆን አለበት፡፡ ሆኖም በጣም እግሬን ሲያመኝ የሚሰማኝ እኔ ነኝ፡፡ አካል ጉዳተኛው፣ በአካል ጉዳተኛው ጉዳይ አብሮ ቢሠራ ለውጤቱ መልካም ነው፡፡ በተለይ የተማረው አካል ጉዳተኛ ስለአካል ጉዳተኛ አብሮ ካልሠራ አደጋ አለው፡፡ በመከራ ሊሆን ይችላል የተማረው፡፡ ደህና ቤተሰብ የነበረው ደግሞ በር ሳይዘጋበትና ከትምህርት ሳይታገድ ተምሯል፡፡ አሁንም ግን ብዙዎች ከቤት አልወጡም፡፡ አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት የተማረው አካል ጉዳተኛ የግድ ዋጋ መክፈል አለበት፡፡ ሰው የመሆን ትርጉሙም ለሌሎች መኖር ነው፡፡ በነበረው የዘመን አስተሳሰብ ተገልለው የነበሩ አካል ጉዳተኞች ዛሬ ድረስ ተፅዕኖ አለባቸው፡፡ የሥጋ ደዌ፣ የአዕምሮ ውስንነት፣ ዓይነ ስውራንና ሌሎች ሰባት የሚደርሱ የአካል ጉዳት ያለባቸውን መርዳት የልብ ሸክምን ማዳመጥ ማለት ነው፡፡ የተማረው አካል ጉዳተኛ ያልተማረውን፣ ተምሮም ሥራ ማግኘት ያልቻለውን ቀድሞ ካልረዳ ማን ሊረዳ ነው? መንግሥት አካል ጉዳተኞችን አቅም በፈቀደ መጠን እረዳለሁ ሲል ሌሎችም እንዲረዱት በማሰብ ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት አካል ጉዳተኞችን ‹‹አቅም በፈቀደ›› ሳይሆን በሙሉ አቅም መርዳት አለበት፡፡ ከሌሎች እኩል የምንማርበት፣ የምንታከምበት፣ የምንጓዝበት፣ የምንኖርበት ዕድል መፈጠር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ላይ የተሻሉ ዕድሎችና አሠራሮች ብቅ እያሉ ነው ብለው አያምኑም?

አቶ ዮሴፍ፡- የተሻለ ነገር አለ፡፡ ከዜሮ አንድ ይሻላል፡፡ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የዓይነ ስውራን ማኅበር ተመሥርቷል፡፡ የደረት፣ የእጅ፣ የእግር አካል ጉዳት ያለባቸው ማኅበር ለመመሥረት በ1980ዎቹ ጥረት ስናደርግ አልተሳካም ነበር፡፡ አሁን ላይ ተደራጁ እየተባልን ነው፡፡ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የአካል ጉዳተኛው ጉዳይ እየተካተተ ነው፡፡ የሚኒስቴርና የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የአካል ጉዳተኞችንና የኤድስ ሕሙማንን አካተው እንዲሠሩ አዋጅ ወጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- አዋጆች፣ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ቢኖሩም መተግበሩ ላይ ክፍተት አለ ይባላል፡፡ ማኅበራችሁ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ምን ይሠራል?

አቶ ዮሴፍ፡- በተለይ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ብዙ ሕጎች ወጥተዋል፡፡ ሆኖም አፈጻጸም ላይ መንግሥት ዛሬም ወገቤን ይላል፡፡ በአካል ጉዳተኛ ዙሪያ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ በመከራ ደረጃ እየወጡ የተማሩ አካል ጉዳተኞች ሥራ አላገኙም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ቁጭ ያሉ አሉ፡፡ ፖሊሲዎች አካል ጉዳተኛውን በሚደግፍ መልኩ ተቀምጠዋል፡፡ አስፈጻሚዎች የት አሉ? አስፈጻሚው የግድ አካል ጉዳተኛ መሆን አለበት? በከተማዋ ያሉት ሕንፃዎች ሁሉንም በእኩል አያስተናግዱም፡፡ አንድ ሕንፃ ለተለያዩ አገልግሎቶች ተገንብቶ ለአካል ጉዳተኛው ግን ተደራሽ አይደለም፡፡ አንድ ሕንፃ ሲገነባ ምን ማሟላት እንዳለበት በአዋጅ፣ በመመሪያ ተቀምጧል፡፡ በቅርቡ የተገነቡት እንኳን መመሪያውን አያሟሉም፡፡ አካል ጉዳተኛውን ሊታደግ የሚችል መንግሥት የለም ወይ? እስኪባል አብዛኞቹ ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ ለአካል ጉዳተኛ መረማመጃ ቢሠሩም ምቹ አድርገው አልሠሯቸውም፡፡ በጣም የተንጋለሉ ናቸው፡፡ የተሠሩ መወጣጫዎች (ራምፖች) ምቹ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች እሥረኛ ሊፍቶች አሉ፡፡ አካል ጉዳተኛውን ብቻ ሳይሆን ነፍሰጡርና አረጋውያንን ጭምር ያስጨንቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሊፍቶች ከሁለተኛ አንዳንዶቹ ከአራተኛ ፎቅ ይጀምራሉ፡፡ ጎዶሎ ቁጥር የማይሠሩባቸው አንድ ወደላይ ወይም አንድ ወደታች እንዲወርድ የሚያስገድዱም አሉ፡፡ እሥረኛ ሊፍቶች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በተለያዩ ተቋማትም አሉ፡፡ ሕጉ ከወጣ መከበር አለበት፡፡ ግን እየተከበረ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ማኀበር አካል ጉዳተኛውን ያማከለ ሕንፃ እንዲገነባ ሕንፃ ዲዛይን ከሚያደርጉ ባለሙያዎች ጋር ተመካክራችሁ አታውቁም?

አቶ ዮሴፍ፡- ሕጉ ራሱ ሕንፃ ዲዛይን የሚያደርጉ ሰዎች አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ እንዲያደርጉ ያዛል፡፡ ለአካል ጉዳተኛ የሚያስፈልግ መፀዳጃ፣ ሊፍት ውስጥ ለዓይነ ስውራን የሚሆን ብሬልና ሌሎችም መሟላት ያለባቸውን ሁሉ አንድ ሕንፃ እንዲያሟላ በሕጉ ተቀምጧል፡፡ በእኛ በኩል አቅም ያላቸውንና ጨረታ ተወዳድረው ሊያሸንፉ ይችላሉ ያልናቸውን አርክቴክቶች ጠርተን በአዲስ አበባና በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ውይይት አካሂደናል፡፡ በእነሱ በኩል የተነሳው ጉዳይ የሕንፃው ባለቤት እንደፈለገ የሚያዝ በመሆኑ ሕጉን ለመተግበር አለመቻሉን ነው፡፡ ሆኖም ችግሩ ከሕንፃ አስገንቢዎችም ቢሆንም አርክቴክቶች ባለሀብቶችን ስለሕጉ መምከር አለባቸው፡፡ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ፣ መኖሪያ ቤቶችም አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ አድርገው መሠራት አለባቸው፡፡ የአቅም ችግርና ተጨማሪ ወጪ የሚሉት ጉዳይ ቢኖርም፣ አካል ጉዳተኛውም ተጨማሪ አገልግሎት ፈላጊ ይሆናል፡፡ አካል ጉዳተኛው ገንዘቡን ባንክ አስቀምጦ የማያወጣበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ብዙዎቹ በደረጃ የሚወጡ ናቸው፡፡ ዓይነስውራን ገንዘባቸውን ባንክ ማስገባት ይችላሉ፡፡ ለማውጣት ግን እማኝ አብሮ መገኘት አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ባንኮች በብሬልም ስለማያስተናግዱ ነው፡፡ በአውሮፓ ከአፍሪካም በደቡብ አፍሪካ ዓይነስውራን በራሳቸው ገንዘባቸውን ባንክ ማስገባትም ሆነ ማውጣት ይችላሉ፡፡ ሥርዓቱ ተዘርግቷል፡፡ አሳታፊ ሕግና ፖሊሲ ቢኖረንም ካልተገበርነው ዋጋ የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- የተማረውን አካል ጉዳተኛ፣ በአካል ጉዳተኛው ዙሪያ ማሳተፍ ችግሮችን ለማቅለል ይረዳል፡፡ ማኅበራችሁ እነዚህ ተሳታፊ እንዲሆኑ ይጎተጉታል?

አቶ ዮሴፍ፡- በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው አንዱ ጉዳያችን የተማረውን አካል ጉዳተኛ እባክህ ተሳተፍ እያልን መወትወት ነው፡፡ አንዳንዶች ደፍረን ወጥተናል፡፡ አንዳንዶች ለራሳቸው ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ መክረናል፣ ተወያይተናል፡፡ አመለካከት መገንባት ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ የአካል ጉዳተኛውን ጉዳይ ልናስታምመው የሚገባ ፖለቲካ ነው፡፡ ብዙ መገለል፣ ጫና፣ ማኅበራዊ ነውጥ አለ፡፡ ሥራ ማግኘት፣ መማር መከራ ነው፡፡ በትምህርት ላይ ያለው አካቶ ትምህርት መልካም ነው፡፡ ጥሩ ነገር አለ፡፡ ግን አፈጻጸም ላይ ገና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉንም ያሳተፈ ትምህርት ለማዳረስ ቢተጋም አካል ጉዳተኞችን የሚያሳትፉ ትምህርት ቤቶች እምብዛም የሉም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ቢሆን በጣት የሚቆጠሩት ናቸው ለአካል ጉዳተኛው የሚሆኑት፡፡ ይህም የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን ያሳያል፡፡ ማኅበራችሁ ይህንን ለመቀልበስ ምን ይሠራል?

አቶ ዮሴፍ፡- የአካቶ ትምህርት ቢባልም፣ አካል ጉዳተኞችን የሚያስተናግዱ መሠረተ ልማቶች ገና ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች የትምህርት አገልግሎት የሚሰጡት ጥቂት ናቸው፡፡ ማኅበራችን መንግሥትን በማስገንዘብና ችግሮችን በማሳየት ማኅበረሰቡ አካል ጉዳተኛ ቤተሰቡን ወደ ትምህርት እንዲልክ እንሠራለን፡፡ አካል ጉዳተኝነት ዘሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ የመኪና አደጋ፣ የሕንፃ መፍረስ ብዙ ሌሎች አጋጣሚዎች ሙሉ አካል የነበረውን አካል ጉዳተኛ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአካል ጉዳተኛ አብዮት ተቀጣጥሎ ለውጥ እንዲመጣ፣ የተማረው አካል ጉዳተኛ መሳተፍ አለበት የምንለው፡፡ ብዙዎቹ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ተጎድተዋል፡፡ ይህ የአካል ጉዳተኛውን መብት ካለመጠበቅ የመጣ ነው፡፡ ስለአካል ጉዳተኛው በዓመት አንዴ ሳይሆን ችግሩ እስኪረግብና መስመር እስኪይዝ በየጊዜው መሠራት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የአካል ጉዳተኛው የአካል ድጋፍ ለማግኘት እንደሚቸገር በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የማኅበራችሁ አስተዋጽኦ ምን ይመስላል?

አቶ ዮሴፍ፡- ማኅበሩ የአካል ድጋፍ በነፃ አስመጥቶ ለአካል ጉዳተኛው ያከፋፍላል፡፡ የዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት የገቢ ምንጭ እንደሌላቸው የሚያረጋግጡና በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖሩ ናቸው፡፡ 2008 ዓ.ም. ላይ ግን የአካል ድጋፍ ጥራቱ የጎደለ ስለነበር አልሰጠንም፡፡ የአካል ጉዳት ድጋፍ በአብዛኛው የሚያስፈልገው ከዘራ፣ ክራንችና ብሬስ (ደግፎ የሚይዝ ብረት) ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለአካል ጉዳተኛ የሚያስፈልግ ድጋፍን በተመለከተ ያለው አገልግሎት እዚህ ግባ አይባልም፡፡ ዋጋው ውድ ከመሆኑም በላይ በጥራት አይሠራም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ አምራች ነው ያለው፡፡ እሱም ችግር አለበት፡፡ ችግሩን የሚያውቁት መንግሥታዊ አካላትም መልስ አይሰጡም፡፡ በአካል ድጋፍ ችግር አካል ጉዳተኛው ጭንቀት ላይ ነው፡፡ ካለድጋፍ የማይንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛ ምን ይሁን? አንዳንድ ክልሎች አገልግሎቱ አላቸው፡፡ ከአዲስ አበባ የአካል ድጋፍ ፍለጋ አርባ ምንጭ፣ ደሴ፣ ጂማ ድረስ የሚሄዱም አካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መልስ መስጠት አለበት፡፡ ሌላው አገር ውስጥ መኪና የሚገጣጥሙ ድርጅቶች ለአካል ጉዳተኛው ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ እኛን የሚያነጻጽሩን አውሮፓ ካለ አካል ጉዳተኛ ጋር ነው፡፡ በአገራችን አቅም ቢያነጻጽሩ ኖሮ አገር ውስጥ የተመረተውን መኪና ከቀረጥ ነፃ እንድንገዛ ይፈቅዱ ነበር፡፡ በአካል ጉዳተኛው ላይ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮቹም አካል ጉዳተኝነታችንን እንዳንረሳ እያደረጉን ነው፡፡ ደረጃ መውጣት ሲያቅተን፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ መግቢያ ስንቸገር እናስታውሰዋለን፡፡ ሥራ ለመቀጠር አሻራ መስጠት ግድ ነው፡፡ ጣት የሌለው ሰው በምኑ አሻራ ይሰጣል? እንደዚህ ዓይነት ክፍተቶችን እያዩ ማመቻቸት የመልካም አስተዳደር አንዱ አካል ነው፡፡ አካል ጉዳተኛው ሥራ ማግኘትን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች የተገለለበትን ዘመን የሚክስ አሠራርና አፈጻጸም ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኞችን በትምህርቱ ማሳተፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ወሳኝ ቢሆንም፣ ትምህርት ገብተው ሲያቋርጡ፣ ጭራሹንም ሲቀሩ ይስተዋላል፡፡ ማኅበራችሁ በዚህ ላይ ምን ሠራ?

አቶ ዮሴፍ፡- በ1990ዎቹ ዓ.ም. መጀመሪያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን በማታው ክፍለ ጊዜ አንድ ክፍል ውስጥ ሦስት ተማሪዎች በነፃ እንዲማሩ አድርገን ነበር፡፡ ቀን ይነግዳሉ ማታ ይማራሉ፡፡ ይህ ከ1ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ነበር፡፡ ሆኖም ከአራት ዓመት በላይ መሄድ አልቻለም፡፡ በኋላ ‹‹የልዩ ፍላጎት›› የሚል አጀንዳ መጣ፡፡ ብዙ ታግለን አሁን መሠረት ይዟል፡፡ ሆኖም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለአካል ጉዳተኛው የተመቸ ነገር የለም፡፡ ገና ናቸው፡፡ በግንዛቤ ሥራችን ሁሌም የምንወተውተውም የትምህርትን ጉዳይ ነው፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...