የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቅርቡ አቋቁሞት በነበረው አጣሪ ግብረ ኃይል ውሳኔ መሠረት ተጣርተው ከሕግ ውጪ ሆነው ቢገኙ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ከተዘረዘሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ 18ቱ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መዝግበው እንደያዟቸው የሚጠቀሱት የአባላት ቁጥርን ብዛትን የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡
ከምክር ቤቶች መካከል የተወሰኑት አሉን በማለት ያቀረባቸውን የአባላት ብዛትን በትክክል ለመለየት በተቀመጡት የማጣሪያ መሥፈርቶች መሠረት፣ ግብረ ኃይሉ የማጣራት ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ግብረ ኃይሉ እንዲያስፈጽም የወከለው የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤትም በተቀመጠለት መሥፈርት መሠረት እስካሁን ባካሄደው ማጣራት፣ ከ100 ሺሕ በላይ ለሚገመቱ አባላት ምክር ቤቶቹ የአባልነት መረጃ ማቅረብ ሳይችሉ እንደተገኙ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቶቹ እንዳሏቸው በመጥቀስ ያስመዘገቧቸው አባላት ቁጥር ትክክለኛነት እንዲጣራ ከመወሰኑ ቀደም ብሎ 18ቱም አባል ምክር ቤቶች ያስመዘገቧቸው ነጋዴ አባላት ቁጥር ከ500 ሺሕ በላይ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም ትክክለኛ አባል መሆን አለመሆናቸውን ለመለየት የሚያስችሉ ፍተሻዎች ተካሂደው የተገኘው ውጤት ግን ለየት ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ እያንዳንዱ ንግድ ምክር ቤት ያሉት አባላት ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ያስችላሉ ተብለው ከተካሄዱት የፍተሻ ሥራዎች መካከል ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ፣ ስለአባልነታቸው የሚያረጋግጥ የአባላት ምዝገባ መግለጫዎችና የመመዝገበያ ሰነዶች እንዲሁም ሌሎች ደጋፊ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል፡፡ በዚህ መሠረት የተፈለጉት መረጃዎች ሊገኝላቸው ያልቻሉ፣ መረጃ ያልቀረበባቸው ነገር ግን ተመዝግበው የተገኙ አባላት ቁጥር ከ100 ሺሕ በላይ ሊደርስ እንደቻለ ተረጋግጧል፡፡ የትክክለኛ አባላት ቁጥርን የማጣራት ሥራው እስካሁንም እየተካሄደ ሲሆን፣ በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት መረጃ ላይቀርብባቸው የሚችሉ አባላት ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሚያሻቅብ ይገመታል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚገልጹት፣ በአባላት ቁጥር ዙሪያ እየተደረገ ያለው ማጣራት መካሄዱ በመቀጠሉ፣ በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት መረጃ ላይቀርብባቸው ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ አባላት ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ፍንጮች መታየተቸው አልቀረም፡፡
ፍተሻውና ማጣራቱ በተለይ ከፍተኛ የአባላት ቁጥር እንዳሏቸው በማሳወቅ አስመዝግበው የነበሩ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ ከዚህ ቀደም ያስመዘገቡትን የአባላት ቁጥር እንደሚቀንስባቸው ሲጠበቅ፣ ይህ ሆኖ ከተገኘም ንግድ ምክር ቤቶቹ የሚኖራቸውን የድምፅ ብዛት በቀነሰው የአባላት ቁጥር መጠን ሊያሳንስባቸው እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡
የማጣራቱ ሥራ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የቀጠለ ሲሆን፣ በተለይ የአባል ምክር ቤቶች መሪዎችን በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለመወከል ከሥር የሚገኙ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ተገቢውን የምርጫ ሥነ ሥርዓት አካሂደው፣ በዚያው መሠረት ተወክለው ስለመምጣት አለመምጣታቸው ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው የማጣራት ሒደትም ከአባላት ቁጥር ባሻገር ብዙ ነገሮችን ይዞ ብቅ ሊል እንደሚችል እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡ በዚህ ረገድ እስካሁን የሁለት ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ጉዳይ እየታየ መሆኑ ታውቋል፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች በተገቢው የምርጫ ሒደት ሳይወከሉ ተመርጠው የመጡ አመራሮችን ልከዋል የተባሉት የእነዚህ ምክር ቤቶች ጉዳይ እየታየ ሲሆን፣ በማጣራቱ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ግን ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎች እየተሰበሰቡ ነው ተብሏል፡፡
በተለይ ከ18ቱ መካከል በአንዱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሳይወከሉ ወደ ላይኛው ዕርከን በመምጣት፣ ተመርጠውና ተወክለው መላካቸው አሳውቀው የነበሩ አመራሮች ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ እንደቀጠለ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ቀጣዩንና የመጨረሻውን ውሳኔ ምንነት ሁሉም በጉጉት እንዲጠብቀው ማድረጉ ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡
ይኸውም በማጣራቱ ሒደት ወቅት አንዳንዶቹ አመራሮች ከሥር ንግድ ምክር ቤቶች ወደ ላይኛው እርከን የመጡበት አግባብ በምርጫ ተወዳድረውና አሸንፈው ያልመጡ ናቸው የሚሉ መረጃዎች እየቀረቡባቸው በመሆኑ እንደሆነ እኚሁ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ በተገቢው መንገድ አልመጡም የተባሉት እነዚህ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን የተለያዩ የአመራር ቦታዎችን ለመያዝ ተዘጋጅተው ሲጠባበቁ የነበሩ መኖራቸውም እየተነገረ ነው፡፡
እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን እያስተናገደ ያለው የማጣራት ሒደት የመጨረሻውን ድምዳሜ አግኝቶ፣ ቀን የተቆረጠለትም ጉባዔና ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማካሄድ የአጣሪ ግብረ ኃይሉ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህም መሠረት የሕግ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት ጉዳዮች ላይ ግብረ ኃይሉ የወከለው ጽሕፈት ቤቱና የምክር ቤቱ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔያቸውን ከዋናው ጉባዔ በፊት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ ውሳኔ 18ቱ አባል ምክር ቤቶች በሕግ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት በትክክል ስለመወከላቸው ማረጋገጫ ካልተገኘ ወይም ከሕግ ውጭ በተደረገ ምርጫ ወደ ላይኛው እርከን ተመርጠውና ተወክለው መምጣታቸው ከተረጋገጠ በጠቅላላ ጉባዔው እንዳይሳተፉ የሚደርስ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችልም እየተገረ ነው፡፡
በዚህ መንገድ ውሳኔ የሚተላለፍ ከሆነ ደግሞ ከ18ቱ አባል ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመገኘትና ለመሳተፍ ከሚወከሉ ተሳታፊዎች መካከል ታጭተው የነበሩ አንዳንዶቹን ከመንገድ ሊያስቀር እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡
ፈታኝና አድካሚ ነበር በተባለው የማጣራት ሥራ፣ በአጣሪ ኮሚቴው ውሳኔ መሠረት ጽሕፈት ቤቱና ቦርዱ እያንዳንዱ አባል ምክር ቤት በመጣራቱ ሒደት በትክክል የአባሎቹ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በይፋ እንዲገለጽ የሚደረግ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረትም የሚኖራቸው የድምፅ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን ለየምክር ቤቶቹ እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ ሕጉን ሳይከተሉና ከታች ምርጫ ሳያካሂዱ የተወከሉና የተመረጡም አመራሮች ካሉም ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ግን አሁንም ተጨማሪ መረጃዎች እንዲሟሉ እየተጠበቀ ነው መባሉ ጉዳዩን ሳያወሳስበው እንዳልቀረ የሚገልጹ አሉ፡፡ የማጣራት ሥራውን ተከትሎ፣ በሚገኘው ውጤት መነሻነት እስከማገድ የሚደርስ ዕርምጃ ከተወሰደ፣ በቅርቡ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ላይ አዳዲስ ዕጩዎች እንዲቀርቡ ዕድል ይሰጣል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖችም ግምታቸውን ከወዲሁ እያቀረቡ ነው፡፡ ግምታቸውን ከሚገልጹት ወገኖች ለመረዳት እንደተቻለው፣ አጋጣሚው ነባርና ብዙ የቆዩ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮችን በአዳዲስ ተተኪዎች ለመለወጥ ዕድል ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በኃላፊነት ላይ የሚገኘውን አመራር ለመተካት ራሱን በዕጩነት ያቀረበ አዲስ ተወዳዳሪ አልታየም፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች በተለይ ለፕሬዚዳንትነት ሊወዳደር የሚችሉ ዕጩዎች ከምርጫው ቀድሞ ማንነታቸው ይታወቅ የነበረ ቢሆንም፣ በዘንድሮው ምርጫ ለቦታው የተጠቆመ አዲስ ዕጩ እስካሁን አልታየም፡፡
ከንግድ ምክር ቤቱ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቷል፡፡ በጉባዔው 18ቱም አባል ምክር ቤቶች፣ የሚወክሏቸውን ሁለት ሁለት ዕጩዎች እንዲያቀርቡ በመወሰኑ፣ በዚሁ መሠረት አባል ምክር ቤቶቹ ከሚልኳቸው ሁለት ተወካዮች ውስጥ ለፕሬዚዳንትነትም ይሁን ለቦርድ አባልነት ተወዳዳሪዎች የሚያቀርቡ ከሆነ፣ ይህንኑ እንዲያሳውቁ ደብዳቤ ተፅፎላቸው ከምክር ቤቶቹ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡