Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምፕሬዚዳንት ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ቀናት

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ቀናት

ቀን:

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን ፈጽመው ቀጣዮቹን አራት ዓመታት አገሪቱን ለመምራት ቢሮ ከተረከቡበት ከጥር 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ወዲህ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ብዙዎች አልታደሙም በማለት ሚዲያው የናኘውን በመኮነን፣ ከበዓለ ሲመታቸው በፊት ሲናገሩ የነበሯቸውን የፖሊሲ ለውጦች ዕውን ለማድረግ ወደ ተግባር የገቡትም ሰዓታትን ሳያባክኑ ነበር፡፡

ትራምፕ ከንግግር ወደ ተግባር በተሸጋገሩበትና ሥልጣን በተረከቡበት በመጀመሪያዎቹ 72 ሰዓታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ ውሳኔዎቹ በአሜሪካ ላይ በአጭር ጊዜ የሚያመጡት ተፅዕኖ ባይኖርም፣ በረዥም ጊዜ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ትራምፕ ሥራቸውን የጀመሩት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባማ ዘመን ይሁንታ ያገኙ ስምምነቶችንና በድርድር ላይ የነበሩትን በማፍረስ ነው፡፡ ዕጩ ፕሬዚዳንት ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ የኦባማን አስተዳደር ሲወቅሱበት የነበረውንና 12 አገሮችን በአባልነት የያዘው ነፃ የንግድ ስምምነት (ትራንስ ፓስፊክ ፓርትነርሺፕ)፣ በሳቸው ዘመን ተቀባይነት እንደማያገኝ በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡

ትራንስ ፓስፊክ ፓርትነርሺፕ (ቲፒፒ) የአሜሪካውያን ሠራተኞችን ጥቅም የማያስጠብቅ ሲሉም ስምምነቱን ተችተውታል፡፡ ትራምፕ ቲፒፒን ላለመቀላቀል ያሳለፉት ውሳኔ በሌሎች ዘንድ ግርታን ቢፈጥርም፣ እሳቸው በዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነቶች ላይ ያላቸው አቋም የአሜሪካን ጥቅም ከማስጠበቅ የመነጨ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሥራ አጦችን ያበዛል፣ የኢንዱስትሪ ምድር የሆነችውን አሜሪካ ያኮስሳል ባይም ናቸው፡፡

 ኦባማ የአሜሪካ ቲፒፒን መቀላቀል በቀጣናው ቻይና የተቆጣጠረችውን የንግድ የበላይነት ለማመጣጠን ይረዳል የሚል መከራከሪያ ቢኖራቸውም፣ ሐሳባቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ በትራምፕ የአንቀላቀልም ፊርማ ተቋጭቷል፡፡

በዋይት ሐውስ በነበረው የፊርማ ሥነ ሥርዓትም ‹‹ስለንግድ ስምምነቱ ለረዥም ጊዜ ስንናገር፣ ስንቃወም ቆይተናል፡፡ ለአሜሪካ ሠራተኞች ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ ቲፒፒ በአብዛኛው በሪፐብሊካኑ በተያዘው ኮንግረስ መቼም አይፀድቅም፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የትራምፕ አካሄድ በሰሜን አሜሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት (Nafta) ላይም አጥልቷል፡፡ 17 ዓመታትን ባስቆጠረው የናፍታ ስምምነት ላይ ከካናዳና ከሜክሲኮ ጋር መልሶ ለመደራደር የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸውም ተነግሯል፡፡

ውርጃን የሚቃወሙት ትራምፕ፣ መንግሥት ውርጃ ላይ ለሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቋርጥ የተዘጋጀውን መመርያም በፊርማቸው ደግፈዋል፡፡

 ውርጃን ለሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ውርጃን እንደ አንድ የቤተሰብ ምጣኔ መንገድ አድርገው የሚያስተምሩትም ከመንግሥት የገንዘብ ድጎማ እንዳያገኙ አግደዋል፡፡ መመርያው ከታክስ ከፋዩ የሚሰበሰብ ገንዘብ ውርጃን ሕጋዊ ለማድረግ ለሚሠሩ ድርጅቶች እንዳይሰጥም አግዷል፡፡

ትራምፕ ውሳኔውን ያስተላለፉት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ በ1973 ሕጋዊ ያደረገውን ውርጃ አስመልክቶ ዓመታዊ በዓል በተከበረ ማግሥት ነው፡፡ ውርጃ መፈቀድ አለበት የሚሉ አቀንቃኞች በበኩላቸው ሥራው አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ተናግረዋል፡፡

በአሜሪካ ሴኔት አነስተኛ ውክልና ያለው የዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ናንሲ ፔሎሲ፣ ‹‹አሁን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በውጭ አገሮች ያሉዋቸውን ፕሮግራሞች ለማስቀጠል፣ ለሴቶች ያልተሟላ የጤና ምክርና አገልግሎት እንዲሰጡ ይገደዳሉ፤›› ብለዋል፡፡

ፔሎሲ እንደሚሉት፣ እ.ኤ.አ ከ1973 ወዲህ አሜሪካ ውርጃን ለማስተዋወቅም ሆነ እንዲተገበር ገንዘብ ረድታ አታውቅም፡፡ ያልተፈለገ እርግዝና፣ የጤና እክልና ጉዳት፣ በሽታና ከኤድስ ጋር በተያያዘ ካልሆነ በስተቀር ውርጃን አልደገፈችም ሲሉም ተከራክረዋል፡፡

የሪፐብሊካን እንደራሴ (ኮንግረስማን) እና የቤቱ የጤና ኮሚቴ መሪ ማይክል በርጌስ የትራምፕን ውሳኔ ‹‹ተቀባይነት ያለው›› ብለውታል፡፡ ‹‹ሕይወት ውድ ዋጋ አለው፡፡ ከስጦታም ሁሉ በትንሹ የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም ሕይወትን ለማዳን በማንኛውም መንገድ መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህን ውሳኔ በመወሰናቸው ምሥጋና ሊቸራቸው ይገባል፤›› ያሉት በርጌስ፣ ሕይወትን የሚያስቀጥሉ ፖሊሲዎችን ለመደገፍና የታክስ ከፋዩን ገንዘብ ለማዳን አብረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ ከቱጃር ነጋዴዎች ጋርም ተወያይተዋል፡፡ ከዴል ኮምፒዩተር፣ ከስፔስ ኤክስ፣ ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ ከሎክሂድ ማርቲን ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በነበራቸው ውይይትም በአሜሪካ ውስጥ የሚሠሩ ነጋዴዎች ይከፍሉት የነበረው  የ35 በመቶ ድርጅታዊ ታክስ፣ ከ20 በመቶ እስከ 15 በመቶ ድረስ ዝቅ ለማድረግ ማሰባቸውን አሳውቀዋል፡፡

ትራምፕ እንደሚሉት፣ ብዙ አምራቾችንና ባለሀብቶችን ወደ አሜሪካ መሳብ ይፈልጋሉ፡፡ ‹‹ሌላ ሰው  የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ ከሚቀመጥ እኔ የተቀመጥኩት ለአገሬ ባለሀብት ለመሳብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሜሪካ የራሷን ምርት ዳግም ማምረት መጀመር እንዳለባት፣ ያለቀላቸውን ምርቶች ከሌሎች አገሮች ማስገባት ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ማምረትና የንግድ ልውውጡንም ማጠናከር ይጠበቅብናል፤›› ብለዋል፡፡

አሜሪካ የነበሩ አምራች ኩባንያዎች ከአሜሪካ በመውጣት ሌሎች አገሮች ውስጥ አምርተው ምርቶቻቸውን የሚልኩ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም የተቃወሙት ትራምፕ፣ ‹‹በከፍተኛ ግብር ይቀጣሉ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነውም ሆነ ከተመረጡ በኋላ ማምረቻቸውን ወደ ሜክሲኮ ባሸጋገሩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ትልቅ ታሪፍ እንደሚጥሉ ሲናገሩ የከረሙ ሲሆን፣ ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ ደግሞ በአሜሪካ ለሚያመርቱ ኩባንያዎች ጥቅማ ጥቅም እንደሚኖር አሳውቀዋል፡፡

የዶው ኬሚካልስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንድሪው ሊቨርስ፣ በአሜሪካ የአምራች ዘርፍን ለማነቃቃት የሚረዳ ዕቅድ በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርቡ በትራምፕ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል፡፡

የሞርጌጅ ኢንሹራንስ ፕሪሚየም እንዲቀንስ፣ የኦባማ ‘አፎርደብል አክት ኬር’ እንዲቆም፣ የመንግሥት ተቋማት አዳዲስ ሕጎችን እንዲያመክኑና አዲሱ አስተዳደር እንዲከልሳቸው ጊዜ እንዲሰጡም ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የሲአይኤን ሠራተኞች ያነጋገሩ ሲሆን፣ የኑክሌር ቁልፉንም ተቀብለዋል፡፡ መንግሥት ከወታደሮች፣ ከማኅበረሰብ ደኅንነትና ከጤና ሠራተኞች በስተቀር ቅጥር እንዳያካሂድም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ በእስራኤል ቴሌአቪቭ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም ለማዘዋወርም ውይይት ጀምረዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚዳንትነታቸውን ሥራ በሚያስጀምራቸው በዓለ ሲመት ማግሥት በአሜሪካና በተለያዩ አገሮች ከተሞች በሴቶች የተጠሩ የተቃውሞ ሠልፎች ተካሂደውባቸዋል፡፡ ‹‹ተቃውሞ የማድረግ መብት የዴሞክራሲያችን መገለጫ ነው፤›› ያሉት ትራምፕ፣ ቀደም ብለው ግን፣ ‹‹ለምንድነው እነዚህ ሰዎች በምርጫ ድምፃቸውን ያልሰጡት?›› ሲሉ ቀልደዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...