Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመንፈቀ ዓመቱ ከሚጠበቀው ከግማሽ በታች የወጪ ንግድ አፈጻጸም አሳይቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የዘርፉ ችግሮች ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሚቀረፉ መንግሥት ያምናል

– ‹‹በገና በዓል ማግሥት ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ሆን ብለው ዋጋ አንረዋል›› አቶ ወንዱ ለገሠ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

የቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራች ፋብሪካዎች በየዓመቱ የሚልኩት የቆዳና የቆዳ ውጤቶች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን ጭማሪ እያሳየ መምጣቱ ቢገለጽም፣ ወደ ውጭ ከተላኩት ምርቶች እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ግን ከታቀደውም፣ ከሚታሰበውም በታች እየሆነ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡

በዚህ መንፈቀ ዓመት ካለቀለት ቆዳ፣ ከጫማ እንዲሁም ከጓንት፣ ከቆዳ አልባሳትና ከልዩ ልዩ የቆዳ መገልገያዎች የወጪ ንግድ ይጠበቅ የነበረው ገቢ 113 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በመሆኑም ካለቀለት የቆዳ የወጪ ንግድ 31.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጫማ 19.2 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቆዳ ጓንት 2.4 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከቆዳ አልባሳትና ከተለያዩ የቆዳ ውጤቶች 1.6 ሚሊዮን ዶላር፣ በድምሩ 54.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በስድስት ወራት ውስጥ ተገኝቷል፡፡ ይሁንና ከዘርፉ ይጠበቅ ከነበረው የገቢ መጠን ሊገኝ የቻለው 47 ከመቶ ብቻ መሆኑን ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከዘርፉ ስለተገኘው ገቢ ከሪፖርተር ተጠይቀው የገለጹት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሠ፣ ከዘርፉ እንዲገኝ ይጠበቅ የነበረው ገቢ ሊገኝ ያልቻለበት ዋናው ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቀዛቅዞ በቆየው የዓለም ገበያ ችግር ነው፡፡ በዓለም ገበያ በታየው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ፍላጎት መቀዛቀዝ ምክንያት የአገር ውስጥ አምራቾች ገበያ አጥተው ተቸግረው ቆይተዋል፡፡ በዚህም የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ሲያጥራቸውም ተስተውለዋል በማለት አቶ ወንዱ አብራርተዋል፡፡ ከሌሎች ሸቀጦች ተርታ በዋጋ ደረጃ ከፍተኛ ማሽቆልቆል ሲያሳይ የከረመው የቆዳ ዘርፍም በዚህ የዋጋ ቁልቁለት እየተመታ መቆየቱን የገለጹት አቶ ወንዱ፣ ከዓለም ገበያ መቀዛቀዝ ባሻገር ግን አምራቾች የሚታይባቸውም ችግር አስተዋጽኦ ነበረው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ከ30 በላይ ቆዳ፣ የቆዳ ውጤቶችና ጫማ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና ዘመናዊ የምርት አመራረት ሥርዓትን በመከተል ዓለም አቀፍ ገበያዎች የሚጠይቋቸውን ደረጃዎች አሟልተው ለመላክ ችግር እንደሚታይባቸው ተናግረዋል፡፡

ይህም ሆኖ በአብዛኛው የዓለም ገበያ ላይ ከ25 እስከ 30 በመቶ የገበያ ቅናሽ መታየቱን፣ ይህ የገበያ ችግር በተለይ ባለቀለት የቆዳ ገበያ ላይ በከፍተኛ ደረጃ መታየቱን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ይሁንና ከሰሞኑ ገበያው መንሰራራት እያሳየ እንሚገኝ፣ በዚህ ሳቢያም ዋጋው መልሶ ሊጨምር እንደሚችል ፍንጮች መታየታቸው ተብራርቷል፡፡

ለቆዳ ኢንዱስትሪው የወጪ ንግድ አፈጻጸም መቀዛቀዝ የሚቀርቡ ምክንያቶች እንዲህ ቢቀርቡም፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው ውጤት ግን የሚፈልገውን ያህል እንዳልሆነ መረጃዎች እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሰባት ዓመታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው አዋጅ ለዚህ ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ በጥሬ ቆዳ የወጪ ንግድ ላይ እስከ 150 ከመቶ ታክስ እንዲጣል የሚደነግገውን አዋጅ ፓርላማው ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ መረጃዎቹ ይህ አዋጅ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ እየታየ ያለው የወጪ ንግድ አፈጻጸም መነሻው መንግሥት በታክስ ሰበብ ወደ ውጭ ይላክ የነበረውን የጥሬ ቆዳና ሌጦ ንግድ እንዲገታ በማድረጉ እንደሆነ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

መንግሥት ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ በማስቀመጥ የጥሬ ቆዳ ወጪ ንግድ እንዲገታ ያደረገው አገሪቱ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እሴት እየታከለባቸው ወደ ውጭ እንዲላኩ በማሰብ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በወቅቱ አብራርቷል፡፡ ይሁንና ገቢው እያደገ እንደሚመጣ ሲበጠቅ ቢቆይም የሚታሰበውን ያህል አለማደጉ ታይቷል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ያብራሩት ዋና ዳይሬክትሩ፣  ኢትዮጵያ ከፍተኛ የታክስ ጫና በመጣል የጥሬ ቆዳን እንዳይላክ በመግታቷ ምክንያት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የጥሬ ቆዳ ይቀርብላቸው ከነበሩ ፋብሪካዎች በኩል የሚደረግ ከፍተኛ ጫናና ግፊት እንዳለ አቶ ወንዱ ጠቁመዋል፡፡ አንደኛው የግፊቱ ምንጭ አገር ውስጥ ያሉ ነገር ግን ከቀደመው ጊዜ ይልቅ የተሻለ አቅም እንዳይፈጠር (ጥቅማቸው የሚነካ) የሚፈልጉ ፋብሪካዎች መኖራቸው ነው፡፡

ይሁንና መንግሥት ያለቀለት ቆዳ ብቻ ወደ ውጭ እንዲላክ በማለት ያወጣው ሕግና የሚከተለውን ፖሊሲ በመመልከት ለመግዛት የሚመጡትም ኩባንያዎች ቢሆኑ የሚፈልጉትን ማግኘት እንዳልቻሉ ዋና ዳይሬክተሩ ያምናሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉት ፋብሪካዎች የገዢዎቹን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ብዛትና ጥራት ያለው ምርት በአጭር ጊዜ ውስጥ የማምረት ብቃታቸው ደካማ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ እንደ አቶ ወልዱ ማብራሪያ በቀን እስከ 35 ሺሕ አንዳንዶቹም እስከ 22 ሺሕ ጥንድ ጫማ የማምረት አቅም ያላቸውን ፋብሪካዎች ለመትከል ሲያካሂዱት የቆዩትን የማስፋፊያ ግንባታ ገና አላጠናቀቁም፡፡ ይህ ግን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚያገኝ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ቀድሞው ጥሬ ቆዳና ሌጦ በመላክ አሁን ከሚገኘው ይልቅ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ የሚያሚኑ አካላት ወደ ቀደመው አሠራር እንዲመለስ መንግሥትን ቢወተውቱም፣ መንግሥት የእሴት ጭማሬው በጥሬው ከመላክ ከሚገኘውም በላይ ጥቅም እንደሚሰጥ ይሞግታል፡፡ አቶ ወልዱ እንደሚያብራሩትም በሺዎች ሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ትልልቅ ፋብሪካዎች እንዲተክሉ የሚያስችለው ያለቀለት ቆዳ እንዲሁም የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ እንዲስፋፋ ሲደረግ ነው፡፡ ‹‹እስካሁን የነበረው ችግራችን በሙሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እናልፈዋለን፤›› ያሉት አቶ ወንዱ፣ ፋብሪካዎቹ ከሚያደርሱት አካባቢ ብክለት አኳያ ጭምር በከፊል ያለቀለት ቆዳ እየላኩ ይቀጥሉ ማለቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ይናገራሉ፡፡

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ሲጠበቅበት የነበሩትን ውጤቶች ማስገኘት እንደሚጀምር፣ እስካሁንም በርካታ ድጋፍና እገዛ ሲደረግለት እደቆየ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አዳዲስ ለውጦችና በርካታ ትልልቅ ገዠዎችም ከኢትዮጵያ በቀጥታ ለመግዛት ደጋግመው መምጣት በመጀመራቸው ነገሮች እንደሚቀየሩ ገልጸዋል፡፡ ይህም ቢሆን ባለፉት ስድስት ወራት ብቻም ሳይሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከታዩት ለውጦች በተለይ የጫማ፣ የጓንት፣ የቆዳ አልባሳትና ሌሎች ውጤቶች ካለቀለት ቆዳ የወጪ ንግድ ይልቅ ጥሩ ለውጥ እያሳዩ መምጣታቸውም ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባሻገር የቴክሎጂ አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ በርካታ የመዳረሻ ገበያዎች አለመፈጠራቸው፣ የገበያ ማስፋፊያና የፕሮሞሽን ሥራዎች ደካማ መሆን፣ ትልልቅ ገዥዎች ኢትዮጵያ በቆዳም ሆነ በጫማ ዘርፍ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ገና አለማወቃቸው ሌሎች ምክንያቶች ናቸው፡፡

ከወጪ ንግዱ በተጓዳኝ በአገር ውስጥ ያለው የቆዳ ጫማም ሆነ የሌሎች ውጤቶች ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያስረዳል፡፡ በየዓመቱ የቆዳ ውጤቶች 15 ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎች መቅረብ እንደሚጠበቅባቸው፣ የሌሎች ቆዳ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ሲታከልበትም ወደ 42 ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎች እንደሚያሻቅብ ይታሰባል፡፡ ይሁንና የአገሪቱ ፋብሪካዎች በቀን ሊያመርቱ ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቀው መጠን 20 ሺሕ ጥንድ ጫማዎችን ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከ15 ሚሊዮኑ ወደ ግማሽ የሚጠጋውን መጠን የሚወክል በመሆኑ፣ ፍላጎቱን ለማሟላት ብዙ እንደሚቀራቸው የሚጠቁም ሆኖ ይገኛል፡፡ ከውጭው ገበያ ይልቅ የአገር ውስጥ ገበያው ከፍተኛ የገበያና የዋጋ አማራጭ እየሰጠ እንደሚገኝም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩል በጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ላይ የሰላ ትችተ ያሰሙት አቶ ወንዱ፣ አቅራቢዎቹ ለወራት ተቀዛቅዞ የሰነበተው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንቅስቃሴ መጠነኛ ማንሰራራት ማሳየት መጀመሩን ተገን አድርገው የጥሬ ቆዳና ሌጦ ዋጋ አንርዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡ ‹‹በገና በዓል ማግሥት ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ሆን ብለው ዋጋ አንረዋል፤›› በማለት የወረፏቸው ሲሆን፣ ለአንድ የበግ ቆዳ ፋብሪካዎችን ከ60 እስከ 70 ብር እንዲከፍሏቸው እየጠየቁ፣ ለኅብረተሰቡ ግን ከ15 ብር እስከ 25 ብር ቢበዛ እስከ 30 ብር ሲከፍሉ መታየታቸውን አብራርተዋል፡፡

በገና በዓል ማግሥት እንደታየው ከሆነ በአብዛኛው በየመንደሩ የበግ ቆዳ ሲሸጥ የነበረው ከ15 እስከ 20 ብር መሆኑ ከምን የመጣ ነው? ለሚለው ጥያቄ ሲያብራሩም፣ ተቀዛቅዞ የቆየው የቆዳ ገበያ ማንሰራራት ሲጀምር በገበያ ዕጦት ምክንያት የሥራ ማስኬጃ ዕጥረት ስላጋጠማቸው ይህንን መነሻ በማድረግ ከኅብረተሰቡ የገዙበትን ዝቅተኛ ዋጋ፣ ከሚገባው በላይ በማናር ቆዳ ፋብሪካዎችን እንደጠየቁ አቶ ወንዱ ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በተለይ በእንቁጣጣሽ በዓል ወቅት በቆዳ አቅራቢዎችና በቆዳ ፋብሪካዎች መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት፣ ፋብሪካዎቹ ለበግ ጥሬ ቆዳ 50 ብር ድረስ ለመክፈል ተስማምተው ነበር፡፡ እንደ አቶ ወንዱ ማብራሪያ ከሆነም ፋብሪካዎቹ ለገና በዓል ከነበረው ዕርድ ከ45 እስከ 50 ብር ለበግ ቆዳ ለመክፈል ዝግጁ እንደነበሩ ቢያሳውቁም፣ አቅራቢዎቹ ግን ከ60 እስከ 70 ብር ይከፈለን ማለታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅርቦት ዕጥረት አሁንም ድረስ ያልተፈታ ችግር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ወንዱ፣ ‹‹ዕጥረቱ ስሌለ ሳይሆን ሆን ተብሎ እንዲፈጠር የተደረገ ዕጥረት ነው፤›› ብለውታል፡፡

‹‹የቆዳ አቅራቢዎች የበግ ቆዳ ከኅብረተሰቡ እስከ 30 ብር በመክፈል ቢሰበስቡ፣ ወጪና ትርፋቸውን አክለውበት ለፋብሪካዎች ከ45 እስከ 50 ብር ቢያቀርቡ በቂያቸው ነበር፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የትርፍ ህዳጋቸውን ያለአግባብ በመለጠጥ የፈጠሩት የገበያ መዛባት መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ቆዳ አቅራቢዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ሲያነሷቸው ከቆዩ ችግሮች መካከል በአብዛኛው በዱቤ ካልገዛን እያሉ ፋብሪካዎች እንደሚያስቸግሯቸው፣ የቆዳ ጥራት እንዲጠበቅላቸው በርካታ ወጪ የሚያስከትሉና ቆዳ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ በጨው የማልፋት ሥራዎችና ሌሎችም ታክለውበት የሚቀርብላቸው ቆዳን አንቀበልም እስከማለት እንደሚደርሱ፣ ዋጋውንም ሆን ብለው እንደሚያራክሱ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በዚያም ላይ ከዚህ ቀደም ገበያውን ያመሱት የውጭ ፋብሪካዎች መሆናቸውን፣ ምርቱን በብዛት ለማግኘት ሌሎች ፋብሪካዎች ከሚከፍሉት ይልቅ ጭማሪ በመስጠት ቆዳ የመሻማት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር ሲነገር መቆየቱም አይዘነጋም፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች